BRIDGE Research & Innovation - Parliaments. Peace. Policy

ወሩ መጋቢት እንደመሆኑ፣ ኢትዮጵያም 50ኛውን የሴቶች ቀን ደርበብ ባለ ሥርዓት አስባው ውላለች። ሴት እንደራሴዎቹም በ‘የዓመቱ መጋቢት 4 ቀን የሚከበረውን ይኽንኑ ዓለም ዓቀፉን የሴቶች ቀን አክብረው ውለዋል። የእንደራሴዎቹ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አመራሮች እና ሠራተኞች በተገኙበት ዓለም ዓቀፉ የሴቶች ቀን፣ “የሴቶች ድምጽ ለእኩልነት እና ለበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች መከበሩን የምክር ቤቱ ዘገባ ጠቅሷል። ይኽ ኹነትም፣ ስለ ኢትዮጵያ ሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ፣ የእንስት እንደራሴዎቹ ትናትናዎች እና ተግዳሮቶች እንዲኹም ዛሬዎቻቸውን አጠር አድርጎ ለመዳሰስ የብሪጅ የመጋቢት ዳሰሳ ርዕሰ-ጉዳይ ገፊ ምክንያት ሆኗል። ከዚኽ አኳያም፣ እነዚኽን መሠረታዊ ጥያቄዎች በጥቂት ኃልዮታዊ ነጥቦች አስደግፈን እና አሃዛዊ መረጃዎቹን እያሰባጠርን ልንመለከታቸው መርጠናል።

የሴቶቻችን ትናንቶች

በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንደ እቴጌ ጣይቱ እና ንግሥት ዘውዲቱ ያሉ ብርቱ ሴቶች አንድም በአገረ-መንግሥቱ ላይ በነበራቸው የመሪነት ቦታ፤ አንድም በዓድዋ ጦርነት ወቅት በነበራቸው ሚና ቢታወቁም፣ የሴቶች ተቋማዊ የፖለቲካ ውክልና ግን የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው። በኢትዮጵያ ዘመናዊ የእንደራሴዎች ምክር ቤት ታሪክ፣ በ1923 ዓ.ም. በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ሲጀመር የሴቶች ውክልና እጅግ አነስተኛ ነበር። በወቅቱ በሕዝባዊ የፖለቲካ ተዋስዖ ውስጥ የሚታዩት ጥቂት የባላባቶች፣ የመኳንንት እና የጦር መኮንኖች ሚስቶች ብቻ ነበሩ።

ለሴቶች የመምረጥ መብት የሕግ መሠረት የሆነው የ1948ቱ የተሻሻለው ሕገ-መንግሥት ቢሆንም፣ የመጀመሪያዋ ሴት እንደራሴ የተመረጠችው በ1949 ዓ.ም. ነበር። በዚኽም ምክንያት ሴቶች ከከፍተኛ የአመራር ቦታዎች ተገልለው የቆዩ ሲሆን፣ በ1957 እና በ1961 ዓ.ም. በነበሩት ምርጫዎች የሴቶች ቁጥር በተከታታይ 2 እና 5 ብቻ ነበር። ምንም እንኳ በወቅቱ የሴቶች ንቅናቄዎች ቢጀመሩም ቅሉ፣ ንቅናቄዎቹ ወደ ጠንካራ የፖለቲካ ተጽዕኖ አምጪነት የመለወጥ አቅም አልነበራቸውም። 

ኢትዮጵያውያን ሴቶች ዋጋ ባለው መንገድ ያሳዩት የፖለቲከኝነት ተላምዶት፣ እንደሌሎች የአገሪቱ ዘመናዊ የፖለቲካ ጅማሮዎች ኹሉ ዘመኑን ከ1960ዎቹ መጀመሪያ ይዋረሳል። ፖለቲካዊ አደባባዩ ላይ መቆም ለወንዶች ብቻ የተፈቀደ አድርጎ በሚያስብ ማኅበረሰባዊ ሥርዓት ውስጥ የእንስቶቹ ወደፊት መምጣት፣ የተማሪዎች ንቅናቄ አንደኛው ግዙፍ አስተዋጽዖ እንደሆነ የንቅናቄውን ዘመን የሚተርኩ ፀሐፊዎች ሁሉ ይስማማሉ።

ጸሓፍቱ እንደሚያመለክቱት፣ ራሱን በዋናነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያጠረው የተማሪዎች ንቅናቄ፣ ለሴቶቹ የ‘ራሳቸውን ድምፅ የሚያሰሙበት ከወንዶች ተጽዕኖ የፀዱ ተቋማት እንዲኖራቸው ባይፈቅድላቸውም፣ ዘግይተው በተመሰረቱት ፓርቲዎች በኩል ፆታን ማዕከል የሚያደርጉ ፖለቲካዊ ፍላጎቶቻቸውን ለመወከል ተሞክሯል። ጥናቶቹ እንደሚያትቱት፣ መኢሶን እና ኢሕአፓ የኢትዮጵያውያን ሴቶችን ጥያቄ፣ የመደብ እና የፆታ መንታ መልክ አድርገው አቅርበውታል። ከውስጠ-ፓርቲ መዋቅራቸው እና ከርዕዮተ-ዓለም ዝማሜያቸው አንፃር የፆታ-ፖለቲካውን በዚኽ መንገድ ሊበይኑት ቢሞክሩም፣ የፓርቲዎቹ ከፖለቲካው መድረክ በጭካኔ መወገድ በኋላ የሴቶች መነቃቃትም በከፍተኛ ኹኔታ ተቀዛቀዘ።

