BRIDGE Research & Innovation - Parliaments. Peace. Policy

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴዎች፣ በወርኃ የካቲት ተለምዷዊ የሆኑትን ሕገ-መንግሥታዊ ተግባራቶቻቸውን አከናውነዋል። በዚኽ ወር ያደረጉት መደበኛ ስብሰባ አንድ አስቸኳይ ስብሰባ ብቻ ነበር። ከዚያ ባለፈ ወሩ የካቲት እንደመሆኑ፣ ከሐምሌ እስከ መስከረም መጨረሻ ድረስ ከሚያካሂዱት የውክልና ሥራ በተጨማሪ፣ ከየካቲት አንድ አንስቶ እስከ የካቲት ሠላሳ ድረስም እንዲኹ የውክልና ሥራቸውን የሚከውኑበት መሆኑ ይታወቃል። ከዚኽ አኳያም፣ በዚኹ ወርኃ የካቲት በዛ ያሉ እንደራሴዎቻቸውን ወደ ተመረጡባቸው የምርጫ ክልሎች በመላክ፣ ዜጎች ያሳስቡናል ባሏቸው ከመልካም አሥተዳደር እስከ የባሕር በር አኹነኛ ኹኔታ፣ ከመሠረተ-ልማት እስከ ጸጥታ እና የሰላም ጉዳዮች መራጮቻቸውን አወያይተዋል። ይኽች የብሪጅ ቅጽ ኹለት ዐሥራ ሦሥተኛ ዕትምም፣ እኒኽን ጉዳዮች በመልክ በመልካቸው አጠናቅራ እና የወሩን የብሪጅ ዳሰሳዊ ምልከታ አካታ እንዲኽ ተጠንቅራለች።

እነሆ እንደራሴ ብለን የሰየምናት የእንደራሴዎቹን ወርኃዊ ክራሞት የምትተነትነው መጽሔታችን፣ አንዱን ዓመት አጠናቃ ወደ ኹለተኛ ዓመቷ መሻገሯን ስናብስራችኹ እጅጉን በሀሴት ነው። ያለፉትን ዐሥራ ኹለት ዕትሞች ስላነበባችኹልን፣ አስተያቶቻችኹንም ስለለገሳችኹን እጅ እንነሳለን።