ኢትዮጵያውያን በብዙ ተስፋም፣ በከፊል ጥርጣሬም እየተመለከቱት ያለው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በተለያዩ ድርብርብ ምክንያቶች የተነሳ ባቀደው ልክ መጓዝ አለመቻሉ በወርኃ የካቲት አጋማሽ ላይ ተሰምቷል። ይኽን ግንዛቤ ውስጥ የከተተው የኢትዮጵያ እንደራሴዎች ምክር ቤትም፣ የኮሚሽኑን ተግዳሮቶች አሳማኝ ሆነው ስላገኛቸውም የተቋሙን ዕድሜ በስምንት ወራት አራዝሟል። ምክር ቤቱ ለ8 ወራት እንዲራዘም የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በሙሉ ድምፅ አጸድቆታል። የእንደራሴዎቹ ምክር ቤት የካቲት 11 2018 ዓ.ም. ባካሄደው የ5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባው፣ ኮሚሽኑ የእስካሁን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ በመወያየት ቀጣይ አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል። ይኽች የእንደራሴ ኹለተኛ ዓመት የመጀመሪያ ዕትምም፣ ይኽን የእንደራሴዎቹን ውሳኔ ተንተርሳ፣ በአገራዊ ምክክር ምንነት፣ በኮሚሽኑ ተግዳሮቶች እና የተቋማችን ምክረ-ሐሳቦች አጠቃልላ በሚከተለው መልኩ ሰፋ ያለ ትንታኔ መስጠትን መርጣለች።
ለምን ወደ ምክክር?
በአገራዊ ምክክር አስፈላጊነት ዙሪያ የተጻፉ ብዙ ድርሳናት እንደሚያወሱት፣ አገራት ብሔራዊ ምክክርን እንዲያካሂዱ የሚያስገድዷቸውን ሁኔታዎች ሲዘረዝሩ በዋናነት የሚጠቅሱት፣ የአንድ አገር መሠረት ወይም የመንግሥት ሕጋዊ ቅቡልና አደጋ ላይ ሲወድቅ መሆኑን አበክረው ያነሳሉ። ያን መሰል አደገኛ ኹኔታ ሲገጥምም፣ አገራዊ ምክክሩ በመንግሥት፣ በፖለቲካ ተዋናዮች እና በኅብረተሰቡ መካከል ያለውን ማኅበራዊ ውል እንደገና መቅረጽን ዓይነተኛ ግቡ አድርጎ ይካሄዳል። ከዛ ባለፈም፣ በለውጥ እና በነባር ኃይሎች መካከል የበረታ ፍጥጫ ሲገጥምም ልሂቃኑ ወደ ምክክር ለመሄድ ተጨባጭ ግፊት እንደሚገጥማቸው ይነሳል። ከዚሑ ጋር በተያያዘም፣ እንደ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች፣ አድማዎች ወይም አብዮቶችን መሰል ከታች ወደላይ የሚነሱ ሰፊ መሠረት የያዙ ግፊቶች መንግሥታትን ወደ ምክክር ጠረጴዛ እንዲመጡም ያስገድዳሉ።ሌላው ሳይጠቀስ የማይታለፈው፣ በትጥቅ ግጭት ወይም በከፍተኛ ፖለቲካዊ አለመግባባት ወቅት ውጥረትን ለማርገብ እና ወደ ሰላማዊ ሽግግር ለመግባት አገራት ፊታቸውን ወደ ምክክር ያዞራሉ።
ምንም እንኳን ብሔራዊ ምክክር እንደ ሳይንሳዊ የጥናት ዘርፍ በቅርብ ጊዜ ጎልቶ ቢወጣም፣ በተግባር ግን ለበርካታ ዐሥርታት በተለያዩ አገራት ሲሠራበት ቆይቷል። በተለይም በደቡብ አፍሪካ፣ ከአፓርታይድ በኋላ የተደረገው የሽግግር ፍትሕ ሂደት እና የዕውነት እና የእርቅ ኮሚሽን ምስረታ ለዓለም የቅርብ ዘመኑ ትልቅ ተሞክሮ ሆኗል። ከደቡብ አፍሪካ ባለፈም፣ እንደ ቤኒን፣ ጋቦን፣ ኮንጎ፣ ቶጎ፣ ማሊ እና ኒጀር ያሉ አገራት የኢኮኖሚ ቀውስን እና የፖለቲካ ተቀባይነት ማጣትን ለመፍታት በተለያዩ ዘመናት ብሔራዊ ጉባኤዎችን አካሂደዋል። ከዓረቡ አብዮት በኋላ በቱኒዚያ እና የመን የተደረጉት ምክክሮችም የፖለቲካ ሽግግርን ለመምራት በጉዳዩ ላይ የተጻፉት ድርሳኖች እንደ ተጨማሪ ምሳሌነት ይጠቀሳሉ።
የአሜሪካ የሕገ-መንግሥት ቀረጻ ሂደት፣ የፖርቱጋል እና የስፔን የ1970ዎቹ የሽግግር ሂደቶች፣ እንዲሁም በታይላንድ፣ አፍጋኒስታን እና ኔፓል የተከናወኑ ተግባራት የብሔራዊ ምክክር መልክ ያላቸው ሂደቶች እንደነበሩም ይታወሳል። ከቶጎ እስከ የመን ባሉት ሂደቶች እንደታየው፣ አገራዊ ቀውሶችን ለመፍታት እና አካታች የሆኑ ድርድሮችን ለማካሄድ፣ አገራዊ እጅግ ተመራጭ መንገድ እየሆነ መጥቷል። ሂደቱ የተሳካ የሚሆነው ግን ኹሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ማካተት ሲችል እና ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ስምምነት ላይ መድረስ ሲችል መሆኑን ልብ ይሏል።
ኢትዮጵያን ወደ ብሔራዊ ምክክር የመራት ምንድር ነው?
