BRIDGE Research & Innovation - Parliaments. Peace. Policy

በአፍሪካ ኅብረት ሥር የሚገኘው አህጉራዊው የፓን አፍሪካ ፓርላማ፣ ከሚያዝያ 28 እስከ 30 ድረስ፣ መቀመጫው በሆነው በደቡብ አፍሪካዋ ሚድራን ከተማ ባካሄደው ሰባተኛው ጉባኤው፣ ፕሬዝደንቱን እና ምክትል ፕሬዝደንቶቹን መርጧል። በዚያ የሦሥት ቀናት ጉባኤውም ከመረጣቸው ምክትል ፕሬዝደንቶቹ መካከል፣ የኢትዮጵያው እንደራሴ የተከበሩ ዶ.ር. አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል። የተከበሩ ዶ.ር. አሸብር፣ በዚኽ የአመራር ቦታቸውም፣ የምሥራቅ አፍሪካን ቀጠና ውክልናን ይዘው በተቋሙ ውስጥ ለቀጣዮቹ ሦሥት ዓመታት ያገለግላሉ። እነሆ እንደራሴም፣ የፓን አፍሪካ ፓርላማን ምሥረታ እና ተቋማዊ አደረጃጀት፣ ይኽ የአመራሮች ምርጫ ዳግም የቀሰቀሰውን ተቋሙ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ያሉትን መገፋፋቶች እና የራስ ገዝነት ውስጣዊ እና ውጪያዊ ግፊቶችን፣ እንዲኹም ኢትዮጵያ ጭምር ያላጸደቀችው እና ለተቋሙ ጥርስ ያወጣለታል ተብሎ ተስፋ የተደረገበት የማላቦ ፕሮቶኮልን ለመዳሰስ መርጣለች፤ ምናልባትም፣ ፓርላመንታዊ ተቋሙ እንደ አቻው መሆን አለበት ከሚባለው የአውሮፓ ፓርላማ የሚወስዳቸው ቁም ነገሮች ይኖሩ እንደውም ስንል፣ ከዳሰስናቸው ጥናታዊ ጹሑፎች እና ሙግቶች ተንተርሰን ጥቂት ነጥቦችን እናነሳለን።

እንደራሴው ለሦሥተኛ ጊዜ

የኢትዮጵያ የእንደራሴዎች ምክር ቤት አባል የሆኑት የተከበሩ ዶ.ር. አሸብር ወልደጊዮርጊስ፣ የፓን አፍሪካ ፓርላማ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል። ዶ.ር. አሸብር ከዚኽ በፊት ፓርላማውን በኹለተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት እና በተጠባባቂ ፕሬዚዳንትነት ለሦሥት ጊዜያት ማገልገላቸው ይታወሳል። የአፍሪካ ኅብረት አካል የሆነው የፓን አፍሪካን ፓርላማ፣ ከሚያዝያ 28 እስከ 30 በደቡብ አፍሪካ ሚድራንድ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤቱ ባካሄደው ሰባተኛው የሕግ አውጪ ጉባኤ ልዩ ስብሰባ፣ ተቋሙን ለቀጣዮቹ ሦሥት ዓመታት ይመሩት ዘንድ የመረጣቸው፤ ፕሬዝዳንት (ሰሜን አፍሪካ)፦ የተከበሩ ፋተህ ቡትቢግ (አልጄሪያ) 1 ምክትል ፕሬዝዳንት (ምሥራቅ አፍሪካ)፦ የተከበሩ ዶ.ር. አሸብር ወልደጊዮርጊስ ጋዮ (ኢትዮጵያ)፤ 2 ምክትል ፕሬዝዳንት (ምዕራብ አፍሪካ)፦ ክብርት ዛኔቶር አግዬማን-ራውሊንግስ (ጋና)፤ 3 ምክትል ፕሬዝዳንት (መካከለኛው አፍሪካ)፦ ክቡር ጅዳ ማማር ማሃማት (ቻድ) እና 4 ምክትል ፕሬዝዳንት (ደቡባዊ አፍሪካ)፦ ክብርት ዶ.ር. አርሌት ቦርገስ (አንጎላ) ሆነው መመረጣቸውን ተቋሙ አስታውቋል።
description
ምርጫው የተከናወነው በአፍሪካ ኅብረት የሥራ አሥፈጻሚ ምክር ቤት ውሳኔዎች 1288 (XLVI) እና 1663 (XLVII) መሠረት ሲሆን፣ መጋቢት 27 2026 በጸደቀው ተጨማሪ ውሳኔ እና በፓን አፍሪካን ፓርላማ የአሠራር ደንብ ቁጥር 29 መሠረት ተፈጽሟል ተብሏል። ሂደቱን የአፍሪካ ኅብረትን ሊቀመንበር በመወከል የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ በበላይነት የመሩት ሲሆን፣ የምርጫውን ግልጽነት፣ ተዓማኒነት እና የአፍሪካ ኅብረት ሕጋዊ እና ተቋማዊ ማዕቀፎችን መከተሉን የሚያረጋግጥ ከፍተኛ የልዑካን ቡድንም ድጋፍ አድርጎለታል። የፓን አፍሪካን ፓርላማ ፕሬዝዳንት ፋተህ ቡትቢግ እንደገለጹት፣ “የምርጫው በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቅ በፓን አፍሪካ ፓርላማ ተከታታይ ተቋማዊ እድሳት ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ሲሆን፣ ለዲሞክራሲያዊ አሥተዳደር፣ ተጠያቂነት እና ለሕግ የበላይነት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያጠናክር ነው” ብለዋል። ፕሬዝደንቱ አክለውም፣ ምርጫው አምስቱም የአህጉሪቱ ቀጠናዎች ፍትሓዊ በሆነ መልኩ ተዋጽዖቸው እንዲጠበቅ የሚያደርገውን የአፍሪካ ኅብረት ቀጠናዊ የፍርርቅ መርህ የሚያንጸባርቅ መሆኑን ገልጸዋል። አዲስ የተመረጠው እና በተቋሙ ተለምዷዊ አጠራር ‘ቢሮ’  የተሰኘው አዲሱ አመራር ለሦሥት ዓመታት የሚያገለግል ሲሆን፣ የአፍሪካ ሕዝቦች እና ዳያስፖራዎች በአህጉሪቱ ልማት እና ምጣኔ ሀብታዊ ውህደት ውስጥ ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከሚሰጠው ሥልጣን ጋር በተጣጣመ መልኩ ለፓርላማው ስልታዊ አቅጣጫ እና አመራር እንደሚሰጥም ተነግሯል። ቢሮው የፓርላማው ዋና አመራር እና አሥተዳደራዊ አካል በመሆን የተቋሙን እና የተጠሪ አካላቱን አጠቃላይ አሥተዳደር የመምራት፣ እንዲኹም መዋቅሮቹ ከአፍሪካ ኅብረት የፋይናንስ ደንቦች እና አሠራሮች ጋር በተጣጣመ መልኩ ውጤታማ ሥራ እንዲያከናውኑ የማረጋገጥ ኃላፊነትም እንዳለበት የተቋሙ መረጃ ይጠቅሳል። ከዚያ ጉባኤ ማግስት፣ የፓን አፍሪካ ፓርላማ የሴቶች ስብስብም፣ የሰባተኛው የፓርላማ ዘመን የአመራር መዋቅር እድሳት አካል የሆነውን አዲስ ቢሮ አመራር መርጧል። ምርጫው በየተራ የመምራት መርህን የተከተለ ሲሆን፣ በኬንያዊቷ ክቡር ራሃብ ሙካሚ ዋቺራ የሚመራው አዲሱ አመራርም የሚከተለው ስብጥር እንዳለው የተቋሙ መረጃ ይጠቅሳል፤ ፕሬዝዳንት (ከምሥራቅ አፍሪካ ስብስብ)፦ ክቡር ራሃብ ሙካሚ ዋቺራ (ኬንያ)፣ 1 ምክትል ፕሬዝዳንት (ከደቡብ አፍሪካ)፦ ክቡር አይሻ አዳምስ (ማላዊ)፣ 2 ምክትል ፕሬዝዳንት (ከምዕራብ አፍሪካ)፦ ክቡር ፋቱማታ ንጃይ (ጋምቢያ)፣ 3 ምክትል ፕሬዝዳንት (ከሰሜን አፍሪካ)፦ ክቡር አዋተፍ ቼኒቲ (ቱንዚያ) እና፣ 4 ምክትል ፕሬዝዳንት (ከመካከለኛው አፍሪካ)፦ ክቡር ሊዮካዲ ንዳካዪዛባ (ቡሩንዲ) ሆነው ተመርጠዋል። በዚኽ ሂደት የፓን አፍሪካን ፓርላማ የአጀንዳ 2063፣ አልያም “የምንመኛት አፍሪካ” ተብሎ የተሰየመውን ርዕይ ለማራመድ እና በአፍሪካ ኅብረት መዋቅር ውስጥ ምላሽ ሰጪ፣ ግልጽ እና ለዜጎች ያተኮረ ተቋም የመሆን ሚናውን ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት ዳግም አረጋግጧል ተብሏል። የአዲሱ ቢሮ መመረጥ ለሌሎች የፓርላማው የአመራር መዋቅሮች፣ ማለትም ለቋሚ ኮሚቴዎች ቢሮዎች፣ ለቀጠናዊ ኮከሶች እድሳት መንገድ ይከፍታል ተብሎም ተስፋ ተጥሎበታል።

