BRIDGE Research & Innovation - Parliaments. Peace. Policy

የተሻሻለው የኦሮሚያ ክልል ሕገ-መንግስት (1994) ስለ ጨፌ ኦሮሚያ

 

አንቀጽ 48

ስለ ጨፌ ኦሮሚያ

  1. የጨፌ አባላት ነፃ፤ ቀጥተኛ ትክክለኛ በሆነና ድምጽ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ፡፡
  2. የጨፌ አባላት በአንድ የምርጫ ክልል ወስጥ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች መካከል አብላጫ ድምጽ ያገኘ ተወዳዳሪ አሸናፈ በሚሆንበት የምርጫ ሥርዓት ይመረጣሉ፡፡
  3. የጨፌ አባላት የመላው ሕዝብ ተወካዮች ናቸው፡፡ ተገዥነታቸውም፣

 

ሀ/ ለሕገ-መንግስቱ

ለ/ ለህዝቡና

ሐ/ ለራሳቸው ህሊና ብቻ ይሆናል፡፡

  1. ማንኛውም የጨፌ አባል በምክር ቤቱ ስብሰባ በሚሰጠው ድምጽ ወይም አስተያየት ምክንያት አይከሰስም፣ አስተዳደራዊ እርምጃም አይወስድበትም፡፡
  2. ማንኛውም የጨፌ አባል ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለምክር ቤቱ ፈቃድ አይያዝም፡፡ በወንጀል አይከሰስም፡፡
  3. ማንኛም የጨፌ አባል የመረጠው ህዝብ አመኔታ ባጣበት ጊዜ በህግ መሠረት ከጨፌ ቤት አባልነት ይወገዳል፡፡
  4. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቅጽ 6 ድንግጌ እንደአግባብነቱ በየደረጃው በሚኙ ምክር ቤቶች ተፈፃሚነት ይኖረዋል፤

 

 

አንቀጽ 49

የጨፌ ሥልጣንና ተግባር

  1. ጨፌ በዚህ ሕገ መንግስት መሠት የክልሉ ሕግ አውጭ አካል ነው፡፡
  2. የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪበፑብሊ ሕገ-መንግስት ድንጋጌ እንደጠበቀ ሆኖ ጨፌ በክልሉ የውስጥ ጉዳዮች ላይ የበላይ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት ነው፡፡
  3. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 ድንጋጌዎች ሥር የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ጨፌው በተለይ የሚከተሉት ሥልጣንና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፡፡

ሀ.  በዚህ ሕገ- መንግስት መሠረት የፌደራሉን ሕገ-መንግስትና ሌሎች ሕጎችን የማይፃረሩ ልዩ  ልዩ ሕጎችን ያወጣል፡፡

ለ. የሕዝቡን ብዛት፣ የክልሉን ስፋትና ማህበራዊና -ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ግምት ውስጥ በማስገባት በክልሉ ውስጥ ተጨማሪ የአስተዳዳር እርከኖች ወይም የራስ በራስ አስተዳደራዊ አከባቢዎችን ያቋቁማል፡፡

ሐ. የፌደራሉ መንግስት ሥልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ ከአጐራባች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር የሚደረጉ ስምምነት ያፀድቃል፡፡

መ. የራሱን አፈ-ጉባኤ ይመርጣል፣ለምክር ቤቱ ሥራ የሚያስፈልጉትን ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎችን ይሰይማል፡፡

ሠ. ከጨፌ አባላት መካከል ርዕሰ መስተዳድሩን ኘሬዚዳንት ይመርጣል፣ የክልሉን መስተዳድር ምክር ቤት አባላት ሹመት ያፀድቃል፤

ረ. የኦዲትና የቁጥጥር አካል ያቋቁማል፡፡

ሰ. በህጉ መሰረት ምህረት ያደርጋል

ሸ. የክልሉን ሠላምና ፀጥታ ለመጠበቅ የፀጥታና የፖሊስ ኃይል ያቋቁማል፤

ቀ. የክልሉን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች ስትራቴጂዎችና ዕቅዶች ያፀድቃል፤