ኢትዮጵያን ወደ ብሔራዊ ምክክር የመራት ለዘመናት የተከማቹ ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቅራኔዎች መሆናቸው አሌ አይባልም። ጠቅለል አድርገን እንመልከታቸው ስንልም፣ ከታሪክ ቁስሎች እስከ የማንነት ጥያቄዎች ድረስ ረዘም ያሉ ያልተፈቱ ስር ያላቸው ውዝግቦች መሆናቸውን እንመለከታለን። ኢትዮጵያ በታሪኳ ለችግሮቿ ዘላቂ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ኃይልን እንደ መሣሪያ ስትጠቀም ቆይታለች። ሥልጣን የሚያዘው እና የሚጠበቀው በጉልበት በመሆኑ፣ የአሸናፊዎች ፍትሕ ባህል ሰፍኖ ቆይቷል። በተለይም በዳግማዊ አፄ ምኒልክ የማስፋፋት ሂደት፣ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ማዕከላዊ አስተዳደር እና በደርግ ጭቆና ወቅት የተፈጠሩ ቅሬታዎች እስካሁንም አልተፈቱም።
ከ1983 ወዲህ የሰፈነው በብሔር ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም፣ የታሪክ በደሎችን ለመመለስ ያለመ ቢሆንም፣ አዳዲስ የብሔር ግጭቶችን፣ የሥልጣን ሽኩቻን እና የሀብት ክፍፍል ቅራኔዎችን ወልዷል። ይህ ሦሥት ዐሥርት ያለፈው ሥርዓትም አገራዊ አንድነትን ከመፍጠር ይልቅ ልዩነትን አጉልቷል ተብሎ በአንዳንዶች ይተቻል። ከስምንት ዓመታት በፊትም፣ በተለይም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የተቀሰቀሱት ሰፊ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ለሥልጣን መልቀቅ እና የዶ.ር ዐቢይ አሕመድን አሥተዳደር ወደ ሥልጣን እንዲመጣ ምክንያት ሆነዋል። በፌዴራል መንግሥቱ እና በሕወሓት መካከል የተደረገው አስከፊው የሰሜኑ ጦርነትም ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል። ከእነዚህ በተጨማሪም፣ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የተስተዋሉት የትጥቅ ግጭቶች፣ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በሶማሌ፣ በደቡብ እና በአፋር ክልሎች የሚታዩ የማንነት እና የሀብት ግጭቶች አገሪቱን ወደ ምክክር እንድትገባ አስገድደዋታል ቢባል ተጨባጩን ሃቅ አጠር አድርጎ ማቅረብ ብቻ ይመስለናል።
ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ፦ የጎርዲያኑ ቋጠሮ?
ብዙዎች ብዙ እያሉበት ያለው እና ቀጣዮቹ ስምንት ወራት ወሳኝ ናቸው የተባለለት አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ፣ እስከዛሬ ከሰበሰባቸው አጀንዳዎች አኳያ እና ከነባሩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አኳያ፣ ከባዱ ተግዳሮቱ በሕገ-መንግሥቱ ዙሪያ ሊያካሂድ የሚችለው አገራዊ ምክክር እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። የተሰበሰቡት አጀንዳዎችም ሆኑ፣ በቀጣይ የአጀንዳ ማሰባሰብ ይካሂድባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁት ክልሎች እና አካባቢዎች አንጻርም ስንመለከትም፣ እጅግ ብዙዎቹ አጅንዳዎች እና ቀጣይ ተሳታፊዎች ምክክር ያስፈልጋቸዋል ብለው የሚያነሷቸው አጀንዳዎች በአንድ ሰነድ ዙሪያ የሚሽከረከሩ ይመስላል፤ በሕገ-መንግሥቱ ዙሪያ። ይኽን ርዕሰ-ጉዳይም፣ የምክክር ኮሚሽኑ የጎርዲያን ቋጠሮ* ብለን ብንሰይመው ከእውነቱ ብዙም አንርቅም።
ባለፉት ብዙ ዓሥርታት የተካሄዱት የፖለቲካ ግጭቶች በኢትዮጵያ ላይ ከፍ ያለ ጉዳት አድርሰዋል። ይህም በእጅጉ የተከፋፈለችውን አገር ወደ አንድ ለማምጣት የሚደረጉ ረዥም ጥረቶችን አስከትሏል። በኢትዮጵያ የተለያዩ ሕዝቦች መካከል በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ስምምነት አለመኖሩም ለአገረ-መንግሥቱ አለመረጋጋት መሠረታዊ ምክንያት ሆኗል። በተለይም የ1987ቱ የፌዴራል ሕገ-መንግሥት ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ፣ ሰነዱ አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። በብሔር እና በቋንቋ ላይ የተመሰረተው የመንግሥት መዋቅር እንዲሁም ለ“ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች” የተሰጠው የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ስፋት ዋነኛው የአለመግባባት ማዕከሎች ናቸው። የሥርዓቱ ደጋፊዎች እና ተቺዎች መካከል ያለው ልዩነት በ2010 ከተካሄደው የፖለቲካ ሽግግር በኋላም ይበልጥ ጎልቶ ታይቷል። የብልጽግና ፓርቲም፣ ሕገ-መንግሥታዊ ቀውሱን የመፍታትን አስፈላጊነት እንደሚገነዘብ እና በስምምነት ላይ የተመሰረተ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያን እንደሚደግፍም ሲገልጽ ተስተውሏል።
