የኢትዮጵያ እንደራሴዎች ምክር ቤት፣ በወርኃ ሚያዚያ ከከወናቸው ሕገ-መንግሥታዊ ኅላፊነቶች መካከል አንዱ፣ የፌደራል ተቋማትን የዚኽን በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም መገምገም ነበር። ወደ እንደራሴዎቹ አዳራሽ ተጠርተው የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ካቀረቡት ተቋማት መካከልም፣ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ባለሥልጣን በጊዜ ምጣኔ ቀዳሚው ነበር።
በእንደራሴዎቹ ምክር ቤት የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የተቋሙን ሪፖርት ማድመጡ ሲዘገብ፣ ባለሥልጣኑም፣ በሲቪል ማኅበራት አሠራር፣ የማኅበራት ምዝገባ ሒደት፣ የማኅበራት ገንዘብ አጠቃቀም እና በቀጣዩ ምርጫ ዝግጅት ዙሪያ ያተኮረ ሪፖርት አቅርቧል።
7ኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ተአማኒ እንዲሆን የሲቪል ማኅበራት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ፣ በምርጫ ዙሪያ የሚሰሩ ማኅበራትን አቅም የማብቃት ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ማኅበራቱ በማንኛውም ወገን ተጽዕኖ ሥር ሳይወድቁ ነፃ እና ገለልተኛ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግም በቋሚ ኮሚቴው በኩል ጠንከር ያለ ትዕዛዝ ለባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ መሰጠቱም ተዘግቧል።
በዚኽ መነሻነትም፣ ተቋማችን ብሪጅ፣ የሲቪል ማኅበረሰቡን ከየት ወዴትነት፣ በሦሥቱ ሥርዓታት ያለፈበትን ጉዞ እንዲኹም አኹናዊ ኹለንተናዊ ገጽታውን አጠር አድርጋ በመዳሰስ፣ ተያያዥ ተቋማዊ ምክረ-ሐሳቦችንም ለመሰንዘር ይኽችን ሳምንታዊ ዳሰሳ እነሆ ትላለች።
1. ሲቪል ማኅበረሰብ ሲሉ…
ሲቪል ማኅበረሰብ ማለት ምንድን ነው? ለሚለው የሚቀርበው ብያኔ በከፊልም ቢሆን ልዩነቶች ይታዩበታል። በማኅበረሰቡ ውስጥ ስለሚኖራቸው ሚናም የተለያዩ የሐሳብ ጫፎች ሲነገሩ ይስተዋላል። እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ሲቪል ማኅበረሰብ ማለት፣ ለመንግሥታት በተለዋጭነት የሚውል ንባበ-ቃል ነበር። ከበኩር አሳቢዎች መካከል ቀዳሚው የሆነው ጀርመናዊው ፍሬዴሪክ ሄግል፣ በሲቪል ማኅበረሰብ እና በመንግሥት መካከል ልዩነት መኖር እንዳለበት በመከራከር የመጀመሪያው ጸሐፊ ነው። ለ‘ርሱ ሲቪል ማኅበረሰብ ማለት በቤተሰብ እና በመንግሥት መካከል የሚቆም፣ በፖለቲካ ማኅበረሰቡ የተገፉ ዜጎች ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር እና እውቅና ለማግኘት በሚል የሚፈጥሩት ተቋም ነው።
በብላቴናነቱ ዘመን ሄግል ያደላለት እና ክስተቶችን በሙሉ ከመደብ ትግል አንጻር ለሚያየው ካርል ማርክስ የሄግል ብያኔ የሚስማማው ቢመስልም፣ እንደሌላው ኹኔታ ኹሉ ሲቪል ማኅበረሰቡም የግለሰባዊ ፍላጎቶች እና የመደብ ጥያቄ ትግል የሚያካሂዱበት መድረክ እና የትግሉ ውጤትም ማዕከላዊ መንግሥቱን በአብዮት ለመጣል ድርሻ እንዳለው አድርጎ ያቀርበዋል።
ከማርክስ፣ “መንግሥትን ከማኅበረሰቡ ስናወጣው” ከሚለው የሲቪል ማኅበረሰብ ትርጓሜ ይልቅ፣ የጣሊያናዊው ማርክሲስት አንቶኒዮ ግራምሺ ዕይታ የተሻለ ነው ተብሎ ይታመናል። በግራምሺ ዕይታ መሰረት ዜጎች በቤተ-እምነቶቻቸው፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሙያ ማኅበራት እና የትምህርት ተቋማት በኩል ራሳቸውን እና ሐሳባቸውን የሚወክሉባቸው ተቋማት ስብስብ ሲቪል ማኅበረሰብ ተብሎ መጠራት እንዳለበት ‘የእስር ቤት ማስታወሻዎች’ በሚለው ስብስብ ድርሳኑ ጽፏል።
ምንም እንኳን በምሁራን እና በሲቪል ማኅበረሰብ ተዋናዮች መካከል ብያኔውን በተመለከተ ምን ዓይነት መስፈርቶችን መጠቀም አለብን የሚለው የልዩነታቸው ምንጭ ቢሆንም፣ አስማሚ የሚመስለው ሐሳብ፣ በዜጎች ሙሉ ፈቃደኝነት ከመንግስት እና ትርፍን ከማግኘት ውጪ የሚደራጁ ተቋማት በዚኽ ስም ሊጠሩ ይችላሉ የሚለው ምልከታ ነው። የሚመሰርቷቸውን ዜጎች ፍላጎቶች የተለያዩ ሕጋዊ መንገዶችን በመጠቀም ለመፈጸም የሚተጉ፣ መንግስት በሚያወጣቸው ፖሊሲዎች ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር የሚሹ፣ በማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ በፖለቲካ ምኅዳር መስፋፋት እና በዲሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ ላይ አዎንታዊ ጫና ለማድረግ የሚችሉ የተለያዩ ሀገር-በቀል አልያም በሌሎች ደጋፊነት የሚንቀሳቀሱ ተቋማት በዚኽ ብያኔ ውስጥ ያርፋሉ።