ዳራውን በጨረፍታ

የ1991ዱ የአቡጃ ስምምነት የአፍሪካ ሕዝቦች በአህጉሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ ልማት እና ውህደት ውስጥ ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ የፓን አፍሪካን ፓርላማ መቋቋም እንዳለበት ይደነግጋል። ይኽ ሐሳብ በአፍሪካ ኅብረት መስራች ሕግ አንቀጽ 17 ላይ በበለጠ ተጠናክሮ ቀርቧል። ከዚኽ ዳራም በመነሳት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብን ለማቋቋም ከቀረበው ስምምነት ጋር ተያያዥ የሆነው እና ስለ ፓን አፍሪካን ፓርላማ የሚደነግገው ፕሮቶኮል መጋቢት 2 2001 በሲርቴ፣ ሊቢያ ጸድቋል። በዚኽም መሠረት የፓን አፍሪካን ፓርላማ እንደ አንዱ የአፍሪካ ኅብረት አካል ሆኖ መጋቢት 2004 በአዲስ አበባ ተመርቋል። የፓርላማው የመጀመሪያው መደበኛ ጉባኤ የተካሄደው ደግሞ፣ የፓርላማው ቋሚ መቀመጫ በሆነችው ደቡብ አፍሪካ መጋቢት 2005 ላይ ነበር። የፓን አፍሪካን ፓርላማ በዓመት ኹለት መደበኛ ጉባኤዎችን የሚያካሂድ ሲሆን፣ እነዚኽ ጉባኤዎች ከመካሄዳቸው አስቀድሞ በፓርላማው አጀንዳዎች ዙሪያ የሚመክሩ የተለያዩ የኮሚቴ ስብሰባዎች ይደረጋሉ። የፓን አፍሪካን ፓርላማ እንዲመሰረት ያስፈለገው፣ የአፍሪካ ፓርላማ አባላት በአህጉሪቱ ችግሮች እና ተግዳሮቶች ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች እና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ላይ በስፋት የሚሳተፉበት አህጉራዊ መድረክ ለመፍጠር ካለው ርዕይ በመነሳት እንደሆነ ስለ ተቋሙ የተጻፉት ሰነዶች ይጠቅሳሉ። የአህጉሪቱ የተለያዩ ሕዝቦች ውክልና እንዲረጋገጥ ለማድረግም፣ አንቀጽ 4፣ ብሔራዊ ፓርላማዎች ወደ ፓን አፍሪካን ፓርላማ ከሚልኳቸው አምስት አባላት መካከል ኹለቱ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች መሆን እንዳለባቸው ያዛል። የፓን አፍሪካን ፓርላማ አባላት የአምስት ዓመት የሥራ ዘመን አላቸው። ፓርላማው ከመጋቢት 2005 እስከ 2009 በነበረው የመጀመሪያው የሥራ ዘመኑ በአማካሪነት ደረጃ ይንቀሳቀስ ነበር። ይኽም ማለት አህጉራዊ የሆኑ ፖለቲካዊ እና ልማታዊ ጉዳዮችን በመወያየት እንደ አፍሪካ ኅብረት አካላት፣ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦች እና የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት ላሉ ባለድርሻ አካላት የውሳኔ ሐሳቦችን ያቀርባል። በኹለተኛው የሥራ ዘመን እና ከዚያ በኋላ ግን ፓርላማው አህጉራዊ ሕጎችን የማውጣት ሥልጣን ወዳለው የሕግ አውጪ አካልነት ይሸጋገራል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚኽ አኳያም፣ ይህንን ሽግግር ለማመቻቸት የፓን አፍሪካን ፓርላማ ፕሮቶኮልን መከለስ አስፈላጊ ሆኗል።
description
በሰኔ 2016 ዓ.ም 6ኛው የፓን አፍሪካ ፓርላማ 3ኛ መደበኛ ጉባኤ በደቡብ አፍሪካ ሚድራንድ በተጀመረበት ወቅት ኢትዮጵያውያን የፓርላማው አባላት ከግራ ወደ ቀኝ የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በዶ፣ የተከበሩ አሽኔ አስቴ የተከበሩ ወ/ሮ መሰረት አየለ፣ እና የተከበሩ ዶ.ር. አወቀ ሀምዛዬ።

በአሁኑ ተቋማዊ ቅርፁ የፓን አፍሪካን ፓርላማ በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ምርመራ የሚያደርግ፣ የሚወያይ፣ የውሳኔ ሐሳቦችን የሚያቀርብ እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ድጋፍ የሚሰጥ አማካሪ አካል ነው። በዋናነትም የመጀመሪያው የሥራ ዘመን ፓርላማው ሙሉ በሙሉ ሥራውን ለማከናወን የሚያስችሉትን የአሠራር ሂደቶች እና አሥተዳደራዊ መዋቅሮችን ይዘረጋል ተብሎ የሚጠበቅበት ወቅት ነው። በዚኽ ረገድ ፓርላማው የተቋሙን ባህሪ እና አወቃቀር በዝርዝር የሚያብራራውን የአሠራር ደንብ በ2004 አጽድቋል። በተጨማሪም ፓርላማው እስከ መጀመሪያው የሥራ ዘመን ማብቂያ ድረስ የሚያከናውናቸውን ተግባራት የሚመራ የድርጊት መርሃ-ግብር አዘጋጅቶ አጽድቋል። ልክ እንደሌሎች የአፍሪካ ኅብረት አካላት ሁሉ፣ የፓን አፍሪካን ፓርላማ በጀት የሚሸፈነው አባል አገራት ለአፍሪካ ኅብረት በሚያደርጉት መደበኛ መዋጮ ነው። ከአፍሪካ ኅብረት በጀት የሚመደበው ገንዘብ በቂ ባለመሆኑም፣ ፓርላማው ከለጋሽ አካላት የገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ የሚያስችል የትረስት ፈንድም አቋቁሟል። ከዚኽ ባለፈም አባል አገራት በፓርላማው ጉባኤዎች ላይ የሚሳተፉ አባላቶቻቸውን የገንዘብ ወጪ እንዲሸፍኑ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ መወሰኑ ይታወሳል።

የፓርላማው ሥልጣን

የፓን አፍሪካን ፓርላማ ተግባራት እና ሥልጣን የአፍሪካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብን ለማቋቋም ከቀረበው ስምምነት ጋር ተያያዥ በሆነው ስለ ፓን አፍሪካን ፓርላማ በሚደነግገው ፕሮቶኮል አንቀጽ 11 ላይ ተለይተው ተቀምጠዋል። በዚኽም መሠረት ፓርላማው ካሉት ሥልጣናት እና ተግባራት ጥቂቶቹን መጥቀስ፣ ስለ ተቋሙ ምሉዕ ስዕል ለማግኘት ረብ ይኖረዋል። ከእነዚኽም ዋንኞቹ፦
  • በራሱ ተነሳሽነት ወይም በጉባኤው ወይም በሌሎች የፖሊሲ አካላት ጥያቄ መሠረት በማንኛውም ጉዳይ ላይ ምርመራ ማድረግ፣ መወያየት ወይም አስተያየት መስጠት፤ እንዲኹም የሰብዓዊ መብቶች መከበርን፣ የዲሞክራሲያዊ ተቋማት መጠናከርን እና የዲሞክራሲ ባህልን፣ መልካም አሥተዳደርን እና የሕግ የበላይነትን ከማስፈን ጋር በተያያዙ እና በሌሎች መሰል ጉዳዮች ላይ ተገቢ መስሎ የታየውን የውሳኔ ሐሳብ ማቅረብ፤
  • የራሱን በጀት እንዲኹም በአፍሪካ ኅብረት በጀት ዙሪያ መወያየት እና በጀቱም በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከመጽደቁ አስቀድሞ የውሳኔ ሐሳቦችን ማቅረብ፤
  • የአባል አገራትን ሕግጋት ለማጣጣም ወይም ለማስተባበር መሥራት፤ እና፣
  • የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዓላማዎች እንዲሳኩ አስተዋጽዖ የሚያደርጉ የውሳኔ ሐሳቦችን ማቅረብ፤ እንዲኹም በአፍሪካ የውህደት ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን እና የመፍትሔ ስልቶችን መጠቆም የሚሉት ዋንኞቹ ናቸው።
አወቃቀሩን አስመልክቶም፣ የተቋሙ መምስረቻ ሰነዶች እንደሚጠቅሱት፣ የፓን አፍሪካን ፓርላማ ፕሮቶኮልን ያጸደቀ እያንዳንዱ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገር በአምስት የፓርላማ አባላት የመወከል መብት አለው። እነዚኽ አባላት የሚመረጡት ከብሔራዊ ፓርላማዎች ሲሆን፣ በፓን አፍሪካን ፓርላማ ጉባኤዎች ላይ እንዲገኙም ይጠበቃል። ፕሬዝዳንቱ የፓን አፍሪካን ፓርላማ ሰብሳቢ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ የሥራ ዘመን የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ ከፓርላማው አባላት መካከል እንደሚመረጥም ተደንግጓል። የፕሬዝዳንቱ ዋና ተግባር፣ በጉባኤዎች ወቅት የሚደረጉ ውይይቶችን ማመቻቸት፣ የፓርላማው ፖለቲካዊ መሪ ሆኖ ማገልገል እንዲኹም የአህጉራዊውን ፓርላማ የሥራ እንቅስቃሴዎች መቆጣጠር ሲሆን፤ ለዚኽም ፕሬዝዳንቱ ሌሎቹን አራት የአህጉሪቱን ቀጣናዎች በሚወክሉ አራት ምክትል ፕሬዝዳንቶች ይረዳል።