መንግሥት አስፈላጊውን ስምምነት ለመፍጠር የመረጠው መንገድ ብሔራዊ ምክክርን ሲሆን፣ ይህም ከሦሥት ዓመታት በፊት በእንደራሴዎች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ሲቋቋም የተጀመረ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሕገ-መንግሥቱን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ወደ ምክክሩ እየተመሩ ሲሆን፣ ማሻሻያ እንዲደረግ የሚቀርቡ ጥሪዎችም እውን የመሆን ዕድል ያላቸው ይመስላሉ። በመሆኑም ብሔራዊ ምክክሩ ለሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ወሳኝ ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሎም ተገምቷል። በመጀመሪያ ደረጃ የማሻሻያ አስፈላጊነት መኖሩን እንደሚያረጋግጥ እና አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም የሚፈለጉትን የለውጥ ዝርዝሮች እንደሚያሰባስብ ይጠበቃል። በተጨማሪም ምክክሩ በተለያዩ አመለካከቶች ባሏቸው ተሳታፊዎች መካከል ስምምነትን ለመፍጠር ያለመ ነው። አገሪቱ ያለችበትን ጽንፍ የረገጠ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ይህንን ግብ ማሳካት ያለውን አስቸጋሪነት አሳንሶ ማየት እንደማይቻል ግን ማስታወስ ያሻል።
*የጎርዲያን ቋጠሮ (Gordian Knot) የሚለው አገላለጽ መነሻው ጥንታዊው የግሪክ ተረታ-ተረት ሲሆን፣ ትርጉሙም እጅግ ውስብስብ እና በቀላሉ የማይፈታ ችግርን ያመለክታል። ተረኩ እንደሚለው፣ የፍርግያ ንጉሥ የነበረው ጎርዲየስ ጋሪውን ከእንጨት ምሶሶ ጋር በጣም ውስብስብ በሆነ ቋጠሮ ያስረዋል፤ ቋጠሮውም የገመዱ ጫፎች የማይታዩበትና ማንም ሊፈታው የማይችል ነበርም ተብሏል። ቋጠሮውን እንዲያ ካጠበቀው በኋላም፣ “ይህንን ቋጠሮ የፈታ የእስያ ንጉሥ ይሆናል” የሚል ትንቢትም መናገሩ ተጽፏል። ይኽን ትንቢት እየሰማ ያደገው ታላቁ እስክንድርም፣ በተለመደ ኹሉን ቻይ ጥማቱ ቋጠሮውን ሊፈታው ሻተ። በ333 ዓ.ዓ. ላይ ወደ ፍርግያ የመጣው እስክንድር፣ ቋጠሮውን ለመፍታት ብዙ ቢሞክርም አልተሳካለትም። በመጨረሻም እስክንድር የተለየ መፍትሔ አመጣ፤ ተረታ ተረቱ እንደሚለውም፣ ሰይፉን መዝዞ ቋጠሮውን በመቁረጥ ለሁለት ሲሰነጥቀው ገመዱ ወዲያው ተፈታ። የዚኽ ተረክ ትዕምርታዊ ትርጉምም፣ አንድን ውስብስብ ችግር በቀጥታ እና ባልተለመደ ደፋር እርምጃ መፍታትን ያመለክታል።
ሰፊ መሠረት ያለው ብሔራዊ ምክክር አስፈላጊነት በሰፊው ተቀባይነት ያለው ሲሆን፣ አካታች የሕዝብ ተሳትፎ ለስኬታማ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ሂደት ቁልፍ ነው። ሆኖም አሁን ያለው ምክክር እውነተኛ ስምምነት ሊያመጣ ወይም ለሕገ-መንግሥታዊ ቀውሱ መፍትሔ ሊሰጥ ይችላል ብለው የሚጠራጠሩ ብዙዎች ናቸው። እንዲያውም በቂ ስምምነት ሳይኖር የሚደረግ ማሻሻያ ግጭቱን ሊያባብሰው ይችላል የሚሉ ስጋቶች ከተለያዩ ፖለቲከኞች እየቀረቡ ነው።
ምክክሩ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ልዩነት ያላቸውን የፖለቲካ እና የአስተያየት መሪዎችን እንዲሁም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ሕዝባዊ ውይይት በማምጣት ብሔራዊ ስምምነትን ለመፍጠር ያልማል። አሥራ አንድ አባላት ያሉት ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን የእነዚህን ልዩነቶች መንስኤ የመለየት፣ አጀንዳዎችን የመቅረጽ እና በክልል እና በብሔራዊ ደረጃ አካታች መድረኮችን የማመቻቸት ሥልጣን ተሰጥቶታል። ኮሚሽኑ በምክክሩ ውጤቶች ላይ በመመስረት የውሳኔ ሐሳቦችን የማቅረብ፣ እንዲሁም አፈጻጸማቸውን የመደገፍ እና የመከታተል ኃላፊነትም አለበት። ከተሰጠው ሰፊ ተግባር በተጨማሪ ኮሚሽኑ በትከሻው ላይ ብዙ ሸክሞችን ተሸክሟል። ይህም የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ የወደፊቱን የኢትዮጵያ መንግሥት መዋቅር የሚወስን በመሆኑ አገሪቱን ወደ ሰላም ወይም ወደ ተጨማሪ ጦርነት ሊመራት የሚችል ትልቅ ፋይዳ ስላለው ነው። የኮሚሽኑ ግኝቶች እና ጥቆማዎች ለሕገ-መንግሥታዊ ለውጦች እና ለሚከተሉት ሂደቶች መሠረት የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ማንኛውም የሚመጣ ማሻሻያ ተቀባይነት እንዲኖረው በኮሚሽኑ ላይ ያለው የሕዝብ አመኔታ እንደ ገለልተኛ አስታራቂነቱ ወሳኝ መሆኑን አንስተን እንለፍ።