በዲሞክራሲ ሂደት መፋጠን እና በሲቪል ማኅበረሰብ ሚና ላይ የሚጽፉ ምሁራን፣ በኹለቱ መካከል ቀጥተኛ የሆነ ዝምድና እንዳለ ይከራከራሉ። ጠንካራ የሲቪል ማኅበረሰብ የሐሳብ ብዝሓነትን በማስፋፋት የዲሞክራሲ እሴቶች በአገሪቱ ተቋማት ውስጥ እንዲሰርጹ ማድረግ የሚያስችል አቅም ይኖረዋል። ድምፃቸው የታፈነ እና በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ጥግ የተገፉትን የማኅበረሰብ ክፍሎች በመወከል ማኅበራዊ ፍትሕን ለማምጣትም በጎ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ። የፖለቲካ ሥርዓቱም ቢሆን ባወጣቸው ሕግጋት መጠን ልክ ሲቆጣጠሩ፣ የሙስና መስፋፋትን ሲገቱ፣ በመንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የሚካሄዱ ውሳኔዎች ግልፅነት እንዲኖራቸው ሲያነሳሱ፣ የዜጎች የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያሳድጉበትን ኹኔታዎች ሊያመቻቹ የሚችሉ ተቋማዊ ባህሪያት አሏቸው። በብዙ ጸሐፊዎች መካከልም እነዚኽ ተግባራት የሚከናወኑ ተቋማት መብዛት የዲሞክራሲያዊ ሂደቶችን መጠናከር ሲያመለክቱ፣ በተቃራኒው የድርጅቶቹ መዳከም የአምባገነናዊ የፖለቲካ ሥርዓትን ስር መስደድ መሆኑን ቢያነስ ያለፉት ሦሥት ዓሥርታት በበቂ የሚያሳዩት ሃቅ ነው።
2. የአጼው ዘመነ-መንግሥት
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ-መንግሥት የነበረው የሲቪል ማኅበረሰብ እንቅስቃሴ፣ ከባሕላዊ እና ማኅበረሰብ-ተኮር የራስ-እገዛ ማኅበራት ወደ ዘመናዊ እና መደበኛ ማኅበራት የተሸጋገረበት ወቅት ነበር። ይኹን እንጂ አጠቃላይ ምኅዳሩ በንጉሠ ነገሥቱ መዳፍ ሥር የወደቀ እና ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት እንደነበር ብዙ ተጽፎበታል።
ለዘመናት ኢትዮጵያ ጠንካራ ባሕላዊ የሲቪክ ተቋማትን ጠብቃ የቆየች ሲሆን፣ ከእነዚኽም መካከል ዕድር፣ ዕቁብ እና ደቦ ተጠቃሾች ናቸው። በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ግን የሠራተኛ ማኅበራት፣ ሌሎች የሙያ ማኅበራት እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ጨምሮ ዘመናዊ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። እነዚኽ መደበኛ ድርጅቶች በዐዋጅ ቁጥር 321/1959 መሠረት በአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር ይመዘገቡም ነበር።
የንጉሠ ነገሥቱ የዘመናዊነት እና የትምህርት መስፋፋት ፖሊሲ፣ ለሲቪል ማኅበራት መፈጠር መሠረት የሆነውን የተማረ የሰው ኃይል እና መካከለኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ለመፍጠር ረድቷል። በእነዚኽ የዘመኑ ምሁራን ዘንድም የጃፓንን ፈለግ በመከተል የታመነ እና አገሪቱን ለማዘመን የሚተጋ እንቅስቃሴ ተፈጥሮ ነበር። በዘመነ-መንግሥቱ ማብቂያ ላይ ግን የመሬት ይዞታ ማሻሻያ እና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የሚወተውት ሥር-ነቀል የተማሪዎች ንቅናቄ ብቅ ብሎ የነበረ ሲሆን፤ ይኽም ሥርዓቱን በግልጽ የሚቃወም ነበር። በተጨማሪም በ1966 ዓ.ም የተከሰተው ድርቅ እና ችጋር፣ የመንግሥትን ድክመት ከማጋለጡ ባለፈ፣ እንደ የክርስቲያን ረድኤት እና ልማት ማኅበር ያሉ ቀደምት የረድኤት ድርጅቶች እንዲመሰረቱ ምክንያት ሆኗል።
ምንም እንኳ በዚኽ መልኩ ዘመናዊ የሲቪል ማኅበራት ቢፈጠሩም፣ መንግሥት ጥብቅ ክትትል ያደርግባቸው ስለነበር በነፃነት የመንቀሳቀስ ዕድላቸው ውስን ነበር። የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ግልጽ ተቃውሞዎች ይታገዱ እንደነበረው ኹሉ፣ ሌሎቹም ተቋማዊ ለመሆን ይጥሩ የነበሩ ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበራትም ዕጣቸው እንዲያው ሆነ። እነዚያ ብቅ ያሉት የሲቪል ማኅበረሰብ መዋቅሮችም ቢሆኑ፣ በብዛት ተጠቃሚ ያደረጉት ከተሜውን እንጂ ገበሬውን አልነበረም። ይኽ በንጉሡ ዘመን የተጀመረው በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ፣ ከ1966ቱ አብዮት በኋላ በመጣው የደርግ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ፣ ገለልተኛ ማኅበራት በመንግሥት በሚመሩ የሕዝብ ድርጅቶች እንዲተኩ ተደርጓል።
3. ጸረ-ሲቪል ማኅበረሰቡ ደርግ
ከ1967 እስከ 1983 ዓ.ም ኢትዮጵያን የገዛው ደርግ፣ በሰፊ የፖለቲካ ጭቆና እና በሲቪል ማኅበረሰቡ ላይ በተጣለ ጥብቅ ቁጥጥር የሚታወቅ ነበር። በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ይመራ የነበረው ወታደራዊው መንግሥት፣ በግራ ዘመም መርሆዎች ላይ የተመሠረተ የሶሻሊስት ርዕዮተ-ዓለምን ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል። ሥርዓቱ መሬትን እና ኢንዱስትሪዎችን ወደ መንግሥት ይዞታ በማዛወር ኢኮኖሚያዊ ርዕታዊነት ያለው ማኅበረሰብ ለመፍጠር ቢመኝም፣ ፖሊሲዎቹ ግን ለኢኮኖሚ ውድቀት፣ ለምግብ እጥረት እና ለከፋ ድህነት ዳርገዋል። ይኽም በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን እና ኋላም የትጥቅ ትግልን ቀስቅሷል።
