ኢትዮጵያ በዓለም ንግድ ድርጅት ማጠናቀቂያ መስመር ላይ መሆኗ እየተነገረ ነው፤ የመጨረሻው የአባልነት ግፊትም ጠንክሯል። ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እ.ኤ.አ. በ2003 በይፋ ካመለከተችበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 23 ዓመታት፣ ድርድሩን በመግታት እና መልሶ በመጀመር ረዘም ያለ ጉዞ አሳልፋለች። ከስምንት ዓመታት በፊት የተካሄደውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎም፣ የድርድር ሂደቷን ስታፋጥን፣ ቢገፋ በቀጣዩ ዓመት አጋማሽ የአባልነቷ ጥያቄ ይፈታል ተብሎም ታምኗል።
የኢትዮጵያ የእንደራሴዎች ምክር ቤት፣ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነትን ተከትሎ የሚመጡ በርካታ ረቂቅ ዐዋጆችን (የጉምሩክ ዐዋጅ ማሻሻያ፣ የንግድ ፈቃድ አገልግሎት ክፍያ ደንብ፣ የበርን ኮንቬንሽን እና የቅጂ መብት ጥበቃ ሕግጋትን) በዝርዝር መርምሮ የሚያጸድቅ ሕግ አውጪ ተቋም ስለመሆኑ፣ በሕገ-መንግሥቱ መደንገጉ ይታወቃል። ከዚኽ አኳያም፣ ምክር ቤቱ እነዚኽን ዓለም ዓቀፍ ሕግጋት በሚያጸድቅበት ወቅት ሊመለከታቸው ይገባሉ የምንላቸውን ፖሊሲ ተኮር ነጥቦች ወረድ ብለን እንመለከታለን።
ይኽንን የአባልነት ጥያቄ ያፋጥናሉ በሚል መነሾም፣ የተለያዩ የዐብይ-ኢኮኖሚ መሠረታዊ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን መተግበር ከጀመረች ዋለ አደር ብላለች። ከእነዚኽም መካከል፣ የውጭ ምንዛሬ ተመንን ሙሉ በሙሉ በገበያ ኃይሎች እንዲወሰን ማድረግ፣ የባንክ፣ ቴሌኮም እና የሎጂስቲክስ ዘርፎችን ለውጭ ውድድር መከፋፍት፣ እንዲኹም የሕግ እና የተቋማዊ ማሻሻያዎችን ማከናወኗ ሊጠቀሱ የሚችሉ ተግባራቶቿ ናቸው።
ይኹን እንጂ፣ አባልነቱ ሰፊ የገበያ ዕድል፣ የውጭ መዋዕለ-ንዋይ ፍሰት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ይዞ የመምጣት ከፍተኛ ተስፋ ያለው ቢሆንም፤ የአገር ውስጥ አምራቾች፣ አርሶ አደሮች እና የፋይናንስ ተቋማት ሊገጥማቸው ከሚችለው የህልውና ውድድር አንጻር የራሱ የሆኑ መዋቅራዊ ተግዳሮቶች እንዳሉትም ይነሳል። በዚኽ ረገድም፣ በዓለም ንግድ ድርጅት ታሪክ ውስጥ በሂደት አልፈው የገቡት እና ኹለቱ ብቸኛ ታዳጊ አገራት* የሆኑት የካምቦዲያ እና የኔፓል ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ተጨባጭ መማሪያዎች ስለመሆናቸውም ሙግቶች ይደመጣሉ።
ይኽም ሆኖ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ተደራዳሪዎች፣ ከኹለት ሳምንት በፊት፣ በካሜሮን ያውንዴ ከተማ የተካሄደውን 14ኛውን የዓለም ንግድ ድርጅት ሚኒስትሮች ጉባኤ ተሳትፈው በተመለሱ ማግስት፣ አገሪቷ ለአባልነት የሚያበቋትን ብዙዎቹን መስፈርቶች እያሟላች ስለመምጣቷ ሲናገሩ ተደምጠዋል። አኹን የአባልነት ጉዳዩ የመጨረሻው መስመር ላይ ስለመሆኑም ተነግሯል።
እነሆ፣ ተቋማችን ብሪጅም፣ ይኽንን ወሳኝ የአባልነት ሰሞነኛ መረጃ ተንተርሳ፣ የአባልነቱን ጉዞ በመጥቀስ፣ የዚኽ ሉላዊ ተቋም አባል መሆን የሚያመጣቸውን በረከቶች እና የሚቀሰቅሳቸውን ተግዳሮቶች፣ ከሌሎቹ መሰል ታዳጊ አገራት ተሞክሮ እና ከኢትዮጵያ አኹናዊ መንግስታዊ አቋም ጋር አሰናስላ፣ ይኽንን ሳምንታዊ ዳሰሳ ማዘጋጀትን መርጣለች።
ከካሜሮን መልስ
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የጀመረችው የረጅም ጊዜ ጥረት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እና የዓለም ዓቀፍ ንግድ ተቋሙ መሪዎች፣ አባልነቱ በዚኽ የአውሮፓውያኑ ዓመት ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢው ዶ.ር. እዮብ ተካልኝ በኤክስ ገጻቸው ላይ፣ ኢትዮጵያ አኹን ላይ በአባልነት ሂደቱ ማጠናቀቂያ መስመር ላይ ትገኛለች ብለዋል። ገዢው ይኽንን የገለጹት በካሜሩን በተካሄደው የሚኒስትሮች ጉባኤ ወቅት፣ የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ በሰጡት ማረጋገጫ ላይ በመመሥረት ነበር። ኦኮንጆ-ኢዌላ፣ በቀደመው ወር መገባደጂያ በካሜሩን በተካሄደው 14ኛው የዓለም ንግድ ድርጅት ሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ አባልነትን ከሚፈልጉ 22 አገራት መካከል ኢትዮጵያን እጅግ የላቀ ደረጃ ላይ ከደረሱ ዕጩዎች አንዷ አድርገው በተለየ ሁኔታ ጠቅሰዋታል። በስብሰባው ላይ ለተገኙት ከፍተኛ የአገራት ተወካዮች ንግግር ሲያደርጉም፦ “ኡዝቤኪስታን እና ኢትዮጵያ እጅግ በጣም ጠንክረው እየሠሩ ነው፤ በዚኽ ዓመት አባልነትን ያገኛሉ ብለን ትልቅ ተስፋ አድርገናል” ብለዋል።
የዓለም ንግድ ድርጅት መሪዋ በሌላ የኤክስ መልዕክታቸው ላይም፣ ከንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ዶ.ር. ካሳሁን ጎፌ እና ከኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ ኢትዮጵያ በአባልነት ድርድሯ ላይ “ጥሩ እድገት እያሳየች ነው” ያሉ ሲሆን፤ ያ የሚኒስትሮቹ ጉባኤም ሂደቱን ይበልጥ ያፋጥነዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አክለዋል። ይኽ የኢትዮጵያ የታደሰ መነቃቃት የመጣው፣ ከ166 አገራት የተወከሉ ከ4,000 በላይ ልዑካን በጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረት ውስጥ ባለው የባለብዙ ወገን የንግድ ሥርዓት ማሻሻያ ላይ ለመምከር ያውንዴ ላይ ጉባኤ በተቀመጡበት ወቅት ነው።
የሩብ ክፍለ ዘመን ጉዞ
የተጠቀሱት የድርጅቱ መሪ ኦኮንጆ-ኢዌላ፣ የኢትዮጵያን የአባልነት ጉዞ “አድካሚ” ሲሉም ጠቅሰው፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አባልነትን የሚጠባበቁትን አገራት ለጽናታቸው አድንቀዋቸዋል። በእርግጥም የኢትዮጵያ መንገድ አድካሚ ሳይሆን አልቀረም።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ያደረገችው ረጅም ዲፕሎማሲያዊ እና ሕጋዊ ጉዞ፣ የአገሪቱን የፖለቲካ- ኢኮኖሚ ውጣ ውረዶችን በጉልህ የሚያሳይ ታሪካዊ ሂደት ነው። አገሪቱ፣ እ.አ.አ. በ2003 በይፋ የመቀላቀል ፍላጎቷን ካሳወቀች በኋላ፣ በድርጅቱ ዘንድ የዕጩነት ወይም የታዛቢነት ደረጃን አግኝታ የመጀመሪያውን መደበኛ የድርድር ምዕራፍ ጀመረች። ይኹን እንጂ ይኽ ሂደት እንደ ሌሎቹ ታዳጊ አገራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊጠናቀቅ አልቻለም። ይኽ የድርድር መዘግየት የመነጨው ከቴክኒክ አቅም ማነስ ብቻ ሳይሆን፣ በአገሪቱ የነበረው ኢሕአዴግ መሩ “ልማታዊ መንግስት” የተከተለው የኢኮኖሚ መስመር፣ ከድርጅቱ መሠረታዊ መመሪያዎች ጋር ፍጹም ተቃራኒ በመሆኑ ነበር።