ከዚህ አንጻር በርካታ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮሚሽኑ ከመንግሥት ያለውን ነፃነት ሲተቹ እና የሂደቱን ቅንነት ሲጠራጠሩ ቆይተዋል። የሚያሳስበው ደግሞ በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምክክሩ ላይ ላለመሳተፍ መወሰናቸው እና መውጣታቸው ነው። ምንም እንኳን ብዙ ፓርቲዎች በኋላ ላይ ቢመለሱም፣ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች አጀንዳ በሚሰበሰብበት ወቅት ተሳትፎው እንደገና እየቀነሰ መጥቷል። በታኅሣሥ ወር የእናት ፓርቲ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)ን ጨምሮ ሰባት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሁለት የተለያዩ መግለጫዎች የብሔራዊ ምክክሩ ስኬታማ የመሆን ዕድል እየጠበበ መምጣቱን ገልጸዋል። ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት ኮሚሽኑ ተሳታፊ ያልሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወደ ምክክሩ ለመመለስ ጥረት እያደረገ ነው። ከጥቂት ወራት በፊትም ኮሚሽኑ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ ከመኢአድ እና ከእናት ፓርቲ ጋር ውይይት ማድረጉን ገልጾ፣ ሁሉም ፓርቲዎች ግን ለመመለስ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል። እነዚህም ቀጣይነት ያላቸው ግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ እና ተዋጊዎች በብሔራዊ ምክክሩ እንዲካተቱ፣ እንዲሁም የተገለሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የታሰሩ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና አክቲቪስቶች በምክክሩ እንዲሳተፉ የሚሉ ናቸው። ፓርቲዎቹ እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት በዋነኝነት በመንግሥት አካላት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ያምናሉ። ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት ከተሳትፎ ውጪ ያሉ ሌሎች ፓርቲዎች ጋር ውይይቱን እንደሚቀጥልም ገልጿል።
በዚኽ ንዑስ ርዕስ ስር ከጠቀስነው የሕገ-መንግሥቱ የጎርዲያን ቋጠሮነ አንጻርም፣ የተለያዩ አመለካከቶች በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ታይተዋል። ለምሳሌ በኦሮሚያ ተሳታፊዎች ካነሷቸው ነጥቦች መካከል የመዲናዋ አዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ መጠቃለል፣ የመገንጠልን መብት ጨምሮ የብሔሮች ራስን የመወሰን መብቶች መጠበቅ እና አከራካሪው ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ የብሔር እኩልነት ምልክት በመሆኑ ሳይለወጥ እንዲቆይ የሚሉ ይገኙበታል። እነዚህ የሕገ-መንግሥት ድንጋጌዎች በአማራው ክልል መድረኮች ላይ ደግሞ የበረታ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ መሰል ልዩነቶቹ በፌደራሎቹ ክልሎች መካከልም ተስተውለዋል። በክልል ደረጃ የብሔር ራስን የመወሰን ድጋፍ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ እና በደቡብ በሚገኙ አዳዲስ ክልሎች ዘንድ ድጋፍ ሲኖረው፤ በአማራ ክልል ደግሞ ሕገ-መንግሥቱ ከልክ በላይ በብሔር ላይ ያተኮረ ነው በማለት ማሻሻያ እንዲደረግ መጠየቅ ተጀምሯል። ሂደቱ ከቀጠለ አሥራ ሁለቱም ክልሎች በሆነ መንገድ በማሻሻያው ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ይኖራቸዋል። በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የተቀመጡት የማሻሻያ ድንጋጌዎች በጥብቅ የሚከተሉ ከሆነ፣ ማንኛውም ክልል የፌዴሬሽኑ እኩል አባል እንደመሆኑ መጠን በብሔር ራስን ማስተዳደር መብቶች ላይ የሚቀርቡ የማሻሻያ ሐሳቦችን ውድቅ የማድረግ ሕገ-መንግሥታዊ አቅም አለው። በዚህ ረገድ ስምምነት ላይ መድረስ እያንዳንዱ ክልል ለብሔራዊ አንድነት ሲባል የራስን ማስተዳደር መብቱን በተወሰነ ደረጃ መተው ሳይጠበቅበት አይቀርም፤ ይህ ደግሞ ቢያንስ በአሁኑ ተጨባጭ ኹኔታ ሊሆን የማይችል ይመስላል።
በቅርብ ጊዜ ውስጥ በሆነ መንገድ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ሊደረግ የሚችልበት እውነተኛ ተስፋ ቢኖርም፣ ግጭቶችን በማለዘብ እና ሰላምን በማምጣት ረገድ ያለው የስኬት ዕድል ግን ሩቅ ይመስላል። እንዲያውም የሕገ-መንግሥት ለውጥን የሚደግፉትን ጨምሮ ብዙዎች አሁን ያለው የማሻሻያ መንገድ ትርምሱን ሊያባብሰው ይችላል የሚል ስጋት አላቸው፤ ከብሔር ፌዴራሊዝም በድንገት የመውጣት አደጋዎችም ከበርካታ ወገኖች በተደጋጋሚ ሲነሱ ይደመጣሉና።
ምን ተብሎ ነበር?