በዚኽ ዘመን የነበረው የሲቪል ማኅበረሰቡ እንቅስቃሴ ከመንግሥት በደረሰበት ከፍተኛ እገዳ እና አፈና ምክንያት ሽባ ሆኖ ነበር። ደርግ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በማገድ በሕዝባዊ ስብሰባዎች፣ በሚዲያ እና በተቃዋሚ ድምፆች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ጥሏል። የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በስፋት ይፈጸሙ የነበረም ሲሆን፣ የሥርዓቱ ተቃዋሚ ናቸው ተብለው በሚጠረጠሩ ዜጎች ላይ ድብደባ፣ ያለ ፍርድ ግድያ እና አስገዳጅ ስወራዎች ይፈጸሙባቸው ነበር።
በንጉሡ ዘመን የነበሩ እንደ ተማሪዎች ቡድን፣ የሠራተኛ ማኅበራት እና የሃይማኖት ድርጅቶች ያሉ ንቁ የሲቪል ማኅበረሰብ ተዋናዮች ከፍተኛ ስደት እና ስቃይ ደርሶባቸዋል። በርካታ የሲቪክ መሪዎች ታስረዋል፤ ተገድለዋል ወይም አገር ጥለው እንዲሰደዱ ተገድደዋል። ይኽ አፈና የሲቪል ማኅበረሰቡን አቅም በማዳከሙ፣ ሥርዓቱን በሰላማዊ መንገድ መሞገት የማይቻልበት ደረጃ ላይ አደረሰው። ይኽ የጭቆና ዘመን በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ትስስር ላይ የከፋ ጠባሳ ጥሎ ከማለፉ ባለፈ፣ ሥርዓቱ ከወደቀ በኋላም ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የፍርሃት እና የመተማመን እጥረት እንዲሰፍን አድርጓል።
ደርግ ገለልተኛ የሲቪል ማኅበራትን በማፍረስ፣ በእነሱ ምትክ በመንግሥት እና በፓርቲው (ኢሠፓ) የሚመሩ የጅምላ ማኅበራትን አቋቁሟል። ከእነዚኽ መካከል ሊጠቀሱ የሚችሉት አብዮታዊ የኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበር (አኢወማ)፣ አብዮታዊ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር (አኢሴማ) እና የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር (ኢሠማ) ናቸው።
ነገር ግን የእነዚኽ ድርጅቶች ምሥረታ ያስፈለገው የዜጎችን ፍላጎት ለማንፀባረቅ ሳይሆን፣ ማኅበረሰቡን ለመቆጣጠር፣ ወታደራዊ ቅስቀሳ ለማድረግ እና የመንግሥትን ፖሊሲዎች ለማስፈጸም በተቀጥላነት እንዲያገለግሉ ነበር፤ አባልነት እንኳ በግዴታ መሆኑን ያስታውሷል። በዚኽ መልኩም፣ ንጉሡ ሳይነኳቸው የቆዩት እንደ ዕድር ያሉ ባሕላዊ ተቋማት ሳይቀሩ በደርግ ዘመን ለፖለቲካዊ ዓላማ እንዲውሉ ተደርገዋል። ዕድሮች ከመቃብር እና ከማኅበራዊ ድጋፍ ባለፈ፣ የመንግሥት መልዕክት ማስተላለፊያ እና አልፎ ተርፎም ተቃዋሚዎችን መከታተያ እንዲሆኑ ጫና ይደረግባቸው ነበር።
በደርግ ዘመን ብቸኛው ነፃ ሊባል የሚችል የሲቪል ማኅበረሰብ እንቅስቃሴ የታየው በሰብዓዊ እርዳታው ዘርፍ ነበር። በተለይ በ1977ቱ አስከፊ ችጋር ወቅት፣ መንግሥት ዓለም ዓቀፍ ዕርዳታን ለመቀበል በመገደዱ፣ በርካታ ዓለም ዓቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ፈቅዷል። ይኽም ዘመናዊው ኣና በዕርዳታ ላይ የተመሠረተው የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ታሪክ መሠረት እንዲጥል አድርጓል። ሆኖም እንቅስቃሴያቸው በረሃብ እና በምግብ ድጋፍ ላይ የተገደበ እንጂ በፖለቲካ እና በሰብዓዊ መብቶች ላይ እንዳይሳተፉ ጥብቅ ገደብ መጣሉ፣ ኢትዮጵያ ልታገኝ ትችል የነበረውን የዘመናዊ ሲቪል ማኅበረሰብ ዕድገት ቀጭቶታል።
4. የኢሕአዴግ ሦሥቱ ምዕራፎች
የቀዝቃዛውን ጦርነት ማብቃት ተከትሎ፣ ሉላዊው ዓለም ከሊበራል ዕሴቶች ውጪ የመመልከት ዕድል ለማጣት ተገደደ። በዚኽ የተነሳም፣ በዚያ ዘመን ወደ ሥልጣን የመጡ ገዚዎች፣ የሊበራል ፖለቲካ ሥርዓት መንበር አንዱ አምድ የሆነውን የሲቪል ማኅበራት ሚናን ለመቀበል ተገደዱ። በኢትዮጵያም የሆነው እንዲኹ ነበር፤ በደርግ መውደቅ ማግስት ወደ መንበሩ የመጣው ኢሕአዴግ፣ የሲቪል ማህበራትን ዲሞክራሲያዊ ሚና ከመቀበል ውጪ፣ ዘመኑ ሌላ አማራጭ አልሰጠውም። በዋናነት በዚኽ ውጪያዊ ግፊት የተነሳ፣ በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ታሪክ ውስጥ በበጎ የሚነሳው ዘመን አሀዱ አለ። ከዚኽ አኳያም፣ የዚኽን ዘመን የተለያዩ ገጾች ሰፋ አድርጎ መመልከት፣ ለጥቆ ለመጣው ላለንበት ዘመን ሰፋ ያለ ስዕል ሳይሰጠን አይቀርም።
