BRIDGE Research & Innovation - Parliaments. Peace. Policy

COP 32

Ethiopia has been officially selected to host the 32nd United Nations Climate Change Conference (COP32), which is scheduled to take place in Addis Ababa in November 2027. 

Key Details of COP32 in Ethiopia

  • Official Selection: The decision was finalized and officially announced during the closing plenary of COP30 in Belém, Brazil in November 2025.
  • Leadership: Ethiopia’s Minister of Foreign Affairs, Dr. Gedion Timotheos, has been appointed as the COP32 President-Designate.
  • Focus Areas: The summit is expected to highlight African climate priorities, including climate finance, green investment, and sustainability education.
  • Hosting Rationale: Ethiopia’s selection was supported by the African Group of Negotiators, citing its leadership in green initiatives like the Green Legacy Initiative and its extensive use of renewable energy, specifically the Great Ethiopian Renaissance Dam (GERD).
  • Expected Scale: The event is anticipated to attract approximately 50,000 participants, including world leaders and climate stakeholders.

የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ጉባኤ አስተናጋጅነት እና አህጉራዊ ፋይዳው

ኢትዮጵያ፣ እ.አ.አ. በ2027 ሊካሄድ ቀጠሮ የተያዘለትን የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ (አልያም በእንግሊዘኛ ምኅጻረ ቃሉ፦ COP32, the 32nd Conference of the Parties (COP) to the United Nations Framework Convention on Climate Change (UNFCCC)) እንድታስተናግድ ተመርጣለች። ኢትዮጵያ ይኽን 32ውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤ ለማስተናገድ መመረጧ የተሰማው በኅዳር መጀመሪያ ሲሆን፣ ይኽንን ዕድልም ያገኘችው ከናይጄሪያ ጋር ስታደርግ የነበረውን የበረታ ውድድር ፉክክር በማሸነፍ ነበር። ኢትዮጵያ ናይጄሪያ አቅርባው የነበረውን ተቀናቃኝነት በመርታት፣ የጉባኤውን አጀንዳዎች እና ውጤቶች ለመቅረጽ የሚያስችላትን ይኽንን ከፍ ያለ ተደማጭነት ያለውን ሚና ለመረከብ በቅታለች። በብራዚል በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ፣ ኢትዮጵያ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ጉባኤው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ድጋፋቸውን እንደሰጧትም አረጋግጣለች። በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰም ለጉባኤው ተሳታፊዎች በሰጡት መግለጫ፣ “በኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ላይ ለተጣለብን እምነት እና መተማመን ጥልቅ ምስጋናችንን እናቀርባለን” ብለዋል። አምባሳደሩ አክለውም፣ “ኮፕ32፣ በዚኽ ወሳኝ ዐሥርት ዓመት ውስጥ የአየር ንብረት እርምጃዎችን በመምራት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል” ሲሉ፣ የቀጣዩን የአዲስ አበባውን ጉባኤ ዓለም ዓቀፍ ፋይዳ በአማዞን ደን አቅራቢያ በምትገኘው የብራዚሏ ቤሌም ከተማ ውስጥ ተሰብስበው ለነበሩት ጉባኤተኞች ጠቅሰውላቸዋል። እኒኽ የአየር ንብረት ጉባኤዎች በዓለም ዙሪያ ባሉ አህጉራዊ ቀጠናዎች በየተራ የሚስተናገዱ ሲሆን፣ አዘጋጅ አገርን የመምረጥ ውሳኔው በዚያ ቀጠና ውስጥ ባሉ አገራት ሙሉ ስምምነት መጽደቅ ይኖርበታል። የጉባኤው አስተናጋጅ አገራት የፕሬዝዳንትነት ሚናን የሚይዙ ሲሆን፣ ይኽም ለጉባኤው ግቦችን እንዲያወጡ፣ የ‘ራሳቸውን የአየር ንብረት ጉዳዮች ለዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያሳዩ፣ እንዲኹም በድርድር ወቅት የሚነሱ ግጭቶችን በመፍታት ረገድ ወሳኝ ቦታ እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል ተብሎ ይታመናል።
→ ተጨማሪ ያንብቡ

ኢትዮጵያ እንደ የአፍሪካ ድምፅ መወከያ?