ምርጫው እና ተቋማዊ እንድምታው

በፓን አፍሪካ ፓርላማ ዙሪያ የሚነሱ ክርክሮች፣ በቀደመው ወር በተደረገው ምርጫም መንጸባረቃቸው ተስተውሏል።ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ፣ በቀደመው ወር የተካሄደው ምርጫ፣ ተከስቷል የተባለው ውዝግብ፣ በአፍሪካ ኅብረት ሥርዓት ውስጥ በቁጥጥር ሚና እና በአሥተዳደራዊ ሥልጣን መካከል ያለው ሚዛን እንዴት መጠበቅ እንዳለበት ጥልቅ ጥያቄዎችን አስነስቶ አልፏል። በዚያ ምርጫ ሰፋ ብሎ የተስተዋለው ውዝግብ፣ በሕግ አውጪዎች እና በተንታኞች ዘንድ ሰፋ ካለ ተቋማዊ ዕይታ አኳያ እየታየ ይገኛል፤ ይኽም በአፍሪካ ኅብረት የአሥተዳደር መዋቅር ውስጥ ያሉ መሠረታዊ መዋቅራዊ ጥያቄዎችን የሚጠቁም መሆኑን ይገልጻሉ። ምንም እንኳ የቅርብ ጊዜ ውይይቶች በምርጫው ወቅት እና በሕግ ሰነዶች ትርጓሜ ላይ ያተኮሩ ቢሆኑም፣ አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሉት ግን ውዝግቡ ይበልጥ መሠረታዊ የሆነ ጉዳይን ያንጸባርቃል። ይኸውም በፓን አፍሪካን ፓርላማ የቁጥጥር ሥልጣን እና በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ላይ ባለው አሥተዳደራዊ ጥገኝነት መካከል ያለውን ግንኙነት ነው።

