በአዲሱ የ2019 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት በጥቅሉ 1 ነጥብ 817 ትሪሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ያቀደ ሲሆን፣ ይኽ የገቢ ዕቅድ በ2018 በጀት ዓመት ይሰበሰባል ተብሎ ከተገመተው ጠቅላላ ገቢ አንጻር የ17 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት እንዳለው የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ፣ የበጀት ማብራሪያውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ ከ2019 በጀት ዓመት አጠቃላይ በጀት 88 ነጥብ 7 በመቶውን ከታክስ እና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች ለመሰብሰብ ታቅዷል። ይኽንን የታክስ ገቢ ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግም፣ በታክስ ፖሊሲ እና በታክስ አሥተዳደር ረገድ የተያዙ ማሻሻያዎችን፣ የታክስ ዲጂታላይዜሽንን እና የኤክሳይዝ ስታምፕ አሠራርን በተጠናከረ ኹኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል።

ለ2019 ዓ.ም በጀት ዓመት የተቀመጠው የተጣራ የበጀት ጉድለት፣ መንግስት በተሟላ የዐብይ-ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተረጋጋ የፋይናንስ ሥነ-ምኅዳር ለመፍጠር ከተቀመጠው ግብ ጋር የተጣጣመ መሆኑ ይጠቀሳል። በዚኽ አውድ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ሆኖ የተመዘገበው፣ መንግስት ከብሔራዊ ባንክ የበጀት ጉድለት መሸፈኛ ይወስደው የነበረውን ብድር ሙሉ በሙሉ ማቆሙ ሲሆን፣ ይኽም የዋጋ ንረትን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል ተብሏል። ከዚኽ በተጨማሪ፣ የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ወለድ ምጣኔ ተግባራዊ በመደረጉ ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲውን የሚያጠናክሩ በርካታ ለውጦች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ሲጠቀስ፣ ይኽንን ፖሊሲ ዘላቂ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ሚኒስትሩ ሲናገሩ ተደምጠዋል። የዐብይ-ኢኮኖሚው ማሻሻያ የዋጋ ንረትን በማረጋጋት ረገድ የጎላ ድርሻ ያለው ሲሆን፣ መንግስት በምግብ ዘይት፣ በመሠረታዊ ሸቀጦች እንዲኹም በመድኃኒቶች ላይ ተመጣጣኝ የድጎማ በጀት በመመደብ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራልም ተብሏል። በእነዚኽ መዋቅራዊ እርምጃዎች መነሻነት፣ በቀጣዩ የ2019 በጀት ዓመት የ10 ነጥብ 1 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚመዘገብ የተገመተ ሲሆን፣ ለዚኽ ዕድገትም የኢንዱስትሪ፣ የአገልግሎት እና የግብርና ዘርፎች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ ተነግሯል።

የበጀቱ አዘጋጆች፣ ከካፒታል በጀቱ ውስጥ 424.2 ቢሊዮን ብር (74.7 በመቶ) በአገር ውስጥ ግምጃ ቤት የፋይናንስ ምንጭ ለመሸፈን አቅደዋል። በተጓዳኝም የውጭ ዕርዳታ 112.6 ቢሊዮን ብር ያበረከተ ሲሆን፣ የውጭ ብድር ደግሞ 30.9 ቢሊዮን ብር ሆኗል። በዚኽም መሠረት የአገር ውስጥ ግምጃ ቤቱ የዕዳ ክፍያን በመፈጸም እና ለክልሎች የሚደረጉ የበጀት ድልድሎችን በገንዘብ በመደገፍ ላይ ሳለ፣ አብዛኛውን የልማት ፕሮግራም ወጪም በዋናነት የተሸከመ ሆኗል። አጠቃላይ የውጭ ዕርዳታ 204.8 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ አጠቃላይ የውጭ ብድር ደግሞ 193.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል፤ ይኽም ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ ከዓለም ባንክ፣ ከጣሊያን እና ከፈረንሳይ በቀጥታ የተገኘውን 162.8 ቢሊዮን ብር የበጀት ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ያጠቃለለ ሆኗል። ከዚሁ የውጭ ፋይናንስ ምንጭ ጋር በተያያዘም፣ የዓለም ባንክ ሰኔ 18 ቀን 2018 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ መንግስት የ1.45 ቢሊዮን ዶላር የበጀት ድጋፍ ለማጽደቅ መወሰኑን አስታውቋል። ይኽ አዲሱ ድጋፍ፣ ቀደም ሲል ለአገሪቱ ከተመደበው የ17 ቢሊዮን ዶላር የብድር እና የዕዳ አገልግሎት ማቅለያ ድጋፍ ድልድል ቀጥሎ የመጣ የፋይናንስ ምንጭ መሆኑን ያስታውሷል።

ብድሯ እና በጀቷ

የፌደራሉ መንግስት፣ በመጪው ሐምሌ ወር ለሚጀምረው የ2019 በጀት ዓመት ካዘጋጀው 2.34 ትሪሊዮን ብር የበጀት መጠን ውስጥ 542.1 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ዕዳ ክፍያ እንዲውል መድቧል። ይኽ የገንዘብ መጠን በዘንድሮው በጀት ዓመት ለተመሳሳይ ጉዳይ ከተመደበው በ79 ቢሊዮን ብር ገደማ ያሻቀበ ሆኗል። ይኽ በጀት ሲዘጋጅ ታሳቢ ተደርገዋል ከተባሉት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል፣ በ2019 ሊኖር የሚችለውን የአገር ውስጥ ብድር ጫና አንዱ መሆኑን ለምክር ቤቱ ከቀረበው የበጀት ማብራሪያ ሰነድ ላይ ተጠቅሷል። በዚኽም ምክንያት በጀቱ ሲዘጋጅ፣ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ዕዳ ክፍያን ግምት ውስጥ ማስገባቱን ለፓርላማው አባላት የተሰራጨው የበጀት ማብራሪያ ጥራዝ አመልክቷል። በ2019 በጀት ከፍተኛ ድርሻ የያዘው መደበኛ ወጪ ዝርዝር ሲዘጋጅም፣ የዕዳ ክፍያ ጉዳይ ታሳቢ መደረጉም ተገልጿል። ከዚኽ አኳያም፣ ከመደበኛ ወጪ ውስጥ 43.3 በመቶ ድርሻን በመያዝ ቀዳሚ የሆነው ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ዕዳ ክፍያ የተመደበው 542.1 ቢሊዮን ብር ሆኗል። ግማሽ ትሪሊዮን ብር የተሻገረው ይኽ የገንዘብ መጠን፣ ዘንድሮ ለተመሳሳይ ጉዳይ ከተበጀተው ጋር ሲነጻጸር በ17 በመቶ የጨመረ ሲሆን፣ በ2019 በጀት ዓመት ለውጭ አገር ዕዳ ክፍያ የተመደበው የገንዘብ መጠን 293.3 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ለአገር ውስጥ ዕዳ የተያዘው ደግሞ 248.7 ቢሊዮን ብር ሆኗል።