ኢሕአዴግ ከሲቪል ማኅበረሰቡ ጋር የነበረው የግንኙነት ተዛምዶም ሦሥት ምዕራፎች እንዳሉት ርዕሰ-ጉዳዩን ያጠኑ ተንታኞች ይሟገታሉ። የመጀመሪያውን ደመናዊ ጥላቻ ያረበበት ዘመን ሲሉ የሚጠሩት እኒኽ ጸሓፍት፣ እስከ 1993ቱ የኢትዮ-ኤርትራው ጦርነት መጀመሪያ ድረስ የቀጠለውን ይኽን የኹለቱ የግንባሩን እና የሲቪል ማኅበረሰቡን ሒደት ይጠቀልላል። ይኽም ፓርቲው ከትጥቅ ትግል ታሪኩ ካሳየው ባህሪ ጋር እንደሚቆራኝ ይጠቅሳሉ። እንደ ጉሬላ ታጣቂ ቡድን እና ርዕዮተ-ዓለሙን በግራ-ዘመም አስተምህሮት እንደቃኘ ግንባር፣ ነፃ የሆኑ ተቋማትን የሚያያቸው በከፍተኛ ጥርጣሬ ነበር። ሥልጣን ከያዘ በኋላ በተከተሉት ዓመታትም ቢሆን፣ ከዚህ የጥርጣሬ መንፈሱ አልተላቀቀም። አንዳንዶቹ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በትጥቅ ትግሉ ወቅት ለፓርቲው ድጋፍ ሲሰጡ የቆዩ ቢሆኑም፣ እርሱ ከሚቆጣጠራቸው ማኅበራት ውጪ ያሉትን ድርጅቶች ሥልጣኑን እንደሚቀናቀኑ ኃይሎች ማየቱ በጊዜው ለነበሩት የመያዶች ቁጥር መቀነስ አንደኛው ምክንያት ነበር። ይኽ የፓርቲው የተጠራጣሪነት አካሄድም ይመስላል፤ እንደሌሎቹ የአፍሪካ አገራት ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ በኋላ የመያዶች ቁጥር መጨመር በኢትዮጵያ የተከሰተበት ዕድል እንዲጠብ ያደረገው የሚለው አንዱ በዛ ብሎ የሚጠቀስ የክርክር ነጥብ ነው።
አጥኚዎቹ የሚያነሱት ኹለተኛው ምዕራፍ፣ ጸሓፍቱ ዝግ ብለው የሰየሙት ሲሆን፣ ይኽም ከ1980ዎቹ መጨረሻ እስከ ድህረ-97 ምርጫ ድረስ የሚዘልቀውን ዘመን ያቅፋል። ጸሐፍቱ ዝግ ብለው በሰየሙት በዚኽ ምዕራፍ፣ ሲቪል ማኅበረሰቡ ከመንግሥት ጋር የነበረው መስተጋብር ሦሥት መሠረታዊ መልኮችን ይዞ ታይቷል።
የመጀመሪያው መልክ፣ የድርጅቶቹ ቁጥር መጨመር እና የተሰማሩበት ዘርፍ ብዝኃነት ነው። በዚኽ ወቅት መያዶች ከተለመዱት የረድኤት እና የልማት ሥራ ወጥተው፣ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ በዲሞክራሲያዊ ግንባታ እና በመልካም አሥተዳደር ዙሪያ በስፋት ወደ ሕዝባዊ አደባባዩ መውጣት የጀመሩበት ነበር። ይኽም ሲቪል ማኅበረሰቡ እንደ አንድ ገለልተኛ ሥርዓታዊ ተዋናይ እና የለውጥ ኃይል ዕውቅና ማግኘት እንዲጀምር መንገድ ከፍቷል።
ኹለተኛው መልክ፣ በፖሊሲ ቀረጻ እና በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ የተስተዋለው የተሳትፎ ዝንባሌ ነው። መንግሥት በዚኽ ወቅት እንደ ድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ ባሉ አገራዊ ፖሊሲዎች ላይ የሲቪል ማኅበረሰቡን ድምፅ እና ግብዓት ለማካተት በማዕከላዊ መንግስቱ በኩል ከፍተኛ ፍላጎት መታየቱ ተስተውሏል። ይኽም ድርጅቶቹ ከሕዝብ ጋር ያላቸውን ቅርበት በመጠቀም የመንግስትን የልማት አቅጣጫዎች እንዲሞግቱ እና አማራጭ ሐሳቦችን እንዲያቀርቡ ዕድል ሰጥቷቸዋል። ይኽም በኹለቱ አካላት መካከል የነበረውን የቆየ ጥርጣሬ በማርገብ፣ ወደ መደበኛ የምክክር ባህል የመሸጋገር ተስፋን አጭሮ ነበር።
ሦሥተኛው የዚኽ ምዕራፍ መልክ ደግሞ በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት እና በሲቪል ማኅበረሰቡ ተወካዮች መካከል የተፈጠረው መዋቅራዊ ትስስር ነው። በዚኽ ወቅት በምክር ቤቱ አባላት እና በመያዶች መካከል መደበኛ የግንኙነት ስምምነት ተደርጎ የነበረ ሲሆን፣ ይኽም ሲቪል ማኅበራት በምክር ቤቱ የሕግ ማርቀቅ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ እና በቋሚ ኮሚቴዎች በኩል የሙያ ድጋፍ እንዲሰጡ የሚያስችል ነበር። ምንም እንኳ ይህ ግንኙነት በ1997ቱ ምርጫ ማግስት ቢቋረጥም፣ ለጥቂት መያዶች ግን መንግስትን የመወትወት እና በሕግ አወጣጥ ሂደት ላይ ተፅዕኖ የማሳደር ኋላ ያልተደገመ ታሪካዊ ዕድል ፈጥሮላቸው ነበር።
ገዢው ፓርቲ ከድህረ-97 ምርጫ በኋላ የተከሰተውን የአገሪቱን የፖለቲካ ሥርዓት የገመገመበትን እይታ መመልከትም ግድ ይላል። ይኽ ሦሥተኛው ምዕራፍ ተብሎ የተጠራው ዘመን፣ በራሱ በፓርቲው መልካም ፈቃድ መራጮችን በማስተማር ምርጫውን በመገምገም ላይ የተሰማሩትን መያዶች፣ የገመተውን የምርጫ ውጤት ካጣ በኋላ ከክስተቱ፣ ‘ድርጅቶቹ ከተቃዋሚዎች ጋር ሰርተዋል’ የሚል እምነት እንዲወስድ አድርጎታል። በ1999 ዓ.ም. “ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት የሚደረግ ትግል” በሚል ርዕስ ፓርቲው ያሳተመው ድርሰትም መያዶቹን እንዴት ይመለከታቸው እንደነበር ከፊል እይታ ይሰጣል። ብዙ ተንታኞች፣ ምክንያታዊነት የሌለው ባዶ ሃቲት ሲሉ በጠሩት በዚኽ ጹሑፍ፣ ፓርቲው ስለ “ኪራይ ሰብሳቢነት” ይተነትናል፤ እንደ ፓርቲው ሙግት ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል እና ተቋማዊ ገቢን እርሱ “ልማታዊ ያልሆኑ” ላላቸው ጉዳዮች ማዋል የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫዎች ሆነው ቀረቡ። ከ“ኪራይ ሰብሳቢ” መንግስታት የሚመጡ የገንዘብ ምንጮችን የሚጠቅመው አልያም የድርጅቶቹን የበላይ አመራሮች ጥቅሞች ብቻ ለማስጠበቅ የቆሙ ናቸው ሲል መያዶችን የሚከሰው ይኸው ሰነድ፣ ተቋማቱ በተፈጥሯቸው ጭምር “ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው” ሲል ይራገማል።
ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ-ዓለም ውጭ ያሉ የሐሳብ ሥርዓቶች ለአገሪቱ ልማትም ሆነ ለዲሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ የሚረባ አበርክቶ እንደማይኖራቸው ያመነው ገዢው ፓርቲ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ እና አማራጭ የፖሊሲ ሐሳቦችን በማቅረብ ላይ የተሰማሩ ተቋማትን፣ የፓርቲውን ኹሉ ቦታ የመኖር እና ኹሉን የመቆጣጠር ህልም እንደሚገዳደሩ ክፍሎች በማየቱ፣ በድህረ-97 ምርጫ የሕገ-መንግስቱን መንፈስ የሚንዱ ሕግጋትን እንዲያወጣ አስገደደው።