አወዛጋቢው አንቀጽ 11

የፓን አፍሪካን ፓርላማ የተቋቋመው የአፍሪካ ሕዝቦችን እንዲወክል፣ የዲሞክራሲያዊ አሥተዳደር እና ተጠያቂነትን እንዲያሰፍን፣ እንዲኹም በአፍሪካ ኅብረት ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞች እና ተቋማት ላይ የቁጥጥር ሥራ እንዲያከናውን ተብሎ እንደ ኅብረቱ የሕግ አውጪ አካል ተደርጎ መሆኑ ይታወቃል። በንድፈ ሐሳብ ደረጃ፣ ፓርላማው የኅብረቱ ተግባራት፣ በጥንቃቄ እንዲመረመሩ እና ከሰፊው የውህደት እና የአሥተዳደር ግቦች ጋር እንዲጣጣሙ በማድረግ ረገድ ማዕከላዊ ሚና ይጫወታል። ይኹን እንጂ በተግባር ሲታይ፣ የፓርላማው የሕግ አውጪነት ሥልጣን ውስን ሆኖ እንደሚገኝ እና ሥልጣኑም በአብዛኛው በአማካሪነት እና በውሳኔ ሐሳብ አቅራቢነት ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆኑን ታዛቢዎች ያነሳሉ። ፓርላማው በክርክሮች ላይ ቢሳተፍ፣ የውሳኔ ሰነዶችን ቢያጸድቅ እና ምክረ ሐሳቦችን ቢያቀርብም፣ የቁጥጥር ውጤቶችን በተግባር የማስፈጸም አቅሙ አኹን ባለው ተቋማዊ ማዕቀፍ ውስጥ የተገደበ መሆኑም ይነሳል። የፓርላማው ፕሮቶኮል አንቀጽ 11 ላይ ያለው፣ ‘አማካሪ እና የውሳኔ ሐሳብ አቅራቢ’ የሚለው ድንጋጌ የፓርላማውን ሥልጣን ለመገደብ እንደ ምክንያት በተደጋጋሚ ይጠቀሳል። ተቋሙን ያጠኑ በበኩላቸው፣ አንቀጹን በጥልቀት ስንመለከተው ድንጋጌው የበታችነትን የሚያመለክት ሳይሆን፣ ደረጃ በደረጃ የሚከናወን ተቋማዊ የሥልጣን አሰጣጥ ስለመሆኑ ይከራከራሉ። ይኽ አንቀጽ ፓርላማውን በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ወይም በሕግ መዋቅሩ የአሠራር ቁጥጥር ሥር አያደርገውም የሚሉት ተከራካሪዎች፣ ይልቁንም የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ የሕግ አውጪነት ሥልጣን እስኪሰጠው ድረስ ያለውን ጊዜያዊ ተግባራዊ የሥራ ድርሻ ይገልጻል ባዮች ናቸው። እዚኽ ጋር ያለው ወሳኝ ልዩነትም ይኸው ነው፦ አንቀጽ 11 ፓርላማው የሚለማመደውን የሥልጣን ዓይነት ይገድባል እንጂ (ከሕግ አውጪነት ይልቅ አማካሪነት እንዲሆን)፣ ያንን ሥልጣን ወደ ሌላ አካል አያስተላልፍም፤ አልያም እነዚያ የአማካሪነት ተግባራት እንዴት መከናወን እንዳለባቸው የውጭ አካል እንዲመራው ፈቃድ አይሰጥም። በሌላ አነጋገር፣ የሕግ አውጪነት ሥልጣን አለመኖር ማለት አሥተዳደራዊ የበታችነት መኖር ማለት አይደለም የሚለው የተሟጋቾቹ ዋንኛ ነጥብ ነው። ይሁን እንጂ በተግባር ይህ ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዘ መጥቷል። በተለይም በኮሚሽኑ የሕግ አማካሪ ቢሮ በኩል የሚወጡ የሕግ ትርጓሜዎች እና አሥተዳደራዊ መመሪያዎች ላይ ያለው ጥገኝነት እየጨመረ መምጣቱ፣ ያንን ጊዜያዊ የሥልጣን ገደብ ወደ አሥተዳደራዊ ጥገኝነት የመለወጥ ውጤት አምጥቷል። ትንቅንቁም ያለው እዚህ ላይ ነው፦ አንቀጽ 11 እንደ ጊዜያዊ ተግባራዊ ገደብ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን እንደ ቋሚ ተቋማዊ ተዋረድ እየተተገበረ ይገኛል ይላሉ ተከራካሪዎቹ። ይህ ትንቅንቅ ፓርላማው በአፍሪካ ኅብረት መዋቅሮች ውስጥ ባለው የበጀት እና የአሥተዳደር ትስስር ይበልጥ ይጠናከራል። አንቀጽ 11 ፓርላማው በበጀት ላይ እንዲወያይ እና ምክረ ሐሳብ እንዲያቀርብ ቢፈቅድም፣ የመጨረሻው የፋይናንስ ይሁንታ ቁጥጥር ግን ከፓርላማው ውጭ ባለ አካል እጅ ላይ ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ፓርላማው ባለሥልጣናትን እና ሰነዶችን መጠየቅ ቢችልም፣ አስገዳጅ የቁጥጥር ሥልጣን ግን የለውም። እነዚህ መደበኛ ያልሆኑ አሠራሮች ፓርላማው አህጉራዊ ቁጥጥር እንዲያደርግ እና በፖሊሲ ላይ ተፅዕኖ እንዲፈጥር እየተጠበቀ፣ በሌላ በኩል ግን ሊቆጣጠራቸው በሚገቡት መዋቅሮች ላይ ቁሳዊ ጥገኝነት እንዲኖረው የሚያደርግ ሥርዓትን አበጅተዋል። ሆኖም የሕግ ውቅሩ፣ ኮሚሽኑ ሰፊ የሆነ የበላይ ተቆጣጣሪነት ሚና እንዲኖረው አይፈቅድም። በአንቀጽ 11ም ሆነ በሌላ የፕሮቶኮሉ ክፍል ላይ ኮሚሽኑ የፓርላማ ሂደቶችን እንዲመራ፣ ተቋማዊ ውጤቶችን እንዲወስን ወይም የፓርላማውን የሥራ ድርሻ እንዲያግድ ሥልጣን አልተሰጠውም። ይልቁንም ፕሮቶኮሉ ፓርላማው የራሱን የአሠራር ደንቦች እንዲያወጣ እና አመራሩን እንዲመርጥ ሥልጣን በመስጠት፣ በተግባራዊ ገደቦች ውስጥ ሆኖ ተቋማዊ ራስ-ገዝነቱን እንዲጠብቅ ያደርጋል። ስለሆነም በአሁኑ ወቅት የደንቦች መጣጣምን፣ የሥራ ዘመንን ትርጓሜ እና የምርጫ ጊዜያትን በተመለከተ የሚነሱት ክርክሮች ጥልቅ መዋቅራዊ ጥያቄን ያጋልጣሉ፦ አንቀጽ 11 ወደ ሕግ አውጪነት ከፍታ የሚያደርስ ድልድይ ሆኖ እያገለገለ ነው? ወይንስ ተቋሙን መቆጣጠሪያ እና ማገጃ መሣሪያ ሆኗል? በሚል ጠርዝ እና ጠርዝ የቆሙ ምላሾች ባሏቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች የተንጠለጠለ ሆኗል። የኋለኛው፣ ማለትም የመቆጣጠሪያ መሣሪያነቱ የሚቀጥል ከሆነ፣ አደጋው የአሠራር ሥርዓት ብቻ ሳይሆን ሥርዓታዊ ይሆናል። በአማካሪነት ተግባር ብቻ ተወስኖ በውጭ አካል መመሪያ ሥር የሚወድቅ ፓርላማ ተአማኒነቱንም ሆነ ተቋማዊ ማንነቱን የማጣት ሥጋት ይጋርጥበታል፤ ይህም ተቋሙን ከማደግ ላይ ካለ የሕግ አውጪ አካልነት ይልቅ ወደ ተራ የአማካሪነት ቢሮ ዝቅ ያደርገዋል። በተቃራኒው ግን፣ በፕሮቶኮሉ ሰፊ ማዕቀፍ ላይ የተመሠረተ ትክክለኛ የአንቀጽ 11 ንባብ፣ ፓርላማው የራሱ የሆነ ነፃ የአማካሪነት ሥልጣን ኖሮት ቀስ በቀስ ወደ ሙሉ የሕግ አውጪነት ብቃት እንዲሸጋገር ድጋፍ ይሰጣል። በተመሳሳይ ሁኔታ፣ የፓን አፍሪካን