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ፣ ባሳለፍነው የካቲት ወር ዕድሜዬ ይራዘምልኝ ሲል ያቅረባቸውን ዋና ዋና ምክንያቶች ከማየታችን በፊት፣ ከዚኽ ቀደም በኮሚሽኑ ከተነገሩት ውስጥ ከዓመት በፊት የተነገረውን ብንጠቅስ ርዕሰ-ጉዳያችንን ምልዑ ያድርግልናል። ኅዳር 10 2017 ዓ.ም. ላይ የተሰበሰበው የእንደራሴዎቹ ምክር ቤት፣ በዚኹ ጉዳይ ላይ ተወያይቶ እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱም፣ ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል አጀንዳ እና ተሳታፊዎችን ለመለየት የእንደራሴዎቹ ምክር ቤትን እገዛ እንደሚፈልግ ገለጾ ነበር። የምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው “አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር ጠንካራ ሥራ በጋራ ተቀናጅተን እንሠራለን። ከክልሉም ጋር እንመካከራለን” ብለዋል። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያም፣ ኮሚሽኑ ያከናወናቸውን እና ቀሪ ሥራዎች ለምክር ቤት አባላት አብራርተው ነበር። “ዛሬ ላይ ለእናንተ ሥራችንን ጨርሰን የምንወጣበትን ሪፖርት ነበር ማቅረብ ያለብን” ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ተቋማቸው ይህን እንዳያደርግ ምክንያት የሆኑ ክፍተቶችንም ጠቃቅሰው ነበር። ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ ቦታዎች ያጋጠሙት ሁኔታዎች ከእነዚህ ክፍተቶች መካከል መሆናቸውን ፕ/ር መስፍን ገልጸዋል። “ምዕራብ ኢትዮጵያ ችግር በነበረበት ወቅት ነው የእኛ ሥራ የተጀመረው” ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ “ምዕራብ ኦሮሚያ በተመሳሳይ መልኩ ችግሮች ያጋጥማሉ። አማራ ስንጀምር ችግር አልነበረም፤ በአሁኑ ሰዓት ግን አስቻይ ሁኔታ እና አንጻራዊ የሆነ ሰላም ያስፈልጋል” ብለዋል። ፕሮፈሰር መስፍን ምዕራብ ኢትዮጵያ ነበር ያሉት ችግር ተቀርፎ ኮሚሽኑ በቤኒሻነጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ክልሎች ሥራውን ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቁን ጠቅሰው፣ በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታም በዚያ ሪፖርታቸው ጠቅሰውት ነበር።
ዋና ኮሚሽነሩ “የትግራይ አረጓዴ መብራት አግኝተን ሙሉ በሙሉ ሥራዎች መሠራት አለባቸው፤ ግን በዚያ በኩል ደግሞ የሚቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፤ ይህ እንግዲህ የሕዝብ ተወካዮች ኃላፊነት ነው ብለን ነው የምናምነው” ብለዋል። “ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጋር የተወሰነ ጊዜ በመውሰድ መክረናል” ያሉት ፕ/ር መስፍን፤ “በዚያ ምክክር ላይ የተግባባነው ነገር ቢኖር ይህን የአገራዊ ምክክር ሂደት በእርግጥም እንደሚያምኑበት፣ የአገራዊ ምክክር ሂደትን በመርኅ ደረጃ እንደሚቀበሉት እና ተገቢ እንደሆነም ነግረውናል” ሲሉ ተናግረዋል። ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም “ሁኔታዎች በሚመቻቹበት ጊዜ ካቢኔውን እና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እንደምናነጋግር እና እንደሚያገናኙን ቃል ገብተውልን ነበር” ብለዋል። ከፕሬዝዳንቱ ጋር ተደጋጋሚ ስብሰባዎች መደረጋቸውን የጠቀሱት ፕ/ር መስፍን ለምክር ቤት አባላቱ “ግልጽ በሆነ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ወደ ትግራይ የገባንበት አካሄድ የለም” ብለዋል። ዋና ኮሚሽነሩ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት “ግልጽ ናቸው” ያሏቸውን ምክንያቶች ግን አልዘረዘሩም።ኮሚሽኑ ከትግራይ ክልል ነዋሪዎች ጋር ውይይቶችን ባያደርግም ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና በክልሉ ከሚገኙ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ጋር ውይይቶች መደረጋቸውን ዋና ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
ፕ/ር መስፍን ሪፖርታቸውን ካቀረቡ በኋላም እንደራሴዎቹ ጥያቄዎችን አቅርበዋል። የቀረቡት ጥያቄዎች በዋናነት ከታጠቁ ቡድኖች ተሳትፎ፣ የኮሚሽኑ የሥራ ዘመን እንዲሁም የአማራ፣ የኦሮሚያ እና የትግራይ ክልል ተሳታፊዎች እና አጀንዳ ልየታ ላይ ያተኮሩ ነበሩ። በዚያ ዕለትም ፕ/ር መስፍን በቀሩት ሦስት ወራት ውስጥ አወያይታችሁ፣ ምክረ ሃሳብ ሰብስባችሁ ሪፖርት በማቅረብ ታጠናቅቃላችሁ ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ “እኛ የካቲት 14/2014 ቃለ መሃላ ስንፈጽም ከአንድ ሰዓት በኋላ አፈ ጉባኤው በመሩት ስብሰባ ላይ ተገኝተን ስንነጋገር ቃል የገባነው በሦስት ዓመት ውስጥ ሥራችንን ልንጨርስ ነው። ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ሥራችንን እየሠራን አገባደን እናንተ ፊት መቅረብ ነው የእኛ አጀንዳ” ሲሉ መልሰውም ነበር። ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም “ጊዜን በተመለከተ እኛ ይሄን ያህል ጊዜ ይሰጠን ወይም እንዲህ ይደረግልን ለሚለው ጥያቄ አይደለም ዝግጁነታችን። እኛ ዝግጁነታችን አሁንም በዚህ በቀረን ጊዜ ሠርተን የት መድረስ እንችላለን የሚል ነው” ብለዋል። የኮሚሽኑን የሥራ ጊዜ ማራዘምን በተመለከተም፤ “ስታቋቁሙ እናንተ ናችሁ ያቋቋማችሁት፤ ሦስት ዓመት ብላችሁ የወሰናችሁት እናንተ ናችሁ። ከዚህ በኋላ ይብቃኝ ማለት መብት አላችሁ፤ ይቀጥል ማለትም መብት አላችሁ። ስለዚያ ምንም እኛ የምንለው ነገር የለም። ነገር ግን በጊዜ ሂደት ከአፈ ጉባኤው እና ከሚመለከታችሁ አመራሮች ጋር ቁጭ ብለን በዝርዝር የምናስረዳበት ሂደት ግን አለ” ሲሉ አብራርተዋል።
ለምን ይራዘምልንስ አሉ?