ከኮፕ 30ው የብራዚሉ ጉባኤ በኋላ በተደረጉ ውይይቶች ይፋ በሆነው በዚኽ ውሳኔ፣ ይኽ ታላቅ የዓለም የአየር ንብረት መድረክ ከዐሥር ዓመታት በላይ በኃላ ወደ ከሰሃራ በታች ወዳለው የአፍሪካ ቀጣና ሲመለስ የመጀመሪያው ነው። የከዚኽ አኳያም የኢትዮጵያ መመረጥ ከቀጣናዊ ሽግግር ባለፈ፣ አፍሪካ በዓለም ዓቀፍ ዘላቂ ልማት አጀንዳዎች ላይ ያላትን ተሰሚነት ማሳየቱ ግልጽ ነው። የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት መሥራች እና የበርካታ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን፣ አዲስ አበባ ለጉባኤው ተምሳሌታዊነትን ታበረክታለች። ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ጥበቃ ፖሊሲዎቿ ትታወቃለች። ከእነዚኽ ፖሊሲዎቿ መካከልም በዋነኝነት፣ ኢትዮጵያ በፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት መሰረት ለተባበሩት መንግሥታት ያቀረበችው የካርቦን የልቀትን መጠንን በ68.8 በመቶ የመቀነስ ዕቅድ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ.ር. ዐቢይ አሕመድ ሐሳብ አመንጪነት ከ2011 ዓ.ም. አንስቶ መተግበር የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እና የካርቦን ልቀትን የሚያመጡ የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ መከልከል እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ማበረታታት ሊጠቀሱ የሚችሉት ናቸው። ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ከ30 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ከጀመረችበት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አንስቶ፣ በታዳሽ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል እና በአረንጓዴ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ የምታፈሰው መዋዕለ-ንዋይ አገሪቱ ዕድገቷን ከአየር ንብረት ጥበቃ ጋር ለማጣጣም የምታደርገውን ጥረት በቅጡ የሚያሳይ ክንውን ነው። የኮፕ 32 ጉባኤን ማስተናገዷም ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ያለውን ልማት በመደገፍ ረገድ ያላትን ጥረት ያጠናክረዋል ተብሎ ይታመናል። ርዕሰ-ጉዳዩን የሚከታተሉ ኹነኛ ታዛቢዎችም፣ ኮፕ 32 የናይሮቢ ዐዋጅ የሚሰኙትን ግቦችን እንደሚያፋጥን እና በአፍሪካ የካርቦን ገበያ እንዲኹም በታዳሽ ኃይል እና በአረንጓዴ ሃይድሮጅን ስልቶች ላይ መሻሻል እንደሚያሳይ ይጠብቃሉ።

ለኢትዮጵያ ምን ዕድሎችን ይፈጥራል? ተግዳሮቶቹስ?