የቀድሞው የኢትዮጵያ መንግስት፣ እንደ ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ የፋይናንስ ዘርፍ (ባንክ እና ኢንሹራንስ) እና የኃይል አቅርቦት ያሉ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚው አዕማድን፣ በመንግስት ኹለንተናዊ መዳፍ ስር ማቆየትን፣ የአገራዊ ደኅንነት እና የሉዓላዊነት መገለጫ አድርጎ ይወስደው ነበር። በዚኽም ምክንያት፣ ከዋና ዋናዎቹ የምዕራባውያን የንግድ አጋሮች (በተለይም ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ኅብረት) የሚቀርቡትን፣ የአገልግሎት ዘርፉን ለድንበር-ዘለል ገበያ ክፍት የማድረግ ጥያቄዎችን ለዓመታት ሲከላከል ቆይቷል።
በድርድሩ ሂደት ላይ ትልቅ መዋቅራዊ ለውጥ የመጣው፣ የ2010ን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ ነበር። መንግስት የአገሪቱን የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ በሚል፣ “አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ” ፖሊሲን ይፋ አደረገ። ይኽ የዐብይ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያም፣ ቀደም ሲል ለድንበር-ዘለል የንግድ ተቋማት ተዘግተው የነበሩትን ስትራቴጂካዊ ዘርፎች ለግል እና ለባሕር ማዶ ባለሀብቶች በከፊልም ሆነ በሙሉ ክፍት ለማድረግ መንገድ የጠረገ በመሆኑ፣ ከዓለም የንግድ ድርጅት መሠረታዊ መርሆዎች ጋር አዲስ መጣጣምን ፈጠረ።
ይኽንን ተከትሎም፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2020 ዐራተኛውን እና በንግድ ድርጅቱ ቢሮክራሲያዊ ቃላት የሥራ ቡድን ስብሰባ በተሰኘው የጄኔቫው ስብሰባ ላይ በመገኘት፣ ለዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የንግድ ዲፕሎማሲ በይፋ አነቃቅታዋለች። ምንም እንኳን በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ተከስቶ የነበረው ግጭት እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሂደቱን ለተወሰኑ ዓመታት እንደገና ቢያቀዛቅዙትም፣ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማግስት እና ከዚያ በኋላም በተወሰዱት ተከታታይ የዐብይ-ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጦች በኋላ የድርድር ሂደቱ ወደማይመለስበት እጅግ ፈጣን የተሰኘ ምዕራፍ ውስጥ ገብቷል።
ዛሬ ላይ
በአኹኑ ወቅት ኢትዮጵያ፣ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል አገራት ያቀረቡላትን በመቶዎች የሚቆጠሩ የቴክኒክ ጥያቄዎች ምላሽ በዝርዝር አዘጋጅታ፣ በዙር ማስገባቷን ቀጥላለች። አምስተኛው የሥራ ቡድን ስብሰባ ከተካሄደ በኋላም፣ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አኹን ላይ በዋናነት ትኩረት አድርጎ እየሰራ ያለው በኹለትዮሽ የገበያ ተደራሽነት ድርድር ላይ ነው። በዚኽ ደረጃ፣ እንደ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ቻይና እና ህንድ ያሉ ትላልቅ የንግድ አጋሮች ኢትዮጵያ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ የምትጥለውን ከፍተኛ የታሪፍ ጣሪያ እንድትቀንስ እና የሕግ ማዕቀፎቿን (የቅጂ መብት እና የውድድር ሕግጋትን የመሳሰሉትን) ከዓለም ዓቀፍ መለኪያዎች ጋር እንድታጣጥም የጠበቀ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እያደረጉ ስለመሆኑም ይነሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደው የውጭ ምንዛሬ ተመንን ሙሉ በሙሉ በገበያ ኃይሎች እንዲወሰን የማድረግ ሥር ነቀል የፖሊሲ እርምጃ፣ ለዓመታት በዓለም ዓቀፉ የንግድ ድርጅት የድርድር ጠረጴዛ ላይ ለነበረው ትልቅ ማነቆ ቀጥተኛ ምላሽ ሰጥቷል። ቀደም ሲል የነበረው የተገደበ የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት፣ ድርጅቱ ከሚከተለው የነፃ ገበያ እና የካፒታል ፍሰት መርህ ጋር ፍጹም የሚጋጭ ነበር። ይኽ የፖሊሲ ማሻሻያ መተግበሩ፣ የኢትዮጵያን ተደራዳሪ ቡድን ነገሮችን በሂደት እከፋፍታለሁ ከሚል የፖሊሲ ዘገምተኛ መከላከል ወጥቶ፣ ወደ ሂደታዊ የክፍለ-ኢኮኖሚ መከፋፋት እንዲሸጋገር አድርጎታል። የውጭ ምንዛሬ ገበያው ክፍት መሆን የውጭ ባለሀብቶች ትርፋቸውን ያለ ምንም ከልካይ ወደ አገራቸው እንዲመልሱ ስለሚፈቅድ፣ ለአባልነቱ መሳካት ዋነኛውን የሕግ እና የፖሊሲ መተማመኛ ፈጥሯል። የዐብይ-ኢኮኖሚው ማሻሻያ ሌላው ትኩረት፣ የወጪ እና የገቢ ንግድ ዘርፎችን ማላላት ነው። ቀደም ሲል ለአገር ውስጥ ነጋዴዎች ብቻ ተዘግተው የነበሩ የችርቻሮ፣ የጅምላ ንግድ እና የሎጂስቲክስ ዘርፎች ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት መደረጋቸው፣ የተቋሙን ብሔራዊ አያያዝ የተሰኘውን መርህ አስቀድሞ ለመተግበር ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል። በተጨማሪም፣ የንግድ ሕጉ መሻሻል፣ የውል ማስፈጸም አቅም ማደግ እና የቅጂ መብት ጥበቃ ሕግጋትን ከዓለም ዓቀፍ መለኪያዎች ጋር የማጣጣም ሥራዎች በፍጥነት እየተከናወኑ ስለመሆኑም ሲነገር ይደመጣል።
ከአገልግሎት ንግድ አጠቃላይ ስምምነት አኳያም፣ በድርድሩ ውስጥ እጅግ አስቸጋሪው እና የበረታ ጥንቃቄ የሚፈልገው ክፍል ቢሆንም፣ በዚኽ ረገድም ኢትዮጵያ ሊጠቀሱ የሚችሉ የፖሊሲ ለውጦችን ከውናለች። የቴሌኮም ዘርፉን ክፍት በማድረግ ኹለተኛ የውጭ ኦፕሬተር (ሳፋሪኮም) እንዲገባ መፍቀዷ እና የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል አክሲዮን ለገበያ ማቅረቧ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአገልግሎት ዘርፉ የገበያ መርህን እንዲከተል አድርጎታል።
ይበልጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ባንኮች በአገር ውስጥ ቅርንጫፍ ከፍተው ወይም ከአገር ውስጥ ባንኮች ጋር ተዋህደው እንዲሰሩ የፈቀደው አዲስ መመሪያ፣ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለዓለም ዓቀፍ ውድድር ዝግጁ አድርጎታል። ይኽ እርምጃ የንግድ ስምምነቱን ለማፅደቅ የነበረውን ትልቅ የፖሊሲ ጋሬጣ ማንሳቱንም ልብ ይሏል። ይኽ የአገልግሎት ዘርፍ ክፍት መሆን፣ ወደ አገር ውስጥ ከፍተኛ የውጭ ወረት፣ ዘመናዊ የባንክ ቴክኖሎጂ እና የተሻሻለ የብድር አቅርቦት ሥርዓት ይዞ የመምጣት ሰፊ ዕድልም አለውና።
የመንግስት አኹናዊ አቋም ምን ይመስላል?
