የኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ለ65 ዓመታት ያህል ሲመራበት የቆየውን እና በ1954 ዓ.ም. በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የጸደቀውን የሥነ-ሥርዓት ሕግ በመሻር፣ አዲስ ምዕራፍ ተቀላቅሏል። የማርቀቅ ሂደቱ ዐሥራ አምስት ዓመታት በላይ የፈጀው ይኽ ታሪካዊ ሰነድ፣ መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. በዋለው 13ኛው የኢፌድሪ የእንደራሴዎች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1410/2018 ሆኖ ጸድቋል። በአጠቃላይ 228 ገጾች እና 444 አንቀጾችን የያዘው ይኽ ሕግ፣ የተበታተኑ የሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግጋትን በአንድ ላይ በማጣመር የሕግ የበላይነትን ለማስፈን እና የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ለማክበር የተነደፈ ነው ተብሎም ተነግሯል። ከዚኽ አንጻርም፣ ብሪጅ በዚኽ ዐዋጅ ዙሪያ ለመወያያ ይሆን ዘንድ አጠር ያለ ዳሰሳ ማድረግን ሽታለች።
የማሻሻያው ዳራ
የ1954ቱ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ የበይነ-መረብ፣ ድንበር ዘለል የፋይናንስ ሥርዓቶች እና ዘመናዊ የተደራጁ ወንጀሎች ባልነበሩበት ዘመን የወጣ ሕግ መሆኑ ይታወቃል። ያ ሕግ ለኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች መሠረታዊ መዋቅር የሰጠ ቢሆንም፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ግን ውስንነቶቹ ጎልተው ታይተዋል። በተለይም ስለ ማስረጃ ሕግ ያለው ዝምታ ትልቁ ጉድለቱ ተብሎ ሲጠቀስ ኖሯል። ኢትዮጵያ የተሟላ የማስረጃ ሕግ ስላልነበራት፣ ፍርድ ቤቶች በፍትሐ ብሔር፣ በወንጀል እና በባህላዊ ሕግጋት ውስጥ የተበታተኑ ድንጋጌዎችን ወይም የሮበርት ቢ. ሲድማንን ያልጸደቀ ረቂቅን ለመጠቀም ይገደዱ ነበር። ሕጉ ለ60 ዓመታት ሳይሻሻል የዘለቀ ቢሆንም፣ የእንደራሴዎቹ ምክር ቤቱ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ በረቂቅ ደረጃ ሲወያይበት እንደሰነበተ ተነግሯል። የጸደቀው ሕግ 195 ማሻሻያዎች ተደርጎለታል የተባለ ሲሆን፤ ከዚኽ ቀደም በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ሲነሱ የቆዩ ጉዳዮችን መልስ የሚሰጥ ነውም ተብሎለታል። ከዚያ ባለፈም ሕጉ፣ ይኽንን የሥድስት ዐሥርታት ክፍተት በመሙላት፣ ዘመናዊውን የወንጀል ውስብስብነት የሚፈታ፣ ቴክኖሎጂን ያገናዘበ እና ሰብዓዊ መብትን ማዕከል ያደረገ ሰነድ ሆኖ ቀርቧል በሚል በአርቃቂዎቹ ተወድሷል።
አሟጓቹ አንቀጽ