በ2017 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት አጠቃላይ ዕዳ 52.75 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር የቀደሙት መረጃዎች ያሳያሉ። ከዚኽ ውስጥ 64.4 በመቶው የውጭ ዕዳ እንደሆነ ሲታወስ፣ የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ ክምችት በ2014 እስከ 2015 በጀት ዓመታት መጠነኛ ቅናሽ ቢያሳይም፣ በ2017 በጀት ዓመት ጭማሪ አሳይቷል። ጭማሪው የተመዘገበው በበጀት ዓመቱ በበጀት ድጋፍ መልክ የተገኘው የውጭ ሀብት ፍሰት በማደጉ እንደሆነ ከገንዘብ ሚንስቴር የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የጭማሪው ምክንያቶችም በዋናነት የዐብይ-ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራውን ለመደገፍ ከኢትዮጵያ የልማት አጋሮች በተለይም ከአይ.ኤም.ኤፍ እና ከዓለም ባንክ የኮንሴንሽናል ብድሮች መለቀቃቸው እንደነበርም እንደራሴ የዳሰሰቻቸው ሰነዶች ያሳያሉ። ይኽን ተከትሎም በ2016 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ 29.6 ቢሊዮን ዶላር የነበረው የውጭ ዕዳ ክምችት፣ በ2017 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ወደ 34 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል። የአገር ውስጥ ዕዳ ክምችቱም፣ ከዓመት ወደ ዓመት ድርሻው እየጨመረ መጥቶ፣ በ2016 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ከጠቅላላ ዕዳ ክምችት ውስጥ የአገር ውስጥ ዕዳ ይዞ የነበረው ድርሻ 57.4 በመቶ የነበረ ቢሆንም፣ ይኽ ከፍተኛ ድርሻ በ2017 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ወደ 35.6 በመቶ መወረዱን ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተገኙ ቁጥራዊ መረጃዎች ያሳያሉ። ለዚኽ በምክንያትነት የሚጠቀሰው፣ በ2017 በጀት ዓመት ተግባራዊ የተደረገው የውጭ ምንዛሬ ግብይት ሥርዓት ማሻሻያ ሲሆን፣ ማሻሻያው ብር ዶላርን ከመሳሰሉ የመገበያያ ገንዘቦች አኳያ ያለውን የምንዛሬ ተመን በከፍተኛ ኹኔታ የቀነሰው ሆኗል።

የኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ብድር ስንት ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ያለው የቅርብ ጊዜ መረጃ፣ ከጥቂት ጊዜያት በፊት የገንዘብ ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ነው። በዚያ ሪፖርት መሠረት፣ እስከ መጋቢት 22 ቀን 2018 ድረስ ያለው የኢትዮጵያ አጠቃላይ የውጭ እና የአገር ውስጥ ብድር 51.8 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። የውጭ ብድሩ 33.5 ቢሊዮን ዶላር ድርሻ ሲይዝ፣ የቀረው 18.3 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ የአገር ውስጥ ብድር ሆኗል። ከአገር ውስጥ ብድር ከፍተኛውን ድርሻ ማለትም 17.5 ቢሊዮን ዶላር የፌደራል መንግስት የያዘ ሲሆን፣ በሚኒስቴሩ ሪፖርት መሠረት የተቀረው 800 ሚሊዮን ዶላር የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከብሔራዊ ባንክ የተበደሩት ሆኗል። የመንግስት የአገር ውስጥ ብድር እንዲጨምሩ ካደረጉ እርምጃዎች አንዱ የገንዘብ ሚኒስቴር የ10 ዓመት ቦንድ በማውጣት የመንግስት የልማት ድርጅቶች የነበረባቸውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕዳ መረከቡ ስለመሆኑ፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሪፖርት ጠቅሶ ነበር። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከንግድ ባንክ የተበደረውን 263.3 ቢሊዮን ብር ጨምሮ የመንግስት የልማት ድርጅቶች 845.3 ቢሊዮን ብር ዕዳ ወደ ረዥም ጊዜ ቦንድ የተቀየረው በጥቅምት 2017 መሆኑ ይታወሳል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀ ዐዋጅ የሚወጡት የዕዳ ሰነዶች ከሦስት ዓመታት የችሮታ ጊዜ በኋላ በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተከፍለው የሚጠናቀቁ ሲሆን፣ በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና በንግድ ባንክ ሥምምነት የሚወሰን ወለድም ይከፈልባቸዋል። እስከ መጋቢት 30 ቀን 2018 መንግስት በግምጃ ቤት ሰነድ 492.3 ቢሊዮን ብር፣ በረዥም ጊዜ ቦንድ እና በግምጃ ቤት ቦንድ 2.2 ትሪሊዮን ብር እንደተበደረ ገንዘብ ሚኒስቴር ለሕግ አውጪው ምክር ቤት ባቀረበው ማብራሪያ አሳይቷል። በአጠቃላይ የመንግስት የአገር ውስጥ ብድር 2.7 ትሪሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች 125.8 ቢሊዮን ብር ብድር ሲታከልበት አጠቃላይ የአገር ውስጥ ዕዳው 2.8 ትሪሊዮን ብር ደርሷል።