በአጭሩ ለማስቀመጥም፣ ፓርቲው ሲቪል ማኅበራትን የተረዳቸው የአብዮታዊ ዲሞክራሲን ልዕልና ለማስጠበቅ ለሚያስችል የፖለቲካ ማስጠመቂያ እና ለፕሮፓጋንዳ መዋያ ሊሆኑ ይገባል በሚል ነበር። ከዚኽ ዕይታው ውጪ፣ ለተመሰረቱበት ተቋማዊ ርዕይ የተገዙ ሲቪል ማኅበራትን፣ አንድም በአፋኝ ሕግጋት፣ አንድም በፖለቲካ እና የጸጥታ መዋቅር ከሕዝባዊ አደባባዩ እንዲከስሙ አደረጋቸው። ብዙዎች ነገረ-ጉዳዩን ያጠኑ እንደሚጠቅሱት፣ ኹላ በ2010 ዓ.ም የመጣውን የሥርዓት ለውጥ ካዋለዱ ኩነቶች አንዱ፣ ተስፋ ሰጪ የነበረው የሲቪል ማኅበረሰቡ የዕድገት ሂደት በዚኽ መልኩ መጨፍለቁ፣ የተስተዋለውን ሕዝባዊ ዕመጽ እንዲቀሰቀስ ነገሮችን ማመቻቸቱ ነው።
በአጠቃላይ የንጉሠ ነገሥቱ ዘመን፣ የዘመናዊ ሲቪል ማኅበራት መሠረት የተጣለበት እና በመንግሥት መር ዘመናዊነት የተቃኘ ቢሆንም፣ የደርግ ዘመን ግን ሥልጣንን በአንድ ማዕከል የጠፈነገበት እና ገለልተኛ የሲቪል ማኅበራት እንቅስቃሴዎች ጭልጭታን ያጠፋበት የጨላለመ ዘመን ነበር። ከዚያ የቀጠለው እና ብዙ ተስፋ የተጣለበት የድህረ-ደርግ ዘመንም፣ በኢሕአዴግ ኹሉን ጠቅላይነት ናፍቆት ዳሸቀ። ይኽ አጭር የታሪክ ሂደት የሚያሳየው፣ በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ዕጣ ፈንታ ምንጊዜም ቢሆን ከፖለቲካዊ ሥርዓቱ ባህሪ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት እንዳለው ነው። እነዚኽን ታሪካዊ እውነታዎች መሠረት በማድረግ፣ አኹን ያለውን የብልጽግና ዘመን ምኅዳር በንፅፅር መመልከት ለነገው የዴሞክራሲ ጉዟችን ትልቅ ትምህርት ይሰጣል የሚል ዕምነት አለን።
5. የባለሥልጣኑ መቋቋም
በደርግ መንግስት መውደቅ ማግስት፣ ከ1983-1987 ዓ.ም. ማኅበራትን የመመዝገብ ሥልጣን እና ተግባር ሲያከናውን የቆየው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰኘው መንግስታዊ ተቋም ሲሆን፤ በ1987 ዓ.ም. አሥፈጻሚ አካላትን ለማቋቋም በወጣው ዐዋጅ ቁጥር 4/1987 የኢፌድሪ የፍትኽ ሚኒስቴር የሃይማኖት ድርጅቶችን፣ አላማቸው ትርፍ ለማግኘት ያልተቋቋሙ ድርጅቶችን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እና ማህበራትን የመመዝገብ ሥልጣን እና ተግባር በሕግ ተሰጥቶት ነበር፡፡ በቀጣይም በዐዋጅ ቁጥር 471/1998 ይኸው ማኅበራትን እና የሃይማት ድርጅቶችን የመመዝገብ ሥልጣን ለፍትሕ ሚኒስቴር እንደተሠጠ በመቀጠሉ፣ ፍትኽ ሚኒስቴር እስከ 2001 ዓ.ም. ድረስ የመመዝገብ ሥራን ሲያከናውን ሰንብቷል።
የፍትሕ ሚኒስቴር በ1999 ዓ.ም. ባካሄደው የመሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ ጥናት መሰረት፣ በዘርፉ የተመዘገበውን ዕድገት ከግምት ውስጥ በማስገባት ከሃይማኖት ድርጅቶች ውጭ ያሉ ማኅበራትን እና ዓላማቸው ለትርፍ ያልሆኑ ድርጅቶችን የመመዝገብ እና ለማሥተዳደር ያስችል ዘንድ፣ በዐዋጅ ቁጥር 621/2001 “የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማኅበራት ኤጀንሲ” በሚል ስያሜ ራሱን የቻለ የመንግስት አሥፈጻሚ አካል እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡
በዐዋጅ ቁጥር 621/2001 መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማኅበራት ተደራጅተው በአገሪቱ ኹለንተናዊ ዕድገት፣ ልማት እና በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ በመመዝገብ እና ፈቃድ በመስጠት እንዲኹም በመከታተል እና በመደገፍ የኅብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በሚል ተልዕኮ ይዞ ቢንቀሳቀስም የመደራጀትን መብት በተሟላ ሁኔታ ያላከበረ እና በአፈፃፀሙም በርካታ ክፍተቶች የነበረበት ስለነበረ ተልእኮውን በተገቢው የተወጣ አልነበረም የሚል ግምት በመንግስት በኩል ተይዞ ሰንብቷል፡፡
በተለይም ዐዋጁ የድርጅቶች እና የማኅበራት የእንቅስቃሴ አድማስ እና የገቢ ምንጭ ላይ ገደብ በመጣሉ የተነሳ ከፍተኛ ቅሬታ ሲቀርብበት የነበረ ዐዋጅ ነበር፡፡ በመሆኑም በአገር ዓቀፍ ደረጃ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ዘርፉን የሚያስተዳድረው ዐዋጅ እና አፈጻመሙ ክፍተት እንዳለበት ስለታመነ ዐዋጅ ቁጥር 621/2001 ሙሉ በሙሉ ተሸሮ በአዲስ ዐዋጅ ቁጥር 1113/2011 ሊተካ ችሏል፡፡ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱም፣ በዐዋጅ ቁጥር 1113/2011 የሕግ ሰውነት ያለው የፌደራል መንግስት መሥሪያ ቤት ሆኖ ዳግም ተደራጅቶ እንዲቋቋም ሆኗል።
6. ተስፋው በኗልን?