አዲሱ ሕግ ምንም እንኳን በ253 ድጋፍ እና በኹለት ተቃውሞ ቢጸድቅም፣ ሂደቱ ጠንከር ባለ ሙግት የታጀበ ነበር። በዕለቱ የተገኙት 255 እንደራሴዎች ብቻ መሆናቸውን ተከትሎ፣ እንደራሴው ዶ.ር. አበባው ደሳለኝ ምልዓተ ጉባኤ ሳይሟላ እና የትግራይ እንደራሴዎች በሌሉበት እንዲኽ ያለ ግዙፍ ሕግ መጽደቅ የለበትም የሚል ጠንካራ ተቃውሞ አቅርበዋል። የእንደራሴዎቹ ምክር ቤት ከዚኽ ቀደም ምልዓተ ጉባኤ ባለመሟላቱ ስብሰባውን ሰርዞ የነበረ ቢሆንም፣ በዕለቱ ግን አፈ-ጉባኤው የተከበሩ ታገሰ ጫፉ ሕጉ ለሥድስት ዓመታት በጥንቃቄ የታየ መሆኑን በመጥቀስ መጽደቁ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል። ምልዕተ-ጉባኤውን አስመልክቶ ከተነሳው የሥነ-ሥርዓት ጥያቄ ባለፈ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ውስጥ በሚገኙ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ተቋማት እና ሠራተኞች ላይ የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን እንዲኖራቸው የሚፈቅደው አንቀጽ 25(3) ከፍተኛ ክርክር አስነስቶ ውሏል። እንደ ዶ.ር. ደሳለኝ ጫኔ ያሉ እንደራሴዎችም፣ “አንድ ክልል በሌላ ግዛት ላይ የዳኝነት ሥልጣን ሊኖረው አይገባም” የሚል የፌዴራሊዝም እና የመሬት ወሰንን የተንተራሰ ሙግት ቢያቀርቡም፣ በእንደራሴዎቹ ምክር ቤት የሕግ እና የፍትሕ ቋሚ ኮሚቴ፣ ይኽ “ሕገ-መንግሥታዊ የልዩ ጥቅም መብት” መሆኑን በመጥቀስ ለተነሱት የተቃውሞ ድምጾች ምላሽ ሰጥቷል።
ክርክር ያስነሳው አንቀጽ 25 (3) ግን ምን ይላል? አንቀጹ፣ “በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ውስጥ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ተቋማት፣ ሰነዶች፣ በጀትና መሰል የክልሉ ጥቅሞች ላይ፣ በተቋማት ውስጥ በሚፈፀሙ ወንጀሎች ላይ፤ በክልሉ የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ውስጥ ከሥራ ኃላፊነታቸው ጋር በተያያዘ በሚፈፅሙ ወንጀሎች ላይ የክልሉ ፍ/ቤቶች የዳኝነት ስልጣን ይኖራቸዋል” ሲል ደንግጓል። አንቀጽ 25(3) በበኩሉ፣ “የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች በክልሉ መንግስት ባለስልጣናትና ሠራተኞች ላይ ከኃላፊነታቸውና ከስራቸው ጋር በተገናኘ በሚፈፀሙ ወንጀሎች ላይ ብቻ የዳኝነት ሥልጣን አላቸው” በሚል የደነገገ ሲሆን፤ በአንቀጽ 25 (1/ረ) ስር ደግሞ “በፌዴራል መንግሥቱ ባለሥልጣናትና ሠራተኞች ከኃላፊነት ጋር በተያያዘ የሚፈጸም ወንጀል” በፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን ስር እንደሚወድቅ ተደንግጓል። እንደራሴዎቹ ዶክተራት የተከበሩ ዶ.ር. ደሳለኝ ጫኔ እና የተከበሩ ዶ.ር. አበባው ደሳለው፣ አንቀጹ የከተማዋን ራስን የማሥተዳደር መብት እና የሕግ የበላይነትን ይጋፋል በሚል እንዲወጣ ከመጠየቃቸው ባሻገር፣ “አንድ ክልል በሌላ ግዛት ላይ የዳኝነት ሥልጣን ሊኖረው አይገባም” የሚል መከራከሪያም አቅርበው ነበር። ከላይ ያነሳነው ቋሚ ኮሚቴውም፣ “ኦሮሚያ ክልል ፍትሕ ቢሮ ይዳኝ ያልነው በከተማዋ በሚገኙ የኦሮሚያ ክልል መስሪያ ቤቶቹ ቅጥር ግቢ የሚፈፀም ወንጀል ነው፤ ይኽም ሕገ-መንግስታዊ መብቱ ነው” ሲል ምላሽ ሰጥቷል። “ለአንዳንድ ጥያቄዎች ደግሞ ምላሽ አያስፈልግም” ያሉት አፈ-ጉባኤው ታገሰ ጫፉ፣ “ይኽ ሕግ ብዙ ተለፍቶበታል እና መጽደቁ ተገቢ ነው”ም ሲሉ ተደምጠዋል።
አዲሱ ሕግ ምን ይዟል?