በዚኽ የቀጣይ ዓመቱ በጀት፣ የዕዳ ክፍያን ተከትሎ በኹለተኛነት የተቀመጠው ለበጀት ድጋፍ የተመደበው 238.1 ቢሊዮን ብር ሆኗል። በተመደበለት የገንዘብ መጠን በ2018 የበጀት ድልድል አራተኛ ደረጃን ይዞ የነበረው የትምህርት ዘርፍ፣ በ2019 በጀት ዓመት ወደ ሦሥተኛ ደረጃ ከፍ ያለ ሲሆን፣ በመጪው ዓመት ለትምህርት ዘርፍ የተያዘው የወጪ መጠን 158.2 ቢሊዮን ብር ሆኗል። ለመጠባበቂያ ወጪ የተያዘው 124.4 ቢሊዮን ብር በአንጻሩ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በ2019 በጀት ዓመት አምስተኛ ደረጃን የያዘው የመንገድ ግንባታ ወጪ ሲሆን፣ ለመጪው ዓመት ለመንገድ የተመደበው የገንዘብ መጠን 123.8 ቢሊዮን ብር ሆኗል። ለዘርፉ የተመደበው የገንዘብ መጠን ከዘንድሮው ጋር ሲነጻጸር በ28.8 ቢሊዮን ብር ከፍ ቢልም፣ በ2018 ባለው አምስተኛ ደረጃው ላይ ግን ለውጥ አላመጣም።

በጀቱ ንሯል?

ይኽንን ኹለት ትሪሊየን ብር የተሻገረውን የ2019 በጀት አስመልክቶ፣ ሊነሳ የሚችለው አንዱ መወያያ ነጥብ፣ በእርግጥ በጀቱ ንሯልን? የሚለው ይመስላል። ከላይ ከፍ ብለን እንደጠቀስነው፣ ኢትዮጵያ ካለባት የዕዳ ጫና እና መክፈል ከሚጠበቅባት ግዴታ አንጻር፣ እንዲኹም በተለይም ምርት እና ምርታማነትን አሳድጎ የዜጎቿን ኑሮ ለማሻሻል ከሚያስፈልጋት የልማት ፍላጎት፣ ካለው የዋጋ ግሽበት እና የብር የመግዛት አቅም መዳከም ጋር በጀቱ ሲመዘን፣ የቁጥሩን ያህል ግዙፍ ነው ወይ የሚል ጥያቄ አስነስቷል። የዚኽ የበጀት መጠን ጤናማነትን ለመለካትም፣ በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ዘንድ የተለያዩ መለኪያዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ።

የመጀመሪያው መለከያ የበጀት ጉድለት ሲሆን፣ አኹን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በበጀት ዓመቱ ሙሉ 2.34 ትሪሊዮን ብር አወጣለሁ ቢልም፣ መሰብሰብ የሚችለው ግን ወደ 1.8 ትሪሊዮን ብር ግድም እንደመሆኑ፣ በመካከል ላይ ወደ 522 ቢሊዮን ብር ጉድለት ይገጥመዋል። በዚህ ልዩነት ሲለካ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተቀመጠ መለኪያው፣ የተጣራ 1.3 በመቶ የበጀት ጉድለት እንደመሆኑ፣ እጅጉን አብዝቶ ለማደግ ለሚፈልግ ኢኮኖሚ ይኽ ቁጥር ግዙ ነው ለማለት አያስችልም የሚለው መከራከሪያ ውኃ ይቋጥራል።

ኹለተኛው መለኪያ በጀቱ ያደገበት ምጣኔ ምን ያህል ነው የሚለው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ቢኖርበትም፣ አኹን በጀቱ ከአምና ወደ ዘንድሮ ያደገው በ21 ከመቶ ሆኗል። የተጣራውን ስንመለከት፣ የዋጋ ንረቱ የገንዘቡን ዋጋ የሚበላው በመሆኑ፣ የተጣራ ዕድገቱን 21 ከመቶ አድጓል ቢባል እና የዋጋ ንረቱ 13 ከመቶ ነው ቢባል፣ ልዩነቱ 8 ከመቶ አካባቢ በመሆኑ የተጣራው ዕድገት 8.1 ከመቶ እንደሆነ ይቆጠራል። በአኹኑ ወቅት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የገንዘብ የመግዛት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ከመዳከሙ ባለፈ፣ የኢትዮጵያ ብዙ የልማት ፕሮጀክቶች ደግሞ የውጭ ምንዛሬ የሚፈልጉ በመሆናቸው፣ አምና የተሠሩት ተመሳሳይ ፕሮጀክትን ዘንድሮ ለመሥራት፣ ምርቶች ከውጪ ስለሚገቡ፣ ይኽንን ለመከወንም ብዙ የኢትዮጵያ ብር አስፈላጊ ይሆናል። ከዚኹ ጋር በተሳሰረ በሌላ ጫፍ ልንመለከተው ስንሞክርም ወደ ተመሳሳይ ድምዳሜ እንደርሳለን፤ ይኽ የ2.34 ትሪሊዮን ብር፣ (ይኽን ዳሰሳ ስናዘጋጅ ባለው የውጭ ምንዛሬ፣ ማለትም በ160 ብር ተመን) በዶላር ቢሰላ ወደ 14.9 ቢሊዮን ዶላር ግድም ሲሆን፣ ይኽ ደግሞ በዶላር ሲታይ ከአምስት ከመቶ የማይበልጥ ጭማሪ ስላለው በጀቱን የናረ ማለትን አስቸጋሪ ያደርገዋል።

በሌላ በኩል ኢኮኖሚው ከፍ ያለ የብድር ዕዳ የተሸከመ መሆኑ ባለፈ፣ ከተያዘው በጀትም ግማሽ ትሪሊዮኑ ተመልሶ ዕዳ የሚከፈልበት በመሆኑ፣ ከእሱ የተረፈው ሲሰላ ትልቅ የሚባል በጀት እንዳልሆነም መመልከት ይቻላል። በጣም ብዙ ዕዳ የተሸከመ ኢኮኖሚ ከሆነ ብዙ በጀት መያዙ፣ ከበጀቱ ውስጥ መደበኛ ሥራውን መሥራት፣ የካፒታል ሥራዎችን ማከናወን፣ የሚደጎመውን መደጎም እና ዕዳውን ማቃለልን ቁጥራዊ አመክንዮቹ ግድ ያደርጉታል። ይኽ ኢኮኖሚ ግማሽ ትሪሊዮን ዕዳ እንደመያዙም፣ ከ2.34 ትሪሊዮን ብር ላይ 542.1 ቢሊዮን ብር ለዕዳ ሲቀነስለት፣ በገቢነት የሚያስገባውን እና የሚያወጣውን የሚያመጣጥን ኢኮኖሚ መሆኑንም እንመለከታለን። ለዚኽም የፌደራሉ መንግስት 1 ነጥብ 817 ትሪሊዮን ብር እሰበስባለሁ ቢልም፣ አጠቃላይ ወጪው 1 ነጥብ 8 ትሪሊዮን ብር በመሆኑ፣ የተረፈውን ገቢ ያለበትን ዕዳ ለመክፈል እንጂ ለሌላ አዲስ የልማት ሥራ የሚያውለው አይሆንም። ስለዚኽም፣ ግዙፍ የሆነ ዕዳ ካለበት በጀቱ ከፍ ሊል መቻሉ ተጋኗል ማለትን አስቸጋሪ ያደርገዋል።