ደርግ ሥልጣን ሲይዝ የሴት እንደራሴዎቹ ቁጥር ወደ 4 ዝቅ ቢልም፣ ሴቶቹ ግን በሴቶች ጥያቄ ዙሪያ በተማሪዎች ንቅናቄ እና በተከታታይ አደባባይ ሰልፎቹ ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸው በስፋት ተመዝግቧል። የሴቶች የተደራጀ የፖለቲካ ተሳትፎ መነሻው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ሲሆን፣ በወቅቱ ስለ ሴቶች ጥያቄ የሚደረጉ ክርክሮች ለንቃተ-ህሊና ዕድገቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው።

ደርግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ በ1967 ዓ.ም. የሴቶች አስተባባሪ ኮሚቴን በማቋቋም ሴቶች ከቤት ውስጥ ሥራ ወጥተው በይፋ እንዲደራጁ መንገድ ከፍቷል። ሆኖም የሥርዓቱ ርዕዮተ-ዓለም መጀመሪያ ላይ የሴቶችን ችግር እንደ ድርብ ጭቆና (የመደብ እና የጾታ) ቢመለከተውም፣ ከ1970 ዓ.ም. በኋላ ግን “የመደብ ጭቆና ከጾታ ጭቆና ይበልጣል” የሚል አቋም በመያዙ የሴቶች ጥያቄ ለሶሻሊዝም ድል ተገዥ እንዲሆን ተደርጓል። ይኽም የጾታ ጭቆናን ትርጉም ባለው መልኩ ለመለወጥ ለተጀመረው ጾታ ተኮር ትግል እንቅፋት መሆኑ አልቀረም።

በ1967 ዓ.ም. የሴቶች አስተባባሪ ኮሚቴ፣ በ1972 ዓ.ም. ደግሞ የኢትዮጵያ ሴቶች አብዮታዊ ማኅበር (ኢሴማ) ተመሠረተ። ደርግ በ1972 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሴቶች አብዮታዊ ማኅበር (ኢሴማ)ን እስከ ታችኛው የሥልጣን እርከን ድረስ በማዋቀር የሴቶችን ተሳትፎ በቁጥር ለማሳደግ ጥረት ማድረጉም ይነሳለታል። ያም ሆኖ የማኅበሩ አመራሮች የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) አባላት ስለነበሩ፣ ሴቶች የራሳቸውን አጀንዳ የመቅረጽ ሥልጣን አልነበራቸውምና ማኅበራቱ የሥርዓቱ ርዕዮተ-ዓለም ማጥመቂያ እንጂ ሴቶችን በፖለቲካው እውነተኛ ተሳታፊ የሚያደርጉ አልነበሩም።

በ1979 ዓ.ም. የጸደቀው የኢሕዲሪ ሕገ-መንግሥት የሴቶችን የእኩልነት መብት በግልጽ እውቅና የሰጠ የመጀመሪያው ሰነድ ቢሆንም፣ በወቅቱ በነበረው የ‘ርስ በ‘ርስ ጦርነት ምክንያት በተግባር ሳይውል መቅረቱ ይታወሳል። እናም ደርግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ የአብዮታዊያን ኢትዮጵያውያን ሴቶች ማኅበርን መሰል የራሱን ክንፍ በማቋቋም ሶሻሊስት እንስታዊነትን ለመተርጎም እንደሞከረ ቢያምንም፣ ጉዳዩን ያጠኑ በዚኽ አይስማሙም። እኒኽ መሰሎቹ ጸሓፍት፣ ደርግ በአኢሴማ በኩል ያደራጃቸው ሴቶች፣ ለሥርዓቱ ወታደሮች ምግብ እንዲያበስሉ ከማድረግ ባለፈ የ‘ነርሱን ፍላጎት ለመፍታት አንዳች ጥረት ባለማድረጉ ይወቅሱታል።

በአንጻራዊነት ሕወሓት በሜዳ ትግሉ ዘመን የተሻሉ ሙከራዎችን አድርጓል ተብሎ ይጠቀስለታል። የወቅቱን የትግራይ ሴቶች ተሳትፎ ታሪካዊ ሲሉ የሚጠሩ የዘመኑ ዘጋቢዎች፣ ግንባሩ ያደረጋቸው በዘመኑ ማኅበረሰብ ውስጥ ስር ሰዶ የነበረውን ጾታዊ ኢ-እኩልነት የሚያስወግዱ ድርጊቶችን ይጠቅሳሉ። የጋብቻ ዕድሜን ከመገደብ አንስቶ በሞከራቸው የመሬት ማሻሻያ ፕሮግራሞቹም፣ የትግራይ ሴቶችን ከቀደመው ጊዜ የተሻለ አቅም እንዲያገኙ ማስቻሉ ይነሳለታል። ያም ቢሆን ግና፣ ብዙዎች እንደሚያምኑት ከደርግ ውድቀት ወዲኽ ፓርቲው ዋጋ የከፈሉለትን ሴቶች ወደ ጎን አሽቀንጥሯቸዋል።

በ1983 ዓ.ም. የደርግ ውድቀትን ተከትሎ ኢሕአዴግ በአገር ዓቀፍ ደረጃ ያለውን የጾታ ኢ-እኩልነትን ለመፍታት ጥረት ያደረገ ሲሆን፣ የ1987ቱ ሕገ-መንግሥት የሴቶችን መብት በግልጽ በማረጋገጥ፣ ሴቶች በፖለቲካው ንቁ እንዲሆኑ ልዩ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ደንግጓል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ሴቶች በኹሉም የሥልጣን እርከኖች ላይ በተገቢው ሁኔታ አልተወከሉም ነበር የሚለው፣ ቢያንስ እስከ 2010 ለነበረው የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ሥርዓት ኹነኛ መደምደሚያ ነው።