የኢትዮጵያ አዲሱ የፈዴራል የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ዋና ዋና ይዘቶቹ እና ለውጦቹን እንደሚከተለው አጠር አድርገን ልናያቸው ይቻለናል፤
ሀ፦ የሥነ–ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ መዋሃድ፤
ቀደም ሲል የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ እና የማስረጃ ሕግ ተለያይተው (የማስረጃ ሕጉም በረቂቅ ደረጃ ብቻ ለረጅም ጊዜ መቆየቱን ልብ ይሏል) የነበረ ቢሆንም፣ አዲሱ ሕግ ግን ኹለቱንም በአንድ ላይ አጣምሮ ይዟል። ይኽ መሆኑ በወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ግልጽነትና ቅልጥፍናን ይፈጥራል የሚል ዕምነትንም አሳድሯል።
ለ፦ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ እና የሕግ የበላይነት፤
ዐዋጁ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት እና ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች የተደነገጉ የሰብዓዊ መብቶችን በተግባር ለመተርጎም የተነደፈ ሲሆን፣ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ጊዜ ጀምሮ እስከ መጨረሻው የፍርድ ሂደት ድረስ ያላቸውን መብቶች በዝርዝር በማስቀመጥ፣ የሕግ አስከባሪ አካላት ሥልጣናቸውን ያለአግባብ እንዳይጠቀሙ ገደብ ይጥላል። በተለይም በምርመራ ወቅት የሚፈጸሙ ኢ-ሰብዓዊ አያያዞችን ለመከላከል እና በግዴታ የተገኘ ቃል በማስረጃነት እንዳይቀርብ የሚያደርጉ ድንጋጌዎች የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እና የዜጎችን ክብር ለመጠበቅ ዋነኛ ዋስትናዎች ከመሆናቸው አኳያ፣ ለውጡ አሌ የሚባል አይደለም።
ሐ፦ የዲጂታል ማስረጃዎች ዕውቅና፤
አዲሱ ሕግ የቴክኖሎጂ ለውጥን ያገናዘበ ሲሆን፣ የዲጂታል ወይም የኤሌክትሮኒክስ ማስረጃዎችን (ለምሳሌ፣ የቪዲዮ ምስሎች፣ የድምፅ ቅጂዎች፣ የኮምፒውተር መረጃዎች፣ የማኅበራዊ ሚዲያ መልዕክቶች) እንደ ትክክለኛ ማስረጃ እንዲቀበሉ ሕጋዊ መሠረት ሰጥቷል። የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለምርመራ የመጠቀም አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ፖሊስ የኤሌክትሮኒክ መረጃዎች እንዲቆዩ ትዕዛዝ መስጠት የሚችለው ለአንድ ወር ብቻ እንዲሆንም ተደንግጓል። ይኽ የጊዜ ገደብ መረጃዎች ያለአግባብ በመንግሥት እጅ እንዳይቆዩ እና የግለሰቦች የዲጂታል ግላዊነት መብት እንዳይጣስ ዋስትና ይሰጣል። ከዚኹ ጋር በተያያዘ፣ እንደ ስልክ ጠለፋ እና የድብቅ ክትትል ያሉ ዘመናዊ የምርመራ ዘዴዎች በምን ዓይነት ጥብቅ የሕግ ማዕቀፍ እና የፍርድ ቤት ፈቃድ መከናወን እንዳለባቸውም ተደንግጓል።
መ፦ የዐቃቤ ሕግ ሥልጣን እና ክስ መመስረት፤
