BRIDGE Research & Innovation - Parliaments. Peace. Policy

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ሕገ መንግሥት (2015)

ስለክልሉ ምክር ቤት

      አንቀጽ  55

    ስለክልሉ ምክር ቤት አባላት

  1. የክልሉ ምክር ቤት አባላት ሁሉ አቀፍ፣ ነፃና ቀጥተኛ በሆነ ድምጽ በምስጢር በሚሰጥበት ስርዓት በየአምስት ዓመቱ በህዝብ ይመረጣሉ፡፡ ሆኖም ልዩ ሁኔታ ሲያጋጥም የፌዴራል
መንግስት በህግ በሚወስነው መሰረት ይፈፀማል፡፡

2 የምክር ቤት አባላት በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች መካከል አብላጫ ድምፅ ያገኘ ተወዳዳሪ አሸናፊ በሚሆንበት የምርጫ ሥርዓት ይመረጣሉ፡፡ የተለየ

ውክልና የሚያስፈልጋቸው ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ቁጥር መሰረት በማድረግ የሚወሰን ይሆናል፡፡ ዝርዝሩ የክልሉ ምክር ቤት በሚያወጣው ሕግ መሰረት ይወሰናል፡፡

 

 3   የክልሉ ምክር ቤት አባላት የመላው የክልሉ ሕዝብ ተወካዮች ናቸው፡፡ተገዥነታቸውም ፡-

 

   ሀ/ ለሕገ መንግሥቱ፣

   ለ/ ለሕዝብ እና

  ሐ/ ለሕሊናቸው ብቻ ይሆናል፡፡ 

  4   በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 እስከ 3 ያሉ ድንጋጌዎች እንደ አግባብነታቸው በየደረጃው ለሚገኙ የምክር ቤት አባላት ተፈጻሚነት አላቸው፡፡

         አንቀጽ  56

     የክልሉ ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር

    1   የክልሉ ምክር ቤት በዚህ ሕገ መንግሥት መሰረት የክልሉ ከፍተኛ የሕግ አውጪ አካል ነው፡፡

    2   የኢትዮጵያ   ፌዴራላዊ  ዴሞክራሲያዊ  ሪፐብሊክ  ሕገ መንግሥት   ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ በክልሉ የውስጥ ጉዳዮች ላይ የበላይ የፖለቲካ

ሥልጣን ባለቤት ነው፡፡

    3   በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 ድንጋጌዎች ሥር የሰፈረዉ አጠቃላይ ሥልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ ምክር ቤቱ በተለይ የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባር ይኖሩታል፡፡

      ሀ) በዚህ ሕገ መንግሥት መሰረት የፌዴራሉን ሕገ መንግሥትና ሌሎች ሕጎችን የማይፃረሩ ልዩ ልዩ ሕጎችን ያወጣል፡፡

    ለ/ በዚህ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፵7 ንዑስ አንቀጽ 6 የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ በክልሉ ዉስጥ ተጨማሪ የአስተዳደር እርከኖችን ወይም የራስ በራስ አስተዳደር አካባቢዎችን በሕግ መሰረት ያቋቁማል፡፡

    ሐ/)የፌዴራል መንግሥት   ሥልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ ክልሉ ከሌሎች ክልል መንግስታት ጋር የሚደረገውን ስምምነት መርምሮ ያጸድቃል፤

    መ/    ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ርዕሰ መስተዳድር ይመርጣል፡፡ በርዕሰ መስተዳድሩ አቅራቢነት የክልል መስተዳድር ምክር ቤት አባላት ሹመት ያጸድቃል፤   

    ሠ/ የዋና ኦዲተርና የቁጥጥር አካሉን ያቋቁማል፤

    ረ/ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ለመጠበቅ የሚያስፈልጉ መመሪያዎችን  ያወጣል፣    የጸጥታና   የፖሊስ   ኃይሉን ያቋቁማል፣

    ሰ/ የክልሉን    የማኅበራዊና  ኢኮኖሚያዊ   ፖሊሲና ፕሮግራሞችን ያጸድቃል፤

    ሸ/ የክልሉን የገቢ ምንጮች የሚመለከቱ ሕጎችን  ያወጣል፡፡ ለክልሉ መንግሥት በተከለለው የገቢ ምንጭ በክልሉ ውስጥ ግብርና ታክስ ይጥላል፡፡ የክልሉን መንግሥት በጀት ያጸድቃል፡፡