ከ2010 ዓ.ም. የፖለቲካ ሽግግር በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ.ር. ዐቢይ አሕመድ በሴቶች የፖለቲካ ውክልና ረገድ አዳዲስ እርምጃዎችን ወስደዋል። ጥቅምት 18 ቀን 2018፣ 20 አባላት ያሉት እና ግማሹ ሴቶች የሆኑበት የጾታ እኩልነት የተጠበቀበት ካቢኔ አቋቁመው እንደነበርም ይታወሳል። ይኽም ቀደም ሲል ከነበሩት 28 ሚኒስትሮች መካከል 4ቱ ብቻ ሴቶች ከነበሩበት ኹኔታ የተቀየረ ትልቅ እርምጃ ተደርጎ ሲወደስ ተስተውሏል። ኢትዮጵያም በዚኽ እርምጃዋ እንደ ሩዋንዳ ያሉ አገራትን ተሞክሮ በመከተል ዓለም ዓቀፍ ሙገሳን አግኝታበት ነበር። በዚኽ አዲስ አደረጃጀት ሴቶች እንደ መከላከያ፣ ሰላም፣ ንግድ፣ ሳይንስ እና ፋይናንስ ያሉ ወሳኝ የሥልጣን ቦታዎችን መያዝ ጀምረዋል።

ኢንጂነር አይሻ መሐመድ የአገሪቱ የመጀመሪያዋ ሴት መከላከያ ሚኒስትር፣ ሙፈሪያት ካሚል የመጀመሪያዋ ሴት የእንደራሴዎቹ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ እና ኋላ የፌደራል መንግሥቱ ሚኒስትር (በሰላም ሚኒስትርነታቸው)፣ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የመጀመሪያዋ ሴት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት፣ ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ፣ እንዲኹም ሳህለወርቅ ዘውዴ የአገሪቱ የመጀመሪያዋ ሴት ርዕሰ-ብሔር በመሆን በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል።

በእርግጥም በሥራ አሥፈጻሚው ዘርፍ የታየው የሴቶች ውክልና ዕድገት እጅግ ከፍተኛው መሆኑ አሌ አይባልም። በዚኽም፣ በ2009 ከነበረው 10 በመቶ የሴት ሚኒስትሮች ቁጥር፣ በኹለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ወደ 47.6 በመቶ ከፍ ብሏል። ይኽ ለውጥ ኢትዮጵያ በጾታ እኩልነት ረገድ የደረሰችበትን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚያረጋግጥ ነው ሲያስብልም ሰንብቷል፤ ሰንብቷል የሚያሰኘውም፣ የተወሰኑት ሴት ሹመኞች በተለያዩ መነሾች ከሥልጣናቸው መነሳታቸው፣ ውዳሴው ላይ ጥላ በማጥላቱ ይመስላል።

እንዴት ይሳተፉ?

የሴቶቻችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ በዚኽ መልኩ በወፍ በረር እንዳየነው፣ እጅጉን ከተባዕቱ ወገን ዝቅ ያለ መሆኑ፣ ዛሬም እንስቶቹ እንዴት በፖለቲካው ውስጥ ይሳተፉ የሚለውን ጥያቄ በመለስ ቀለስ የሚያስነሳ ርዕሰ-ጉዳይ ነው። ከዚኽ አንጻርም፣ ጥቂት ኃልዮታዊ ነጥቦችን ማንሳት ረብ ሳይኖረው አይቀርም።

ሴቶች በፖለቲካዊ ሥርዓት ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ አስመልክቶ ቁጥራቸው በዛ ያሉ ኃልዮቶች ቢኖሩም፤ በጉዳዩ ተከታታዮች በቀዳሚነት የሚቀነቀኑት ሦሥት ሙግቶች ናቸው። የመጀመሪያው ማጠንጠኛ፤ ሴቶቹ ራሳቸው በፖለቲካ ውስጥ ለመሳተፍ ያላቸው ጥልቅ ፍላጎት ላይ ይንተራሳል። ይኽን ፍላጎት የመጀመሪያው ደጃፍ ሲሉ የሚጠሩት አጥኚዎቹ፣ ሴቶቹ የተሳታፊነት ፍላጎት ቢኖራቸውም ይኽ ብቻውን ብዙም እንደማያስኬድ ይናገራሉ። በአገሪቱ ውስጥ ያሉት ነባራዊ አውዶች የተመቻቹ መሆን፣ ይኽን የሴቶቹን ፈቃድ ለመተግበር የግድ አስፈላጊ የሚባሉ ጉዳዮች ናቸው።

አጥኚዎቹ እንደሚያነሱት ኹኔታዎችን የተሻለ የሚያደርጋቸው መልካም ሊባል የሚችል ፖለቲካዊ ሥርዓት ህልው መሆኑ እና ወደ ፖለቲካው የሚመጡ ሴቶች ወደ አደባባይ ለመቅረብ የሚያስችላቸው የገንዘብም ሆነ ቁሳዊ ምንጮች መኖር ነው። እኒኽን ኹነቶች የተሳለጡ ሊያደርጓቸው የሚችሏቸው በዋናነት ማጠንጠኛቸውን በሴቶች ላይ ያደረጉ ንቅናቄዎች አልያም ተቋማት መብዛት ሲሆን፤ ለመሳተፍ ፈቃደኛ የሆኑት ሴቶች፤ ‘ራሳቸውን በፖለቲከኝነት ለማውጣት የሚያስችሉ ቁሳዊም ሆነ የገንዘብ-ነክ ነገሮች መሟላት አልፎም የታየ ኢ-ፍትሓዊነትን ለማርገብ ፖለቲካዊ ውክልና ይገባናል የሚሉ ንቅናቄዎች ጎልተው መውጣት ሴቶችን ወደ ፖለቲካው ይስባል።

ሌላይኛው የሐሳብ ጫፍ፣ የማኅበረሰቡ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ተለዋጮች የሴቶችን ፖለቲካዊ ስኬት አስመልክቶ የሚኖራቸውን ድርሻ ይይዛል። እንደ ሐሳቡ ተሟጋቾች፤ ሴቶች በአንድ አገር ውስጥ የሚኖራቸው የፖለቲካ ተሳትፎ አገሪቷ ውስጥ ባሉት እነዚኽ ጭብጦች ላይ ይወሰናል። የነገሩ ጸሓፍትም ይኽን ጉዳይ በሚገባ ለመረዳት አውዶቹን በሦሥት ዘርፎች ይከፋፍሏቸዋል።