በዚኽ አዲሱ ሕግ የተካተተው አንዱ አዲስ ሥነ-ሥርዓት የክስ ድርድር ሲሆን፤ ደንቡም፣ አንድ ተጠርጣሪ ጥፋተኛነቱን አምኖ ከዐቃቤ ሕግ ጋር በመደራደር ቅጣቱ እንዲቀልለት ወይም ክሱ እንዲቋረጥ የሚያስችል ሥርዓት ነው። ይኽም የፍርድ ቤቶችን የሥራ ጫና ከመቀነሱ ባለፈ፣ ንጹሐንን ለግዳጅ የእምነት ቃል እንዳያጋልጥ፣ ዳኛው ተከሳሹን ለብቻው አነጋግሮ ድርድሩ በፈቃደኝነት መደረጉን የማረጋገጥ ግዴታ ተጥሎበታል። በተጨማሪም፣ ለከባድ ወንጀለኞች የሚደረግ የቅጣት ቅናሽ የሕዝብን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ እንዲሆን በፍርድ ቤት ቁጥጥር እንዲደረግበት ተደርጓል። ከዚኹ ጋር በተሳሰረ፣ ዐቃቤ ሕግ ክስ ለማንሳት የሚችልባቸውን ምክንያቶች እና ቅድመ-ኹኔታዎች በዝርዝር ተቀምጠዋል። ቀደም ሲል ዐቃቤ ሕግ ‘በሕዝብ ጥቅም ስም’ ክስን የማንሳት ሰፊ እና ያልተገደበ ሥልጣን እንደነበረው ይታወሳል። ይኹን እንጂ አዲሱ ማሻሻያ ይኽ ሥልጣን በዝርዝር መመሪያ እንዲገዛ እና የሚሰጠው ምክንያትም ለፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲመረመር ተደንግጓል። ይኽ ለውጥ የአሥተዳደራዊ ውሳኔዎችን ግልጽነት ከማረጋገጡም በላይ፣ ሥልጣንን ያለአግባብ የመጠቀም ዕድልን በእጅጉ ይቀንሳል ተብሎ ይታመናል።
ሠ፦የምሥክሮች እና የጠቋሚዎች ጥበቃ፤
በከባድ ወንጀሎች ላይ መረጃ የሚሰጡ ጥቆማ ሰጪዎች እና ምሥክሮች ከበቀል ወይም ከጥቃት እንዲጠበቁ የሚያስችል የሕግ ከለላም በአዲሱ ሕግ ውስጥ ተካቷል፤ ይኽም በብዙ የሕግ አዋቂዎች ዘንድ ሙገሳ ያገኘ አንቀጽ መሆኑ ተስተውሏል።
ረ፦ የፍርድ ቤት ሥነ–ሥርዓት ቅልጥፍና፤
የፍርድ ቤት ሥነ-ሥርዓት ቅልጥፍና ለማሳለጥ በቅድመ-ችሎት ስብሰባ ክርክሩ ከመጀመሩ በፊት ግልጽ የሆኑ ነጥቦችን ለመለየት እና ሂደቱን ለማፋጠን የሚረዱ አሠራሮችንም አዲሱ ሕግ አስተዋውቋል። ከዚኽ ባለፈም፣ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ አሰጣጥ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ፣ ተጠርጣሪዎች ያለ ፍርድ ለረጅም ጊዜ እንዳይታሰሩ የሚረዱ ድንጋጌዎችንም ይዟል።
ሰ፦ ባህላዊ ሥርዓታት እና የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ፤
በዚኽ አዲሱ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ፣ ባህላዊ የግጭት አፈታት መንገዶች ከዘመናዊው የሰብዓዊ መብት መርሆዎች ጋር እንዲጣጣሙም ተደርጓል። በተለይም በሴቶች እና በሕፃናት ላይ በደል እንዳይደርስ፣ የማኅበረሰብ ውሳኔዎች በፍርድ ቤት መጽደቅ እንዳለባቸው እና ሂደቱም በሠላሳ ቀናት ውስጥ እንዲጠናቀቅ መደረጉ በበጎ ለውጥነት ተነስቷል።
ሦሥት ነጥቦችን በወፍ በረር…
በዚኽ መልኩ አጠር አድርገን ልናያቸው የሞከርናቸውን ለውጦች የያዘውን አዲሱን ሕግ አስመልክቶ ዋንኞች ባልናቸው ሦሥት የሕጉ ድንጋጌዎች ላይ ደግሞ ጥቂት ነጥቦችን በማሳያነት እናንሳ፤ እነዚኽም፣ ዋስትና፣ የጥፋተኝነት ድርድር እና የማስረጃ ሕግ የተሰኙት የሕጉ አዲስ ሥነ-ሥርዓቶች ናቸው።
ሀ፦ ዋስትና