     ቀ/ ለማኅበራዊ አገልግሎት መስፋፋትና ለኢኮኖሚያዊ ልማት መፋጠን አስፈላጊ የሆኑ ተቋማትን ያቋቁማል፡፡

     በ/ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት እና ምክትል   ፕሬዚደንት እና የክልሉ ዋና ኦዲተርና ምክትል ዋና ኦዲተር ሹመት በርዕሰ መስተዳድሩአቅራቢነት ያጸድቃል፤

     ተ/ የዳኞችን ሹመት በዳኝነት አስተዳደር ጉባዔ አቅራቢነት ያጸድቃል፤

      ቸ/ የክልሉን መንግሥት  ሠራተኞች አስተዳደርና የሥራ ሁኔታዎችን በተመለከተ ሕግ ያወጣል፤

      ኀ/ ለክልሉ መንግስት በተሰጠው ስልጣን መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጣል፣

      ነ/  የክልሉን    ርዕሰ   መስተዳድርና   ሌሎች   የክልሉን

    መንግሥት  ባለሥልጣናት     ለጥያቄ    ይጠራል፣ የአስፈጻሚውን አካል አሠራር ይመረምራል፤ ኘ/ በሕግ መሰረት ምህረት ያደርጋል፤ አ/ የራሱን ጽሕፈት ቤት ያደራጃል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡

                         አንቀጽ 57

                     የፖለቲካ ሥልጣን

     1. በክልሉ ምክር ቤት ውስጥ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ  የፖለቲካ ድርጅቶች የክልሉን መስተዳድር ምክር ቤት ያደራጃል ወይም ያደራጃሉ፣
ይመራል ወይም ይመራሉ፡፡ 

 2. በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ የፖለቲካ ድርጅቶች ከክልሉ ምክር ቤት አባላት መካከል የምክር ቤቱን ዋና አፈ-ጉባዔንና ምክትል አፈ-ጉባዔን
በማቅረብ ያሰይማል፡፡ 

 3. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) እና (2) ድንጋጌ እንደአግባብቱ በየእርከኑ ለሚገኙ ምክር ቤቶች ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡

 

                     አንቀጽ 58

       የክልሉ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት

 

      1. የክልሉ ምክር ቤት የራሱ የሆነ አደረጃጀት ያለው ተጠሪነቱ ለምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ የሆነ ጽህፈት ቤት ይኖረዋል፡፡

      2. በምክር ቤቱ ስር ቋሚ ኮሚቴዎች ይደራጃሉ፡፡

      3. የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት የሚከተሉት ስልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡

          ሀ) ጽህፈት ቤቱን በሰው ኃይልና ቁሳቁስ ያደራጃል፣

          ለ) የምክር ቤቱን ሰነዶች በአግባቡ ይይዛል፤ ይጠብቃል፣

         ሐ) የምክር ቤቱን ቃለ-ጉባዔ በሚገባ መያዙን ያረጋግጣል፣

        መ) በአፈ-ጉባዔ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት ያከናዉናል፡፡

     4. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 እስከ 3 ያሉ ድንጋጌዎች እንደአግባብነቱ በየደረጃዉ ለተቋቋሙ ምክር ቤቶች ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡ 

 

 

                     አንቀጽ 59

             የአፈጉባዔው ሥልጣንና ተግባር

  አፈጉባዔው፤-

   1   የምክር ቤቱን መደበኛና አስቸኳይ ስብሰባዎች ይጠራል፣ ይመራል፤

   2   ምክር ቤቱን በመወከል ጠቅላላ የአስተዳደር ሥራዎችን ይመራል፡፡

   3   ምክር ቤቱ በአባሎቹ ላይ የወሰነዉን የዲስፕሊን እርምጃ ያስፈጽማል፡፡

   4   የምክር ቤቱን ጽሕፈት ቤት አደረጃጀት በሕግ ይወስናል፡፡

   5   የምክር ቤቱን ቋሚና ጊዚያዊ ኮሚቴዎችን ያስተባብራል፡፡

   6   በሕግ የተሰጡትን ሌሎች ተግባራት ያከናዉናል፡፡

             አንቀጽ 60

     የምክትል አፈጉባዔው ሥልጣንና ተግባር


     1 በአፈጉባዔው     ተለይተው     የተሰጡትን     ተግባራት ያከናውናል፤

     2 አፈጉባዔው በማይኖርበት ወይም ሥራውን ለማከናወን በማይችልበት ጊዜ ተክቶ ይሠራል፤

 

           አንቀጽ 61

     የምክር ቤቱ የስብሰባ ጊዜ እና የሥራ ዘመን

 