ይኽ ጉባኤ ለኢትዮጵያ የሚያስገኘው ጥቅም ሰፊ ይሆናል ተብሎ ይገመታል። ኮፕ 32 የመሠረተ-ልማት ግንባታዎችን፣ የአረንጓዴ መዋዕለ-ንዋይ ፍሰትን እና ዓለም ዓቀፍ ተደማጭነትን ያፋጥናል። ጉባኤው በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ልዑካንን የሚስብ በመሆኑ ለቱሪዝም፣ ለኃይል እና ለትራንስፖርት ዘርፎች ሰፊ ዕድል ከመፍጠሩ ባለፈ፣ አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ እና የዘላቂ ልማት ማዕከል እንድትሆን ያደርጋታል የሚሉ አስተያየቶችም ይደመጣሉ። በሰፊው አህጉራዊ ማዕቀፍ ሲታይ ደግሞ፣ አፍሪካ በዓለም ዓቀፍ የአየር ንብረት የገንዘብ ድጋፍ ሙግቶች ላይ የበላይነት እንድታገኝ ሊያስችላት ይችላል። በአፍሪካ በአየር ንብረት ዙሪያ በየዓመቱ ከ250 ቢሊዮን ዶላር በላይ የመዋዕለ-ንዋይ ፍሰት ስለሚያስፈልግ፣ ጉባኤውን ማስተናገድ አፍሪካ ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ጉዳዮች ለማስፈጸም ብርቱ አህጉራዊ አቅም ይሰጣታል። ኢትዮጵያ ይኽን ጉባኤ ማስተናገዷ ዕውቅናም ፈተናም ሳይሆን ግን አልቀረም። ዕውቅናው ለኢትዮጵያ መሪነት እና ለአፍሪካ የጋራ ዕድገት ሲሆን፤ ፈተናው ደግሞ አህጉሪቱ አሁንም ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ መሆኗን ማስታወሱ ነው ይላሉ ጉባኤውን እና ተከታይ የፖሊሲ መር ውሳኔዎቹን የሚከታተሉ። ይኽ ጉባኤውን የማስተናገዱ ዕድል በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ፣ የአፍሪካን የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ አዲስ መልክ ሊሰጠው ይችላል። አንዱ ተደራዳሪ እንደተናገሩት፣ “አሁን አፍሪካ ውይይቱን የምታስተናግድበት ብቻ ሳይሆን የምትመራበትም ጊዜ ነው!”ና። ኢትዮጵያ ለዚኽ ዕድል እንድትበቃ ካደረጓት ኩነቶች አንዱ፣ በካርቦን ንግድ ዙሪያ 70 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት አዲስ ስኬት ማስመዘገቧ እንደሆነም መጥቀስ ያሻል። አገሪቷ ከዓለም ዓቀፍ አጋሮቿ ጋር ባደረገችው የካርቦን ንግድ ስምምነት መሠረት፣ ወደ 70 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ገቢ በማግኘት ረገድ ትልቅ ስኬት አስመዝግባለች። ይኽ ውጤት አገሪቱ በአካባቢ ጥበቃ ረገድ ያላትን ተሰሚነት እና በዓለም ዓቀፍ የካርቦን ገበያ ውስጥ እያደገ የመጣውን ተሳትፏውን ከማሳየቱ በተጨማሪ፣ ለዚኽ ጉባኤ አካሂያጅነት እንድትመረጥ እንዳደረጋት ዘገባዎች ያሳያሉ። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ.ር. ዐቢይ አሕመድ መሪነት በ2011 ዓ.ም. የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርም ለዚኽ አስተዋጽዖ ማደርጉ ይጠቀሳል። ይኽ የጠቅላዩ አነሳሽ መርሃ-ግብር የደን ጭፍጨፋን በመከላከል፣ የተጎዱ ሥነ-ምኅዳሮችን በመመለስ እና የአየር ንብረት የመቋቋም አቅምን በማሳደግ ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል፤ እየተጫወተም ነው። እስከ መጋቢት 2017 ዓ.