በ. የክልሉን የመንግስት ገቢ ምንጮች የሚመለከቱ ሕጐችን ያወጣል፤ የክልሉን በጀት  ያፀድቃል፤

ተ. ለማህበራዊ አገልግሎት መስፋፋት፤ ለኢኮኖሚያዊ ልማት መፋጠን  አስፈላጊ የሆኑ ተቋማትን ያቋቁማል፤ያደራጃል፤

ቸ. የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ኘሬዚዳንት፤ ም/ኘሬዚዳንት፤ እና ዋና  ኦዲተሩን ይሾማል፤

ኀ. ለክልሉ መንግስት በተከለለው የገቢ ምንጭ ግብርና ታክስ ይጥላል፤

ነ. የክልሉን የሠራተኛ አስተዳደርና  የስራ ሁኔታዎችን በተመለከተ ሕግ ያወጣል፤

ኘ. በዚህ ሕገ መንግስት አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ /2/ /ከ/ መሠረት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጣል፤

ከ. የክልሉን ኘሬዚዳንትና ሌሎች የክልሉን መንግስት አካላት ባለስልጣናት ለጥያቄ ይጠራል፤ የክልል መስተዳደሩን ምክርቤት አሠራር ይመረምራል፤

 

                           አንቀጽ 50

ስለ ጨፌ አመራር

  1. ጨፌ የራሱ አፈ ጉባዔ ምክትል አፈ ጉባኤና እንደአስፈላጊነቱ ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎች ይኖሩታል፡፡
  2. አፈ ጉባኤና ምክልትል አፈ ጉባኤው አሸናፊ በሆነው ወይም አብላጫ ድምጽ ባገኘው የፖለቲካ ድርጅት/ድርጅቶች አቅራቢነት ከአባላቱ መሃከል ይመርጣሉ፡፡
  3. አፈጉባዔው

ሀ/ የጨፌውን መደበኛ አስቸኳይ ስብሰባዎች ይጠራል፤ ይመራል፤

ለ/ የጨፌን ጠቅላላ ያስተዳደር ሥራዎች ይመራል፤

ሐ/ ጨፌ በአባሎች ላይ የወሰነውን የዲሲፒሊን እርምጃ ያስፈጽማል፡፡

  1. ምክትል አፈ ጉባኤ፡-

ሀ/ በአአ ጉባዔው ተለይተው የሚጡትን ተግባራት ያከናውናል፤

ለ/ አፈ ጉባዔው በማይኖርበት ጊዜ ተክቶ ይሰራል፡፡

  1. የአፈ ጉባዔው ሌሎች ተግባራት በሕግ ይወሰናሉ፡፡

 

                           አንቅጽ 51

የጨፌ የስብሰባ ጌዜና የስራ ዘመን

  1. ጨፌ ቢያንስ ሁለት መደበኛ ስብሰባ ያደርጋል፤
  2. የጨፌ አባላት የስራ ዘመን ለአምስት ዓመት ነው፡፡ የስራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሄዶ ይጠናቀቃል፤ የቀድሞው ጨፌ የስራ ዘመን በተጠናቀቀ በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ አዲሱ ጨፌ ሥራውን ይጀምራል፡፡
  3. የጨፌ መደበኛ ስብሰባ በማይኖርበት ወቅት አፈጉባኤው አስቸኳይ ስብሰባ ሊጠራ ይችላል፡፡ ከጨፌ አባላት መካከል ከአንድ ሶስተኛ በላይ የሚሆኑት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ ከጠየቁ አፈጉባኤው ስብሰባ የመጥራት ግዴታ አለበት፡፡
  4. የጨፌ ስብሰባ በግልጽ ይካሄዳል፤ ሆኖም ስብሰባው በዝግ እንዲካሄድ በአባላቱ ወይም በክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ከተጠየቀና ከጨፌ አባላት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ጥያቄውን ከደገፉት ዝግ ስብሰባ ሊደረግ ይችላል፡፡

አንቀጽ 52

የውሳኔ አሰጣጥና የአሠራር ሥነ ሥርዓቶች

  1. ከጨፌ አባላት መካከል ከሁለት ሶስተኛ በላይ ፤ የሚሆኑት ከተገኙ ምልዓተ ጉባኤ ይሆናል፡፡
  2. ማናቸውም ውሳኔ የሚላለፈው በጨፌ ስብሰባ ላይ በተገኙት አባላት አብላጫ ድምጽ ይሆናል፡፡
  3. ጨፌ አሠራሩንና የሕግ አወጣጥ ሂደቱን አስመልክትቶ ዝርዝር ሕጐችን ሊያወጣ ይችላል፡፡