  1 ከምክር ቤቱ አባላት ውስጥ ሁለት ሦስተኛው ከተገኘ ምልዓተ-ጉባዔ ይሆናል፤

  2  የክልሉ  ምክር  ቤት  አባላት  የሚመረጡት  ለአምስት ዓመታት ነው፡፡ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሄዶ ይጠናቀቃል፡፡ የቀድሞው ምክር ቤት የሥራ ዘመን በተጠናቀቀ በአንድ ወር ውስጥ አዲሱ ምክር ቤት ሥራውን ይጀምራል፡፡

  3 ምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ በማያደርግበት ወቅት አፈ-ጉባዔው አስቸኳይ

ስብሰባ ሊጠራ ይችላል፡፡ ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ከአንድ ሶስተኛ በላይ የሆኑት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ ከጠየቁ አፈጉባዔው የምክር ቤቱን ስብሰባ የመጥራት ግዴታ አለበት፤

 4 የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ በግልጽ ይካሄዳል፣ ሆኖም ስብሰባው በዝግ እንዲካሄድ በምክር ቤቱ አባላት ወይም በክልሉ አስፈጻሚ አካል ከተጠየቀና ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ጥያቄውን ከደገፉ ምክር ቤቱ ዝግ ስብሰባ ሊያደርግ ይችላል፡፡

 

 

                አንቀጽ 62

    የክልሉ ምክር ቤት የውሳኔ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት

 

  1  በዚህ ሕገ መንግሥት ውስጥ ተገልጾ በተለየ ሁኔታ ካልተደነገገ በስተቀር ማናቸውም ውሳኔዎች የሚተላለፉት በስብሰባው ላይ ከተገኙት የምክር ቤት አባላት ውስጥ በአብላጫ ድምፅ ይሆናል፡፡

 2   ምክር ቤቱ ውስጣዊ አሠራሩና የሕግ አወጣጡን ሂደት አስመልክቶ ደንቦችን ሊያወጣ ይችላል፡፡

  

                 አንቀጽ 63

          ስለክልሉ ምክር ቤት መበተን

 1   ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ ምክር ቤቱ የሥልጣን ዘመን ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሄድ በምክር ቤቱ ፈቃድ እንዲበተን ለማድረግ ይችላል፡፡

2  በጣምራ የክልሉን መንግሥት ሥልጣን የያዙ የፖለቲካ ድርጅቶች ጣምራነታቸው ፈርሶ በምክር ቤቱ የነበራቸውን አብላጫነት ያጡ እንደሆነ የክልሉ

መስተዳድር ምክር ቤት ተበትኖ በምክር ቤቱ ባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሌላ ጣምራ መንግሥት በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለመመስረት ርዕሰ መስተዳድሩ

የፖለቲካ ድርጅቶችን ይጋብዛል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶቹ አዲስ መንግሥት ለመመስረት ወይም የነበረውን ጣምራነት ለመቀጠል ካልቻሉ የክልሉ ምክር ቤት ተበትኖ አዲስ ምርጫ ይደረጋል፡፡

3   በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ወይም (2) መሰረት የክልሉ ምክር ቤት የተበተነ እንደሆነ ከስድስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አዲስ ምርጫ

መደረግ አለበት፡፡

4   ምርጫው በተጠናቀቀ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ አዲሱ የክልል ምክር ቤት ሥራውን ይጀምራል፡፡

5  የክልሉ ምክር ቤት ከተበተነ በኋላ ክልሉን የሚመራው ሥልጣን ይዞ የነበረው የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ የፖለቲካ ድርጅቶች የዕለት ተዕለት የመንግሥት ሥራ ከማከናወንና ምርጫ ከማካሄድ በስተቀር አዲስ አዋጆችን፣ ደንቦችንና ድንጋጌዎችን ማውጣት ወይም ነባር ሕጎችንና ድንጋጌዎችን መሻርና ማሻሻል አይችልም፡፡

6   የዚህ አንቀጽ ድንጋጌዎች እንደ አግባብነቱ በዞን፣ በወረዳ፣ በከተማ አስተዳደር እና በቀበሌ ምክር ቤቶች ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡


                   ክፍል ሦስት

          የብሔረሰቦች ምክር ቤት

                አንቀጽ 64

      የብሔረሰቦች ምክር ቤት አባላት


1   የብሔረሰቦች ምክር ቤት በክልሉ የሚገኙት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና    ሕዝቦች     ቢያንስ     በሁለት     አባላት የሚወከሉበት ምክር ቤት ነዉ፡፡