በእርግጥ ይኽ የ2019 በጀት ተጋኗል ሊያስብል የሚችለው አስተያየት የሚነሳው፣ የብር የመግዛት አቅም መዳከም ጋር በተያያዘ የሞኒተሪ ኢኮኖሚክስ ክርክር ይመስላል። ከዚኽ አንጻርም፣ ይኸው በጀት ከአምናው አንጻር እጅግ ከፍ ብሎ የታየው፣ በጀቱ በዋናነት የገንዘብ መግዛት አቅም መዳከምን በመጠቆሙ ነው። ከብር አኳያ ስናየው፣ የዘንድሮው በጀት ወደ አራት ቢሊየን ብር ጭማሪ እንደማሳየቱ፣ ብር ለበጀቱ ደህና መመዘኛ አለመሆኑን መመልከት ይቻላል። ያም ሆኖ፣ ለበጀቱ በከፍተኛ ኹኔታ መጨመር ቢያንስ የዋጋ ግሽበት እና የፌደራሉ መንግስት ወጪ መጨመር ዋንኛ አስተዋጽዖ እንዳላቸው ማስታወስ ያሻል።

ቁጥሮቹ ሲነጻጸሩ

ይኽንን በጀት በቅጡ ለመመልከት፣ የተለያዩ ቁጥራዊ ንጽጽሮሾችን ማድረግ ሰፋ ያለ ዕይታም ይሰጠናልን፣ ከቀደሙት ዓመታት ጋር በከፊል ስናነጻጽረው ቀጣዮቹን ቁጥራዊ ዕይታዎች እናገኛለን።

የፌደራሉ መንግስት ለ2018 ዓ.ም. በጀት ዓመት የመደበው በጀት፣ በብር ሲሰላ በከፍተኛ ፍጥነት የሰፋ ሆኗል። በ2016 በጀት ዓመት ከነበረበት 562 ቢሊዮን ብር፣ በ2017 ወደ 971 ቢሊዮን ብር፣ እንዲኹም በ2018 ወደ 1.93 ትሪሊዮን ብር አድጓል፤ ይህም በአማካይ የ51 በመቶ ዓመታዊ የዕድገት መጠንን ያሳየ ሆኗል። ጠንካራ መለኪያ የሚባለው የውጭ ምንዛሬ በመሆኑ፣ መጀመሪያ የበጀቱን መጠን በዶላር ሠርተን የኢኮኖሚውን እውነታ ስንፈትሽ፣ በጀቱ በብር ሲታይ በከፍተኛ ሁኔታ ያደገ ቢመስልም፣ በዶላር ሲሰላ ግን ዕድገቱ እጅግ አነስተኛ ሆኖ ተመዝግቧል። ለ2018 በጀት ዓመት የተመደበው በጀት 1.93 ትሪሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ ዘንድሮ 2.34 ትሪሊዮን ብር በመሆኑ በብር ሲታይ ግዙፍ ዕድገት ያሳየ ሆኗል። ሆኖም በብር ሲታይ በጀቱ የ21 ከመቶ ዕድገት ሲያሳይ፣ በዶላር ግን ያደገው በ3.5 ከመቶ ብቻ ሆኗል። ይኽም፣ አስቀድመን እንደጠቀስነው የብር የመግዛት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ መዳከሙን ያሳየ ሆኗል።

ባለፈው ሰኔ ወር ላይ የአንድ አሜሪካ ዶላር አማካኝ ዋጋ 135.5 ብር አካባቢ የነበረ ሲሆን (ዝቅተኛው 133፣ ከፍተኛው 137 ብር ነበር)፣ በጀቱ ከጸደቀ በኋላ የነበረውን የ137 ብር የምንዛሬ ተመን መሠረት አድርገን አምና የነበረውን 1.93 ትሪሊዮን ብር ወደ ዶላር ብንቀይረው፣ በጀቱ 14.1 ቢሊዮን ዶላር የነበረ መሆኑን እንረዳለን። የምንዛሬ ተመኑን 160 ብር አድርገን በጀቱን ስናሰላው፣ የቀጣዩ ዓመት በጀት 14.6 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ሆኗል። ይኽም ማለት በጀቱ በገንዘብ መጠን በብር 410 ቢሊዮን ብር የጨመረ ቢመስልም፣ በዶላር ሲሰላ ግን የጨመረው 500 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ሆኗል።

ትንሽ ወደ ኋላ መለስ ስንልም የምናገኘው ወደ ተመሳሳይ ድምዳሜ የሚመራ ነው። ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ በጀቱ በብር ሲለካ የ480 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በአንጻሩ፣ ወደ አሜሪካ ዶላር ሲቀየር የዕድገት መጠኑ እጅግ አነስተኛ ሲሆን፣ የታየው ጭማሪ የ8 በመቶ ብቻ ሆኗል። በኹለቱ የገንዘብ ዓይነቶች መካከል ያለው ልዩነት ጉልህ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፤ በ2013 ዓ.ም. 476 ቢሊዮን ብር የነበረው የፌዴራሉ በጀት፣ ለ2019 ዓ.ም. ወደ 2.3 ትሪሊዮን ብር ደርሷል።

ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ የነበረውን የዕድገት ጉዞ መለስ ብለን ስንቃኝም እኒኽን ቁጥሮች እናገኛለን፤ በ2013 ዓ.ም. 476 ቢሊዮን ብር፣ በ2014 ዓ.ም. 561 ቢሊዮን፣ በ2015 ዓ.ም. 786 ቢሊዮን፣ በ2016 ዓ.ም. 801 ቢሊዮን እና በ2017 ዓ.ም. 971 ቢሊዮን ብር ሆኗል። ይህ መስፋፋት በመቀጠል ለ2019 ዓ.ም. ደግሞ 2.3 ትሪሊዮን ብር ደርሷል። በተቃራኒው፣ በዶላር ሲለካ በጀቱ አነስተኛ ለውጥ ብቻ ያሳየ ሲሆን፣ በ2013 ዓ.ም. ከነበረበት 13.6 ቢሊዮን ዶላር በ2019 ዓ.ም. ወደ 14.9 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ያደገ ሆኗል።

ሌላይኛው የበጀት ማንጸሪያችን እንዲሆነን፣ ባለፉት በጀት ዓመታት ለክልሎች ይሰጥ የነበረውን ድጎማንም በጥቂቱ እንመልከት።

የፌደራል መንግስት ለ2019 ባዘጋጀው በጀት፣ ለ12 ክልሎች እና ለኹለት ከተማ አሥተዳደሮች የተመደበው የገንዘብ ድጎማ መጠን ለመጀመሪያ ጊዜ ግማሽ ትሪሊዮን ብር ተሻግሯል። በዚኽ የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ ባለፈው ዓመት ከድጎማ ዝርዝር ውጭ ተደርጎ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ተመልሶ የተካተተ ቢሆንም፣ የተመደበለት የገንዘብ መጠን ግን ሩብ ቢሊዮን ብር ያልደረሰ ሆኗል። አሥተዳደሩ በ2019 በጀት ዓመት የተመደበለት የገንዘብ ድጋፍ መጠን 74.53 ሚሊዮን ብር ብቻ ሲሆን፣ በ2017 የተመደበለት ድጎማ 5.45 ቢሊዮን ብር፣ በ2016 በጀት ዓመት አምስት ቢሊዮን ብር ነበር። ለመጪው በጀት ዓመት ከተያዘው የክልሎች ድጋፍ ውስጥ ከፍተኛው መጠን የተመደበው ለኦሮሚያ ክልል ሲሆን፣ አማራ እና ሶማሌ ክልሎች በሚያገኙት የድጎማ መጠን በኹለተኛ እና ሦሥተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። የኦሮሚያ ክልል ለ2019 በጀት ዓመት የተመደበለት ድጋፍ 179.35 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ በ2018 በጀት ዓመት ደግሞ 108.4 ቢሊዮን ብር ተመድቦለት ነበር። በተመሳሳይ መልኩ የአማራ ክልልም፤ ከፌደራል በሚገኝ ድጋፍ ኹለተኛውን ከፍተኛ መጠን ሲያገኝ የቆየ ሆኗል። የአማራ ክልል የ2019 በጀት ዓመት የፌዴራል ድጎማ 112 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ከ2018 በጀት ዓመት ከነበረው 90 ነጥብ 25 ቢሊዮን ብር አንጻር የ22 ነጥብ 15 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል።

በሦሥተኛ ደረጃ ደግሞ የሶማሌ ክልል ሲቀመጥ፤ ክልሉ በ2019 በጀት ዓመት የተመደበለት የድጋፍ ገንዘብ 52 ቢሊዮን ብር ሲጠጋ፣ ይኽ የድጎማ መጠንም ለክልሉ በዘንድሮው በጀት ዓመት ከተመደበው ድጎማ በ20 ቢሊዮን ብር የላቀ ሆኗል። በአራተኛ እና በስድስተኛ ደረጃ የተቀመጡት የደቡብ ኢትዮጵያ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ሲሆኑ፤ ኹለቱ አዳዲሶቹ ክልሎች ለመጀመሪያ ጊዜ በበጀት ዝርዝር ውስጥ የገቡት በ2017 ዓ.ም የነበረ ሲሆን፣ በዚሁ በጀት ዓመት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 15.2 ቢሊዮን የድጋፍ ገንዘብ የተመደበለት ሲሆን፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደግሞ 12.8 ቢሊዮን ብር ተበጅቶለታል። ከኹለት ዓመት በኋላ ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተመደበው ድጎማ ከኹለት እጥፍ በላይ ጨምሮ 36.5 ቢሊዮን ብር ሲደርስ፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ድጋፍም በተመሳሳይ 30.9 ቢሊዮን ብር ገብቷል። በክልሎች የድጋፍ ክፍፍል አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የትግራይ ክልል፣ ለመጪው 2019 በጀት ዓመት የተመደበለት የድጋፍ ገንዘብ 31.3 ቢሊዮን ብር ሆኗል። ይህ የድጎማ መጠን ለክልሉ ዘንድሮ ከተመደበው ድጎማ በ12.4 ቢሊዮን ብር ከፍ ያለ ሆኗል።

በዚኹ ጉዳይ ላይ የተናገሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ፣ መንግስታቸው አኹንም እየተገበረ ያለው አዲሱን የክልሎች አደረጃጀት ሙሉ በሙሉ የማያንጸባርቀውን አሮጌውን የበጀት ቀመር መሆኑን ጠቅሰው፣ አኹንም ቢሆን የትኩረት ማዕከሉ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ከመጀመር ይልቅ ተጀምረው በመስራት ላይ ያሉትን አጠናቆ ለማስረከብ ክፍያዎችን መፈጸም ላይ እንደሆነም ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ዐብይ ኦኮኖሚውን በጨረፍታ

የተቀናጁ የፊስካል እና የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያዎች ፈጣን ዕድገትን እና ዝቅተኛ የዋጋ ንረትን እያስገኙ መሆናቸውን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ፣ በዕለተ ሐሙስ የ2019ኙን የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ገልጸዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ የኢትዮጵያ የዐብይ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ አገሪቱን በዓለም ላይ በፍጥነት ከሚያድጉ ኢኮኖሚዎች ተርታ የሚያሰልፍ እና የዋጋ ንረትን በከፍተኛ ሁኔታ ያረጋጋ ውጤት ያስመዘገበ ሆኗል።