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 19/6 በግልጽ እንደተደነገገው፣ የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት አላቸው። ይኽ መብት ሕገ-መንግሥታዊ ሲሆን፣ የተያዙ ወይም የተከሰሱ ሰዎችን መብት ከማስከበር አኳያ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉትም ግልጽ ነው። የመጀመሪያ ጠቀሜታው ሌሎች ሕገ-መንግሥታዊ መብቶችን ማስከበር መቻሉ እና በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ሰዎች ሊታሰሩ አይገባም ከሚለው የሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌ ጋር የተቆራኘ መሆኑ ነው። የግለሰቦች ነፃነት እንዳይሸረሸር እና ከፍርድ በፊት ያለአግባብ እንዳይታሰሩ በዋስ የመፈታት መብታቸውንም ያስጠብቃል፡፡ አዲሱ ሕግ የዋስትና መብትን እንደ መሠረታዊ መብት፣ ዋስትና መከልከልን ደግሞ እንደ ልዩ ሁኔታ ይመለከተዋል። ሕጉ ግልጽ የሆኑ የዋስትና ዓይነቶችንም አስቀምጧል፤ እነሱም፤ በግል ማረጋገጫ፣ በሰው ዋስትና፣ በንብረት ዋስትና ወይም በገንዘብ ማስያዝ የሚሉት ናቸው፤ ሆኖም ተጠርጣሪው ዋስትና ቢፈቀድለት ይጠፋል ወይም ማስረጃ ያጠፋል ወይም ተጨማሪ ወንጀል ይፈጽማል ተብሎ ሲታመን ዋስትና ሊከለከል ይችላል። እንዲሁም የቅጣቱ መጠን ከባድ በሆነባቸው (ለምሳሌ በሞት ወይም በዕድሜ ልክ እስራት በሚያስቀጡ) ወንጀሎች ላይ ገደብ ሊኖር ይችላል። ፍርድ ቤቱ ዋስትና ሲፈቅድ ተጠርጣሪው ከአገር እንዳይወጣ ፓስፖርት እንዲያስረክብ፣ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ እንዳይገኝ ወይም በየጊዜው ፖሊስ ጣቢያ ቀርቦ እንዲፈርም ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል። ዋስትና የተከለከለ ተጠርጣሪ ወይም ዋስትና የተፈቀደለትን ተቃውሞ ያለው ዐቃቤ ሕግ ለበላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ የማለት መብቱም በግልጽ ተቀምጧል።
የዚኽ መሰሉ ድንጋጌ ዋንኛ ጠቀሜታ፣ በወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው በዋስ ሲለቀቅ ከተከሰሰበት ክስ ‘ራሱን ለመከላከል የሚያስችለውን ማስረጃ ለማሰባሰብ እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለማድረግ የተሻለ ነፃነት ማግኘቱ ነው። በዚህም ሂደት የፍትሕ አካላት እውነትን ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት ከማገዙ ባለፈ፣ የተያዘን ሰው በዋስ መልቀቅ በማረሚያ ቤት ያለውን የእስረኞች መጨናነቅ በመቀነስም አስተዋጽዖ እንደሚኖረውም ማስታወስ ያሻል። በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩትን ሰዎች በሕግ አግባብ በዋስ መልቀቅ፣ ከፍርድ ሂደት በኋላ በነፃ ሊለቀቁ የሚችሉ ሰዎች በሞራላቸው እና በቁሳዊ ሀብታቸው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በመቀነስ የዜጎችን ሰብዓዊ ክብር እና ቁሳዊ ጥቅሞችን ለመጠበቅም አንዱ ዘዴ ነውና።
ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆነው፣ የፌዴሬሽኑ ሕገ-መንግሥት የዋስትና መብት ፍፁም እንዳልሆነም፣ በአንቀጽ 19/6 ከተቀመጠው ድንጋጌ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚህም መሠረት በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት የዋስትና ጥያቄዎችን ላለመቀበል ይችላል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎችም፣ የወንጀል ዓይነቶች(ለምሳሌ የሽብርተኝነት ወንጀል)ን፣ የወንጀል ዓይነት እና የቅጣት መጠን (ለምሳሌ የሙስና ወንጀል ሆኖ ከአስር ዓመት በላይ የሚያስቀጣ)ን፣ የቅጣቱ ጣራ (ለምሳሌ በሞት የሚያስቀጣ ከሆነ)ን፣ የተጎጂዎች ዓይነት (ለምሳሌ ሕፃናት እና ሴቶች ከሆኑ)ን የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል።
ለ፦ የጥፋተኝነት ድርድር
አዲሱ ሕግ ከያዛቸው አዲስ ስርዓቶች መካከል አንዱ የጥፋተኝነት ድርድር የሚለው ሥርዓት ነው። ይኽም፣ አንድ ተጠርጣሪ ጥፋተኛነቱን አምኖ ከዐቃቤ ሕግ ጋር በመደራደር ቅጣቱ እንዲቀልለት ወይም ክሱ እንዲቋረጥ የሚያስችል ሥርዓት ነው። የጥፋተኝነት ድርድር በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ አዲስ ሲሆን፣ ዓላማውም ጊዜን እና ወጪን ለመቆጠብ እንዲሁም የፍርድ ቤቶችን ጫና ለመቀነስ ነው ተብሏል። ክስ ከመመሥረቱ በፊት ወይም ክስ ከተመሠረተ በኋላ ፍርድ እስከሚሰጥ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ተጠርጣሪው ጥፋተኛነቱን አምኖ ከዐቃቤ ሕግ ጋር ሊደራደር ይችላል። በ‘ርግጥ ብዙ ሰዎች ይኽ አሰራር ምንም እንኳ በውጪ ሀገር የተለመደ ቢሆንም እንደኛ ባሉ ሀገራት ለሙስና በር ከፋች ከመሆኑም በላይ ፖሊስ ተከሳሾች ላይ አላስፈላጊ ጫና እንዲፈጥር ሊያደርግ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
የጥፋተኛነት ድርድር ዓይነቶች ኹለት ሲሆኑ፣ ከባድ የሆነውን ክስ ወደ ቀለል ያለ የወንጀል ዓይነት በመቀየር መደራደር እና በክሱ ላይ ተስማምቶ ቅጣቱ እንዲቀልለት መደራደር ናቸው። ይሁንና ድርድሩ የተደረገው በፈቃደኝነት መሆኑን፣ ተከሳሹ መብቶቹን መረዳቱን እና ድርድሩ የሕዝብን ጥቅም የማይጎዳ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ማረጋገጥ ይኖርበታል። ከዚኽ በተጨማሪም፣ ፍርድ ቤቱ ድርድሩን ውድቅ የማድረግ ሥልጣን አለው። ዐቃቤ ሕግ የክስ ድርድር ሲያደርግ የወንጀል ተጎጂዎችን ፍላጎት እና ስሜት ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበትም ሕጉ ይደነግጋል። ተጎጂው ካሳ የሚያገኝበት መንገድም በድርድሩ ውስጥ ሊካተት ከመቻሉ ባለፈ፣ ተከሳሹ የቅጣት ቅናሽ ያገኛል፤ መንግስት ለምስክሮች እና ለረጅም ክርክር የሚያወጣውን ወጪ ይቆጥባል፤ ተጎጂዎች ደግሞ የፍርድ ሂደቱን ሳይጠብቁ ካሳ ወይም ይቅርታ ሊያገኙ የሚችሉበትን ኹኔታ ይፈጥራል።