የኢትዮጵያ መንግስት፣ ድርድሩን አስመልክቶ አኹን ላይ ያለውን መረዳት የምናገኘው፣ በተለይም የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ዶ.ር. ካሳሁን ጎፌ፣ ከሳምንት በፊት በተካሄደው የያውንዴው ጉባኤ መለስ ከሰጧቸው ቃለ መጠይቆች ነው። የሚኒስትሩን ንግግሮች ጨመቅም፣ እንደሚከተለው አጠር አድርገን መመለከት እንችላለን።
ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ ሂደቱ ከተፋዘዘበት ወደ ሚነቃቃበት ደረጃ ለማድረስ በመንግስት በኩል ሰፊ ጥረት እና ቁርጠኝነት በመወሰዱ፣ አዲስ የድርድር ቡድን ተቋቁሞ ከዛሬ ዓመት በፊት አምስተኛውን የሥራ ቡድን ስብሰባ ጄኔቫ ላይ ለማካሄድ ተችሏል። ይኽ የድርድር ቡድን በንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ዋና ተደራዳሪነት የሚመራ ሲሆን፣ ከተለያዩ ወሳኝ የማክሮ ተቋማት አባል የሆኑበት የብሔራዊ ባንክ ገዢ፣ የጉምሩክ ኮሚሽን፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የተመደቡበት ብሔራዊ የድርድር ኮሚቴ፣ ብሎም ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴም ጭምር ተደራጅቶ ሥራ ከጀመረ ዋል አደር ብሏል።
ቡድኑ ሥራ ሲጀምር ባጠረ ጊዜ ውስጥ ሂደቱን ሙሉ በሙሉ መቋጨት እንኳን ባይቻል በከፍተኛ ደረጃ ማገባደድ የሚቻልበትን ዕቅድ ይዞ የገባ ሲሆን፣ በዚኽም መሠረት በአምስተኛው የሥራ ላይ ቡድን ስብሰባ መጋቢት 2017 ዓ.ም.፣ ስድስተኛው የሥራ ላይ ቡድን ስብሰባ መስከረም 2018 ዓ.ም.፣ እና ባሳለፍነው ወርኃ ሚያዝያ ላይ ደግሞ ሰባተኛውን የሥራ ላይ ቡድን ስብሰባ ማከናወን ተችሏል ተብሏል። እነዚኽ ሦሥቱ የሥራ ላይ ቡድን ስብሰባዎች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ (ከወራት አንፃር በ13 ወራት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ) የተደረጉ በመሆናቸው፣ ይኽም ፈጣኑ የሚባል የድርድር ሂደት ተደርጎ ተወስዷል። ከላይ በጠቀስነው 14ኛው የዓለም የንግድ ሚኒስትሮች ጉባኤ ካሜሩን ያውንዴ ላይ ሲከናወንም፣ ለኢትዮጵያ መንግሥት ላለው ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እና ለድርድር ቡድኑ አመራር የዓለም ንግድ ሚኒስትሮች በተገኙበት ዕውቅና መሰጠቱን ዶ.ር. ካሳሁን ሲናገሩ ተደምጠዋል።
በሰባተኛው የሥራ ላይ ቡድን ስብሰባ ላይ የተገኘው ተሳትፎ እንደሚያሳየው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአገሪቱ የድርድር ሪፖርት እየዳበረ ሄዷልም ተብሏል። በስድስተኛው ቡድን ስብሰባ ላይ የቀረበው ትልቁ ውጤት፣ ሪፖርቱ ከፍሬ ነገር ወደ ተተግባሪነት የተሸጋገረበት ምዕራፍ ስለመሆኑም ተጠቅሷል። እንደ ሚኒስትሩ መረጃ ከሆነም፣ ይኽ ረቂቅ ሰነድ ለመጽደቅ በቂ የሆነ የዕድገት ደረጃን የሚያሳይ ሲሆን፣ በአኹኑ ወቅት በሰባተኛው የሥራ ላይ ቡድን ሪፖርት ውስጥ ወደ 769 አንቀጾች ያሉት፣ 400 ገጽ የሚሸፍን፣ 52 ተቀጽላ ዶክመንቶች የተካተቱበት፣ 419 የሚጠጉ የሕግ ማዕቀፎች የቀረቡበት እና 32 የግዴታ አንቀጾች ከሪፖርቱ ጋር ተካቶ የተገመገመበት ሰነድ ተዘጋጅቷል።
እነዚኽን ይዞ በባለብዙ ወገን ድርድር ላይ በመሳተፉ፣ የኢትዮጵያ የአባልነት ጉዞ ከምንም ጊዜ በላይ በይዘት ደረጃ የተገመገመበት፣ ፍሬ ነገር የገባበት፣ የተሻለ ሪፖርት የቀረበበት እና የአባል አገራትን ቀልብ የሳበ መድረክ እንደነበርም፣ ሚኒስትሩ በቃለ-መጠይቃቸው ላይ አንስተዋል። በዚኽም ምክንያት፣ አብዛኞቹ አባል አገራት ኢትዮጵያ በዚኹ የአውሮፓውያኑ ዓመት ሂደቱን ማጠናቀቅ እንደምትችል የተስማሙበት ሁኔታ መኖሩን ያነሱት ዶ.ር. ካሳሁን፣ ቀሪ ነገሮች ባይጠፉም በሰባተኛው ስብሰባ ላይ ትልልቅ ውሳኔዎች ተወስደዋል ብለዋል።
ከእነዚህም መካከል የጉምሩክ ታሪፍ ትመና ዐዋጅን በማሻሻል፣ ሌሎች ቀረጦች እና ክፍያዎችን አባል ከሚኮንበት ጊዜ ጀምሮ ለማስቀረት ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል። እንዲኹም የፍራንኮ ቫሉታ ክፍያ መመሪያ የጸደቀበት፣ የካርጎ ስካኒንግ ፊንን ለማስቀረት ስምምነት የተደረሰብት እና ብዙዎች በዚኽ ቡድን ስብሰባ ላይ እንደ ጥያቄ የሚያነሷቸው ጉዳዮች የተወገዱበት በመሆኑ፣ ይበልጥ መተማመን ተፈጥሮ የኢትዮጵያ የድርድር ሂደት እውነተኛ ወደተባለ ደረጃ አቅንቷል ተብሏል። በኹሉም ምዕራፎች ውይይቶች ተደርገው መግባባት ላይ የተደረሰበት እና ቀሪ የጥያቄዎች ቁጥርም እየቀነሰ ስለመጣ፣ በመጪው ወርኃ መስከረም 8ኛው የሥራ ላይ ቡድን ስብሰባ እንዲከናወን እና ከእዚያ በፊት መቅደም ያሉባቸው ሥራዎች እንዲሰሩ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ኹለተኛው እና ዋናው የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድር የሚከናወንበት መድረክ፣ የባለኹለትዮሽ የገበያ ዕድል ድርድር ተብሎ የሚታወቀው ነው። በዚኽም፣ ከ56ቱ የሥራ ላይ ቡድን አባላት መካከል 22ቱ አገራት በኹለትዮሽ ለመደራደር ጠይቀው የነበረ ቢሆንም፣ ሂደቱ እያደገ ሲመጣ እና በተለይም በአምስተኛ እና በስድስተኛው የሥራ ላይ ቡድን ስብሰባዎች ላይ በቂ ምላሽ እና ማብራሪያ በባለብዙ ወገን መድረክ በመሰጠቱ፣ አምስቱ አገራት ጥያቄያቸውን ትተው በባለብዙ ወገን ድርድሩ ይበቃል በማለታቸው የተደራዳሪ አገራቱ ቁጥር ወደ 17 ዝቅ ብሏል። ከእነዚኽ ከ17ቱ አገራት መካከልም የዘጠኙ የኹለትዮሽ የገበያ ዕድል ድርድር ሙሉ በሙሉ የተቋጨ ሲሆን፣ ከአገራቱ ጋር ያለው ድርድር በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ሚኒስትሩ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ይኽን ኢትዮጵያ እያጠናቀኩ ነው ያለችውን የአባልነት ሂደት ጠቅለል አድርጎ የሚያሳየን፣ ሚኒስትሩ ዶ.ር. ካሳሁን፣ በዚያ የያውንዴው ጉባኤ ላይ ካደረጓቸው ኹለት ንግግሮች መካከል ዋንኛ የሆኑትን ነጥቦች ጠቅለል አድርገን ስንመለከታቸው ነው፤ ሚኒስትሩ ለጉባኤው ባቀረቡት ወቅታዊ ሪፖርት፣ የሚከተሉትን ፖሊሲ ነክ ጉዳዮች መንግስታቸው እያከናወነ ስለመሆኑ ለጉባኤው እንድምተኞች ነገርዋቸዋል፤ እነዚህም፦
- የፍራንኮ ቫሉታ አሠራርን በተመለከተ፦ የፍራንኮ ቫሉታ ግብይቶችን በበላይነት የሚመራ እና የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ መመሪያ ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ መዋሉ፤