የብልጽግና ፓርቲ ወደ ሥልጣን መምጣት በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ምኅዳር ላይ የታሪክ ሽግግር ያመጣ ክስተት ነበር። መንግሥት መጀመሪያ ላይ ያከናወናቸው የሕግ ማሻሻያዎች እና የዴሞክራሲ ተስፋዎች፣ በዘርፉ ተዋናዮች ዘንድ ከመንግሥት ጋር በቅርበት ለመሥራት እና ሰፊ ለውጦችን ለማምጣት ትልቅ መነቃቃትን ፈጥረው ነበር። የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ዴሞክራሲያዊ ዕሴቶችን በማስፋፋት፣ ለሰብዓዊ መብቶች በመሟገት እና ለተገለሉ ማኅበረሰቦች መሠረታዊ አገልግሎቶችን በመስጠት ረገድ ጠቃሚ ሚናዎችን መጫወት ጀመሩ።
በተለይም በ2011 ዓ.ም. የወጣው ዐዋጅ (ቁጥር 1113/2011) በውጭ የገንዘብ ድጋፍ ላይ ተጥሎ የነበረውን ገደብ በማንሳቱ፣ በሰብዓዊ መብት እና በሰላም ግንባታ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ዳግም እንዲያንሰራሩ አድርጓል። በዚኽም በ2011 እና 2014 ዓ.ም. መካከል ብቻ 250 የሚጠጉ አዳዲስ የሰላም ግንባታ ድርጅቶች ተመስርተው ለዴሞክራሲ ግንባታው አጋርነታቸውን አሳይተዋል።
በአሁኑ ወቅት በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከተመዘገቡት 4938 ድርጅቶች ውስጥ ከ4395 በላይ የሚሆኑት ሀገር በቀል ድርጅቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ከ543 በላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ደግሞ የውጪ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ከ415 በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተለያዩ ሙያዎችን መሰረት አድርገው የተደራጁ የሙያ ማህበራት ሲሆኑ፤ ከ165 በላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አካል ጉዳተኞችን መሰረት አድርገው የሚሰሩ ድርጅቶች መሆናቸውን የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ድረ-ገጽ ይጠቁማል። እነዚኽ ድርጅቶች ከሀገር በቀል ጥቃቅን ማኅበራት እስከ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት የሚዘልቁ ሲሆን፣ ይኽም በሲቪል ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ዙሪያ ከታችኛው የማኅበረሰብ ክፍል ጀምሮ እስከ ሰፊው ዓለም ዓቀፍ ትብብር ድረስ ያሉ ልዩ ልዩ የሥራ አቀራረቦችን መኖራቸውን ያሳያል።
በተጨማሪም፣ በርካታ በሰብዓዊ መብት እና በልማት ላይ ያተኮሩ ድርጅቶች እንዲሁም በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩ ድርጅቶች በመረጡት የሲቪል ማኅበረሰብ ሥራዎች ላይ ተሰማርተዋል። እነዚኽ ድርጅቶች አብዛኛውን ጊዜ ከግጭቶች ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የሥርዓተ-ጾታ እና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን እንደሚዳስሱም ብሪጅ ባደረገችው አጭር ዳሰሳ መረዳት ችላለች። ይኽም የሰላም ግንባታ ሥራ ግጭቶችን ከመከላከል ባለፈ የሰብዓዊ መብቶችን ማስከበርን እና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥን የሚያካትት ኹለንተናዊ ተግባር መሆኑን ያሳያል።
7. ከተቋሙ ሪፖርቶች ጥቂት ነጥቦች
በመግቢያችን እንደጠቀስነው፣ ለዚኽ ዳሰሳ መነሻ የሆነን የኢፌድሪ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ባለሥልጣን የዚኽ በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ነውና፣ ከዚኹ የተቋሙ ሪፖርት አንኳር ነጥቦችን መመልከት ፋይዳ ይኖረዋል። የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የምዝገባ ፈቃድ የሚያገኙት፣ ጥያቄያቸው ከአገር ደኅንነት አኳያ ተመርምሮ መሆኑን ባለሥልጣኑ መናገሩ ተዘግቧል። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ፣ ፈቃድ ለማግኘት የሚያመለክቱ ድርጅቶችን ጉዳይ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በመሆን፣ በተለይም ከአገር ደኅንነት አንጻር በጥንቃቄ ከተመለከተ በኋላ ፈቃድ እንደሚሰጥ አስታውቋል።
የዘጠኝ ወራት የአፈጻጸም ሪፖርቱን፣ በእንደራሴዎቹ ምክር ቤት የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ያቀረቡት የባለሥልጣኑ የስትራቴጂ ጉዳዮች መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ወይዘሮ ቃልኪዳን መንግሥቴ፣ ድርጅቶች አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው እስከቀረቡ ድረስ የምስክር ወረቀት እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል ተብሏል። በዚኽም መሠረት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 209 ድርጅቶች የዕውቅና ምስክር ወረቀት ያገኙ ሲሆን፣ ከእነዚኽ መካከል 199 የሚሆኑት የውጭ ድርጅቶች መሆናቸው ታውቋል። ከዚኽም በተጨማሪ አዲሱ ዐዋጅ ከወጣ በኋላ ዳግም ያልተመዘገቡ እና አድራሻቸው ያልታወቁ 600 የሚጠጉ ድርጅቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲኮ ሞላ ተናግረዋል፤ እነዚኽ ድርጅቶችም ሕጋዊ ሰውነታቸውን እንዲያጡ መደረጉም ተጠቁሟል። ከእነዚኽ ድርጅቶች መካከል የተገኘ ጥቂት ሀብትም በሕጉ መሠረት ወደ ሌሎች ድርጅቶች ወይም ወደ ሲቪል ሶሳይቲ ፈንድ ገቢ እንዲሆን መደረጉም ተብራርቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወይዘሮ እጸገነት መንግሥቱ በበኩላቸው፣ ምንም እንኳን የዲሞክራሲ ምኅዳሩ እንዲሰፋ ቢደረግም፣ ኹሉም ድርጅት ጤነኛ አስተሳሰብ ይዞ ስለማይመጣ በምዝገባ ወቅት የማጣራት እና ጥብቅ ጥንቃቄ የማድረግ ሥራ በትኩረት ሊከናወን እንደሚገባ ማሳሰባቸው ተሰምቷል።