ሐ፦ የማስረጃ ሕግ
የማስረጃ ሕግ ለፍርድ የሚሆነውን ማስረጃ ለይቶ የሚያሳይ ወይም በፍርድ ሥራ መካሄድ የፍሬ ነገር ጥያቄን ለመወሰን መገልገያ የሆነውን ዘዴ የሚያመለክት ደንብ ነው። ለአንድ ፍርድ ቤት የቀረበ ማስረጃ የሚያስፈልጋቸዉ በጭብጥ የሚያዙ ፍሬ ነገሮችን እና እነዚህን ፍሬ ነገሮች ለማስረዳት የሚቀርቡት ፍሬ ነገሮችን እና አግባብነት እና ተገቢነት ያላቸው መሆናቸውን የሚወስን ነው፡፡ በግዙፍ ነገር፣ በሠነድ፣ በቃል፣ በዳኞች ግንዛቤ ወይም በተከራካሪዎች እምነት አማካኝነት የሚቀርበውን የማስረጃ ዓይነት፣ እንዲሁም አከራካሪዉ ጉዳይ እውነት መሆኑን እና አለመሆኑን ፍርድ ቤቱ እንዲያምን የሚደረግበትን መንገድ የሚገዛም ነው። በመሆኑም አዲሱ ሕግ እነዚህን በሙሉ ከመዘርዘርም ባሻገር አንድ ማስረጃ ፍርድ ቤት ለመቅረብ ተገቢ የሚሆነው መቼ እንደሆነ እና ውድቅ የሚሆነው መቼ መሆኑን በግልጽ ይደነግጋል፡፡ ለምሳሌ ፖሊስ በድብደባ ከተከሳሹ ያገኘው የእምነት ቃል ወይም ፍርድ ቤቱን ሳያስፈቅድ ስልክ በመጥለፍ (ልዩ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ) ያገኘው ማስረጃ ተቀባይነት የለውም።
በተጨማሪም፣ ከላይ እንደጠቀስነው አዲሱ ሕግ የዲጂታል ወይም የኤሌክትሮኒክስ ማስረጃዎችን እንደ ትክክለኛ ማስረጃ እንዲቀርቡ ሕጋዊ መሠረት ሰጥቷል። ሆኖም እንደ ስልክ ጠለፋ እና የድብቅ ክትትል ያሉ ዘመናዊ የምርመራ ዘዴዎች በምን ዓይነት ጥብቅ የሕግ ማዕቀፍ እና የፍርድ ቤት ፈቃድ መከናወን እንዳለባቸውም ደንግጓል። ምክንያቱም ጥፋተኛ ሆኖ ያለመቆጠር መብት ከአገሪቷ የሕገ-መንግሥት መርሆዎች መካከል አንዱ መሆኑን ያስታውሷል። አዲሱ ሕግ ካስተዋወቀው መሰረታዊ የማስረጃ መርሆዎች አንዱ የማረጋገጫ ደረጃ ነው። ተከሳሹ በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ የሚቀጣው ዐቃቤ ሕግ ተከሳሹ የተከሰሰበትን ወንጀል መፈፀሙን በማስረጃ ካረጋገጠ ብቻ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የተከሳሹ ጥፋተኝነት የሚረጋገጥበት ደረጃ ከፍ እና ጠበቅ ያለ መሆን አለበት። አዲሱ ሕግ ዐቃቤ ሕግ አንድን ተከሳሽ ጥፋተኛ ለማስባል ‘ከበቂ ጥርጣሬ በላይ’ ክሱን ለፍርድ ቤቱ ማስረዳት እንዳለበት በግልጽ አስቀምጧል። ይኽ መርህ በሕግ ደረጃ መደንገጉ የተከሰሾችን ሕገ-መንግሥታዊ እና ዓለም ዓቀፋዊ መብት ከማስጠበቅ አኳያ ትልቅ እመርታ ሆኖም ተቆጥሯል። በ‘ርግጥ ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ ባለባቸው የአቅም ውስንነት በዚህ ደረጃ የምርመራ እና የክስ ሂደቱን ማከናወን መቻላቸው አጠያያቂ ቢሆንም፣ አቅም ያጥረኛል በሚል ከዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት መርሆዎች መጉደል ተገቢነትም፣ የሚጠበቅም አይሆንም።