የመጀመሪያው፤ ሴቶች ከፖለቲካው ውጪ በሌሎች ማኅበራዊ ፈርጆች ላይ የሚኖራቸው ስኬት ፖለቲካዊ ተጋብሮነታቸውን እንደሚወስን ጸሐፊዎቹ ይጠቅሳሉ። ከዚኽ አንጻርም፣ የሴቶች በትምህርት ስኬታማ መሆን ወደ ፖለቲካው ለመምጣት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው ሲሉ ጸሐፊዎቹ ይከራከራሉ። ሴቶቹ ጋዜጠኞች፣ የሕግ ትምህርት ባለሙያዎች አልያም የቢዝነስ ሰዎች ከሆኑ ከሌሎች አቻዎቻቸው ይልቅ በፖለቲካው ስኬታማ መሆን ይቻላቸዋል ሲሉም ይሟገታሉ። ለርዕሰ-ጉዳዩ አጥኚዎች የዚህ ምክንያቱ ግልፅ ነው፤ በተጠቀሱት ሙያዎች ስኬታማ መሆን የቻሉ ሴቶች፣ ከእነዚህ ፈርጆች በራስ መተማመንን፣ በሕዝባዊ አደባባዮች የመናገር ድፍረትን እንዲያገኙ እንዲኹም ከአገሪቱ ሕግጋት እና ነባራዊ ፖለቲካዊ ጭብጦች ጋር ጥልቅ ተላምዶት ስለሚኖራቸው ራሳቸውን ወደፖለቲከኝነት ለመቀየር አይቸገሩም።

ኹለተኛው ነጥብ ከላይ ከጠቀስነው ሐሳብ ጋር ይዛመዳል። ይኽም በአገሪቱ ውስጥ እጅግ ጠንካራ ሊባል የሚችል ጾታ-ተኮር ንቅናቄ መኖር ሲሆን፣ የዚኽ ፋይዳም በሥርዓቱ የሚተገበሩትን ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊም ሆነ የፖለቲካ አጀንዳዎች በመጫን የሴቶችን ጥያቄ ወደ ሐሳቦቹ መቀላቀል ያስችላል የሚል ነው። ከጾታዊ የተንሸዋረሩ ዕይታዎች የነጻ ማኅበረሰብ መኖር ለሴቶች የፖለቲካ ተወካይነት መጎልበት የተጠቀሰ የመጨረሻው ነጥብ ሲሆን፣ እንደ ጸሓፍቱ ክርክርም፣ የፖለቲካ ባህሉ በወንዶች ብቻ የማይበየን፣ ‘ፖለቲካን መስራት ለሴቶችም እንግዳ ኹነት አይደለም’ ብሎ የሚያምን ማኅበረሰብ፣ አንስቶቹን በፖለቲካ ለማጎልበት አይቸገርም።

ሦሥተኛው የጉዳዩ መተንተኛ የሐሳብ ማዕቀፍ በዋናነት የምርጫ ሥርዓትን እና የፆታ ኮታን የሚያቅፈው ፖለቲካዊ ኃቲት ነው። ድምጾችን ወደ ወንበር ቁጥር የመቀየሪያ መንገድ ተብሎ በተለምዶ የሚጠራው የምርጫ ሥርዓት፣ አኹን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በሥራ ላይ ካሉት የምርጫ ሥርዓት አማራጮች የተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓት፣ እንስቶችን ወደ ፖለቲካው ለማቅረብ የተሻለ እንደሆነ ሰፊ ምሁራዊ ዕምነት የተጣለበት የምርጫ ሥርዓት ሆኗል።

በፆታ-ተኮር የፖለቲካ ተዋስዖ ላይ በስፋት የሰሩት እንደሚከራከሩት፤ በተመጣጣኝ የምርጫ ውክልና አካሄድ አንድ የምርጫ ተወዳዳሪ ፓርቲ ለአንድ የምርጫ ወረዳ በዛ ያለቁጥር ያላቸውን አባላቱን በዕጩነት እንዲያቀርብ ስለሚያስችለው፣ ሴቶችን ማዕከል የሚያደርጉ ፖሊሲዎችን ተንተርሶ ድጋፉን ለማስፋት ሴት ዕጩዎችን እንዲያቀርብ ይገፋፋል። እንደሚታመነውም፣ ፓርቲዎች አንድ ዕጩ ብቻ የሚያቀርቡበት አካሄድ ከተጠቀሰው በተጻራሪው ለወንድ ፖለቲከኞች የተመቻቸ ዕድል ስለሚፈጥር የሴቶችን ተሳትፎ ያጎድላል።

በፈርስት-ፓስት-ዘ-ፖስት የምርጫ ሕግ መራጮች እንዲመርጡ የሚገደዱት ለምርጫ ከቀረቡት ፓርቲዎች የመሆን እድሉ ሲሰፋ፤ ከዚኽ በግልባጩ በተመጣጣኝ ውክልና አካሄድ እያንዳንዶቹ ፓርቲዎች ካቀረቧቸው ከአንድ በላይ የሆኑ ዕጩዎች ውስጥ የማስመረጥ ዕድልን ያገኛሉ። ይኼም ለሴቶች የተሻለ ዐውድ ይፈጥርላቸዋል። ይኽ አውድም፣ የሴቶችን ወደ ጎን መገፋት መግታት የሚቻለው ‘ነርሱን ወደ ፖለቲካዊ ተቋማት በማምጣት ነው ለሚሉ የአንስታዊነት የሐሳብ ጫፎች በማኅበረሰቡ ውስጥ መፋፋት ከፍተኛ አስተዋጾዖ ያደርጋል። ከዚኹ ጭብጥ ጋር በተሰናኘ በአጥኚዎቹ የሚነሳው፣ በአንድ ምርጫ ወረዳ ላይ ለተለያዩ የምርጫ ዕርከኖች (ለፌዴራል፤ ለክልል አልያም ለአካባቢ ምክር ቤቶች) በማዕከላዊ መንግሥቱ የሚፈቀደው የወንበር ቁጥር ሲሆን፣ ቁጥሩ እየበዛ ሲመጣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሴቶቻቸውን ወደፊት ለማምጣት ሲደፋፈሩ፤ በግልባጩ የተፈቀዱት ወንበሮች ቁጥር ካነሰ የሴቶቹም የተሳታፊነት ዕድል በዛው ልክ ይሸረሸራል የሚለው የሙግት ሥነ-ሐሳብ ነው።