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለአንድ ዓመት የተራዘመለት የሥራ ጊዜው ሊያበቃ አንድ ሳምንት ብቻ ሲቀረው፣ ለቀጣዮቹ ስምንት ወራት ይራዘምለት ዘንድ እንደራሴዎቹ ፍቃዳቸው ሆኗል። ኮሚሽኑ ሥራውን እንዲያጠናቅቅ በሚል የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ዓመት የካቲት 11፤ 2017 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰብ ነበር ጊዜው ለአንድ ዓመት ያራዘመው። ኮሚሽኑ የግማሽ ዓመት ሥራውን በምክር ቤቱ ለዴሞክራሲ ፖዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርብ እስካሁን የተሰበሰቡ አጀንዳዎች በሚገባ ተብላልተው በተረጋጋ ኹኔታ መታየት ያለባቸው በመሆኑ ጊዜ አንደሚያስፈልገው ገልጿል። እስካሁን የኮሚሽኑ ሥራ ያልተጀመረበትን ትግራይ ክልል በተመለከተም የግድ መሳተፍ እንዳለበት ተገልጾ፣ ሕዝብ መታገት የለበትም በሚልም ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ኮሚሽኑ የስድስት ወራት ሥራውን አርብ ጥር 29 ቀን 2018 ዓ.ም. በእንደራሴዎቹ ምክር ቤት ለሚገኘው የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርብ ይህ ርዕሰ0ጉዳይ ጉዳይ ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ተቋሙ አጀንዳ የመሰብሰብ ሥራው ተጠናቆ ጥር 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ዋናው ምክክር ለመግባት አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ሥራው በትግራይ ክልል ባለመጀመሩ የምክክሩ ጉባኤው መቼ እንደሚጀመር ለመግለጽ አስቸጋሪ እንደሆነበት ጠቅሷል። ኮሚሽነር ዘገየ አስፋውም፣ ይህንን በስፋት ካነሱት የተቋሙ መሪዎች አንዱ ነበሩ። እርሳቸውም፣ “በመቻኮል ፍሬ ቢስ እንዳናደርገው አታቻኩልን” ብለዋል። ይህንን በታላቅ ተስፋ ሕዝብ የሚጠባበቀውን ያሉትን የምክክር ሥራ ውጤት ጊዜ አሳጥረን ውሽልሽል ነገር ማቅረብ የለብንም ያሉት ኮሚሽነር ዘገዬ፣ የተሰበሰበውን አጀንዳ ለመለየት ራሱ ከፍተኛ ችግር እንደሆነ እና አጀንዳ ለመለየት ሥነ ሥርዓት ብናበጅም ገና አልገባንበትም የሚለው ለዚህ አቋማቸው ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ሌላኛው ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር በፊናቸው፣ ሥራው በትግራይ ክልል አለመጀመሩን መነሻ በማድረግ ሕዝብ መታገት የለበትም ሲሉ አሳስበዋል። በትግራይ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ተከትሎ ያሉትን ሥራዎች ከክልሉ ውጪም ቢሆን ኮሚሽኑ ለምን በሚመቸ ቦታ አያደርግም በሚል ለቀረበለት ጥያቄ ይህ የሚሆን እንዳልሆነ ዋና ኮሚሽነሩ ምላሽ ሰጥተዋል። “ምክክር መቼ ያልቃል? በቀላሉ የሚገመት እና የሚነገር ሂደት አይደለም”ም ብለዋል። አክለውም በሚቀጥሉት ወራት እንዴት ማስጀመር እንችላለን ሲሉ የምክር ቤቱን ከፍተኛ እገዛ እንሻለን ሲሉ ከዓመት በፊት ያሉትን ደግመውታል።
ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት የገጠሙትን ከፍተኛ ችግሮች እና አሁንም እየፈተኑኝ ነው ያላቸውን አራት ጉዳዮችን ለይቶ ለምክር ቤቱ አቅርቧል። ኮሚሽኑ ገጠሙኝ ያላቸውን ፈተናዎች በዋናነት ከሠላምና ጸጥታ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ለምክር ቤቱ የተበተነው ሪፖርት ያመላክታል። የምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳ በማሰባሰብ ሂደት ተለዋዋጭ እና ፈታኝ ተግዳሮቶች እንደገጥሙት በሪፖርቱ ገልጧል። ሥራው በበርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች የተሞላ መሆኑን የገለጠው ኮሚሽኑ፣ በተለይም የግጭት ተጽእኖ ቀዳሚው ነው ብሏል። ኹለተኛው ኮሚሽኑ ገጥሞኛል ያለው ፈተና ከነጻነትና ገለልተኝነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው ብሏል። ከኮሚሽኑ ነጻነትና ገለልተኝነት ጋር በተያያዘ የተዛቡ መረጃዎች ስርጭት ከፍተኛ ፈተና መሆኑንም በሪፖርቱ ተገልጧል። አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በራሳቸው ሲል ኮሚሽኑ በጠራቸው ምክንያቶች በምክክር ሂደቱ አለመሳተፋቸው ተግዳሮት እንደሆነበትም ጠቁሟል፡፡ በአራተኛነት የተቀመጠው የኮሚሽኑ ፈተና የታጠቁ ቡድኖች ተሳትፎ አለመኖር ነው። በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ ወገኖችን ለማሳተፍ ምቹ ሁኔታ አለመኖሩ፣ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነበት ኮሚሽኑ ለምክር ቤቱ ባቀረበው ሪፖርት አስታውቋል። ኮሚሽኑ የታጠቁ ቡድኖች በምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ ለማስቻል ዝግጁነት እንዳለው የገለጠ ቢሆንም፣ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት ግን ከመንግሥት እና ከታጣቂ ቡድኖች ተጨማሪ ጥረቶች ያስፈልጋሉ ብሏል።
ትችቶቹ ምንድር ናቸው?