- የፌደራል መንግሥት የልማት ድርጅቶች አጠቃላይ ሀብት መረጃን በተመለከተ፦ የእነዚኽን ተቋማት ጠቅላላ የሀብት ዝርዝር መረጃ የማቅረብ ሥራ በአኹኑ ወቅት በግምገማ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በቅርቡ ተጠናቆ በሪፖርቱ ውስጥ እንደሚካተት፤
- የንግድ ፈቃድ አገልግሎት ክፍያ ደንብን በተመለከተ፦ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርን የንግድ ፈቃድ አገልግሎት ክፍያ ደንብ በድጋሚ የተገመገመ ሲሆን፣ የረቂቅ ደንቡ ሰነድ እንዲጸድቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥያቄ መቅረቡ፤
- የካርጎ ስካኒንግ ክፍያን በተመለከተ፦ በምርት ዋጋ ላይ ተመስርቶ የሚጣለውን የካርጎ ስካኒንግ ክፍያ፣ ከሐምሌ 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ ውሳኔ መተላለፉ፤
- ያገለገሉ አልባሳት ዕገዳን በተመለከተ፦ ያገለገሉ አልባሳት ወደ አገር እንዳይገቡ ተጥሎ የነበረው ዕገዳ የተነሳ ሲሆን፣ በምትኩ ከዓለም ንግድ ድርጅት ድንጋጌዎች ጋር በሚስማማ መልኩ ተፈጻሚ የሚሆን የጉምሩክ ቀረጥ እንዲጣልበት መደረጉ፤
- የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ዕገዳን በተመለከተ፦ በነዳጅ በሚሠሩ መኪኖች እና ባለሦሥት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጆች) ላይ የተጣለውን የገቢ ንግድ ገደብ በተመለከተ፣ ኢትዮጵያ ድርጅቱን ከመቀላቀሏ በፊት ተመሳሳይ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫ ለመከተል አቅዳለች ተብሏል፤ አኹን ያለው ገደብ በጊዜያዊነት እንዲቀጥል የተደረገው በመካከለኛው ምሥራቅ ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ በተፈጠረው የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ምክንያት መሆኑ መነገሩ፤
- የዕቃዎች መገኛ መታወቂያ ቅድመ-ውሳኔን በተመለከተ፦ የዕቃዎች መገኛ መታወቂያ ቅድመ-ውሳኔ መመሪያ የወጣ ሲሆን፣ አሠራሩ ይበልጥ ግልጽ እና አስቀድሞ መገመት የሚቻል እንዲሆን ለማድረግም፣ እነዚኽ የቅድመ-ውሳኔ ውጤቶች በኢንተርኔት አማካኝነት በይፋ ማተም መጀመሩ፤
- የጉምሩክ ሕግ ማሻሻያን በተመለከተ፦ የጉምሩክ ሕግ ማሻሻያ አጀንዳ አካል የሆነው የጉምሩክ ዐዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ በእንደራሴዎቹ ምክር ቤት እየተመከረበት መሆኑ፤
- የበርን ኮንቬንሽን (የሥነ-ጽሑፍ እና የሥነ-ጥበብ ሥራዎች የባለቤትነት ጥበቃ ስምምነት) ማጽደቅን በተመለከተ፦ የበርን ኮንቬንሽን ለማጽደቅ የተዘጋጀው ረቂቅ ሕግ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡ፤ እንዲኹም፣
- ሌሎች ቀረጦች እና ክፍያዎችን ሙሉ በሙሉ ማስቀረትን በተመለከተ፦ የአባል አገራትን ስጋቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ እንዲኹም ይኽ ጉዳይ የኢትዮጵያን የአባልነት ጉዞ በማጓተት ረገድ ትልቅ ማነቆ ሆኖ እንደቆየ በመገንዘብ፤ የኢትዮጵያ መንግስት አገሪቱ የድርጅቱ አባል ከምትሆንበት ዕለት ጀምሮ ማናቸውንም ሌሎች ቀረጦች እና ክፍያዎችን ሙሉ በሙሉ ለመሰረዝ ውሳኔ ላይ መድረሱ የሚሉት መሠረታዊዎቹ ነጥቦች ናቸው።
ኢትዮጵያ ምን መማር አለባት?
የኤዢያዎቹ አገራት ኔፓል እና ካምቦዲያ፣ በድርድር እና በአባልነት ዝግጅት ሂደት ውስጥ አልፈው የዓለም ንግድ ድርጅትን የተቀላቀሉ ብቸኞቹ ያላደጉ አገራት ናቸው። እነዚኽ አገራት በአባልነት ጉዟቸው ወቅት በርካታ ፈተናዎች የገጠሟቸው ሲሆን፣ ለዚኽም ዋናው ምክንያት የቴክኒክ ድጋፍ ማነስ እና የድርድር አቅም ማጣት እንደነበር በአገራቱ የአባልነት ጥምዝምሾች ዙሪያ የተጻፉ መጣጥፎች ያትታሉ።
በዚኽም የተነሳ፣ ከ‘ራሳቸው አቅም በላይ የሆኑ እና ሌላው ቀርቶ የዓለም ንግድ ድርጅት ራሱ በግዴታነት ከሚያስቀምጣቸው መስፈርቶች የሚልቁ እጅግ ከባባድ የድርድር ውሎችን ለመቀበል ተገድደዋል። ኢትዮጵያም በአሁኑ ወቅት ድርጅቱን ለመቀላቀል በሂደት ላይ የምትገኝ ታዳጊ አገር እንደመሆኗ፣ ካምቦዲያ እና ኔፓል ቀደም ሲል የገጠሟቸውን መሰናክሎች ልታስተናግድ እንደምትችል መገመት ምክንያታዊ ነው። በመሆኑም፣ የእነዚኽ አገራት ተሞክሮ ኢትዮጵያ በአባልነት እና በትግበራ ሂደቷ ወቅት በቀላሉ ሊቀሩ የሚችሉ ስህተቶችን ደግማ እንዳትሠራ ትልቅ እገዛ ያደርጋል። ከኹለቱ አገራት የአባልነት ጉዞ፣ የስምምነት ሰነዶች እና ከተግባር ተሞክሮዎቻቸው ሊወሰዱ የሚችሉት እና ኢትዮጵያም በቅጡ ብታስብባቸው ረብ ይኖራቸዋል የምንላቸውን ጥቂት ነጥቦች እናንሳ፤
ሀ፦ የተንዛዛው ድርድር እና የኹለትዮሽ ፈተናዎች፤
የማራኬሽ ስምምነት* አንቀጽ 12፣ በተቀላቃይ አገር እና በድርጅቱ መካከል ሊደረሱ ስለሚገባቸው ውሎች ግልጽ መመሪያ የማያስቀምጥ በመሆኑ፣ የአባልነት ሂደቱ እጅግ ፈታኝ እና የተራዘመ መሆኑ በአገራቱ ተሞክሮ ታይቷል። የዓለም ንግድ ድርጅት አባላት ለታዳጊ አገራት የድርድር ሂደቱን ለማቅለል እና ለማፋጠን ቃል የገቡ ቢሆንም፣ በተግባር ግን ኔፓል እና ካምቦዲያ እንደ ሌሎቹ ያደጉ አገራት ሁሉ ውስብስብ የሆኑ የድርድር ደረጃዎችን እንዲያልፉ ተደርገዋል። ከዚኽም በላይ፣ በድርጅቱ ውስጥ ቀድመው የነበሩት በኢኮኖሚ የበለጸጉ አባል አገራት በኹለትዮሽ ድርድር ምዕራፍ ላይ እጅግ ጥብቅ እና ከባድ ጥያቄዎችን ስላቀረቡባቸው፣ ኹለቱ አገራት በተለይ በዚህኛው ደረጃ ላይ ከፍተኛ ፈተና ገጥሟቸው ነበር።
ለ፦ የሉላዊው ድርጅት ግዴታዎች ተጽዕኖ እና የአቅም አለመመጣጠን፤
ኹለቱ አገራት እንዲገቡበት የተጠየቁት አሳሪ ውሎች፣ የበለጸጉት የድርጅቱ አባል አገራት በተለይ በታዳጊ አገራት ላይ ከድርጅቱ መደበኛ ሕግጋት በላይ የሆኑ ግዴታዎችን የመጫን አዝማሚያ እንዳላቸው በግልጽ አሳይቷል። በድርድሩ ወቅት ካምቦዲያ እና ኔፓል ከኢኮኖሚ እድገታቸው፣ ከአቅማቸው፣ እንዲኹም ከንግድ እና ፋይናንስ ፍላጎቶቻቸው ጋር የማይመጣጠኑ ውሎችን እንዲቀበሉ ተጠይቀዋል።