ሌላይኛው የመከራከሪያ ነጥብ፣ የፖለቲካው ሥርዓት ተለዋጭ ጾታዊ አለመመጣጠንን ለማርገብ በብዙ አገራት የሚተገበረው የኮታ ሥርዓት ነው። በጭብጡ ላይ ያጠኑት ምሁራን የኮታ ሥርዓቱን በሦሥት ይከፍሉታል። የመጀመሪያው ሴቶች ሕግ አውጪ ምክር ቤት ውስጥ የተወሰኑ ለ‘ነርሱ ብቻ የተተዉ ወንበሮች እንዲያዙላቸው የሚያስገድድ የሕግ ማዕቀፍ ሲሆን፤ ይኽን እየተገበሩ ያሉትም የኮታ አካሄድን በቅርቡ መጠቀም የጀመሩ አገራት ናቸው።

ኹለተኛው አፈራረጅ፣ በአገሪቱ ውስጥ ያሉት ፓርቲዎች እያንዳንዳቸው የሴቶችን የተሳታፊነት ቁጥር አስመልክቶ የሚኖራቸው የውስጠ-ፓርቲ ደንብ ነው። ይኽ ደንብም፣ ፓርቲዎች ለዕጩነት ከሚያቀርቧቸው አባላት መካከል የተወሰኑት በሴቶች መሞላት እንዳለበት የሚደነግጉበት አግባብ ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩትም፣ በብዙ አገራት ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይኽን አማራጭ ሲጠቀሙ ለዚህ በምክንያትነት የተጠቀሰው፣ የሴቶችን በፖለቲካው ማሳተፍ ግድ የሚሉ የፌዴራል ሕግጋት መኖር ነው።

በመጨረሻ የሚነሳው የኮታ ዓይነት መለዮዎቹን ከቀደሙት ኹለቱ ጋር ያስተሳስራል። ኹሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሴቶች የተወሰኑ ልኬቶችን እንዲያስቀምጡ በሕግ ሲገደዱ እና ፓርቲዎቹም በ‘ራሳቸው አቅም ልክ መነሻ የሚሆኑ የድርሻ ማዕቀፎችን ሲያስቀምጡ ይኽን ዓይነት የኮታ አካሄድ ይተገበራል ይላሉ ጸሓፍቱ። እነዚኽን የኮታ የአፈራረጅ መንገዶች በኹለት ጭብጦች መጠቅለል እንደሚቻል የሚናገሩት የነገሩ ፀሐፊዎች፣ ኢ-ፍትሓዊ ምርጫዎች በሚያደርጉ አምባገነን መንግሥታት የጾታ ተኮር ፖለቲካን የድጋፍ ማሰባሰቢያ ለማድረግ ሲያስቡ፣ ሴቶችን በስፋት እና በፍጥነት ወደ ፖለቲካው ለማካተት ይመርጣሉ ይላሉ፤ በሌላ ጫፍ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት በጎለበተባቸው አገራት ያሉ ገዢ ፓርቲዎች የሚመረጡት አካሄድ የእንስቶቹን ዘገምተኛ የተሳታፊነት ሂደት ነው።

የሴት እንደራሴዎቹ የውክልና ምጣኔ በወፍ በረር

ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በኢፌድሪ የእንደራሴዎች ምክር ቤት ውስጥ የሴቶች ውክልና ጉልህ ለውጦችን አስተናግዷል። በኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ በ‘የምርጫ ዘመኑ በከፍተኛ ኹኔታ እየጨመረ መጥቷል።

በ1987 ዓ.ም. በተካሄደው የመጀመሪያው አገር ዓቀፍ ምርጫ በእንደራሴዎቹ ምክር ቤት ውስጥ የነበረው የሴቶች ቁጥር 15 (2.7 በመቶ) ብቻ የነበረ ቢሆንም፤ በኹለተኛው የምርጫ ዘመን ወደ 42 (7.7 በመቶ) አድጓል።

በሦሥተኛው የ1997ቱ ፌደራላዊ ምርጫ ደግሞ ይኽ ቁጥር ከፍ ብሎ ወደ 116 (21.4 በመቶ) ደርሷል። ዕድገቱም ቀጥሎ በ2002ቱ አራተኛው ብሔራዊ ምርጫ 152 (27.8 በመቶ) የደረሰ ሲሆን፣ በ2007 ደግሞ ከጠቅላላው 547 የምክር ቤት ወንበሮች ውስጥ በ210ሩ ምርጫ 38.8 በመቶ፣ እንዲኹም በ2013ቱ 42 በ መቶ ድርሻን በመያዝ ከፍ ያለ ምጣኔን አሳይቷል። ከዚኽ አኳያም፣ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ውስጥ በእንደራሴዎቹ ምክር ቤት የሴቶች አማካይ ውክልና በ‘የምርጫው የ6.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ይኹን እንጂ አጠቃላይ የሠላሳ ዓመታት አማካዩን ስንመለከት፣ ሴቶች የያዙት ወንበር 23 በመቶ ብቻ ሲሆን፣ ቀሪው 77 በመቶ በወንዶች የተያዘ መሆኑ የጾታ ስብጥሩ አኹንም ወደ ወንዶች ያዘነበለ መሆኑን በሚገባ ይጠቁማል።