የኢትዮጵያ የ2019 በጀት ዓመት በውስብስብ እጥረት ውስጥ የታየን ትልቅ ምኞት የሚተርክ ሆኗል። መንግስት 2.339 ትሪሊዮን ብር ያቀደ ሲሆን፣ ይኽም ከባለፈው ዓመት የ1.93 ትሪሊዮን ብር በጀት ጋር ሲነጻጸር የ21.3 በመቶ ከፍተኛ ጭማሪ ያለው ሆኖ ተመዝግቧል፤ በአንጻሩ ከአገር ውስጥ ገቢ፣ ከዕርዳታ እና ከበጀት ድጋፍ በጥቅሉ 1.817 ትሪሊዮን ብር ይሰበስባል ተብሎ ይጠበቃል። በኹለቱ መካከል ያለው የ522 ቢሊዮን ብር የተጣራ የበጀት ጉድለት ከአገሪቱ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አንጻር ሲሰላ 1.3 በመቶ በመሆኑ፣ በብርቱ ለማደግ ለሚፈልግ ኢኮኖሚ ቁጥሩ ግዙፍ ነው ለማለት አያስችልም። ይኹን እንጂ ዋናው ፈተና ያለው በበጀት ጉድለቱ መጠን ላይ ሳይሆን፣ በጀቱ መንግስት እንደ ልብ ለመንቀሳቀስ ስላለው ጠባብ ዕድል በሚያሳየው እውነታ ላይ ሆኗል።

አሁን ላይ የዕዳ ክፍያ ትልቁ ነጠላ የወጪ መደብ ሆኗል። የዕዳ ክፍያው 542.1 ቢሊዮን ብር ሲሆን (293.3 ቢሊዮን ብር ለውጭ እና 248.7 ቢሊዮን ብር ለአገር ውስጥ ዕዳ)፣ ይኽም ከአጠቃላይ መደበኛ ወጪው 43.3 በመቶ ያህሉን የዋጠ ሆኗል። ይኽ ማለት መንግስት መንገዶችን ከመገንባቱ፣ ትምህርት ቤቶችን ከመደገፉ ወይም ለክልሎች የንዑስ በጀት ድልድል ከማድረጉ በፊት፣ አብዛኛው የፋይናንስ ምንጭ ቀድሞውኑ ለዕዳ የተያዘ እንዲሆን አድርጎታል። ስለሆነም በጀቱ በአጠቃላይ ሲታይ ተስፋፊ ቢመስልም፣ በውስጠ-ይዘቱ ግን በእጅጉ የተገደበ ሆኗል።

የወጪው አወቃቀርም ይኽንኑ ነጥብ ያጠናክረዋል። ለመደበኛ ወጪ 1.236 ትሪሊዮን ብር (የበጀቱን 52.9 በመቶ) ሲመደብ፣ ለካፒታል ወጪ ደግሞ 568.2 ቢሊዮን ብር (24.3 በመቶ ገደማ) ተመድቧል፤ ይኽም አዳዲስ ጅምሮችን ከመደገፍ ይልቅ ነባር ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ላይ ያተኮረ አድርጎታል። መደበኛ ወጪ የመንግስትን መዋቅር ህልው አድርጎ ሲያቆይ (ማለትም ደሞዝ ከመክፈል አስንቶ እንደ ማዳበሪያና ነዳጅ ላሉ መሠረታዊ ሸቀጦች ድጎማ ማድረግን ድረስ የደረሱ)፣ በአንጻሩ የካፒታል ወጪ የቀጣይ ጊዜ የማምረት አቅምን የሚያሰፋ መሆኑ ይታወቃል። ከዚኽ አንጻርም በጀቱ የነገን የረዥም ጊዜ ዕድገት ከመገንባት ይልቅ፣ የዛሬን ማኅበራዊ እና የዕዳ ጫናዎች ማርገብ ላይ ትኩረት ማድረጉን እንረዳለን። በገቢው በኩል መንግስት ከኢኮኖሚው ብዙ እንዲጠይቅ ያደርገዋል።

የፌደራሉ መንግስት ካለው የገቢ ዕቅድ ውስጥ 1.6 ትሪሊዮን ብሩ በቀጥታ ከታክስ እና ታክስ ካልሆኑ የአገር ውስጥ ገቢዎች ለመሰብሰብ ታቅዷል። እንደ ተጨማሪ እሴት ታክስ፣ የታክስ ዲጂታላይዜሽን እና የኤክሳይዝ ስታምፕ አሠራር ያሉ ማሻሻያዎችም የአገር ውስጥ ሀብትን የመሰብሰብ አቅምን ለማጠናከር የታለሙ ሆነዋል። የኢትዮጵያ የታክስ መሠረት አሁንም ጠባብ በመሆኑ፣ መንግስት በብድር ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ ገቢ ያስፈልገዋል፤ ሆኖም ይኽ ሸክም በተጠቃሚው ማኅበረሰብ ላይ ጫና የመፍጠር ሥጋት ያለው መሆኑን መመልከት አይከብድም።

የብርን ዝውውር ስንመለከትም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አጠቃላይ የገንዘብ ዝውውር ዕድገትን የገደበ ሲሆን፣ ይኽም የገንዘብ አቅርቦትን በጥብቅ የመቆጣጠር እርምጃ የማሻሻያ ስትራቴጂው መሠረታዊ ምሰሶ ሆኗል። ከዚኽም በተጨማሪ ኢትዮጵያ የፌዴራል በጀት ጉድለቷን በቀጥታ ከማዕከላዊ ባንክ በሚወሰድ የቅድሚያ ብድር መሸፈን ሙሉ በሙሉ ማቆሟ የቀጥታ ማዕከላዊ ባንክ ብድርን እንደመግታቱ፣ ይኽም የዋጋ ንረትን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል ተብሏል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ፣ የኑሮ ውድነት ጫናን በማቃለል ረገድ በተለያዩ ዘርፎች የተደረጉ ስትራቴጂካዊ ጣልቃ ገብነቶችን ያደነቁ ሲሆን፣ መንግሥት በምግብ ዘይት፣ በመሠረታዊ ሸቀጦች እና በመድኃኒቶች ላይ ተመጣጣኝ የድጎማ በጀት በመመደብ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራል ቢሉም፣ ከማኅበራዊ ልማት በኩል ርዕሰ-ጉዳዮቹን መመልከትም ሌላ ዕይታ ይሰጣል።