ፓርላማ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ጋር በቅርበት የተሳሰረ አሥተዳደራዊ ማዕቀፍ ውስጥ ይንቀሳቀሳል። በተግባር ሲታይ፣ የተቋሙ አሠራር በከፍተኛ ሁኔታ በአፍሪካ ኅብረት መዋቅሮች በኩል በሚጸድቅ የበጀት ድልድል፣ በኮሚሽኑ በሚሰጥ አሥተዳደራዊ ድጋፍ፣ በሕግ አማካሪ ቢሮ በሚወጡ የሕግ ትርጓሜዎች እና በኅብረቱ ዋና መሥሪያ ቤት ላይ የተመሰረቱ ተቋማዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሰረተ ነው። የዚኽ ግንኙነት የፋይናንስ ገጽታ በፓርላማው ፕሮቶኮል አንቀጽ 15 ሥር በግልጽ ተደንግጓል፤ ይህም የፓርላማው ዓመታዊ በጀት የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ በጀት አካል እንዲሆን ያደርጋል። ፓርላማው በኅብረቱ የፋይናንስ ደንቦች መሠረት በጀቱን የማዘጋጀት ኃላፊነት ቢኖረውም፣ የመጨረሻው ይሁንታ ግን፣ በመንግሥታት እና በመሪዎች ጉባኤ እጅ ላይ ነው። እነዚህ አሠራሮች ተዳምረው፣ እንደ አንዳንድ ተንታኞች ምልከታ፣ ፓርላማው በአፍሪካ ኅብረት ተቋማት ላይ የቁጥጥር ሥራ እንዲያከናውን ሥልጣን ቢሰጠውም፣ በተግባር እና በፋይናንስ ረገድ ግን በእነዚሁ ሊቆጣጠራቸው በሚገቡ መዋቅሮች ላይ ጥገኛ ሆኖ ቀጥሏል። ይህም ቁጥጥር እንዲያደርግ የታዘዘው አካል ሊመረምራቸው በሚገቡት ተቋማት በተቀረጸ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲሠራ በማድረጉ፣ በውስጡ የቆየ ተቋማዊ ትንቅንቅ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ከዚህ ዳራ አንጻር፣ ባለፈው ወር የተካሄደው ምርጫ ተኮር ውዝግብ ሰፋ ያለ ትርጉም ይዟል። አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት እንደሚከራከሩት፣ በምርጫው የጊዜ ሰሌዳ፣ በውስጥ ደንብ ክለሳ እና በሕግ አማካሪ ቢሮ ሚና ዙሪያ የታዩት ክስተቶች፣ የውጭ አሥተዳደራዊ እና ሕጋዊ ሂደቶች በፓርላማው የውስጥ አሥተዳደር ላይ እንዴት ተፅዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ የሚያሳዩ መሆናቸውን ታዛቢዎች ያነሳሉ። በተለይም የፓርላማው የአሠራር ደንብ ላይ እየተደረገ ያለው ክለሳ፣ ተቋማዊ አሰላለፍን የማስተካከል ሂደቶች ከፓርላማው ውጭ ያሉ አካላትን እንዴት ሊያሳትፉ እንደሚችሉ ትኩረት የሳበ ሲሆን፣ ይህም የፓርላማው የውስጥ ነፃነት በተግባር እንዴት እየተተገበረ ነው? የሚል ጥያቄ አስነስቷል። እነዚህ ሂደቶች ከፓርላማው ፕሮቶኮል እና ከኅብረቱ ሕጋዊ ሰነዶች ጋር መጣጣምን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች ተደርገው ቢቀርቡም፣ አንዳንድ ሕግ አውጪዎች ግን የፓርላማው የውስጥ አሠራሮች በኅብረቱ ሰፊ አሥተዳደራዊ ማዕቀፍ እየተቀረጹ ነው የሚል አመለካከት እንዲፈጠር ማድረጉን ይገልጻሉ። ይኽ ውይይት ለአፍሪካ ኅብረት መሠረታዊ ቁርጠኝነቶች ዳግም ትኩረት እንዲሰጥም አድርጓል እየተባለ ነው። የአፍሪካ ኅብረት መመሥረቻ ዐዋጅ መግቢያ አባል አገራቱ ካሉባቸው ኃላፊነቶች መካከል፣ ‘የጋራ ተቋሞቻችንን ለማጠናከር እና የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት እንዲወጡ የሚያስችላቸውን አስፈላጊ ሥልጣን እና ሀብት ለማሟላት ሁሉንም አስፈላጊ እርምጃዎችን ለመውሰድ ቆርጠናል” የሚለው ንዑስ አንቀጽ ይነሳል። አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነም፣ አሁን ያለው ክርክር ይህንን ቁርጠኝነት ወደ ተግባር የመለወጥ ቀጣይ ተግዳሮትን የሚያጎላ ነው። የአፍሪካ ኅብረት ተቋማት ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ዕድገት ቢያሳዩም፣ እንደ ፓን አፍሪካን ፓርላማ ያሉ አካላት ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት የሚያስችል አስፈላጊ ሥልጣን፣ ሀብት እና የሥራ ነፃነት ማግኘታቸውን እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል? የሚለው ጥያቄ አሁንም ምላሽ ይሻል ባዮች ናቸው። ለብዙ ታዛቢዎች፣ በፓርላማው የቢሮ ምርጫ ውዝግብ ሳቢያ የተነሱት ጉዳዮች ከአመራር ሽግግር ጥያቄ ባለፈ ጥልቅ ትርጉም አላቸው። ይልቁንም በአፍሪካ ኅብረት ሥርዓት ውስጥ ያለውን ሰፋ ያለ የአስተዳደር ጥያቄ ይጠቁማሉ፥፡ ኅብረቱ በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን በኩል ያለውን አሥተዳደራዊ ቅንጅት እና እንደ ፓን አፍሪካን ፓርላማ ያሉ ተቋማት ሊኖራቸው የሚገባውን ነፃነት እንዴት ማመጣጠን አለበት? የሚለው ስለመሆኑም ይደመጣል። ይህ ጥያቄ ለአሁኑ ወቅት ብቻ የሚነሳ ሳይሆን፣ የአፍሪካ ኅብረት ተቋማት ይበልጥ ውስብስብ እየሆነ በመጣው የአሥተዳደር መዋቅር ውስጥ የየራሳቸውን ሚና እና ግንኙነት ለመለየት በሚያደርጉት ቀጣይ የዕድገት ሂደት ውስጥ የሚንጸባረቅ ነው። ዲፕሎማቶች፣ የሕግ ባለሙያዎች እና የተቋማዊ አሥተዳደር ተንታኞች እንደሚገልጹት፣ ይኽ ሚዛን እንዴት ይጠበቃል የሚለው ጉዳይ ለፓን አፍሪካን ፓርላማ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ የአፍሪካ ኅብረት አሠራር ትልቅ አንድምታ ይኖረዋል። ውጤታማ ቁጥጥር እንዲኖር ተቋማት የመመርመር ሥልጣን እና በገለልተኝነት የመሥራት አቅም ሊኖራቸው ይገባል፤ በተመሳሳይ ጊዜም በኅብረቱ አጠቃላይ አስተዳደራዊ ማዕቀፍ ውስጥ ቅንጅታቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል የሚሉ ታዛቢዎች በዛ ያሉ ናቸው።