ከእንደራሴነት ባለፈም እንደ አፈ-ጉባኤ እና ምክትል አፈ-ጉባኤ ያሉ ከፍተኛ የውሳኔ ሰጪነት ቦታዎችም የውክልናው መለኪያ መሆናቸውን ልብ ይሏል። ባለፉት የምርጫ ዘመናት ሴቶች በምክትል አፈ-ጉባኤነት ሚና የተሻለ ተሳትፎ የነበራቸው ቢሆንም፣ በእንደራሴዎቹ ምክር ቤት ታሪክ ውስጥ ግን እስከ አኹን አንድ ሴት አፈ-ጉባኤ ብቻ መሾሟ፣ ወደፊት የጾታ እኩልነትን በተሟላ እና በዘላቂነት ለማረጋገጥ ተጨማሪ የሕግ እና የመዋቅር ማሻሻያዎች እንደሚያስፈልጉ ያመላክታል።

ነገረ-ጉዳያችንን ከእንደራሴዎቹ ምክር ቤት ሻገር አድርገን ወደ ፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ስንወስደውም ብዙም የተለዩ አሃዛዊ መረጃዎችን አናገኝም። ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በኢትዮጵያ በተካሄዱት ሥድስት ተከታታይ አገር ዓቀፍ ምርጫዎች በፌዴሬሽን ምክር ቤት የነበረው የሴቶች ውክልና አዝጋሚ ለውጥ አሳይቷል።

በ1987 ዓ.ም. በተካሄደው የመጀመሪያው አገር ዓቀፍ ምርጫ ከነበሩት 110 የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት መካከል ሴቶቹ 7 (6.7 በመቶ) ብቻ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ 103 ወንበሮች በወንዶች የተያዙ ነበሩ። ከእንደራሴዎቹ ምክር ቤት በተለየ ኹኔታ፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ከፍተኛው የሴቶች ውክልና የተመዘገበው በ2007 ዓ.ም. በነበረው አምስተኛው አገር ዓቀፍ ምርጫ ሲሆን፣ ይኽም 50 (32.6 በመቶ) ወንበሮችን የያዙበት ዓመተ-ምርጫ ነበር። ሆኖም ይኽ ቁጥር በ2013 ዓ.ም. በተካሄደው ሥድስተኛው ምርጫ ወደ 43 (30 በመቶ) ዝቅ ብሏል። ለዚኽ መቀነስም በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል ተከስቶ በነበረው ጦርነት ምክንያት የትግራይ ክልል ተወካዮች በምክር ቤቱ ውስጥ አለመሳተፋቸው እንደ ዋና ምክንያት ይጠቀሳል።

የብሪጅ ዳሰሳ እንደሚያሳየው፣ በሥድስቱ የምርጫ ዘመናት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስጥ የወንዶች ድርሻ 81 በመቶ ሲሆን፣ የሴቶች ደግሞ 19 በመቶ ብቻ ነው። ይኽ አማካይ ውጤት እንደሚያሳየው በፌዴሬሽን ምክር ቤት ያለው የሴቶች ውክልና ከእንደራሴዎቹ ምክር ቤት አንጻር ሲታይ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን ነው። ምንም እንኳ በተለያዩ የምርጫ ዘመናት የቁጥር መዋዥቅ ቢታይም፣ ባለፉት ሥድስት የምርጫ ዘመናት በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሴቶች ውክልና አማካይ ዕድገት 3.88 በመቶ ብቻ ሆኖ ተመዝግቧል። ይኽ የውክልና ማነስ በምክር ቤቱ የሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባኤ ውስጥም ይስተዋላል። የሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባኤ በአገሪቱ የሕግ የበላይነት እና የሕገ-መንግሥት ትርጓሜ ላይ ከፍተኛ ሥልጣን ያለው ተቋም ቢሆንም፣ የሴቶች ተሳትፎ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኝባቸው ተቋማት መካከል ተጠቃሽ ሆኗል። ይኽም በከፍተኛ የሕግ ትርጓሜ እና የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የሴቶች ድምፅ እና አመለካከት አኹንም በተገቢው ኹኔታ እንዳልተካተተ ማሳያ አድርገን ልንቆጥረው ይቻለናል።

የሴቶች ውክልና በእንደራሴዎች ምክር ቤት


ተ.ቁ.የምርጫ ዘመንየሴት አባላት ቁጥርየሴቶች ድርሻ (በመቶኛ)
11ኛው (1987 – 1992)142.6 በመቶ
22ኛው (1993 – 1997)427.7 በመቶ
33ኛው (1998 – 2002)11721.4 በመቶ
44ኛው (2003 – 2007)15227.8 በመቶ
55ኛው (2008 – 2013)21338.9 በመቶ
66ኛው (2014 – 2019)197*41.7 በመቶ

*በ6ኛው የምርጫ ዘመን አልያም አኹን በሥራ ላይ ባለው የእንደራሴዎቹ ምክር ቤት ውስጥ የሴቶች ምጣኔ ከቀደመው ዝቅ ብሎ የሚታየው፣ በወቅቱ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች የተነሳ ክፍት የሆኑ ወንበሮች በመኖራቸው እንጂ በመቶኛ ሲሰላ ግን 41.7 በመቶ በመድረስ በታሪክ ከፍተኛው መሆኑን ልብ ይሏል።