ከፖለቲካዊ አውድ አኳያ፣ እጅግ ስስ የሆነው እና አሳሳቢው ምልክት፣ ድህነትን ለመቀነስ እና ለማኅበራዊ ልማት የሚመደበው የወጪ ድርሻ መዳከሙ ይመስላል። በስማዊ ምጣኔ ሲታይ ይኽ ወጪ አሁንም እያደገ ቢመጣም፣ ከአጠቃላይ የበጀት መዋቅሩ አንጻር ያለው አንጻራዊ ድርሻ ግን እየቀነሰ መጥቷል። የበጀቱ ዋናው ማጠንጠኛ ውጥረትም ይኼው ይመሰላል፤ ማለትም፣ ኢትዮጵያ በዕቅድ ደረጃ ግዙፍ ገንዘብ ለመበጀት ብታቅድም፣ ነገር ግን ከቀጥታ የድህነት ቅነሳ፣ ከማኅበራዊ አገልግሎቶች እና ከልማት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ጋር በቀጥታ ለተያያዙ ፕሮግራሞች የሚውለው የተጣራ አቅም መጣበብ እንዲታይበት ነገሮች አስገድደዋል። ስለሆነም፣ ይኽ በጀት የወጪ መግለጫ ብቻ ሳይሆን፤ ይልቁንም የመንግስትን ስትራቴጂካዊ ምርጫዎች እና ግዴታዎችን፣ አንዱን ለማግኘት ሌላውን የማጣት ውልውል ውስጥ የሚከት መስሏል። የአንበሳውን ድርሻ የወሰደው የዕዳ ክፍያ የመንግስትን የመተጣጠፍ ነፃነት በእጅጉ ከመግታቱ ባለፈ፣ በአንድ በኩል ደሞዝ እና አሥተዳደራዊ መደበኛ ግዴታዎች እያሻቀቡ ሲሄዱ፤ በአንጻሩ ግን ለነገው ዘላቂ ዕድገት መሠረት የሚጥለው የካፒታል ወጪ ድርሻ እንዲቀጥን ሆኗል። መንግስት ደግሞ ይኽንን አስገዳጅ የበጀት መዋቅር በአንድነት አጣብቆ ለማቆየት፣ ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል በአገር ውስጥ ጠንካራ የታክስ አሰባሰብ ላይ ጥገኝነቱን ለመጣል መገደዱ አይቀሬ ይመስላል።

እናም፣ ዋናው የበጀት ስማዊ ቁጥር ተስፋፊ የመንግስት በጀት መኖሩን ቢያመለክትም፣ የውስጠኛው ጥልቅ መልዕክት ግን የበለጠ አሳሳቢ ይመስላል፤ ማለትም፣ ኢትዮጵያ የምትመድበው ብዙ ገንዘብ ቢኖራትም፣ ያንን ገንዘብ እንደ አገራዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ፍላጎት እንዴት እንደምትከፋፍለው የሚኖራት የፖሊሲ ምርጫ ነፃነቷ እጅጉን አነስተኛ እንዳይሆን ያስጋል።

የብሪጅ ምክረሐሳቦች

የ2019 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት በጀት መጽደቁን ተከትሎ፣ የተወካዮች ምክር ቤት የበጀቱን አፈጻጸም፣ የፖሊሲ ግቦችን እና በኢኮኖሚው ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን የጎንዮሽ ተፅዕኖዎች በብርቱ የመከታተል እና የመቆጣጠር ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነት እንዳለበት ግልጽ ነው። ከላይ ካቀርብናቸው ትንተናዎች አኳያም፣ ምክር ቤቱ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ናቸው ብላ ተቋማችን ብሪጅ የምታምንባቸዋን ዋና ዋና ነጥቦች እና ምክረ-ሐሳቦች እንደሚከተለው መሰንዘር ትሻለች፤

·      የታክስ ማሻሻያዎች በመዋዕለንዋይ ፍሰት እና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚጥሉት ሥጋት፦

መንግሥት የግብር እፎይታዎችን እና ከቀረጥ ነፃ የማስገባት መብቶችን በመሰረዝ በጥቅሉ እስከ 78.9 ቢሊዮን ብር አዲስ የአገር ውስጥ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዷል። ይኹን እንጂ ይኽ እርምጃ የሚከተሉትን ተግዳሮቶች ሊያስከትል ስለሚችል የምክር ቤቱ የቅርብ ክትትል ያስፈልገዋል ብለን እናምናለን፤

ሀ፦የመዋዕለንዋይ ፍሰት ማበረታቻዎች መዳከም፦ ከተወሰኑ ዘርፎች ላይ ማበረታቻዎችን በመቀነስ ወደ መደበኛ ታክስ እንዲገቡ ማድረግ ብቻ እስከ 22 ቢሊዮን ብር ገቢ ያስገኛል ተብሎ ቢታቀድም፣ ይኽ አሠራር አዳዲስ የመዋዕለንዋይ ፍሰቶችን ሊያገት እና የአምራች ዘርፉን የመስፋፋት አቅም ሊቀንስ የሚችልበት ዕድል እንዳይፈጠር ያሰጋል።

ለ፦ የሥራ ዕድል ፈጠራ መቀነስ፦ የግብር እፎይታዎች በቀጥታ ከአገር ውስጥ ምርት ማደግ እና ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር የተሳሰሩ በመሆናቸው፣ ማበረታቻዎቹ ሲቀነሱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ምጣኔው አብሮ ሊቀጭጭ ይችላል።

ከዚኽ አኳያም፣ ምክር ቤቱ የገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ መሠረቱን ሲያሰፋ በአምራች እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ የረዥም ጊዜ ጉዳት እንዳይደርስ፣ የማበረታቻዎች አሰራር ሥርዓት፣ የፌደራሉ መንግስት ባስቀመጣቸው የዐብይኢኮኖሚ ዕቅዶች ውስጥ በሚገባ ያረፉ መሆናቸውን፣ ምክር ቤቱ ባሉት ተቋማዊ የቁጥጥር ሥርዓቶች በሚገባ ይቆጣጠራቸውን ዘንድ አበክረን መጥቀስ እንሻለን።