ነባር አባላት በአባልነት ሂደት ላይ ካሉ ታዳጊ አገራት የእቃዎች እና አገልግሎቶች ንግድ ላይ ቅናሾችን እና ግዴታዎችን ከመጠየቅ እንዲቆጠቡ መርህ የተቀመጠ ቢሆንም፣ የኹለቱ አገራት ግዴታዎች ከነባር ታዳጊ አገራት አልፎም ከአንዳንድ በማደግ ላይ ያሉ እና የበለጸጉ አገራት ጭምር እጅግ የበረቱ ነበሩ። ይኽም የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሂደት በአቅም እና በጉልበት የበላይነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን እና አሠራሩም ከንድፈ-ሐሳቡ ፈንገጥ ማለቱን ያሳያል። በተግባር፣ ተቀላቃይ አገራት ከሥርዓቱ ውጭ በመሆናቸው ሕግጋቱን በማውጣት ረገድ አንዳችም ሚና የላቸውምና፣ ሂደቱ በአብዛኛው በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሚመራ እንዲሆን ኹኔታዎች ግድ ብለዋል።
ሐ፦ ከስምምነት በኋላ ያለው የቴክኒክ ድጋፍ እና የክትትል ማዕቀፍ አስፈላጊነት
ኹለቱ አገራት የድርጅቱ አባል ከሆኑ በኋላ ያገኙት የቴክኒክ ድጋፍ በቂ ባይሆንም፣ በአባልነት ሂደቱ ወቅት ያገኙት ድጋፍ ግን ውስብስብ ሰነዶችን ለማዘጋጀት እና አቅምን ለመገንባት እጅግ አስፈላጊ ነገሮች ነበር። አባል ከሆኑ በኋላ ግን በቂ የቴክኒክ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ምክንያት፣ አገራቱ ከአባልነቱ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅሞች በተለይም የወጪ ንግድን ማብዛት እና ማስፋፋትን የመሰሉ ቁልፍ የፖሊሲ ግቦችን ማሳካት አልቻሉም።
ከዚኽ በቂ ካልሆነ የቴክኒክ ድጋፍ በተጨማሪ፣ የአፈጻጸም ክትትል ማዕቀፍ እና የማስገደጃ የጊዜ ገደቦች አለመኖራቸው፣ አገራቱ የተጣሉባቸውን ግዴታዎች በወቅቱ እና በብቃት ለመተግበር ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም የትግበራ ፍጥነታቸው እንዲቀዘቅዝ አድርጓል። በመሆኑም፣ የቴክኒክ ድጋፍ በአባልነት ድርድር ወቅት ብቻ ሳይሆን፣ የተገቡትን ቃል ኪዳኖች በተግባር ለመተርጎም እና ከአባልነቱ የሚገኘውን ጥቅም እውን ለማድረግ ጭምር ለታዳጊ አገራት ወሳኝ መሆኑን መገንዘብ ከአገራቱ ተሞክሮ መገንዘብ ይቻላል።
መ፡ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እና የድርድር ስልት ልዩነት
የአገራቱ የስምምነት ሰነዶች እንደሚያሳዩት፣ ካምቦዲያ ይበልጥ አድካሚ እና ከባድ የሆኑ ውሎችን ለመቀበል የተስማማች ሲሆን፤ ኔፓል ግን በአንፃራዊነት የተሻሉ እና አመቺ የሆኑ የአባልነት ውሎችን መደራደር ችላለች። ኔፓል ከካምቦዲያ ይልቅ ስኬታማ ልትሆን የቻለችበት ምክንያት በድርድሩ ወቅት ባገኘችው የቴክኒክ ድጋፍ እና ከኹሉም በላይ ደግሞ በድርድር ሂደቱ ላይ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በመኖሩ ነው። በኔፓል ኹኔታ እንኳን አብዛኞቹ ባለድርሻ አካላት ከሂደቱ ተገልለናል ብለው ቢያምኑም፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ቡድኖች የቀረቡ የፖሊሲ ትንታኔዎች እና የውይይት መድረኮች የኔፓል መንግስት በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ እጅጉን የከበዱ ግዴታዎችን እንዳይቀበል አስችለውታል። ይኹን እንጂ በመንግስት እና በባለድርሻ አካላት መካከል የነበረው ግንኙነት አባልነቱ ከተረጋገጠ በኋላ ባለመቀጠሉ ክፍተት ተፈጥሯል። ስለዚኽም፣ ነባር አባል አገራት የሚያቀርቧቸውን ጥብቅ እና አሳሪ ጥያቄዎችን በድርድር ለመቋቋም በታዳጊ አገራት የአባልነት ጉዞ ውስጥ የባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ መኖሩ እጅግ ወሳኝ መሆኑን መማር ይቻላል።
ተስፋዎች እና ተግዳሮቶች
እንደየትኞቹም ታዳጊ አገራት፣ ኢትዮጵያም በጀመረችው የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ጉዞ መሳካት፣ የተለያዩ ተስፋዎች እና ተግዳሮቶች ይጠብቋታል። ያም ሆኖ፣ ኹሉም አገር አንድ ዓይነት ተስፋዎች እና ፈተናዎች አይጋረጡበትምና፣ ኢትዮጵያም ከራሷ ውስጣዊ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አውድ አኳያ፣ ሊገጥሟት የሚችሉ ተግዳሮቶችን እና ሊመጡ የሚችሉ ዕድሎችን ከአኹን መመልከትም፣ ተቋሚው ዝግጁነትን ለማሳለጥ መጥቀሙ አሌ አይባልምና፣ በኹለቱ መጪ ኹነቶች ዙሪያ ጥቂት ነጥቦችን ማንሳት ጠቃሚ ይመስለናል።
በረከቶቹ ምንድር ናቸው?
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን ብትቀላቀል ሰፊ የገበያ ዕድሎችን የምታገኝ ሲሆን፣ በተለይም አባልነቱ አገሪቱ በይበልጥ ለምትታወቅባቸው የግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ ቀረጥን በመቀነስ ረገድ አዲስ ባይሆንም ትልቅ የገበያ ዕድል ይፈጥራል። ከዚኽ ጋር በማያያዝ የንግድ ሕግ እና ፖሊሲ ባለሙያዎችም፣ ገበያውን ለአባል አገራት መክፈት ሸቀጦችን ያለ ቀረጥ የመሸጥ ዕድል እንደሚሰጥ እና ቀረጥን የመሳሰሉ የንግድ መሰናክሎችን በማስወገድ እንደ ቡና ያሉ ምርቶችን ያለ ክልከላ በዓለም ገበያ ለማቅረብ በር እንደሚከፍት ይገልጻሉ።
አጥኚዎቹ፣ እንደ አውሮፓ ገበያ ባሉ መድረኮች ለመግባት ለብዙ የአፍሪካ የንግድ ተቋማት ተግዳሮት የሆኑ ከታሪፍ ውጪ ያሉ ግዴታዎች በስምምነት እንደሚነሱ እና ይኽም ትልቅ የገበያ ዕድል እንደሚፈጥር ያብራራሉ። ሌላው ተስፋ የውጪ መዋዕለ-ንዋይን መሳብ ሲሆን፣ የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የሠራተኛ ወጪ እና መሬት ርካሽ መሆናቸው እንዲኹም አገሪቱ የአባልነት ዋስትና ስላላት የውጪ ባለሀብቶችን ለማሳመን ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይታመናል።
ውድድር ወደ ተሻለ የኢኮኖሚ ሥርዓት እንደሚመራ ሲጠቀስ፣ የአገር ውስጥ ገበያን ከውጭ ውድድር ጠብቆ ያቆየው አሮጌው አሠራር አዋጪ አለመሆኑ መንግስትን ወደ ነፃ ገበያ መምራቱም ይነሳል። ድርጅቱ እንደ መማሪያ የሚያገለግል በመሆኑ ውድድር ውስጥ መግባት የራሱ የሆነ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም የኢትዮጵያን የአባልነት ጥያቄ የሚደግፉ ጸሓፍት ይሟገታሉ፤ ሂደቱ የአገሪቱ የንግድ ሥራዎች ከአካባቢያዊ እና ዓለም ዓቀፍ የዕሴት ሰንሰለቶች ጋር እንዲተሳሰሩ ያደርጋል ተብሎም ይጠበቃል።
ይኽንኑ ጥቅም እና ተስፋ መሠረት በማድረግ፣ የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን በተለያዩ የተወሰኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ በርካታ ጥቅሞችን የማስገኘት ትልቅ ተስፋም ተሰንቋል። በአገልግሎት ዘርፍ ረገድ፣ አገልግሎት በማደግ ላይ ባሉ አገራት የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ወሳኝ ሚና የሚጫወት ሲሆን፣ ለአብነት ያህል ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ውስጥ፣ አገልግሎት የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ብዙውን ጊዜ ወደ 40 በመቶ ግድም መሆኑ ይታወቃል።