የማላቦ ጥሪ

አገራችንን ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ ከሠለሳ የማያንሱ የአፍሪካ አገራት ሊያጸድቁት ያልሻቱት ይኽ የማላቦ ፕሮቶኮል ግን ምንድን ነው? ምንስ አይደለም? እነ ኢትዮጵያስ ሰነዱን እንዳይፈርሙት እጃቸውን ምን ያዛቸው? የሚሉትን ጥያቄዎች አጠር አድርጎ መመልከት፣ ተቋሙን አስመልክቶ የሚነሱ ክርክሮችን ለመረዳት በቂ ዕይታ ይሰጥ ይመስለናል። በሰኔ 2014 የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ የማላቦ ፕሮቶኮል በመባል የሚታወቀውን እና የፓን አፍሪካን ፓርላማን ለማቋቋም በ2001 የወጣውን መመሥረቻ ሰነድ የሚያሻሽለውን ፕሮቶኮል አጽድቋል። በ2001ዱ ፕሮቶኮል አንቀጽ 25 መሠረት፣ የፓርላማው ዓላማ እና ርዕይ ከአህጉሪቱ ተለዋዋጭ ፍላጎቶች ጋር መጣጣሙን ለማረጋገጥ በየአምስት እና በየዐሥር ዓመቱ ተቋማዊ ክለሳ እንዲደረግ ቢታቀድም፣ የማላቦ ፕሮቶኮል ግን በቂ የአባል አገራት ይሁንታ ባለማግኘቱ ተግባራዊነቱ ዘግይቷል። ሰነዱ በይፋ ሥራ ላይ እንዲውል ከሚያስፈልጉት 28 አገራት መካከል፣ እስከ አኹን የማጽደቂያ ሰነዳቸውን ያስገቡት 15 አገራት ብቻ በመሆናቸው፣ ስለ አባልነት መስፈርት፣ ስለ ሥልጣን ገደብ እና ስለ ሌሎች ተቋማዊ ግንኙነቶች የተካተቱት አዳዲስ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ሊሆኑ አልቻሉም። እንደ ፕሮቶኮሉ ድንጋጌ፣ እያንዳንዱ አባል አገር አምስት ተወካዮችን ወደ ፓርላማው የሚልክ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ቢያንስ ኹለቱ ሴቶች መሆን አለባቸው፤ ይኽ የጾታ ተዋጽዖ ካልተጠበቀ ልዑኩ ዕውቅና የማግኘት መብት አይኖረውም። ተወካዮቹ በየአገራቱ ብሔራዊ ፓርላማ የሚመረጡ ቢሆንም፣ ተመራጮቹ ግን በወቅቱ የብሔራዊ ፓርላማው አባል መሆን የሌለባቸው እና አባል ከሆኑም መልቀቅ ያለባቸው ሲሆን፤ በምርጫ ወቅትም በብሔራዊ ፓርላማው ውስጥ ያለውን የፖለቲካ አመለካከት ብዝኃነት ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ ይኸው ያልቀደቀው የማላቦ ፕሮቶኮል ያዛል። የአባላት የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ሆኖ ለአንድ ተጨማሪ ጊዜ ብቻ እንዲመረጡ የሚፈቅደው ይኽ ሰነድ፣ የፓርላማውን አመራር ስብጥርም አንድ ፕሬዝዳንት እና አራት ምክትል ፕሬዝዳንቶችን በመያዝ አምስቱንም የአፍሪካ ቀጣናዎች እና የጾታ እኩልነትን ባማከለ መልኩ ለኹለት ዓመት ተኩል የሥራ ዘመን ይወስናል። በሥልጣን ረገድ ፕሮቶኮሉ ፓርላማው በአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ፈቃድ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ አስገዳጅነት የሌላቸው ሞዴል ሕግጋትን እንዲያረቅ ሥልጣን የሚሰጥ ሲሆን፤ ከዚህ ባለፈም ተቋሙ የኅብረቱን በጀት የመወያየት፣ የሐቅ ፍለጋ እና የታዛቢነት ተልዕኮዎችን የማከናወን፣ እንዲኹም የሌሎች የአፍሪካ ኅብረት አካላትን ሪፖርቶች የመመርመር ኃላፊነት እንዲኖረው ደንግጓል። ለአባላቱ የሚከፈለውን ክፍያ እና አበል የመሸፈን ኃላፊነት የየአባል አገራቱ መሆኑን የጠቀሰው ይኽ ፕሮቶኮል፣ ፓርላማው በዓመት ቢያንስ ኹለት ጊዜ መደበኛ ስብሰባውን እንዲያካሂድም ያዛል። በአጠቃላይ የማላቦ ፕሮቶኮል የአባል አገራትን ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ አህጉራዊ ትብብርን ለማሳለጥ የታለመ አማካሪ እና ተባባሪ የሕግ አውጪ ማዕቀፍ ሲሆን፣ ይህም አፍሪካውያን የጋራ ተግዳሮቶቻቸውን በጋራ ለመፍታት ያላቸውን ምኞት የሚያንጸባርቅ ስለመሆኑም፣ ሰንዱን በቅጡ የመረመሩ ተንታኞች ይከራከራሉ። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት አባል እና የፓን አፍሪካን ፓርላማ ተሳታፊ ብትሆንም፣ የማላቦ ፕሮቶኮልን እስከ አሁን አላጸደቀችም። ለዚህ ማንገራገር ዋንኛው ምክንያት ከብሔራዊ ሉዓላዊነት ጋር የተያያዙ ስጋቶች ሲሆኑ፣ ይኽም ፕሮቶኮሉ የፓን አፍሪካን ፓርላማን በአብዛኛው አማካሪ ከሆነ አካልነት ወደ ሕግ አውጪነት በመለወጥ የብሔራዊ ተቋማትን ሥልጣን ሊገድብ ይችላል ከሚል ስጋት የሚመነጭ ነው። በተጨማሪም፣ ፕሮቶኮሉ ከአገር ውስጥ ሕገ-መንግሥታዊ ማዕቀፎች ጋር እንዴት እንደሚጣጣም እንዲሁም ድንጋጌዎቹ በተግባር እንዴት ተፈጻሚ እንደሚሆኑ እና እንደሚከበሩ የሚነሱ ሕጋዊ እና ተቋማዊ ጥርጣሬዎችም አሉ። የኢትዮጵያ አቋም ሰፊውን አህጉራዊ ዝንባሌ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፣ ብዙ የአፍሪካ አገራትም ተመሳሳይ በሆኑ ፖለቲካዊ እና መዋቅራዊ ስጋቶች ምክንያት ፕሮቶኮሉን ለማጽደቅ መዘግየታቸው ይነሳል። የማላቦ ፕሮቶኮል ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ ለፓን አፍሪካን ፓርላማ የተገደበ የሕግ አውጪነት ሥልጣን መስጠት በአንዳንድ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት ዘንድ የብሔራዊ ሉዓላዊነትን የማጣት ሥጋት ሲፈጥር ቆይቷል። ይህ ስጋት ፕሮቶኮሉ ከዐሥር ዓመታት በላይ ተግባራዊ እንዲሆን የሚፈለገው የአገራትን ይሁንታ እንዳያገኝ ካደረጉት ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ ነው። ምንም እንኳን ብዙዎቹ አገራት ስለዚህ ጉዳይ በይፋ ባይናገሩም፣ ሉዓላዊነትን አሳልፎ ስለመስጠት ያላቸው ስጋት አልፎ አልፎ ይገለጻል፤ ለምሳሌ በኡጋንዳ ፓርላማ ውስጥ በተደረገ ክርክር የኡጋንዳ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፕሮቶኮሉን ለማጽደቅ የዘገዩት ፓርላማው ሕግ እንዲያወጣ ሥልጣን የሚሰጥ ሰነድ ላይ በከፍተኛ ጥንቃቄ መፈረም ስለሚገባ መሆኑን ገልጸው፣ የፓርላማው ሕግጋት ከብሔራዊ ሕግጋት ጋር ያላቸው ደረጃ በጥንቃቄ ሊታይ እንደሚገባ እና ሉዓላዊነትን አሳልፎ ከመስጠት በፊት በቂ ዝግጅት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ይህ ስሜት ሌሎች አባል አገራትም አህጉራዊ ፓርላማን ሥልጣን ከመስጠት ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ስጋት ሊኖራቸው እንደሚችል ለመገመት ያስችላል። ይሁን እንጂ የፕሮቶኮሉን ድንጋጌዎች በተለይም አንቀጽ 8.1 (ሀ) እና (ለ)ን በጥልቀት ስንመለከት፣ እነዚህ ስጋቶች መሠረት የሌላቸው መሆናቸውን መረዳት ይቻላል። የማላቦ ፕሮቶኮል ሉዓላዊነትን ከማዳከም ይልቅ የፓን አፍሪካን ፓርላማን እያጠናከረ የአባል አገራትን ነፃነት የሚያስጠብቅ ሚዛናዊ ማዕቀፍ ይዘረጋል። በአንቀጽ 8.1 (ሀ) መሠረት የፓን አፍሪካን ፓርላማ ሞዴል ሕጎችን ሊያረቅባቸው የሚችሉ የጉዳይ ዘርፎችን የሚወስነው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ሲሆን፤ በአንቀጽ 8.1 (ለ) መሠረት ደግሞ ፓርላማው በራሱ ተነሳሽነት የሕግ ሐሳቦችን ማመንጨት ቢችልም፣ ወደ ተግባር ከመግባቱ በፊት የግድ የኅብረቱን ጉባኤ ይሁንታ ማግኘት ይኖርበታል። ይኽ መዋቅር የሕግ አውጪነት ጅምርም ሆነ አቅጣጫው ሙሉ በሙሉ በአባል አገራት እጅ እንዲቆይ የሚያደርግ ባለ ሁለት ደረጃ የቁጥጥር ሥርዓትንም ይፈጥራል። ከዚህም በተጨማሪ ፓርላማው እንዲያረቅ ሥልጣን የተሰጠው አስገዳጅነት የሌላቸውን ሞዴል ሕጎችን ብቻ ነው። እነዚህ ሕግጋት በአህጉሪቱ ሕጎችን ለማጣጣም እንደ ናሙና የሚያገለግሉ እንጂ በየትኛውም አገር ላይ በቀጥታ ተፈጻሚነት አይኖራቸውም። ማንኛውም ሞዴል ሕግ በብሔራዊ ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆን የየአገራቱ የውስጥ የሕግ አውጪነት ሂደት ውስጥ ማለፍ ያለበት ሲሆን፣ ብሔራዊ ፓርላማዎችም ሐሳቡን የመቀበል፣ የመቀየር ወይም ሙሉ በሙሉ የመቃወም ሙሉ ሥልጣን አላቸው። ይህ አሠራር ሉዓላዊነትን ከመጋፋት ይልቅ የብሔራዊ ፓርላማዎችን ነፃነት ባከበረ መልኩ የሕግ ትብብርን ለማጠናከር የታለመ ስለመሆኑ የሚከራከሩ ታዛቢዎች ቁጥራቸው በዛ ያለ ነው። ሌላው ፕሮቶኮሉን ለማጽደቅ እንቅፋት ሆኖ የቆየው የተሳሳተ ግንዛቤ ፓርላማው በአህጉሪቱ ላይ አስገዳጅ ሕግጋትን የሚያወጣ ቋሚ ተቋም ሆኖ ይለወጣል የሚለው ነው። ይሁን እንጂ የማላቦ ፕሮቶኮል አንቀጽ 15.2 በግልጽ እንደሚደነግገው፣ ፓርላማው በመደበኛነት በዓመት ኹለት ጊዜ ብቻ የሚሰበሰብ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ስብሰባም ቢበዛ እስከ አንድ ወር ብቻ የሚቆይ እንዲሆን ተጠቅሷል። ይኽ ድንጋጌ ተቋሙ ቋሚ እና የበላይ የሕግ አውጪ አካል ሳይሆን፣ እንደ አስፈላጊነቱ በየክፍለ ጊዜው የሚሰበሰብ ደጋፊ ተቋም መሆኑን ያረጋግጣል። በመሆኑም የማላቦ ፕሮቶኮል ሉዓላዊነትን እንደ ስጋት ከመቁጠር ይልቅ፣ እንደ ንግድ፣ ሰብዓዊ መብቶች እና የሕዝብ ጤና ባሉ ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ላይ የሕግ ማዕቀፎችን ለማስተሳሰር የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ፈጠራ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባዋል የሚለው መከራከሪያ የተሻለ ውኃ ይቋጥራል። በአጠቃላይ አንቀጽ 8.1 እና 15.2 ፓርላማው በአባል አገራት የተቀመጠለትን ወሰን ተከትሎ እንደሚሠራ ስለሚያረጋግጡ፣ እንደ ናይጄሪያ፣ ግብፅ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ አገራት ፕሮቶኮሉን በአዲስ ዕይታ ቢመለከቱት እና ቢያጸድቁት፣ የተቋሙ አህጉራዊ ፋይዳ ብዙ ነው።