·                የካፒታል በጀት አጠቃቀም እና የፕሮጀክቶች ቅድሚያ አሰጣጥ፦

2019 በጀት ዓመት የተደለደለው 568 ቢሊዮን ብር የካፒታል በጀት የተጠና እና ያልተለጠጠ መሆኑ በአዎንታዊነት ይነሳል። በጀቱ አዳዲስ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ከመጀመር ይልቅ የተጀመሩ እና ያላለቁ ነባር ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ማለሙ በአዎንታዊነቱ ሊጠቀስ የሚችል የፊስካል ሥርዓት ነው። ሆኖም፣ ይኽ የተመጠነ የካፒታል በጀት በተለይ ምርት እና ምርታማነትን በቀጥታ በሚያሳድጉ፣ ለሕዝቡ አንገብጋቢ በሆኑ መሠረተልማቶች ላይ ብቻ እንዲያተኩር ማድረግ ማስፈልጉ አሌ አይባልም። ከዚኽ አንጻርም፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ይኽ 568 ቢሊዮን ብር በጀት በትክክልም ለነባር ፕሮጀክቶች ማጠናቀቂያ መዋሉን እና አዳዲስ ያልተጠኑ ወጪዎች አለመፈጠራቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ እንዲጠናቀቁ የሚጠበቁትን የልማት ፕሮጀክቶች አስመልክቶ፣ የተቋማዊ ኅላፊነታቸው ይመለከታቸዋል የሚባሉትን ሥራ አሥፈጻሚ ተቋማት በበርቱ ይቆጣጥራቸው ዘንድ ማስታወስ አስፈላጊ ይመስለናል።

·                ተጨማሪ የዋጋ ንረት እና የውጭ ምንዛሬ ሽሚያ ስጋት፦

የመንግስት በስፋት ገንዘብ የማውጣት ሂደት በጥቅሉ የአገር ውስጥ ፍላጎትን በመጨመር፣ የተጀመረውን የዋጋ ንረት የመግታት ጉዞ መልሶ ሊገፋው የሚችልበት ዕድል ሊፈጥር መቻሉን ማስተባበል አይቻልም። ምንም እንኳን በርካታ ፕሮጀክቶች በአገር ውስጥ ገቢ ቢጀመሩም፣ ለአፈጻጸማቸው የሚውሉ ማሽነሪዎች እና ግብዓቶች ከባሕር ማዶ በዶላር የሚገዙ መሆናቸው ይታወቃል። ከዚኽ አኳያም በርካታ ፕሮጀክቶችን በአንዴ ማስኬድ፣ በገበያው ላይ ያለውን ጠባብ የውጭ ምንዛሬ ከመንግስት ጋር የመሻማት አዲስ ሥጋት እንዳይፈጥር ያሰጋል። እነዚኽ ኹለት ኹነቶች ደግሞ፣ በምጣኔ ሀብት አስተምህሮ እንደሚታወቀውርስ ርስ ያላቸው ተገፋፊነት አሉታዊ ገጹ ብዙ ነውና፣ ምክር ቤቱም ይኽ እንዳይፈጠር ይመለከታቸዋል የሚባሉትን ዐብይኢኮኖሚውን በበላይነት የሚቆጣጠሩትን(እነ ብሔራዊ ባንክ እና የገንዘብ ሚኒስቴር ያሉትን) ተቋማት በዚኹ ጭብጥ ላይ አተኩሮ፣ የሩብ ዓመትም ሆነ የመንፈቅ የሥራ አፈጻጸማቸውን ሲያቀርቡ ብርቱ ክትትል ያደርግ ዘንድ ማሳሰብ እንሻለን። 

·                የዕዳ ጫና እና የገንዘብ ማተም ስጋት፦

መንግስት የበጀት ክፍተቱን ለመሙላት ከባሕር ማዶ የሚገኝ ብድር እና እርዳታን ዕቅዱ ውስጥ ማካተቱ ይታወቃል። በዚኽ መልኩ ይመጣል ተብሎ የሚጥበቀው ድጋፍ እና እርዳታ የበጀት ክፍተቱን ለማጥበብ ትልቅ እገዛ ቢኖረውም፣ የአገሪቱን የዕዳ ጫና ማሳደጉ ግን አይቀሬ ነው። ከዚኽ አንጻርም መንግስት፣ የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት የግምጃ ቤት ሰነድ በሚያወጣበት ወቅት፣ ለግል ዘርፉ የሚቀርበው የብድር አቅርቦት እንዳይደርቅ እና የአገር ውስጥ ባንኮች እንዳይጨናነቁ የሚሉ ስጋቶች ሲነሱ ይደመጣል። ከዚኹ ጋር በተሳሰረ፣ ከብሔራዊ ባንክ የሚወሰድ የቀጥታ ብድር ሙሉ በሙሉ መቆሙን እና ገንዘብ ባለማተም የተገኘው የዐብይኢኮኖሚያዊ መረጋጋት እንዳይቀለበስ በጥብቅ መቆጣጠር ማስፈለጉ አሌ አይባልም። ስለምን ቢሉ፣ መንግስት ይኽንን የውጭ ብድር እና እርዳታ በበቂ ኹኔታ ካላገኘ፣ ክፍተቱን ለመሙላት ወደ ኹለት አደገኛ አማራጮች ሊያመራ ይችላል፤ እነርሱም፣ የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነድ በብዛት ማውጣት ሲሆን፣ ይኽ በሚሆንበት ጊዜም መንግስት በገበያው ውስጥ ያለውን የብድር ገንዘብ በሙሉ ለራሱ ስለሚወስደው፣ የግል ዘርፉ ብድር አጥቶ ገበያው ይደኸያል። በኹለተኛነትም፣ በቀጥታ ብሔራዊ ባንክ ገንዘብ እንዲያትም ሊገደድበት የሚችልበት አስገዳጅ አማራጭ ውስጥ መግባትም ሊከተል ይችላል። ይኽ ደግሞ፣ ዐብይኢኮኖሚውን መልሶ ወደ ከፋ የዋጋ ንረት አዙሪት ውስጥ መክተቱ አይቀሬ ነው። ከዚኽ አንጻርም፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕገመንግሥታዊ የቁጥጥር ሥልጣኑን በመጠቀም፣ በሚቀጥሉት የበጀት ወራት ውስጥ የገንዘብ ሚኒስቴርንም ሆነ ሌሎቹ ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከታቸው ተቋማት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ይኖርበታል እንላለን።