ከዚኽ አኳያም፣ አገሪቱ በአገልግሎት ዘርፉ ላይ እጅግ ተመራጭ አገር አልያም፣ በንግድ ተቋሙ አጠራር አገራዊ አያያዝ የሚባሉትን መርሆዎች መከተሏ በርካታ ትሩፋቶችን ያስገኛል። ከእነዚኽም መካከል የአገር ውስጥ ውድድርን ማሳደግ እና የአገልግሎት ጥራትን ማሻሻል፣ አዳዲስ የአገልግሎት መስመሮችን በሰፊው ማግኘት እና ፈጣን የአገልግሎት አሰጣጥን እውን ማድረግ፣ የተሻሉ የብድር ምዘና ሥርዓቶችን መዘርጋት፣ የምርት ምርጫዎችን እና የአቅራቢዎችን ብዛት ማስፋፋት፣ የስጋት ማከፋፈያ መንገዶችን ማቃለል፣ የፋይናንስ መካከለኛነት ሚናን ማጎልበ፣ እንዲኹም የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማፋጠን የሚሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ።
በተጨማሪም፣ አገሪቱ ከአገልግሎት ንግድ አጠቃላይ ስምምነት አንቀጽ 19፣ ለታዳጊ አገራት ከሚደረጉ ልዩ አያያዞች፣ እንዲኹም ጥቂት ዘርፎችን ብቻ ለመክፈት እና የተወሰኑ የንግድ ልውውጦችን ብቻ ለገበያው ነፃ ለማድረግ በሚያስችሉ የተደራደሩ የአሠራር ስልቶች ተጠቃሚ መሆን ትችላለች። በመሆኑም፣ በአገልግሎት ዘርፍ ማሻሻያ ላይ የሚኖረው ጥንቃቄ የተሞላበት እና ወጪን ቆጣቢ የሆነ አካሄድ፣ ከአገሪቱ የልማት ግቦች ጋር የሚጣጣም ሲሆን፤ ይኽም አገሪቱ እንደ ልዩ ፍላጎቷ የአገልግሎት ዘርፎቿን እንድትከፍት እና የገበያ ዕድሏን እንድታሰፋ ምቹ ተለዋዋጭነትን ይሰጣታል ተብሎም ይታመናል።
በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ከመዋዕለ-ንዋይ ዘርፍ ዕድሎች አኳያ ሲታይም፣ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የኢኮኖሚ ዕድገት ዋነኛ ሞተር ተደርጎ የሚወሰደውን የውጭ መዋዕለ-ንዋይ ፍሰትን ለመሳብ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል። ምክንያቱም አባልነቱ የባለሀብቶችን ፍላጎት የሚስቡ እንደ የንብረት መብት ጥበቃ እና የፖለቲካ መረጋጋትን የመሰሉ ማረጋገጫዎችን እና ፖለቲካዊ ቁርጠኝነቶችን አብሮ ያቀርባልና። የድርጅቱ አባል መሆን ግልጽ የንግድ ፖሊሲዎች ያሉበት ክፍት እና ግልጽ ገበያን የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በላይ፣ ለባለሀብቶች አስተማማኝ የሕግ ማዕቀፍ ይሰጣል፤ ይኽም ለውጭ የመዋዕለ-ንዋይ ፍሰት ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል።
በአጠቃላይ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የተረጋጋ እና ክፍት የፖሊሲ ከባቢን የሚፈጥር በመሆኑ፣ የመዋዕለ-ንዋይ ፍሰትን በከፍተኛ ሁኔታ ይስባል፤ ባለሀብቶችም አገሪቱ ለክፍት እና የተረጋጋ የፖሊሲ ሥርዓት ያላትን ቁርጠኝነት እንዲተማመኑ ያደርጋል። በተጨማሪም እንደ ከንግድ ጋር የተያያዙ የመዋዕለ-ንዋይ ፍሰትን የሚያሳልጡ እርምጃዎች እና የአእምሯዊ ንብረት መብቶች ስምምነትን የመሰሉ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ የቴክኖሎጂ ግዢን በማበረታታት እና አእምሯዊ ንብረትን በመጠበቅ፣ አገሪቱ የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታስመዘግብ ትልቅ ድጋፍ ይሰጣሉ የሚለው፣ የአባልነቱ ጥያቄ ደጋፊዎች ሙግቶች ናቸው።
ተግዳሮቶች
በሌላ በኩል፣ ሌሎች የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት አባልነቱ በርካታ መዋቅራዊ ፈተናዎችን እና ግዴታዎችን ይዞ የሚመጣ ሲሆን፣ ትልቁ ፈተና አገሪቱ የገበሬዎች እና የአምራቾችን ተወዳዳሪነት ለማጠናከር የምታደርጋቸውን ድጎማዎች እንድትቀንስ መገደዷ ነው፤ ምክንያቱም ሌሎች አባል አገራት ድጎማን የውድድር መድረኩን እንደ ማዛነፍ ስለሚቆጥሩት እንዳታደርግ የመከልከል አሠራር አላቸው። ከዚኽ ባለፈም፣ በአገሪቱ የሕግ ማዕቀፍ፣ የአእምሯዊ ንብረት መብት ጥበቃ ሥርዓት ድክመት፣ እንዲኹም ከፖለቲካ ነፃ የሆነ ተገማች የዳኝነት እና የችግር መፍቻ ሥርዓት አለመኖር የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ላይ ጥያቄ እንደሚያስነሳ አንዳንድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ከንግድ ሥርዓቱ ውጪ ለሆኑ እንደ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ያሉ ችግሮች የሚሰጡ ዓለም አቀፍ መተማመኛዎች አኹንም በኢትዮጵያ እንደሌሉ እና የኢትዮጵያ ድርጅቶች፣ አምራቾች እና ገበሬዎች በዚኽ ክፍት ውድድር ውስጥ ህልውናቸውን አስጠብቀው መቆየት ስለመቻላቸው እርግጠኛ መሆን እንደማይቻልም ያሳስባሉ። የንግድ ሕግ ባለሙያዎች በበኩላቸው፣ ሂደቱን ፈታኝ የሚያደርገው በኢትዮጵያ ገበያ ፍላጎት ካላቸው እንደ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ካሉ በኢኮኖሚ ከበለጸጉ አገራት ጋር የሚደረገው የኹለትዮሽ ድርድር መሆኑን ጠቅሰው፣ እነዚኽ አገራት መድንን ጨምሮ ዝግ የሆኑ ዘርፎች እንዲከፈቱ፣ ቀረጦች እንዲቀነሱ እና ለአገር ቤት ኢንዱስትሪዎች የሚደረጉ አድሏዊ አሠራሮች እንዲወገዱ የሚያደርጉት ግፊት ጊዜ የሚፈጁ ተጨማሪ የሕግ እና የተቋማዊ ማሻሻያዎችን እንደሚጠይቅ ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ የሚጣለው ቀረጥ መቀነሱ በመንግስት ቀጥተኛ የገቢ ምንጭ ላይ የተወሰነ ጫና መፍጠሩ አይቀሬ ነው የሚሉ ተንታኞች፣ ከዚኽ ባለፈም፣ ገና በማደግ ላይ ያለው የአገር ውስጥ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከዓለም ዓቀፉ ርካሽ እና ጥራታቸውን ከጠበቁ ምርቶች ጋር የሚኖረው የገበያ ውድድር የአገር ውስጥ አምራቾችን ከማዳከሙ ባሻገር፣ የጨቅላ ኢንዱስትሪዎች መዋጥ ተብሎ የሚጠራውን ኹነት እንዳይፈጥር ስጋት ያላቸው ባለሙያዎች ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም። ከኹሉም በላይ ግን፣ በአኹኑ ወቅት የዓለም የንግድ ሥርዓት ጫና ውስጥ በመሆኑ እና የተቋሙ መኖር እና የማስገደድ አቅም ራሱ ጥያቄ ውስጥ በገባበት በዚኽ ሰዓት፣ አባል ለመሆን የሚደረግ እንቅስቃሴ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል የሚል ጠንካራ ሥጋት ይደመጣል።