የሴቶቹ ተሳትፎ በቋሚ ኮሚቴዎች ውስጥ

ተ.ቁ.የአገልግሎት ዘመንየቋሚ ኮሚቴዎች ብዛትየሴት ሰብሳቢዎች ቁጥር (በመቶኛ)የሴት ምክትል ሰብሳቢዎች ቁጥር (በመቶኛ)
11988 – 199291 (11 በመቶ)1 (11 በመቶ)
21993 – 1997121 (8 በመቶ)1 (8 በመቶ)
31998 – 2002133 (23 በመቶ)4 (31 በመቶ)
42003 – 2007164 (25 በመቶ)5 (31 በመቶ)
52008 – 2009187 (39 በመቶ)10 (56 በመቶ)
62010 – 2011208 (40 በመቶ)10 (50 በመቶ)
72011 – 2013106 (60 በመቶ)2 (20 በመቶ)
82014115 (45 በመቶ)4 (36 በመቶ)
አማካይ1988 – 201431.5 በመቶበመቶ


ጨመቃዊ ነጥቦች፤



የሴቶች ውክልና በፌዴሬሽን ምክር ቤት

ተ.ቁ.የምርጫ ዘመንጠቅላላ ወንበርየሴት አባላት ቁጥርየሴቶች ድርሻ (በመቶኛ)
11ኛው (1987 – 1992)11076.7 በመቶ
22ኛው (1993 – 1997)11287.1 በመቶ
33ኛው (1998 – 2002)1202218.3 በመቶ
44ኛው (2003 – 2007)1352417.7 በመቶ
55ኛው (2008 – 2013)1535032.6 በመቶ
66ኛው (2014 – 2019)1444330 በመቶ
ጠቅላላ1987 – 201977415419 በመቶ (አማካይ)

ጨመቃዊ ነጥቦች፤

ከላይ ያሉት ሦሥቱም አሃዛዊ መረጃዎ ዘንጠረዦች የተሰናሰሉት በእንደራሴ መጽሔት ነው።

የብሪጅ ምክረ-ሐሳቦች

ከላይ በደምሳሳው እንዳየነው፣ ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎም ሆነ፣ በተያያዥ መለከያ የሚሆነው የእንደራሴነት ጾታዊ ምጣኔ፣ ሰፊ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችም፣ መፍትሔዎችም ቢኖሩትም ቅሉ፣በእንደራሴዎቹ ምክር ቤት ሊተገበሩ የሚችሉ ሕግ እና ፖሊሲ ነክ ምክረ-ሐሳቦች ላይ ብቻ መታጠርን መርጠናል። ከዚኽ አንጻርም፣ ተከታዮቹን አጭር ፖሊሲ ነክ ምክረ-ሐሳቦችን ማጋራት እንሻለን።

በኢሕአዴግ ዘመነ-መንግስት የሴቶች ውክልና በእንደራሴዎቹ ምክር ቤት ቢጨምርም፣ ይኽ ዕድገት በሕግ የተደገፈ ሳይሆን በፓርቲው የውስጥ ያልተጻፈ መመሪያ ላይ የተመሰረተ ነበር። በብልጽግና ፓርቲ ዘመነ-መንግስትም ከፍተኛ የመንግሥት የሥልጣን እርከኖች ለሴቶች ቢሰጡም፣ በእንደራሴዎቹ ምክር ቤት ደረጃ ውክልናን የሚያረጋግጥ አስገዳጅ የሕግ ማዕቀፍ ገና አልተዘረጋም። እንደ ብሪጅ ዕምነትም፣ የሴቶች ውክልና በፓርቲዎች በጎ ፈቃድ ወይም ባልተጻፈ መመሪያ ላይ ብቻ እንዲመሰረት መተው የለበትም። ከዚኽ አንጻርም፣ የሴቶች ውክልና በገዥው ፓርቲ ጊዜያዊ በጎ ፈቃድ ላይ ብቻ እንዳይወድቅ፣ በምርጫ ሕጉ ውስጥ ለሴት ተወዳዳሪዎች የተወሰነ ዝቅተኛ የኮታ መጠን (ለምሳሌ 30 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ) በግልጽ ተደንግጎ እንዲቀመጥ ማድረግ ያስፈልጋል ብለን እናምናለን።

የብሪጅ ዳሰሳ እንደሚያሳየው ሴቶች በገቢ፣ በሰላም፣ በውጭ ጉዳይ፣ በበጀት እና በኢኮኖሚ ነክ ቋሚ ኮሚቴዎች ላይ ያላቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው። ስለዚህም፣ የእንደራሴዎቹ ምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችን እና ምክትል ሰብሳቢዎችን ሲመድብ፣ ሴቶች በኹሉም (በተለይም በኢኮኖሚ እና በደኅንነት) ኮሚቴዎች ውስጥ የላቀ የአመራር ድርሻ እንዲኖራቸው የሚያስገድድ የውስጥ የምክር ቤቱ መመሪያ መቀረጽ ይኖርበታል ብላ ብሪጅ ታምናለች።

በኢሕአዴግ ዘመን የእጩዎች ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በተሰኘው የግንባሩ መርህ የሚመራ በመሆኑ፣ ሴቶች ለዕጩነት የሚቀርቡት ከላይ በሚመጣ ቀጥተኛ ውሳኔ እንጂ በታችኛው መዋቅር ፍላጎት አልነበረም። ብዙዉን የፓርቲ መዋቅር ከኢሕአዴግ መውረሱ ብዙም በማያከራክረው ብልጽግናም ይኽ ከፍተኛ የአመራር ተዋረድ ቁጥጥር እንደቀጠለበት ይስተዋላል። እናም፣ ፓርቲዎች በውስጥ አሠራራቸው ግልጽ፣ ተወዳዳሪ እና ከማዕከላዊ ተፅዕኖ ነፃ የሆነ የእጩ ምልመላ ሥርዓት ቢዘረጉ ፋይዳው ብዙ መሆኑን ከላይ በዳሰሳዊ ነጥቦች ከማየታችን አኳያ፣ ብሎም በምክር ቤቱ አብላጫ ወንበሮችን የያዘው ብልጽግና ፓርቲ ነውና፣ ድርጅቱ ይኽን ምክረ-ሐሳብ ቢያጤነው ሴቶች በራሳቸው ብቃት እና በሕዝብ ድጋፍ እንዲወጡ ዕድል የሚሰጥበትን ሰፊ አገራዊ ኹኔታ ያመቻቻል ማለትን እንሻለን።