በሌላ በኩል፣ ፈቃድ ለማግኘት ካመለከቱ 485 ድርጅቶች መካከል መስፈርቱን ባለማሟላታቸው እና አስፈላጊውን ክትትል ባለማድረጋቸው ጥያቄያቸው ተቋርጦ እንዲሰረዝ የተደረጉ መኖራቸው ሲጠቀስ፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ 319 ድርጅቶች በምዝገባ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል። የተመዘገቡት ድርጅቶች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን በማስመልከት ከቋሚ ኮሚቴው ለቀረበው ጥያቄ፣ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን ቢራቱ ምላሽ ሰጥተዋል። ማንኛውም ዜጋ የመደራጀት እና የመመዝገብ መብት እንዳለው በሕገ-መንግሥቱም ሆነ በባለሥልጣኑ ዐዋጅ የተፈቀደ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሪክተሩ፣ የተወሰኑ ጉዳዮች ግን ከአገር ደኅንነት አኳያ በጥልቀት እንደሚታዩ አብራርተዋል። በተለይም የውጭ አገር ድርጅቶች በሚሆኑበት ወቅት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ጋር በጋራ በመሆን የኋላ ታሪካቸውን የማጥናት ሥራ እንደሚከናወን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለሚሰጧቸው አገልግሎቶች የሚያገኙት ሀብት ለታለመለት ዓላማ ብቻ መዋሉን ለማረጋገጥ ባለሥልጣኑ ጥብቅ ቁጥጥር ያደርጋል ተብሏል። ይኽ ቁጥጥርም ድርጅቶቹ በየዓመቱ በሚያቀርቡት ሪፖርት አማካኝነት ከሀብታቸው አጠቃቀም አንጻር እየታየ የሚገመገም እና ተገቢው ግብረ-መልስ የሚሰጥበት መሆኑን ፋሲካ ሞላ ጨምረው አስረድተዋል።
በዚኹ የባለሥልጣኑ ሪፖርት ላይ የተጠቀሰው ሌላው አንኳር ጉዳይ፣ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በቀጣዩ ምርጫ ይኖራቸዋል ከተባለው ሚና አኳያ ነበር። ከምክር ቤቱ እንደተገኘው መረጃ ከሆነም፣ በሰባተኛው አገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ ነጻነታቸው እና ገለልተኝነታቸው ላይ ጥያቄ ሊነሳባቸው እንደማይገባ ቋሚ ኮሚቴ ማሳሰቡ ተጠቅሷል።
ቋሚ ኮሚቴው፣ ድርጅቶቹ ለተደራጁለት አላማ ብቻ ሀብታቸውን መዋላቸውን ማረጋገጥ እና ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ ገልጿል። በአኹኑ ወቅትም 212 ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በምርጫ ሂደት ላይ ለመሳተፍ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፈቃድ ማግኘታቸው የጠቀሱት የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ምክትል ዳይሪክተሩ ፋሲካ ሞላ መሆናቸው ተዘግቧል፤ ይኽም ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ጋር ሲነጻጸር የተነቃቃ እንቅስቃሴ መኖሩን እንደሚያሳይ ተመላክቷል። ቋሚ ኮሚቴው በምርጫ ማስተማር እና በታዛቢነት ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ ድርጅቶች ገለልተኝነት እጅግ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷልም ተብሏል። ድርጅቶቹ ምርጫውን በገለልተኝነት እንዲደግፉ እና አላስፈላጊ ተግባራት ውስጥ እንዳይገቡ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ክትትል እንዲያደርግ አሳስቧል።
ከዚኽ በላይ አጠር አድርገን ካየናቸው የሦሥቱ መንግሥታት እና የሲቪል ማኅበረሰቡ ያዝ-ለቀቅ መስተጋብር አንጻር፣ አኹን ያለው የማኅበራቱ እንቅስቃሴ በንጽጽር ደህና ይመስላል የሚሉ ሙግቶችም ይደመጣሉ። ያም ቢሆን፣ ከቀጣዩ ምርጫ 2018 አኳያ፣ አኹን ያሉት የሲቪል ማኅበራት ምን አገራዊ ኃላፊነቶች አሉባቸው የሚለውን አስቀድመን በመጥቀስ፣ ከመንግሥትም ሆነ ይመለከታቸዋል ከሚባሉ መንግሥታዊ ተቋማት፣ ሲቪል ማኅበረሰቡን ለማጠናከር ምን ጉዳዮች በቅጡ መታየት እንዳለባቸው አጠር ያሉ ምክረ-ሐሳባዊ ነጥቦችን እናስከትላለን።
8. ምርጫ 2018 እና የሲቪል ማኅበረሰቡ ሚና
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በቀጣዩ ምርጫ ሂደት ውስጥ ከምርጫ አሥፈጻሚው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከመንግስት እና ከተገዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቀጥሎ ሦሥተኛው ወሳኝ ምሰሶ ናቸው። እናም፣ በ2018 ምርጫ የሚከተሉት ሦሥት ዋና ዋና ሚናዎች ይጠበቁባቸዋል ብለን እናምናለን።
ሀ፦ገለልተኛ የምርጫ ታዛቢነት
እንደሚታወቀው ይኽ የሲቪል ማኅበረሰቡ ቀዳሚ ተግባር ነው። ይኽንን ግብር ይከወኑ ዘንድም፣የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 114 እና 117፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ ዐዋጅ ቁጥር 1133/2011 አንቀጽ 7(7) እና አንቀጽ 8(1) ተከትሎ በወጣው የአገር ውስጥ ምርጫ ታዛቢዎች የዕውቅና አሰጣጥ፣ የአሠራር ሥርዓት እና የሥነ-ምግባር መመሪያ ቁጥር 5/2012 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፤ በ7ኛው አጠቃላይ ምርጫ የሚሳተፉ 45 የአገር ውስጥ ምርጫ ታዛቢ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችን መዝግቦ ዕውቅና ሰጥቷል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ያላቸው ተሳትፎ መጨመሩ ለዲሞክራሲ ምኅዳሩ ግንባታ አዎንታዊ እርምጃ ቢሆንም፣ ድርጅቶቹ ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ መሆናቸውን በተግባር ማሳየት ይኖርባቸዋል። ቋሚ ኮሚቴው እንዳሳሰበው፣ ድርጅቶቹ በምርጫ ታዛቢነትም ሆነ በማስተማር ተግባር ላይ ሲሰማሩ “ጤነኛ አስተሳሰብ” ይዘው መቅረባቸውን እና የገለልተኝነት ጥያቄ እንዳይነሳባቸው በገለልተኛ አካል የሚመራ የክትትል ሥርዓት በመዘርጋት የራስ በራስ ቁጥጥር የሚያደርጉበትን መዋቅር መዘርጋት ይኖርባቸዋል ማለት እንሻለን።