የብሪጅ ምክረ-ሐሳቦች
ከላይ የጠቀስናቸውን የኹለቱን ታዳጊ አገራት ተሞክሮ እና በጉዳዩ ላይ የተጻፉ በዛ ያሉ ጥናቶችን ተንተርሰን፣ ምንም እንኳን ድርድሩ የመጨረሻው መስመር ላይ እንደሚገኝ ቢነገርም፣ አባልነቱ የሚሳካው ኹሉም የንግድ ድርጅቱ አባላት በሙሉ ድምጽ ሲስማሙ ነውና፣ በቀጣይ በሚኖሩ ድርድሮች፣ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ሰከን ብለው ሊመለከቷቸው ይገባሉ የምንላቸውን ነጥቦች ማንሳት እንሻለን።
ኢትዮጵያ በተለይ የዓለም ንግድ ድርጅት መሥራች ከሆኑት ታዳጊ አገራት በበለጠ ደረጃ ከባባድ የሆኑ ግዴታዎችን እና ውሎችን ለመቀበል ፈጽሞ መስማማት እንደሌለባት የእነዚያ የኤዢያ አገራት ተሞክሮ በቅጡ ይሳያል። ከአባልነቱ የሚገኘውን ጥቅም በተሟላ ኹኔታ እውን ለማድረግም፣ አገሪቱ በግልጽ የተቀመጡ እና የተለዩ የአባልነት ግቦችን መንደፍ ይኖርባታል።
ከካምቦዲያ እና ከኔፓል ተሞክሮ መረዳት እንደተቻለው፣ የአባልነት ድርድሩ በኹለትዮሽ መድረክ የሚከናወን እና በመጨረሻም በተቀላቃይ አገር ላይ አስገዳጅ ሕግ ሆኖ የሚጸድቅ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ በእቃዎች ንግድ፣ በአገልግሎት ንግድ እና በአእምሯዊ ንብረት መብቶች ዙሪያ ግልጽ የሆኑ የድርድር ግቦችን ልትቀርጽ ይገባታል። በዚኽ ሂደት ውስጥ አገሪቱ የራሷን ልዩ ፍላጎቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት እና ከአቅሟ ጋር የሚመጣጠኑ ቅናሾችን እና መብቶችን ለማስከበር መጣር ይኖርባታል።
እንደ ብሪጅ እምነትም፣ ዋንኞቹን የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ውሳኔ ሰጪ የፌደራል ተቋማትን ያካተተው ተደራዳሪ ቡድኑ፣ በተለይም የሚከተሉትን ነጥቦች ላይ ብርቱ ድርድር ቢያደርግ፣ ከሚመጣው ፈተና መትረፍ የሚቻል ይመስለናል፤
ሀ፦ የቀረጥ ጣሪያን ከፍ አድርጎ መደራደር፦
የነባር አባል አገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ ቀረጥ እጅግ አስፈላጊ የፊስካል ፖሊሲ መሣሪያ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ የታሪፍ ጣሪያዎቿ አሁን በተግባር ላይ ካሉት የታሪፍ መጠኖች እጅግ ከፍ ብለው እንዲቀመጡ ማረጋገጥ አለባት። ይኽ አሠራር እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገራት ዋነኛ የገቢ ምንጭ ጭምር በመሆኑ፣ የአገሪቱን የታሪፍ ጣሪያዎች ከኔፓል እና ከካምቦዲያ መጠኖች በበለጠ ከፍ አድርጎ ለመደራደር መጣር ይኖርባታል። በተጨማሪም፣ ለአገር ውስጥ ጥንቃቄ ለሚሹ ስሱ የንዑስ-ኢኮኖሚ ዘርፎች ከፍተኛ የታሪፍ ጣሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይገባታል እንላለን።
ለ፦ ረጅም የሽግግር ጊዜዎችን ማስከበር፦
የአባልነት ግዴታዎችን ደረጃ በደረጃ ወደ ተግባር ለመተግበር የሚያስችሉ ረጅም የሽግግር ጊዜዎችን ለማግኘት መደራደር ያስፈልጋል። ለምሳሌ፣ ከንግድ ጋር የተያያዙ የአእምሯዊ ንብረት መብቶች ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል (ለምሳሌ ያህልም፣ ለመድኃኒት ምርቶች የባለቤትነት ጥበቃን በተመለከተ እ.አ.አ. እስከ 2016 የነበረውን ዓይነት የሽግግር ጊዜ) በቂ የሽግግር ጊዜ ማግኘትን ማረጋገጥ ይኖርባታል።
ሐ፦ ልዩ እና ተለዋዋጭ አሠራሮችን በአግባቡ መጠቀም፦
ለታዳጊ አገራት የሚፈቀዱትን ልዩ እና ተለዋዋጭ አያያዝ ተብለው የሚጠሩትን መዋቅራዊ ዝግጅቶችን በከፍተኛ ደረጃ በጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባም ማስታውስ እንሻለን። ለምሳሌ፣ ለግብርናው ዘርፍ ድጎማ የመስጠት መብቷን ለማስከበር በፅኑ መታገል ይኖርባታል። የግብርናው ዘርፍ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ካለው ግዙፍ ድርሻ፣ በተለይም በሰብዓዊ ልማት፣ በምግብ ዋስትና እና በገጠር ልማት ላይ ካለው የማይተካ ሚና አንፃር፣ ኢትዮጵያ በድጎማዎች እና በታሪፍ ዙሪያ ጠንካራ ግዴታዎችን እንድትገባ ሊጠየቅባት አይገባም።
ይልቁንም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በታሪፍ፣ በአገር ውስጥ ድጋፎች እና በድጎማ ረገድ የፖሊሲ ተለዋዋጭነትን ይዛ መቀጠል ይኖርባታል። ከዚኽ አኳያም፣ ምንም እንኳን ካምቦዲያ ለግብርና የምታደርገውን ድጎማ ይዛ ለመቀጠል ሳትችል ብትቀርም፣ ኔፓል ግን ይኽንን መብቷን በድርድር ማስከበር መቻሏን፣ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎችም ልብ ሊሉት የሚገባ ተሞክሮ መሆኑን ማስታወስ እንፈልጋለን።
በዚኽ መልኩ ከላይ ከቀረቡት የብሪጅ ዳሰሳዊ ምልከታዎች አኳያም፣ የእንደራሴ ዋንኛ ትኩረት የኢትዮጵያ እንደራሴዎች ናቸውና፣ ለተሰናባቾቹም ሆነ በቀጣዩ ዓመት ለሚመጡት እንደራሴዎች ይበጃሉ ያልናቸውን ምክረ-ሐሳቦች አጠር አድርገን ማንሳት እንሻለን። በዳሰሳችን ላይ ከተነሱት መዋቅራዊ የፖሊሲ ለውጦች፣ ከታዳጊ አገራት (በተለይም ከኔፓል እና ካምቦዲያ) ተሞክሮዎች፣ እንዲኹም አገሪቱ ከገባችባቸው የኹለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን የድርድር ግዴታዎች አኳያ፣ የእንደራሴዎቹ ምክር ቤት እኒኽን ምክረ-ሐሳባዊ ነጥቦች በቅጡ እንዲያያቸው አበክረን እንጠይቃለን፤
ሀ፦ በአገሪቷ ሕገ-መንግሥት እንደተቀመጠው፣ የእንደራሴዎቹ ምክር ቤት፣ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነትን ተከትሎ የሚመጡ በርካታ ረቂቅ ዐዋጆችን (የጉምሩክ ዐዋጅ ማሻሻያ፣ የንግድ ፈቃድ አገልግሎት ክፍያ ደንብ፣ የበርን ኮንቬንሽን እና የቅጂ መብት ጥበቃ ሕግጋትን) በዝርዝር መርምሮ የሚያጸድቅ ሕግ አውጪ ተቋም ነው። እናም ምክር ቤቱ እነዚኽን ዓለም ዓቀፍ ሕግጋት በሚያጸድቅበት ወቅት፣ የሕግ ማዕቀፎቹ ከሉላዊው ድርጅት መመዘኛዎች ጋር መጣጣማቸውን ብቻ ሳይሆን፤ ገና በማደግ ላይ ያሉት የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች፣ አነስተኛ አምራቾች እና አርሶ አደሮች ከውጭ ከሚመጡ ርካሽ እና ጥራታቸውን ከጠበቁ ምርቶች ጋር በሚገጥሙት ገደብ የለሽ ውድድር እንዳይዋጡ የሚከላከሉ ብሔራዊ የደኅንነት መጠበቂያዎችን በሕጉ ውስጥ አብሮ ማካተቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል እንላለን።