የኢትዮጵያ የትኞቹም ምርጫዎች እና ለመሳተፍ የሚካሄዱት የምርጫ ዘመቻዎች በርከት ያለ የፋይናንስ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ግድ የሚሉ መሆናቸው ይታወቃል። ይኽም ለሴቶች ተሳትፎ ትልቅ እንቅፋት መሆኑን ብዙ ጥናቶች ይጠቁማሉ። እንደ ብሪጅ ዕምነትም፣ መንግሥት እና የምርጫ ቦርድ ለሴት ዕጩዎች የሚሰጡትን መንግሥታዊ ድጋፍ ከወንዶች በተሻለ መልኩ የሚጨምርበትን አሠራር ቢዘረጉ ፋይዳው ብዙ ይሆናል። በዚኽ መሰሎቹ ድጋፎች መኖርም፣ ቢያንስ ሴቶቹ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ከምርጫ ፉክክሮች እንዳይገለሉ ይሄ ነው የሚባል አበርክቶ ይኖረዋልና። ከዚኽ ባለፈም፣ ለሴት ዕጩ እንደራሴዎች ብቻ የሚውል የተለየ የመንግሥት የምርጫ ፈንድ ማቋቋም እና የግል ለጋሾች ለሴት ዕጩዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያበረታታ የሕግ ማዕቀፍ ማበጀትም ቢታሰብበት እንላለን።

ምንም እንኳን ቀጣዩ 7 ብሔራዊ ምርጫ፣ በሕገ-መንግሥቱ በተቀመጠው መሠረት፣ አሸናፊው ፓርቲ መንግሥት የሚመሠርትበት ‘ፈርስት-ፓስት-ዘ-ፖስት’ የተሰኘው፣ አሸናፊው ኹሉን የሚወስድበት ጠቅላይ-የበላይ ሊሰኝ የሚችል የምርጫ ሥርዓትን ተከትሎ እንደሚተገብር ብናምንም፣ ቢያንስ ይኽኛው የእንደራሴዎቹ ምክር ቤት፣ የምርጫ ሥርዓቱ ቢያንስ በቀጣዩ ምርጫ ይቀየር ዘንድ ግፊት ሊያደርግ የሚችልበትን አማራጭ ማስሰ እንደሚኖርበት ማስታወስ እንሻለን። የዚኽ የምርጭ ሥርዓት መኖር፣ ሴቶቹ ወደ እንደራሴነት እንዳይመጡ ካገዷቸው መዋቅራዊ መሰናክሎች አንዱ መሆኑን ያስታውሷልና። የምርጫ ሥርዓቱን ወደ ተመጣጣኝ ውክልና አልያም ኹለቱን ወዳደባለቀ ሥርዓት መቀየር፣ ለሴቶች የተሻለ የውክልና ምጣኔ መንገድ መጥረጉንም ብሪጅ ማስታወስ ትሻለች።

በቀደሙት ጊዜያቶች የነበረው ጾታ-ተኮር ጫና ብዙም በአደባባይ ያልወጣ እና መዋቅራዊ ነበር። በአኹኑ ዘመን እንደምንመለከተው ግን፣ ሴት ፖለቲከኞች በማኅበራዊ ሚዲያ እና በአካል ግልጽ የሆኑ ስድቦች፣ ማስፈራሪያዎች እና ጾታ-ተኮር ጥቃቶች ሰለባ ሲሆኑ ይታያል። በሴት ፖለቲከኞች እና የአደባባይ የመብት አራማጆች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን፣ የቃላት ስድቦችን እና ማስፈራሪያዎችን የሚከላከል እና ወንጀለኞችንም ተጠያቂ የሚያደርግ ጠንካራ የሕግ ከለላ ማበጀት። ለቀጣዩ ትውልድ ጭምር ፋይዳው ብዙ ነውና ቢታሰብበት ስትል ብሪጅ ማስታወስ ትሻለች። 

የእንደራሴዎቹ ምክር ቤት የመሰብሰቢያም ሆነ የሌሎች የምክር ቤቱን ሥራዎች የተመለከቱ የሥራ ሰዓቶችን፣ የሕፃናት ማቆያ አገልግሎትን እና የጾታዊ ጥቃት መከላከያ ደንቦችን በማሻሻል ለሴት እንደራሴዎቹ ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር እንዳለበት አሌ አይባልም። እናም፣ እንደ እንደራሴ መረዳት፣ ምክር ቤቱ ይኽን ማድረጉ ሴቶች የቤተሰብ እና የፖለቲካ ሕይወታቸውን በአግባቡ እንዲመሩ እና በእንደራሴዎቹ ምክር ቤት በሚኖሩ ውይይቶች እና ወሳኝ ስብሰባዎች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ያበረታታልና፣ ቢታሰብበት ማለት እንወዳለን።

የእንደራሴዎቹ ምክር ቤት የሚያወጣቸው ሕግጋት እና በሚያጸድቃቸው በጀቶች በሴቶች ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ ለመገምገም የሚያስችል ጾታ-ተኮር ትንታኔ የሚከውንበት አሠራር ሊኖረው እንደሚገባው ግልጽ ነው። ከዚኽ ባለፈም፣ በየደረጃው ያለውን የሴቶችን ውክልና የሚመዘግብ እና ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆን ወቅታዊ የመረጃ ማቆሪያ ሥርዓት በምክር ቤቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት በኩል ቢጠናከር፣ ተቋማዊ ጥቅሙ ብዙ መሆኑን ብሪጅ ታምናለች፤ እናም፣ ይኽንን ምክረ-ሐሳብም የእንደራሴዎቹ ምክር ቤት ቢያጤነው ማለትን እንሻለን።