ከዚኽ ባለፈም፣ ሲቪል ማኅበረሰቡ በምርጫ ጣቢያዎች (በተለይም ከከተማ ወጣ ባሉት ጣቢያዎች) በመገኘት የዜጎች ድምፅ አሰጣጥ እና ድምጽ ቆጠራው በሕግ እና በሥርዓት መከናወኑን በሚገባ መከታተል ይኖርባቸዋል። ከዚያም፣ የታዘቡትን ግድፈትም ሆነ ጥንካሬ ለመራጩ ሕዝብ እና ለዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ ይፋ በማድረግ የምርጫውን ቅቡልነት መወሰኛ መስፈርት ለማድረግ ሊተጉም ይገባል።
ለ፦ የመራጮች ትምህርት
ለቀጣዩ አጠቃላይ ብሔራዊ ምርጫ የመራጮች ትምህርት የሚሰጡ 143 የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችን መዝግቦ ዕውቅና ሰጥቷል። ከዚኽ አኳያ ስንመለከተውም፣ በእርግጥም መራጮች በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ለማድረግ አካታች፣ ተሳታፊ እና ግልጽ የሆነ ትምህርት በመስጠት ረገድ የሲቪክ ማኅበረሰብ ሚና የማይተካ ነው።
እኒኽ እውቅና የተሰጣቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምርጫውን አስመልክቶ የሚሰጧቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፣ ኹሉንም መራጭ የማኅበረሰብ ክፍል ተደራሽ ሊያደርጉ ከመገባቱ በተጨማሪ፣ በሚችሉት ልክ በኹሉም ቋንቋዎች እና በተለይም በሴቶች እና በአካል ጉዳተኞች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚኖርባቸው ማስታወስ ያሻል። ዜጎች ስለ መብታቸው እና ስለ ድምፅ አሰጣጥ ሂደት በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ በዋናነት የሚጠበቀው ከሲቪል ማኅበረሰቡ መሆኑ አሌ አይባልም። በዚኽም ዜጎች በምርጫው በንቃት እንዲሳተፉ ከማነቃቃት አልፎ፣ በምርጫው ወቅት የሚሰራጩ የሐሰት ወሬዎችን በማረም ዜጎች በእውነት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲሰጡ መርዳት ይኖርባቸዋል ብለን እናምናለን።
ሐ፦ መድረኮችን መፍጠር እና ግጭቶችን መከላከል
ብዙ እንደተጻፈውም፣ በእኛም የፖለቲካ ተላምዶ እንደተመለከትነው፣ ምርጫ በተፈጥሮው ውድድር ያለበት በመሆኑ ውጥረቶችን ሊያጭር ይችላል። ከዚኽ አንጻርም፣ በቅድመ-ምርጫውም ሆነ በድህረ-ምርጫው ወቅት፣ ግጭት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ምልክቶችን በመለየት ከመንግሥት እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎችም ይሰሩ ዘንድ ዜግነታዊ ኅላፊነታቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸው ማታወስ እንሻለን። ከዚኹ ጋር በተያያዘም፣ በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ሰላማዊ የሐሳብ ፍሰት እንዲኖር፣ ቀኑ ሳይገፋ የውይይት መድረኮችን ያመቻቹ ዘንድም ብሪጅ አበክራ ትጠይቃለች።
9. የብሪጅ ምክረ-ሐሳቦች
ሲቪል ማኅበረሰቡ እነዚኽን ሚናዎች በቀጣዩ የ2018 ምርጫ ላይም ሆነ ከዚያ በኋላ በሚኖራቸው እንቅስቃሴዎች፣ ለመወጣት ይቻላቸው ዘንድ፣ ብሪጅ ቀጣዮቹን አጠር ያሉ ምክረ-ሐሳቦች ለሚመለከታቸው የመንግሥት መዋቅሮች ማቅረብ ትሻለች።
ሀ፦የሀብት አቅርቦትን መጨመር
በአሜሪካ መንግስት ይደገፍ የነበረው የአሜሪካ በጎ አድራጎት ድርጅት፣ ለሲቪል ማኅበረሰቡ ይሰጥ የነበረውን ድጋፍ ካቋረጠ ዓመት ማለፉ ይታወቃል። ሲቪል ማኅበረሰቡም በነበረበት የፋይናንስ ዕጥረት ላይ ይኽ መከሰቱ፣ ሰፊ ተቋማዊ መዳከምን አምጥቷል። እናም፣ ይኽን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ የፌደራሉ መንግሥትም ሆነ ይመለከተናል የሚሉ መንግስታዊ የልማት ተቋማት፣ ለሀገር በቀል ድርጅቶቹ (በተለይም በቅርቡ ለተቋቋሙት እና አዲስ ለሚቋቋሙት) የተለያዩ ሀገር-በቀል ድጋፎችን የሚያገኙበትን የሕግ ማዕቀፍ ሊያዘጋጁ(ለማሳያም፣ ከገቢ ግብርም ሆነ ከሌሎች የግብር ዓይነቶች የሚኖሩ ማበረታቻዎችን)፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እና ዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ምንጮችን የሚያገኙበትን ዕድል ሊያመቻቹ ይገባል እንላለን። ከዚኽ ባለፈም፣ በውጭ ዕርዳታ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ፣ የአገር ውስጥ በጎ አድራጎት ባህልን ማሳደግ እና ድርጅቶቹ የአገር ውስጥ የገንዘብ ድጋፎችን የሚያገኙበትን የሕግ ሥርዓት መዘርጋትም መዘንጋት እንደሌለበት ማስታወስ ያስፈልገን ይሆናል።
ለ፦ የአገር ደኅንነት ፍተሻ እና የመመዝገብ መብት መጣጣም
ዜጎች የመደራጀት ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ፣ የምዝገባ ሂደቱ ከብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ጋር ተቀናጅቶ መከናወኑ ለአገር ደኅንነት ዋስትና መሆኑ አያከራክርም። ሆኖም፣ ይኽ የደኅንነት ፍተሻ ሂደት ለሲቪክ ማኅበራት ምዝገባ መዘግየት፣ ለቁጥር ማነስ ወይም ለቢሮክራሲያዊ እንቅፋት እንደ ሰበብ ሊቀርብ አይገባም።
ከዚኽ አኳያም፣ የደኅንነት ሥጋትን ከመቀነስ ጎን ለጎን፣ ተቋማዊ ግልጽነትን ለማረጋገጥ እና አላስፈላጊ መስተጓጎልን ለማስወገድ ሊወሰዱ ይገባቸዋል ብላ ብሪጅ ከምታምንባቸው አሥተዳደራዊ እርምጃዎች መካከል ቢያንስ ሦሥቱን መጥቀስ ትሻለች፤ ቀዳሚው የግልጽ መመሪያ መኖር አስፈላጊነት ሲሆን፤ የደኅንነት ምርመራው መመዘኛዎች በግልጽ ተለይተው የሚታወቁበት እና ከሕግ አግባብ ውጭ በሆኑ ግላዊ ውሳኔዎች የማይመሩ መሆን ይኖርባቸዋል።
ሌላይኛው፣ እንደተባለው የምርመራ ሂደቱ በዘመናዊ የዲጂታል ሥርዓት የታገዘ እና የተቀላጠፈ እንዲሆን ሲደረግ፣ በሕግ የተቀመጠውን የምዝገባ የጊዜ ገደብ የሚያከብር መሆን ይኖርበታል። በመጨረሻም፣ የደኅንነት ፍተሻው በዜጎች መሠረታዊ መብት ላይ የማይታይ ቢሮክራሲያዊ አልያም ፖለቲካዊ መሻትን የተንተራሰ ቀይ መስመር ከመሆን ወጥቶ፣ ሕጋዊ ድርጅቶች ያለ አንዳች ቢሮክራሲያዊ ማነቆ ወደ ሥራ የሚገቡበትን ኹኔታ ማመቻቸት ይኖርበታል እንላለን።