ፓን አፍሪካኒስቶቹ ከአውሮፓው ፓርላማ የሚማሩት አለ ይሆን?

በዚኹ አጀንዳ ባደረግነው የፓን አፍሪካው ፓርላማ ዙሪያ ከሚደረጉ ክርክሮች መካከል ምናልባትም ዋንኛው የሐሳብ ሙግት፣ ፓርላማው ከአውሮፓ ኅብረቱ ፓርላማ ሊወስዳቸው የሚገቡ ቁም ነገሮች አሉ በሚለው ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ይሽከረከራል። ለመሆኑ ፓን አፍሪካኒስቶቹ ከአውሮውያኑ የሚቀስሙት ትምህርት አለን? የአውሮፓ ፓርላማ የፓን አፍሪካን ፓርላማ ትምህርት ሊቀስምበት እና እንደ አርአያ ሊከተለው የሚችለው እጅግ የላቀ የአህጉራዊ የሕግ አውጪ አካል ምሳሌ ነው። በመሆኑም፣ የፓን አፍሪካን ፓርላማን ወደ ሕግ አውጪነት ለመለወጥ የሚቀርበው ሐሳብ በሚታይበት ወቅት፣ የአውሮፓ ፓርላማን ዕድገት እና አሁን ላለበት ደረጃ ያበቁትን ወሳኝ እርምጃዎች መመርመር እጅግ አስፈላጊ ነው። በዚኽ መንገድ የአውሮፓ ፓርላማ ከነበረው አነስተኛ የአማካሪነት ሥልጣን በመውጣት፣ በብዙ ዘርፎች (ከውጭ ጉዳይ በስተቀር) ከፍተኛ የሕግ አውጪነት ሥልጣን ወደ መያዝ ተሸጋግሯል፤ እንዲኹም በአውሮፓ ኅብረት የአሥተዳደር መዋቅር ውስጥ ያለው አስፈላጊነት እና ተገቢነት በሂደት እያደገ መጥቷል። ከዚኽ ዕድገት የሚቀሰሙ በርካታ ንጽጽራዊ ትምህርቶች ያሉ ሲሆን፣ ማንኛውም የፓን አፍሪካን ፓርላማ ግምገማ ወይም ሽግግር እነዚኽን ነጥቦች ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል የሚለው ምሁራዊ ድምጽ ጎልቶ ይሰማል። በመጀመሪያ፣ የፓን አፍሪካን ፓርላማ ገና በፅንስ ደረጃ ላይ የሚገኝ ተቋም መሆኑን ልብ ማለት ያሻል። የአውሮፓ ፓርላማ ማንኛውንም ጉልህ ተጨማሪ ሥልጣን ለማግኘት በግምት 29 ዓመታት (እስከ 1987 ድረስ) ፈጅቶበታል። ስለሆነም፣ የፓን አፍሪካን ፓርላማ የሕግ አውጪነት ሥልጣን ለመያዝ ያለውን ዝግጁነት ለማሳየት ገና ብዙ ሥራዎች የሚቀሩት ቢሆንም፣ በዚኽ አጭር ጊዜያት ወደ ሙሉ ሕግ አውጪነት እንዲቀየር መጠበቅ ምን ያህል ተጨባጭ እና ተግባራዊ ሊሆን ይችላል? የሚለው ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። የአውሮፓ ፓርላማ በተመሰረተበት እና የሕግ አውጪነት ሥልጣን ባገኘበት ጊዜ መካከል በነበሩት ዓመታት ትኩረት አድርጎ የነበረው ተቋማዊ አቅሙን በመገንባት እና ሚናውን በማጠናከር ላይ እንደነበር መከራከር ይቻላል። በኹለተኛ ደረጃ፣ የአውሮፓ ፓርላማ ከአማካሪነት ወደ ሕግ አውጪነት ያደረገው ሽግግር ከ1958 ጀምሮ በሂደት የተከናወነ ነበር። ተቋሙ ሲመሰረት ከነበረው የአማካሪነት ሚና ብቻ ተነስቶ እኩል የሕግ አውጪነት ሥልጣን እስከያዘበት ድረስ ያለውን ሂደት ያካትታል። የአውሮፓ ፓርላማ አባላት በቀጥታ እንዲመረጡ 21 ዓመታት፣ ሙሉ የሕግ አውጪ አካል ሆኖ ግቡ ላይ ለመድረስ ደግሞ 41 ዓመታት ወስዶበታል። ታዲያ የፓን አፍሪካን ፓርላማ የሽግግር ሂደትም ሥልጣን በደረጃ የሚሰጥበትን እንዲህ ያለውን መሰል ቀስ በቀስ የሚሄድ ጉዞ መከተል ይኖርበታል ወይስ የለበትም? የሚለው ጥያቄ ተቋሙን አስመልክቶ በሚጻፉ ጹሑፎች በመለስ ቀለስ ሲነሳ ይስተዋላል። በሦሥተኛ ደረጃ፣ የአውሮፓ ፓርላማ ዕድገት የተከናወነው ለብቻው በባዶ ቦታ ላይ ሳይሆን፣ አጠቃላይ የአውሮፓ ማኅበረሰብ ሲያደርግ ከነበረው ሰፊ ዕድገት ጋር ተያይዞ ነበር፤ ይኽ ማኅበረሰብም ነበር፣ በ1993 በማስትሪችት ስምምነት አማካኝነት ወደ አውሮፓ ኅብረትነት የተለወጠው። የማስትሪችት ስምምነት፣ በአውሮፓ ኅብረት ተቋማዊ መዋቅሮች ላይ ከፍተኛ ለውጦችን አምጥቷል። የአውሮፓ ፓርላማን ሥልጣን ከሌሎች የአሥተዳደር ተቋማት አንጻር ከፍ ያደረጉት ለውጦች፣ የሌሎች ተቋማትን (በተለይም የኮሚሽኑን እና የምክር ቤቱን) መዋቅራዊ ለውጦችም ያካተቱ ነበሩ። በዚኽ ረገድ፣ የፓን አፍሪካን ፓርላማ ፕሮቶኮልን ጨምሮ በፓርላማው ሕጋዊ ማዕቀፍ ላይ የሚደረጉ ማናቸውም መሠረታዊ ለውጦች፣ በሌሎች የአፍሪካ ኅብረት የአሥተዳደር ተቋማት መዋቅር እና ከፓርላማው ጋር ባላቸው ትስስር ላይ መሰል ለውጦችን ማስከተላቸው አይቀሬ መሆኑን መገመት ይቻላል። ይኽም ለውጦቹን ለማንጸባረቅ እና የሌሎች አካላትን ለፓርላማው ያላቸውን ተጠያቂነት በይፋ ለማስፈር፣ እንደ መሥራች ሰነድ የሚያገለግለው የአፍሪካ ኅብረት መመሥረቻ ዐዋጅ እንዲሻሻል ሊያስገድድ ይችላል። በአሁኑ ወቅት በፓን አፍሪካን ፓርላማ እና በሌሎች የአፍሪካ ኅብረት አካላት መካከል ያሉት ትስስሮች የሚመሩት በእነዚያ ተቋማት የየራሳቸው ፕሮቶኮሎች አማካኝነት በተናጠል ነው። ተንታኞቹ እንደሚያነሱት፣ ከዚኽ አኳያ፣ ፓን አፍሪካን ፓርላማ ከአውሮፓ ፓርላማ ሊቀስመው የማይችለው አንድ ትልቅ ትምህርት አለ፤ ይኸውም በአፍሪካ ኅብረት እና በአውሮፓ ኅብረት መካከል ካለው ታላቅ ልዩነት ጋር የተያያዘ ነው። የአውሮፓ ኅብረት የውህደት ሂደት ጥቂት አገራትን መሠረት አድርጎ በመጀመር ሌሎች አገራት እንዲቀላቀሉ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ከታች ወደ ላይ የተከናወነ ሲሆን፣ የአፍሪካ ኅብረት የውህደት ሂደት ግን በተቃራኒው ከላይ ወደ ታች የሚመራ ነው። ኹሉም የአፍሪካ አገራት በአህጉሪቱ ውስጥ በመገኘታቸው ብቻ፣ ማለትም ያሉበት ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ እና የልማት ኹኔታ ግምት ውስጥ ሳይገባ የአፍሪካ ኅብረት አባል ተደርገው ታውጀዋል። የአውሮፓ ኅብረት እንደ ማኅበረሰብ ጀምሮ ቀስ በቀስ ከብሔራዊ ሕግጋት በላይ ሥልጣን ወዳለው ኅብረት ሲያድግ፣ የአፍሪካ ኅብረት ግን የጀመረው እንደ ኅብረት ሆኖ አሁን ላይ የጋራ እሴቶች እና ተቋማት ያሉት ማኅበረሰብ የመፍጠር ሂደት ላይ ይገኛል። ስለ ኅብረቱ መንግሥታት በሚያደረጉት ትኩስ ክርክሮች ውስጥ የአፍሪካ ኅብረት ምላሽ ሊሰጥበት የሚገባው እጅግ አስፈላጊው ጉዳይ፣ አባል አገራት የሉዓላዊነታቸውን ወሳኝ ገጽታዎች ለአፍሪካ ኅብረት አሳልፈው ለመስጠት ምን ያህል ፈቃደኛ እና ዝግጁ ናቸው የሚለው ነው። ስለምን ቢሉ፣ ለዚኽ ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ ፓን አፍሪካን ፓርላማን ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን እና የአፍሪካ የፍትሕ ፍርድ ቤት ያሉ ተቋማት ጭምር በሚኖራቸው ባህርይ እና ሥልጣን ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋልና። በመጨረሻ ነጥብነትም፣ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ በአሁኑ ወቅት በፓን አፍሪካን ፓርላማ ሂደቶች እና በአፍሪካ ኅብረት ደረጃ በሚከናወኑ ሂደቶች መካከል የሚያገናኝ ምንም ዓይነት መደበኛ ተቋማዊ አሠራር የለም። ከፓን አፍሪካን ፓርላማ የሚወጡ ውሳኔዎች ወይም ምክረ-ሐሳቦች እንደ ኮሚሽኑ፣ የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ እና የሰላም እና ደኅንነት ምክር ቤት ወደመሳሰሉ የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ የሥልጣን አካላት መድረሳቸውን የሚያረጋግጥ የክትትል ሥርዓት የለም። ምንም እንኳ ፓርላማው እንደ አንዱ የአፍሪካ ኅብረት የሕግ አውጪ አካል ተደርጎ ቢቆጠርም፣ አሁን ያለው የአማካሪነት እና የውሳኔ ሐሳብ አቅራቢነት ሚና በሌሎች የአፍሪካ ኅብረት አካላት በሚተላለፉ ውሳኔዎች ወይም ፖሊሲዎች ላይ የሚኖረው ፋይዳ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ያም ሆኖ፣ የፓን አፍሪካን ፓርላማ ዋነኛ ትኩረት፣ በተለይም ከሽግግር ጉዳይ ጋር በተያያዘ፣ የሕግ አውጪነት ሥልጣን ማግኘት ላይ ብቻ ያነጣጠረ ይመስላል። በፓርላማው ውስጥ በሚደረጉ ውይይቶች ተቋማዊ አቅምን እንዴት ማጠናከር ይቻላል ወይም የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች እንዴት መፍታት ይቻላል በሚሉት ነጥቦች ላይ ያለው ትኩረት በጣም አነስተኛ መሆኑ ይነሳል። ከዚኽ አንጻርም፣ ፓርላማው ከአውሮፓ የስም አቻው ጋር ትዩዩ ተቋማዊ አቅም እንዲኖረው፣ እኒኽን መሰሎቹን ውስጣዊ ክርክሮች በስፋት ከማድረግ ባለፈ፣ እኒኽን ፋይዳ ያላቸውን ነጥቦች፣ ልክ አንደ አውሮፓ ኅብርቱ ፓርላማ ሁሉ ወደ አህጉሪቱ መንግሥታት እና የኅብረቱ ሥራ አሥፈጻሚ በመውሰድ፣ የሚሻውን የሥልጣን አውጪነት ግብ ከማሳካት አኳያ ትምህርት ሊወስድ ይቻለዋል።

የብሪጅ ምክረሐሳቦች

የቀደመውን አጠር ያለ ዳሰሳዊ ሃተታ በመንተራስ፣ ተቋማችን ብሪጅ ቀጣዮቹን ምክረ-ሐሳቦች ታቀርባለች፤

ሀ፦ የማላቦ ጉዳይ፤

የማላቦ ፕሮቶኮልን ማጽደቅ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ በአህጉራዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባታ ላይ ያላቸውን መሪነት በተግባር የሚያረጋግጡበት ወሳኝ እርምጃ መሆኑን አስቀድመን መጥቀስ እንሻለን። እነዚኽ አገራት ፕሮቶኮሉን በመፈረም የፓን አፍሪካ ፓርላማ ከምክረ-ሐሳብ ሰጪነት ወጥቶ ሕግጋትን የማውጣት እና የአፍሪካ ኅብረት አሥፈጻሚ አካላትን የመቆጣጠር ሥልጣን እንዲኖረው በማድረግ የአህጉሪቱን የፖለቲካ ተጠያቂነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግሩታል። ይኽም እንደ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ያሉ ጅምር ላይ ያሉ ግዙፍ አህጉራዊ ፕሮጀክቶች ወጥ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው ከመርዳቱም በላይ፣ የአፍሪካን ሕዝቦች ድምፅ በቀጥታ የሚወክል ጠንካራ ተቋም በመፍጠር የዜጎችን በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ የመወሰን መብት የማክበር ዕድልን ከፍ ያደርጋል። በመሆኑም እነዚኽ የአህጉሪቱ ኃያላን ፕሮቶኮሉን ማጽደቃቸው ለሌሎች አባል አገራት አርአያ በመሆን ለሽግግሩ የሚያስፈልገውን 28 የፊርማ ድርሻ ለማሟላት እና የአፍሪካን አንድነት ከቃላት ባለፈ በተቋማዊ መዋቅር ለማጽናት ዋነኛው መፍትሔ ነው እንላለን።