2   እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ በአንድ ሚሊዮን አንድ ተጨማሪ አባል ይወክላል፡፡

3  የብሔረሰቦች  ምክር  ቤት  አባላት  ከፌዴራል  ሕዝብ ተወካዮች እና ክልል ምክር ቤት ተመራጭ ውጭ በየደረጃዉ ከሚገኙ ምክር ቤት ወይም በአስተዳደር ምክር ቤት ከየብሔረሰቡ የሚወከሉ አባላት ይሆናሉ፡፡ ውክልናቸው በሚመለከተው የዞን ወይም ወረዳ ምክር ቤት የጸደቀ መሆን ይኖርበታል፡፡


            አንቀጽ 65

       የብሔረሰቦች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር 

ምክር ቤቱ፤-

 1. የክልሉን ህገ መንግስት ይተረጉማል፡፡

 2. የክልሉን ህገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ ያደራጃል፡፡

 3. የክልሉን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዲጠናከር እና እንዲጎለብት ያደርጋል፡፡  
 4. በክልሉ ውስጥ በሚገኙ አስተዳደር እርከኖች መካከል ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሔ ያፈላልጋል፡፡
 5. በክልሉ ምክር ቤት ልዩ ውክልና የሚያስፈልጋቸዉ ማህበረሰብ ክፍሎችን ይወሰናል፡፡ ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል፡፡
 6. የክልሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ የሚጠናከርበትን ሁኔታ ያመቻቻል፡፡
 7. የክልሉ ህገ መንግስት ማሻሻያ ሀሳብ በማመንጨትና በማሻሻል ሂደት ዉስጥ ይሳተፋል፡፡
 8. ከአጎራባች ክልል መንግስታት ጋር በሚነሱ አለመግባባቶችና የድንበር መካለል ጥያቄዎችን አጥንቶ ለፌደሬሽን ምክር ቤት የማቅረብና አፈፃፀሙንም የመከታተል ስልጣን ይኖረዋል፡፡
9. የክልሉን የበጀት ቀመር ይወስናል፡፡ ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል፡፡


              አንቀጽ 66

      የብሔረሰቦች ምክር ቤት የስብሰባ ጊዜ፣ የሥራ ዘመን እና የውሳኔ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት


1  ከምክር ቤቱ አባላት ሁለት ሦስተኛው ከተገኘ ምልዓተ-ጉባዔ ይሆናል፡፡ ማናቸውም ውሳኔ የሚያልፈዉ ስብሰባ ላይ ከተገኙት የምክር ቤቱ አባላት ከግማሽ በላይ ድምፅ ሲደገፍ ብቻ ነዉ፡፡

2   የምክር ቤቱ አባላት ድምፅ መስጠት የሚችሉት በአካል ሲገኙ ብቻ ነዉ፡፡

3   ምክር ቤቱ ስለዉስጣዊ አሠራሩ፣ የስብሰባ አመራር ሥነ- ሥርዓት እና የአባላት የሥነ-ምግባር ደንብ ሊያወጣ ይችላል፡፡

4   ምክር ቤቱ ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ መደበኛ ስብሰባ ያደርጋል፡፡

5   የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን አንድ የምርጫ ዘመን ይሆናል፡፡


            አንቀጽ 67

      የብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሥልጣንና ተግባር

 1   የምክር ቤቱን መደበኛና አስቸኳይ ስብሰባዎች ይጠራል፣ ይመራል፤

ምክር ቤቱን ይወክላል፣ ጠቅላላ የአስተዳደር ሥራዎችን ይመራል፤

ምክር ቤቱ በአባላት ላይ የወሰደውን የዲስፒሊን እርምጃ ያስፈጽማል፤

4   የምክር ቤቱን ጽሕፈት ቤት ያደራጃል፡፡

5 የምክር ቤቱን ጊዜያዊና ቋሚ ኮሚቴዎችን ያስተባብራል፤

6   በምክር ቤቱና በሕግ የተሰጡትን ሌሎች ተግባራትን ያከናውናል፤


           አንቀጽ 68

የብሔረሰቦች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ሥልጣንና ተግባር

1   አፈጉባዔው  በማይኖርበት  ወይም  ሥራውን  ማከናወን በማይችልበት ጊዜ ተክቶ ይሠራል፤

2 በአፈጉባዔው     ተለይተው     የተሰጡትን     ተግባራት ያከናውናል፤