ም. ድረስ ባለው መረጃም፣ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ወደ 23.6% ከፍ ብሏል። ይኽም በአንድ ወቅት ከፍተኛ የመሬት መሸርሸር እና የብዝሓ-ሕይወት መጥፋት ለገጠማት አገር እጅግ አስደናቂ ስኬት መሆኑን ልብ ይሏል። ይኽን ከፍ ያለ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ ማስተናገድ ለኢትዮጵያ ተምሳሌታዊ ቦታ ብቻ ሳይሆን፣ ተጨባጭ ኃላፊነትንም ያሸክማል። አዲስ አበባ ድርቅን፣ ጎርፍን እና የምግብ ዋስትና እጥረትን ለሚጋፈጡ አገራት ተደራሽ እና አስተማማኝ የገንዘብ ድጋፍ ሥልቶች እንዲፈጠሩ መታገል ይኖርባታል። ከዚኽ አንጻርም፣ ከዕዳ ነፃ የሆኑ የአየር ንብረት የገንዘብ ድጋፍ አማራጮችን ማቅረብ፣ ለአየር ንብረት መላመድ የሚውሉ የገንዘብ ምንጮችን ማሰስ፣ ለጉዳት እና ለኪሳራ የገንዘብ ድጋፍ አልያም ፈንድ የሚውሉ ገንዘቦች የሚለቀቁበትን ሕግ ማሻሻል እና ለጋሾች የሰጧቸውን እና የሚሰጧቸውን የድጋፍ ቃሎች መሬት ላይ ካሉት ተጨባጭ የአየር ንብረት ተኮር ዕቅዶች ጋር የሚያስተሳስሩ ግልጽ ዕቅዶችን ማዘጋጀትን ይጠይቃል። ይኽ ጉባኤውን የማዘጋጀት ዕድል፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካን የአየር ንብረት ሥጋቶች ለማስተዋወቅ እና በዓለም ዓቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ ያላትን ቦታ ለማጠናከር የሚያስችላት ስትራቴጂካዊ ዕድል እንደመሆኑ፣ ዲፕሎማሲያዊ አካሄዷ ልክ እንደ ጉባኤው ዝግጅቷ ኹሉ እጅጉን አስፈላጊ ነው። የአየር ንብረት ጉባኤን መምራት የተለያዩ ፍላጎቶች ካሏቸው ቡድኖች ጋር አታካች ድርድሮች ማድረግን ይጠይቃል። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ባለፈ አጋርነትን ለመፍጠር ልምድ ያላቸውን ተደራዳሪዎች እና የአየር ንብረት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን ማሰማራት ይኖርባታል። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ልማት፣ በአየር ንብረት መቋቋም በሚችል ግብርና እና በአረንጓዴ አሻራ የደን ልማት መርሃ-ግብር ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች ለዓለም የምታሳያቸው ስኬቶቿ ናቸው። ሆኖም አገራዊ ተግዳሮቶች አሁንም አሉ። በቅርቡ የታዩ የውስጥ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች ኢትዮጵያ ያላትን የማስተባበር አቅም ሊፈታተኑ ይችላሉ። በተጨማሪም ከ30,000 በላይ ተሳታፊዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል የመሠረተ-ልማት ግንባታ፣ አስተማማኝ የኃይል እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትስስር፣ የትራንስፖርት እና የመጓጓዣ ደኅንነት እና የመስተንግዶ አገልግሎት ማቅረብ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ከባድ ሥራ መሆኑን በቅጡ ማሰብ ያስፈልግ ይመስላል። በተለይም፣ ካለፉት ጥቂት ሳምንታት አንስቶ የተቀሰቀሰው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት፣ ጉባኤው በሚካሄድበት ወቅት ጭምር ምን ዓይነት ዓለም ዓቀፋዊ ውጥንቅጦችን እንደሚያመጣም ዛሬ ነገ ሳይሉ ተቋማዊ መላዎችን ማዘጋጀት አሌ የሚባል ሥራ አይደለም።