ለ፦ ተቋማዊ ብቃትን እና የሰው ኃይልን ስለማጠናከር፤

የፓን አፍሪካን ፓርላማ ወደ ሙሉ የሕግ አውጪነት አካልነት ለመሸጋገር በቅድሚያ በውጭ አማካሪዎች እና በለጋሾች ላይ ያለውን ጥገኝነት መቀነስ ይኖርበታል። ይኽንን ለማሳካትም የራሱን ገለልተኛ የምርምር እና የቴክኒክ ድጋፍ ክፍል በማደራጀት፣ የኮሚቴ ጸሐፊዎችን እና የፖሊሲ ተንታኞችን አቅም የሚያሳድጉ ሥልጠናዎችን መተግበር ይኖርበታል። ተቋሙ በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ሚዛናዊ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ የፖሊሲ አማራጮችን ማመንጨት የሚችለው፣ የራሱ የሆነ የሠለጠነ የሰው ኃይል እና ዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ መሠረተ-ልማት ሲኖረው ብቻ ነውና፣ ይኽን ጉዳይ የፓን አፍሪካው ፓርላማ አዲሶቹ አመራሮች ዋል አደር ሳይሉ ቢያስቡበት ስንል እንምከራለን።

ሐ፦ የፋይናንስ ነፃነትን እና የበጀት ሉዓላዊነትን ስለማረጋገጥ፤

ሌላው ወሳኝ ጉዳይ የፓርላማው የበጀት ነፃነት መሆኑን ቀደም ያሉት ዳሰሳዊ ነጥቦች ግልጽ ያደረጉ ይመስለናል። ከዚኽ አኳያም፣ ተቋሙ ከአፍሪካ ኅብረት አሥፈጻሚ አካል ቀጥተኛ ቁጥጥር በመውጣት፣ በራሱ ውስጣዊ ግምገማ ላይ በመመስረት የራሱን በጀት የሚያቅድበት እና የሚያሥተዳድርበት የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልገዋል። ይኽን እንዳያደረግ የሚይዙትን የአሰራር ገደቦች በማሻሻል እና አባል አገራት ቋሚ መዋጮ እንዲያደርጉ በማበረታታት፣ ፓርላማው የራሱን አጀንዳዎች በገለልተኝነት ለማስፈጸም የሚያስችለው አስተማማኝ የገቢ ምንጭ መፍጠር፣ የማላቦ ዲክላሬሽንን ተከትሎ ተስፋ የተደረገበትን ተቋማዊ ሽግግር ለማድረግ እጅግ አስፈላጊው ሂደት መሆኑን ተቋማችን ማስገንዘብ ትሻለች።

መ፦ ፖለቲካዊ መሻትን እና ተዓማኒነትን ስለመገንባት፤

የአፍሪካ መሪዎች በተቋሙ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ለመቅረፍ፣ ፓርላማው ለአህጉራዊ አንድነት እና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ተጨባጭ ፋይዳ በተግባር ማሳየት አለበትም እንላለን። ከቀጠናዊ ፓርላማዎች ጋር ያለውን ትብብር በማጠናከር ኣና በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ የአህጉሪቱን ሕዝብ ድምፅ በማስተጋባት፣ ተቋሙ አስፈላጊነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል። ይኽ ዓይነቱ የተግባር ውጤት መሪዎቹ የፖለቲካ ፍላጎት በማሳደግ፣ የማላቦው ጥሪ ተስፋ እንዳደረገው፣ ፓርላማው ከፍተኛ የሕግ አውጪነት ሥልጣን እንዲኖረው ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ዕድሉ ብዙ ነውና።

ሠ፦ የኢትዮጵያ እንደራሴዎችስ?

በዚኽ ዳሰሳ መግቢያ ላይ እንዳነሳነው፣ የተከበሩ ዶ.ር. አሸብር የፓን አፍሪካ ፓርላማ ምክትል ፕሬዝደንት መሆናቸው አንዱ የዚኽ ዳሰሳ መግፍኤ ሆኗል። ከዶ.ር. አሸብር በተጨማሪ ሌሎቹ አራቱ እንደራሴዎች፣ የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በዶ፣ የተከበሩ ወ/ሮ መሰረት አየለ፣ የተከበሩ ዶ.ር. አወቀ ሀምዛዬ እና የተከበሩ አሽኔ አስቴ ናቸው። ከዚኽ አንጻርም፣ ብሪጅ፣ እኒኹን ኹለት ምክረ-ሐሳቦች ማቅረብ ትሻለች፤
  • ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካ ፓርላማ ውስጥ የሚወክሏት አባላት በአህጉራዊ መድረኮች ላይ ንቁ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ተሳትፎ እንዲኖራቸው፣ ምክር ቤቱ ልዩ የሙያ እና የምርምር ድጋፍ ቡድን ሊያቋቁምላቸው ይገባል እንላለን። ይኽም ተወካዮቹ በአህጉራዊ የሕግ ረቂቆች፣ በሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች እንዲኹም በምጣኔ ሀብታዊ ውህደት አጀንዳዎች ላይ የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ያስከበረ እና አህጉራዊ አንድነትን ያጠናከረ ሙያዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ያስችላቸዋል። (ተቋማችን ብሪጅ፣ እነዚኽን የኢትዮጵያ የፓን አፍሪካ ተወካዮችን በጥናት እና በምርምር ለመደገፍ ያላትን ሙሉ ፍቃደኝነት በዚኹ አጋጣሚ መግለጽ ትወዳለች።)
  • በፓን አፍሪካ ፓርላማ ውስጥ የሚሳተፉ የኢትዮጵያ ተወካዮች፣ በአህጉራዊ መድረክ ስላከናወኗቸው ተግባራት እና ስለተላለፉ ውሳኔዎች ለኢትዮጵያ እንደራሴዎች ምክር ቤት መደበኛ ሪፖርት የሚያቀርቡበት ግልጽ አሠራር ሊዘረጋ ይገባል። ይኽ አሠራርም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአህጉራዊ ደረጃ የሚወከሉበትን መንገድ እንዲያውቅ ከማድረጉም ባለፈ፣ በኹለቱ ተቋማት መካከል ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር ያደርጋል። በዚኽም ምክር ቤቱ በአህጉራዊ ደረጃ የሚነሱ ስጋቶችን እና ዕድሎችን ቀድሞ በመረዳት፣ ለአገር ውስጥ ፖሊሲዎች እንደ ግብዓት እንዲጠቀምባቸው ይረዳዋል።
  • የኢትዮጵያ እንደራሴዎች ምክር ቤት፣ የፓን አፍሪካ ፓርላማን መድረክ በመጠቀም በምሥራቅ አፍሪካ እና በአጠቃላይ በአህጉሪቱ ውስጥ ያሉ ግጭቶችን እና የዲፕሎማሲ ውጥረቶችን ለመፍታት የፓርላማ ዲፕሎማሲን፣ አኹን ከሚያደረገው ከፍ ባለ ኹኔታ በስፋት ሊጠቀምበት ይገባልም ማለት እንሻለን። አባላቱ በፓርላማው ውስጥ ካሉ የሌሎች አገራት ተወካዮች ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት በመፍጠር፣ የኢትዮጵያን አቋም በማስረዳት እና የጋራ መግባባትን በመፍጠር ረገድ ከአስፈጻሚው አካል ዲፕሎማሲ ጎን ለጎን ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉና። ይኽ ዓይነቱ ተሳትፎ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ያላትን ተቀባይነት እና የአመራርነት ሚና ይበልጥ እንዲጎላ ሊያደርገው እንደሚችልም ማስታወስ ያሻል።

የፓን አፍሪካ ፓርላማ  መዋቅራዊ አደረጃጀት

ዋናው ዘርፍ ተዋካይ አካላት ዋና ተግባራት እና ኃላፊነቶች
1. ከፍተኛው የውሳኔ ሰጪ አካል ጠቅላላ ጉባኤ ሁሉንም 275 የፓርላማ አባላት ያቀፈ የፓርላማው የበላይ አካል ነው። ዋና ዋና ውሳኔዎችና ሕጎች የሚጸድቁት እዚህ ነው።
2. የፖለቲካ አመራር • ፕሬዝዳንት • 4 ምክትል ፕሬዝዳንቶች ጠቅላላ ጉባኤውን በበላይነት ይመራል፤ የሥራ አስፈጻሚነት ሚና አለው። ምክትል ፕሬዝዳንቶቹ አምስቱን የአፍሪካ ቀጣናዎች ይወክላሉ።
3. የሕግ አውጪ እና የጥናት ክፍሎች • 10 ቋሚ ኮሚቴዎች • ቀጣናዊ ስብስቦች • ልዩ ስብስቦች በቢሮው ሥር ሆነው በልዩ ልዩ ዘርፎች (ሰላም፣ ጤና፣ ግብርና…) ላይ ምክረ-ሐሳብ ያመነጫሉ። የሴቶችና የወጣቶች ስብስቦችንም ያካትታል።
4. አሥተዳደራዊ ጽሕፈት ቤት • ዋና ጸሐፊ • 2 ምክትል ዋና ጸሐፊዎች ለፓርላማው ዕለታዊ እንቅስቃሴ ቋሚ የቢሮ፣ የቴክኒክ፣ የሕግ አውጪ ሥራዎች እና የፋይናንስ አስተዳደር ድጋፍ ይሰጣል።
5. የድጋፍ ሰጪ የሥራ ክፍሎች • የሕግ አገልግሎት • ጥናት እና ምርምር • የመገናኛ ብዙኃን • አይቲ  እና የቋንቋ አገልግሎቶች
*በዚኽ ዳሰሳ የተጠቀሱት የጊዜ ቀመሮች በተለየ ኹኔታ ካልተጠቀሱ በቀር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር መሆኑን ልብ ይሏል።