በዚኽ ንዕስ ርዕስ ስር ጠቅለል አድርገን ልንጠቅሳቸው የምንሻቸው ትችታዊ ነጥቦች፣ በቀጣይ ኮሚሽኑን ለሚቆጣጠረው የእንደራሴዎቹ ምክር ቤትም ሆነ ለኮሚሽኑ ፋይዳ ይኖራቸዋል ብለን እናምናለና፣ አጠር አድርገን እናንሳቸው።
- ተዓማኒነትና ገለልተኝነት፦ አንዳንድ የኮሚሽኑ አባላት ከገዥው ብልጽግና ፓርቲ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል በተለያዩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች እና አንዳንድ ተንታኞች ዘንድ በጥርጣሬ ሲነሳ ይስተዋላል። ኮሚሽነሮቹ የተመረጡበት ሂደትም ግልጽነት የጎደለው እና ተቃዋሚዎችን ያላሳተፈ ነው በሚልም ጥያቄ ይነሳበታል።
- የፖለቲካ መጠቀሚያ የመሆን ስጋት፦ የብልጽግና መንግሥት ኮሚሽኑን ሥልጣኑን ለማቆያ፣ የዓለም ዓቀፉን ማኅበረሰብ ድጋፍ እና ብድር ለማግኛ እንደ መሣሪያ እየተጠቀመበት ነው የሚል ክስም ይሰማል።
- ወንጀሎችን የመሸፋፈን ሙከራ፦ መንግሥት በአማራ፣ በትግራይ እና በወለጋ አካባቢዎች ላይ ተፈጽመዋል የሚባሉ የጦር ወንጀሎችን እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በምክክሩ ሰበብ ለመሸፈን እየሞከረ ነው የሚል ጠንካራ ትችትም ይነሳል።
- የአካታችነት ጉድለት፦ ትርጉም ላለው የሰላም ሂደት ወሳኝ የሆኑ ዋና ዋና የፖለቲካ ኃይሎችን እና የታጠቁ ቡድኖችን ወደ ምክክሩ ለማምጣት መንግሥትም ሆነ ኮሚሽኑ በቂ ጥረት አላደረገም የሚል ቅሬታ አለ።
- በቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር፦ ኮሚሽኑ ለግጭቶች መንስኤ የሆኑትን መሠረታዊ የፖለቲካ ችግሮች ከመፍታት ይልቅ፣ በቴክኒካዊ እና በሥነ-ሥርዓት ጉዳዮች ላይ መጠመዱ ችግሩን ለመፍታት ያለውን ቅንነት ጥያቄ ውስጥ ከቶብናል የሚሉ ድምጾችም ይደመጣሉ።
የብሪጅ ምክረ-ሐሳቦች
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ፊት የተጋረጡት ችግሮች ለኢትዮጵያ ብቻ ለየት ብለው የተከሰቱ አይደሉም። ታሪክ እንደሚያሳየው መዋቅራዊ ድክመቶች፣ አለመተማመን እና በልሂቃን መጠለፍ የተነሳ በሌሎች አገራትም ብሔራዊ ምክክሮች በተደጋጋሚ ለውድቀት ተዳርገዋል። በደቡብ ሱዳን የሰላም ግንባታ ሂደት ልሂቃንን በማግለል፣ በታሪካዊ ቅሬታዎች እና በብሔር ክፍፍል ምክንያት ተስፋ የተደረገበት አገራዊ ምክክር ተሰናክሏል። በሌላ በኩል በላይቤሪያ ከጦርነት በኋላ የመጣው ዕርቅ አሉታዊ ሰላም ብቻ ሆኖ ቀርቷል፤ ይህም በመንግሥት እና በተቃዋሚዎች ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል ለትጥቅ መፍታት መዘግየት እና ላለመተማመን ምክንያት ሆኗል። የመን፣ ቻድ እና ስሪላንካም ተመሳሳይ የክሽፈት ምሳሌዎች ናቸው። እነዚህ ሁኔታዎች የሚያረጋግጡት አንድ መራራ እውነት አለ፤ ያለ አካታች ተወካዮች፣ ያለ ተቋማዊ ነፃነት እና ያለ ገለልተኛ የአፈጻጸም ሥርዓት እጅግ ተስፋ ሰጪ የሚባሉ ምክክሮች እንኳን መክሸፋቸው። ከዚኽ አንጻርም፣ ብሪጅ ተከታዮቹን ነጥቦች በምክረ-ሐሳብ ደረጃ ለማቅረብ ትሻለች። ወደ ጥቅል ምክረ-ሐሳቦች ለመሄዳችን በፊት ግን፣ የእንደራሴዎቹ ምክር ቤት በዚኽ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ይኖርበታል ብለን የምናምናቸውን ሐሳቦች አጠር አድርገን እንጥቀስ፡
እንደ ብሪጅ መረዳት፣ የእንደራሴዎቹ ምክር ቤት ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽንን በዐዋጅ ያቋቋመ የበላይ አካል እንደመሆኑ መጠን፣ ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆንና አመኔታ እንዲያገኝ የሚከተሉት ወሳኝ ሚናዎች ሊኖሩት ይገባል፦
- የክትትል እና የቁጥጥር ሚና፦ ምክር ቤቱ ኮሚሽኑ ሥራውን በገለልተኝነት እና በአካታችነት እያከናወነ መሆኑን እስከ አኹን ካደረገው በላይ በቅርበት መከታተል ይኖርበታል፤ ስለምን ቢሉ፣ ከዚኽ በኋላ ያሉት የኮሚሽኑ ጊዜያት እጅጉን ወሳኝ ናቸውና።
- የኮሚሽኑን አፈጻጸም ሪፖርት መገምገም፦ ምክር ቤቱም ሆነ የሚመለከተው የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ኮሚሽኑ በየጊዜው የሚያቀርባቸውን ሪፖርቶች ሲገመግም፣ በዝግጅት እና በሂደት ምዕራፎች የታዩ የአካታችነት ጉድለቶች እንዲታረሙ ግፊት ማድረግ ይኖርበታል እንላለን።