እንደ መውጪያ
የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ የኅብረተሰቡን እና የመንግሥትን ደኅንነት እና ሰላም ሲያስጠብቅ ኹለት ተገዳዳሪ ጥቅሞችን በማመዛዘን መሆን ይኖርበታል። በአንድ በኩል የመንግሥት እና የኅብረተሰብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ የወንጀል ሕግ የሚተላለፉ ግለሰቦችን ውጤታማ፣ ፍትሓዊ፣ ቀልጣፋ እና አስተማማኝ በሆነ ሂደት በሕግ ፊት አቅርቦ አራሚ እና አስተማሪ የሆነ ቅጣት እንዲያገኙ በማድረግ፤ በሌላ በኩል ቅጣቱ በንፁሐን ላይ ሳይሆን በአጥፊዎች ላይ ብቻ እንዲፈፀም ብርቱ የጥንቃቄ እርምጃዎች ማስቀመጥ ይጠበቅበታል። ቅጣቱ በአጥፊዎች ላይ ብቻ የሚፈፀምበት ሂደትም ቢሆን የአጥፊውን ሰብዓዊ ክብር እና ማንነት በማይጐዳ ሁኔታ መሆኑን የሚያረጋግጥበት ሥነ-ሥርዓት ማስቀመጥም ይጠበቅበታል። ከኹሉም በላይ ጥፋተኛ ሆኖ ያለመቆጠር መብት ለወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ መርህ የሆነውን ያህል፣ ለማስረጃ ሕግም መርህ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ሌላው ጉዳይ ይኽ መርህ ትርጉም እና ተፈፃሚነት የሚያገኘው አገራት በሚከተሉት የሕግ ሥርዓት ዓይነት ላይ በመመሥረት ነው። ምንም እንኳ በእኛ አገር ሕግ ውስጥ በግልፅ ያልተፃፈ ቢሆንም የአገራችን ፍርድ ቤቶች ‘ከበቂ ጥርጣሬ በላይ’ የሚለውን የጥፋተኝነት ማረጋገጫ ደረጃ የሚጠቀሙበት መሆኑ ይታወቃል። ከጥፋተኛ ሆኖ ያለመቆጠር መብት መርህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ጉዳይ፣ ዐቃቤ ሕግ የተጠርጣሪውን ጥፋተኝነት ሲያረጋግጥ ኹሉንም የወንጀሉን ፍሬ ነገሮች በተቀመጠው የማረጋገጫ ደረጃ መሠረት ማረጋገጥ ይጠበቅበታል የሚለው ነው።
በአጠቃላይ፣ አዲሱ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ‘ንጹሕ ሆኖ የመገመት’ን መርህ ወደ ተግባር የሚቀይር፣ የሕዝብን ሰላም ከግለሰቦች ሰብዓዊ መብት ጋር የሚያመጣጥን ሰነድ ነው ማለት ይቻል ይመስለናል። ሕጉ፣ እንደተባለው ለሥድስት ዓመታት በጥንቃቄ የታየ ቢሆንም፣ የአተገባበሩ ስኬት የሚለካው በፖሊስ፣ በዐቃቤ ሕግ እና በፍርድ ቤቶች ነጻነት እና ተከታታይነት ያለው ተቋማዊ የማስፈጸም አቅም ላይ መሆኑንም መዘንጋት አያስፈልግም። ከዚኽ አኳያም ብሪጅ፣ ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ ‘ከበቂ ጥርጣሬ በላይ’ ለማስረዳት የሚያስችል የፎረንሲክ እና የምርመራ አቅም ሊገነባላቸው ይገባል ብላ ታምናለች። ከላይ ያነሳውነውን፣ የአዲሱን ሕግ አንቀጽ 25(3) ተንተርሶ የተደመጡት ቅሬታዎችም በፖለቲካ ገጾች በኩል ሳይሆን በሕግ ትርጓሜ ብቻ እንዲፈቱ ብርቱ ክትትል ያስፈልጋል እንላለን። ዜጎችም ስለ አዲሱ የዲጂታል መብታቶቻቸው እና ስለ ዋስትና መብታቸው በቂ የግንዛቤ ትምህርት የሚያገኙበትን መንገድ ዋል አደር ሳይባል ሊበጅ እንደሚገባም፣ ተቋማችን ማስታወስ ትሻለች።