ለ፦ እንደ ካምቦዲያ እና ኔፓል ተሞክሮ፣ታዳጊ አገራት ከአቅማቸው በላይ የሆኑ የድርድር ውሎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲተገብሩ ሲገደዱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ መቀስቀሱ ተስተውሏል። ከዚኽ አንጻርም፣ ምክር ቤቱ ከተደራዳሪ ቡድኑ የሚቀርቡለትን የስምምነት ሰነዶች በሚገመግምበት ወቅት፣ በተለይም ጥንቃቄ የሚሹ ስሱ የኢኮኖሚ ዘርፎች (እንደ ፋይናንስ፣ መድን፣ እና የአእምሯዊ ንብረት መብቶች) ላይ አገሪቱ ደረጃ በደረጃ እንድትላመድ የሚያስችሉ ረጅም የሽግግር ጊዜዎች በስምምነቱ ላይ መካተታቸውን እና ይኽም በሕግ ደረጃ እንዲጸድቅ ከፍተኛ ግፊት ማድረግ እንደሚኖርበት ማስታወስ ያሻል።
ሐ፦ በርዕሰ-ጉዳዩ ላይ የተጻፉ የበዙ ጥናቶች እንደሚያስጠነቅቁት፣ግብርናው በአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ በምግብ ዋስትና እና በገጠር ልማት ላይ የማይተካ ሚና ያለው እንደመሆኑ፣ ድርጅቱ የሚጥለው የድጎማ የግዴታ ቅነሳ የማይቀለበስ አገራዊ አደጋ ሊቀስቀስ ይችላል። እናም፣ የኢትዮጵያ ሂያጆቹም ሆኑ መጪዎቹ እንደራሴዎች፣ የኔፓልን የተሳካ የድርድር ተሞክሮ መሠረት በማድረግ፣ መንግስት ለግብርናው ዘርፍ የሚሰጠውን የአገር ውስጥ ድጋፍ እና ድጎማ የመስጠት መብቱን በድርድር ጠረጴዛው ላይ በፅኑ አስከብሮ እንዲወጣ፣ ሳይረፈድ ግፊት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ለአገር ውስጥ ስሱ ንዑሳን የኢኮኖሚ ዘርፎች ከፍተኛ የታሪፍ ጣሪያዎችን የማስቀመጥ የፊስካል ፖሊሲ መብት እንዲጠበቅም፣ በበላይነት መከታተል አለበት እንላለን።
መ፦ በድርድር ሂደቱ ላይ የባለድርሻ አካላትን እና የሲቪል ማኅበረሰቡን ንቁ ተሳትፎን ማረጋገጥ ለነገ የሚባል ክንውን አለመሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም። ስለምን ቢሉ፣ በኔፓል ኹኔታ የታየው ስኬት የሲቪል ማኅበረሰብ ቡድኖች እና የፖሊሲ ተንታኞች ንቁ ተሳትፎ በማድረጋቸው እና መንግስት እጅግ የከበዱ ግዴታዎችን እንዳይቀበል በማስቻላቸው ነውና። የእንደራሴዎቹ ምክር ቤትም፣ የሕዝብ ተደራሽነት እና የውይይት መድረክ እንደመሆኑ፣ አባልነቱ ከመጽደቁ በፊት የአገር ውስጥ የንግድ ምክር ቤቶች፣ የኢንዱስትሪ ማኅበራት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና የምጣኔ ሀብት ምሁራን የተሳተፉበት ሰፊ የሕዝብ የአስተያየት መቀበያ መድረኮችን የማዘጋጀት ኃላፊነት ይኖርበታል። ይኽም ተደራዳሪ ቡድኑ የሕዝብ እና የባለድርሻ አካላትን የጋራ ሥጋት እና ግብ ይዞ፣ በብርታት እንዲደራደር ያስችለዋልና፣ ከአኹኑ ቢታሰብበት እናላለን።
ሠ፦ የካምቦዲያ እና ኔፓል ትልቁ ስህተት፣ አባል ከሆኑ በኋላ ግዴታዎችን በብቃት ለመተግበር እና ጥቅሞችን (እንደ ወጪ ንግድ ማስፋፋት) እውን ለማድረግ የሚያስችል የአፈጻጸም ክትትል ማዕቀፍ እና የቴክኒክ ድጋፍ ማጣት እንደነበር ብዙ የተጻፈበት ጉዳይ ነው። ከዚኽ ተጨባጭ ተሞክሮ አኳም፣ ምክር ቤቱ በሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎቹ በኩል፣ ኢትዮጵያ አባል ከሆነች በኋላ የምተገባባቸውን የግዴታ አንቀጾች እና የአንቀጾች የትግበራ ፍጥነት በየጊዜው የሚገመግምበት፣ ከአባልነቱ የሚጠበቁት በረከቶች በተግባር መተርጎማቸውን የሚያረጋግጥ፣ ምናልባትም እንደ ብሪጅ እምነት “የድኅረ-አባልነት ብሔራዊ የክትትል እና የግምገማ ማዕቀፍ” ተብሎ ሊጠራ የሚችል፣ አንድ ራሱን የቻለ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ እንዲቋቋም ቢያደርግ፣ የአባልነት በረከቶቹን ለመቋደስም ሆነ ፈተናዎቹን ለመሻገር ኹነኛ ተቋማዊ መላ ይሆናልና፣ ቢታስብበት ማለት እንሻለን።
*በዓለም ዓቀፉ የንግድ ድርጅት የአገራት ብየና፣ እጅግ ኋላ ቀር አገራት (LDC-Least Developed Countries) የሚል ስየማ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎቹ የላቲን እና የእዢያ አገራት ላይ ይውላል። እንደ ተቋሙ ፍቺም፣ ይኽን መሰሎቹ አገራት ዝቅተኛ የኢኮኖሚ እድገት ያላቸው፣ የሰው ኃይል ልማታቸው ገና ያልበለጸገ እና ለተፈጥሮም ሆነ ለኢኮኖሚ ቀውስ በቀላሉ ተጋላጭ የሆኑ አገራት ናቸው። ያም ሆኖ፣ በተለይም ይኽን ተቋም እና መቆሚያ መሠረቶቹን የሚተቹ የደቡብ ንፍቀ-ክብቡ (ግሎባል ሳውዝ የሚሰኘው) ምሁራን፣ ምደባው ገለልተኛ የኢኮኖሚ ስየማ ብቻም ሳይሆን፤ ታሪካዊ መሠረት ያለው እና የኃይል የበላይነት ፖለቲካ ያረፈበት ሰው-ሠራሽ መዋቅር ነው ይሉታል። ይኽ ምደባ የቅኝ ግዛት ታሪካዊ ውርሶችን የሚያንጸባርቅ፣ ምዕራባውያን ለልማት የሚያስቀምጧቸውን መመዘኛዎች በብቸኛ መውጫ መንገድነት የሚያስቀምጥ አልፎም በደረጃዎች ልጠፋ አማካኝነት በሉላዊው ዓለም ያለውን ኢ-እኩልነትአጠናክሮ የሚያስቀጥል ነው በሚል በተደጋጋሚ በትችት ይነሳል። እነዚኽ ምሁራን እንደሚሟገቱት፣ በዚኽ ‘የኋላ ቀር ታዳጊ አገራት’ ማዕቀፍ ውስጥ የተጋመደው ‘የልማት’ ብያኔ፣ ሌሎች አማራጭ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ እውነታዎችን ያገለለ ከመሆኑም በላይ፣ የተወሰኑ አገራትን በዓለም ዓቀፉ ሥርዓት ውስጥ በተፈጥሯቸው ጉድለት እንዳለባቸው አድርጎ የሚፈርጅ የትርክት መዋቅርን ዘላቂ ያደርገዋል። እኛም፣ ታዳጊ አገር ብቻ የሚለውን ስየማ ስንጠቀም በዚኹ የደቡቡ ምሁራዊ የተዋስዖ መንፈስ ምሪት መሆኑን ልብ ይሏል።
*የማራኬሽ ስምምነት ተብሎ የሚጠራው፣ እ.ኤ.አ ሚያዚያ 15 1994፣ በሞሮኮዋ ማራኬሽ ከተማ የተፈረመው እና የዓለም የንግድ ድርጅት መመስረቱን ያበሰረውን ዓለም ዓቀፍ ውል ያመለክታል። ስምምነቱ አገራት ዓለም ዓቀፍ ንግድን በነጻነት፣ ግልጽነት እና በፍትሓዊነት እንዲያካሂዱ የሚያስችል የጋራ ማዕቀፍ የፈጠረ ታሪካዊ ሰነድም ሆኗል። ይሁን እንጂ ቃሉ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በሌላ መልኩ የማራኬሽ ስምምነ ተብሎ የሚታወቀውን፣ እ.ኤ.አ በ2013 የተፈረመውን እና ዐይነ-ስውራን፣ የማየት ችግር ያለባቸው ወይም የታተሙ መጻሕፍትን ማንበብ የማይችሉ አቅመ-ደካሞች አጋዥ የሆኑ እንደ ብሬል፣ ድምፅ እና ዲጂታል ላሉ ማንበቢያ ቅርጾች የተዘጋጁ መጻሕፍትን በቅጂ መብት ሕግ ሳይገደቡ በቀላሉ እንዲያገኙ እና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እንዲለዋወጡ የሚያደርገውን የዓለም ዓቀፍ የአእምሯዊ ንብረት ድርጅት ስምምነትም ይጨምራል። ኢትዮጵያም የኋለኛውን ስምምነት ብቻ መፈረሟን ያስታውሷል።