- የኢፌድሪ የእንደራሴዎች ምክር ቤት፣ ቀዳሚ ህልውናውን የሕዝብ ውክልና ነውና፣ ኮሚሽኑ ከአድሎአዊነት ነፃ መሆኑን እና ለሕዝብ ግልጽ መሆኑን ሳያሳልስ ለማረጋገጥ ከዚኽ ይበልጥ መጣር ይኖርበታል እናላለን።
- ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ ካነሳቸው ተግዳሮቶቹ ዋንኛው፣ ታጣቂ ኃይሎችን ለማሳታፍ መቸገሩ መሆኑ ይታወቃል፤ ከዚኽ አንጻርም፣ ምክር ቤቱ ለታጣቂዎቹ የሕግ ከለላ የሚሰጥበትን መላ ቢያበጅ፣ የታጠቁት ቡድኖች ያለ ስጋት በምክክሩ እንዲሳተፉ የሚያስችላቸው ይመስለናልና፣ ቢታሰብበት ስንል የዜግነት ኅላፊነታችንን ተንተርሰን ጥሪ ማድረግ እንፈልጋለን።
ሌላይኛው የምክረ-ሐሳባችን ማጠንጠኛ ራሱ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሲሆን፣ ጥቂት ሐሳቦችን ማዋጣት ደግሞ ተቋማዊ ኅላፊነታችን ነውና፣ የሚከተሉትን ነጥቦች ኮሚሽኑ ቢመለከታቸው ቀሪ ሥራዎቹን ያቀልለታል ብለን እናምናለን።
- እስከ ዛሬ ድረስ ኮሚሽኑ የተከተለው የተሳታፊዎች የመረጣ ስልት፣ ከታች ወደ ላይ የሚሄድ አካሄድን መሆኑ ይታወቃል። ይኽ የአመራረጥ ስልትም፣ የየአካባቢዎችን እውነተኛ የግጭት መንስኤዎች እና ተዋናዮችን ችላ ይላል የሚሉ ስጋቶችን ተቋማችን ታዝባለች። ተሳታፊዎችን ወረዳ ጀምሮ መምረጥ በቡድኖች መካከል ያለውን አግድምዮሽ ግጭቶች እና ቁርሾዎች ይሸፍናል የሚል ተያያዥ ስጋትም አለ። ይኽ አካሄድም ዋና ዋና የግጭት ተዋናዮች ሳይካተቱ እንዲቀሩ ያደርጋልና፣ ባሉት ስምንት ወራት ይኽን ተቋማዊ አካሄድ ኮሚሽኑ በቻለው ልክ ለማስተካከል ቢጥር ፋይዳው ብዙ ነው እንላለን።
- ኮሚሽኑ ተሳታፊዎችን በዘጠኝ የኅብረተሰብ ዘርፎች የመደበበት መንገድም እንዲኹ ከትችት አላመለጠም። ስለምን ቢሉ፣ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ቀውስ መሠረት ነው የሚባለውን የብሔር እና የሃይማኖት ማንነትን ግምት ውስጥ አላስገባምና። በተለይም፣ የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግር በብሔርተኝነት እና በማንነት ፉክክር ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ፣ ተሳታፊዎቹን በሙያ ወይም በኑሮ ኹኔታ ብቻ ማቧደን ይህንን መሠረታዊ ችግር ችላ ይላል። እናም፣ ኮሚሽኑ ይኽንን ተቋማዊ ዝንፈትም ቢያርመው በጎ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ስትል ብሪጅ ምክረ-ሐሳቧን ማቅረብ ትሻለች።
- የተቋማት ቅሬታም ሲነሳ ይሰተዋላል፤ ለማሳያ ያህልም፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተገልያለሁ በሚል ቅሬታ ማቅረቧ ይታወሳል። ከዚኽ አንጻርም፣ ኮሚሽኑ እንደ ሃይማኖት እና ብሔር ያሉ የማንነት ስብስቦችን እንደ አንድ የጋራ አካል ማሳተፍ አለመቻሉን ያሳያልና፣ ይኽም እርምት የሚደርግበት ኹኔታ ቢፈጠር፣ ኮሚሽኑ ላይ ያለው ሕዝባዊ ተስፋ ወደ መሬት ይወርዳልና ቢታስብበት እንላለን።
- አጀንዳዎችን አለመተው አልያም አለማቅለል፤ ኮሚሽኑ አጀንዳ የማስተካከል ሕጋዊ ሥልጣን ቢኖረውም፣ ከተሳታፊዎች እና ከተለያዩ ወገኖች የሚቀርቡ አጀንዳዎች ተቀባይነት እንዲያገኙ እና ያለ አግባብ እንዳይጣሉ ማረጋገጥ ይኖርበታል፤ ይኽንንም፣ ይፋዊ እና ሕዝባዊ መድረኮችን በመጠቀም ቢከውናቸው የተቋሙን ተዓማኒነት ከፍ ያደርጋልና፣ ቢታሰብበት ስትል ብሪጅ መጥቀስ ትፈልጋለች።
ከላይ በምክረ-ሐሳብ ደረጃ ያነሳሳናቸውን ምክረ-ሐሳባዊ ነጥቦችንም፣ በሚከተለው አጭር ሰንጠረዥ ጠቅለል አድርገን በማቅረብ፣ የወሩን የብሪጅ ዳሰሳ እናገባድ፤
የምክክሩን ሂደት የሚያሳልጡ ቁልፍ ተግባራት
| የትኩረት መስክ | መወሰድ ያለበት እርምጃ | የሚጠበቅ ውጤት |
| አካታችነት | የታጠቁ ቡድኖችን እና ያልተካተቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በምልዓት ማሳተፍ፤ | የጦርነት መቆም እና ሰፊ ፖለቲካዊ ተቀባይነት ማስፈን፤ |
| ግልጽነት | የተሳታፊዎችን ዝርዝር፣ የአጀንዳ አሰባሰብ ሂደቱን እና አጀንዳዎቹን በዝርዝር ይፋ ማድረግ፤ | በሕዝብ እና በባለድርሻ አካላት ዘንድ አመኔታ መጨመር፤ |
| ተጠያቂነት | አለ ተብሎ በተለያዩ ወገኖች የሚነሳውን የመንግሥትን ተጽዕኖ መቀነስ እና ገለልተኛ አሠራር ለመኖሩ ሕዝባዊ ይኹንታ እንዲገኝ መሥራት፤ | የምክክሩ ውጤት ተዓማኒ እና ተግባራዊ ማድረግ፤ |