ለአፍሪካ አርአያነት

የኢትዮጵያ ስኬት አህጉሪቱ የአየር ንብረት የገንዘብ ምንጭን ለመጠቀም ካላት ግብ ጋር ይጣጣማል። እንደ ተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ገለጻም፣ የካርቦን ገበያ ለአፍሪካ አገራት ተፈጥሮአዊ ሀብታቸውን ወደ ገንዘብ ለመቀየር ትልቅ ዕድል ይሰጣቸዋል። ኢትዮጵያም በዚኽ ዘርፍ እንደ ኬንያ፣ ሩዋንዳ እና ጋና ካሉ ቀዳሚ አገራት ተርታ ተሰልፋለች። የአረንጓዴ አሻራ ፋይዳ ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ለወጣቶች እና ለሴቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩም ተጠቅሷል። በተጨማሪም የደን ሽፋን መጨመሩ የውኃ ሀብትን ለመጠበቅ፣ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እና የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ይረዳል። ያም ሆኖ ግና፣ ባለሙያዎች እንደሚጠቁሙት ችግኝ መትከል የመጀመሪያው እርምጃ ሲሆን፣ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ ደኖችን መጠበቅ፣ ወጥ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ እና ያልተቋረጠ ሙያዊ እገዛ ያስፈልጋል። ተቋማዊ ገለልተኛ ክትትል እና ግልጽነት ያለው ወቅታዊ ሪፖርት ማቅረብም፣ ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የምታቀርበውን የካርቦን ልቀት እና ተያያዥ የአየር ንብረት ስኬቶች ተዓማኒነት ለማቆየት ወሳኝ መሆናቸውም ይጠቀሳል። ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ጥበቃ እርምጃዎችን ከገንዘብ ምልሰት ጋር በማጣመር በማሳየት ላይ ያለችው ተሞክሮ ለሌሎች በማደግ ላይ ላሉ አገራት ጠቃሚ ትምህርት ይሰጣል ተብሎም በተለያዩ ተቋማት ይወደሳል። የአለም ትኩረት ወደ ተፈጥሮ-ተኮር መፍትሔዎች እየዞረ ባለበት በዚኽ ወቅት፣ የኢትዮጵያ ሞዴል ለደቡባዊው የዓለም ክፍል አገራት አርአያ ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያ የናይጄሪያን ተቀናቃኝነት በመሻገር ይኽንን ዕድል ማግኘቷ፣ አዲስ አበባ የአየር ንብረት ጉዳት ለሚደርስባት፣ የገንዘብ ድጋፍ ለሚያጥራት እና ልማትን ከአየር ንብረት መቋቋም ጋር ማጣጣም ለምትፈልገው አፍሪካ ድምፅ እንድትሆን መድረክ ይፈጥርላታል። የኢትዮጵያ መመረጥ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት አሥተዳደር ላይ አስቸጋሪ ኹኔታዎች ባሉበት ወቅት የመጣ መሆኑንም ማስታወስ ያሻል። ከዚኽ ቀደም በነበሩ ጉባኤዎች ላይ የተገቡ ቃል ኪዳኖች ወደ ተግባር አልተቀየሩም። እ.አ..አ. በ2009 ላይ፣ የበለጸጉ አገራት በየዓመቱ 100 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት የሰጡት ቃል እስከ አኹን አልተተገበረም፤ አፍሪካም በየዓመቱ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ከ7 እስከ 15 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ኪሳራ እየደረሰባት ትገኛለች። ከዚኽ አንጻርም፣ የአፍሪካ የድርድር ዕድል ምን ሊሆን ይችላል ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። እናም፣ የአፍሪካ ተደራዳሪዎች የኢትዮጵያን አዘጋጅነት ተጠቅመው ዓለም ዓቀፍ የአየር ንብረት የመዋዕለ-ንዋይ ፍሰት ነክ ሕግጋትን ከአህጉሪቱ ነባራዊ ኹኔታ ጋር እንዲጣጣሙ ለማድረግ መታገል የሚችሉበትን ዕድል ጉባኤው ይፈጥራል ተብሎ በብዙዎች ዘንድ ይገመታል። በተጨማሪም አፍሪካ በታዳሽ ኃይል እና በአረንጓዴ ማዕድናት ያላትን አቅም በማሳየት የባሕር ማዶ መዋዕለ-ንዋይን የምትስብበትን ዕድል ልታገኝ ትችላለች።

ዳራውን በጨረፍታ

የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን፣ በዓለም ላይ ያሉ አገራት ኹሉ ተሰባስበው የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን አስቸጋሪ ፈተናዎች ለመፍታት የሚመክሩበት መድረክ ነው። በዚኽ ጉባኤ ላይ አገራት በአየር ንብረት መላመድ፣ በልቀት ቅነሳ፣ በገንዘብ ድጋፍ፣ በፍትሕ፣ በጤና እና በዘላቂ ልማት ስልቶች ላይ ይደራደራሉ። በአኹኑ ወቅት 198 ወገኖች (197 አገራት እና የአውሮፓ ኅብረት) የዚኽ ስምምነት አባል ናቸው። የጉባኤው ዋነኛ ግብ በከባቢ አየር ውስጥ ያለውን የግሪንሃውስ ጋዝ ክምችት የሰውን ልጅ እና የአየር ንብረት ሥርዓቱን በማይጎዳ መልኩ ማረጋጋት ነው። እ.አ.አ. በ1994 የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስምምነት በሥራ ላይ ዋለ። ይኽንን ስምምነት ያጸደቁት አገራትም በየዓመቱ በተለያዩ ከተሞች በመገናኘት ‘የአባልት ጉባኤ’ (Conference of the Parties – COP) የተሰኘውን ጉባኤ ማካሄድ ጀመሩ። በ1997 በተካሄደው ሦሥተኛው ዓመታዊ ስብሰባ (ኮፕ3) ላይ የኪዮቶ ፕሮቶኮል የተሰኘው ስምምነት ጸደቀ። በካናዳ ሞንትሪያል ከተማ በተካሄደው ኮፕ11 ላይም፣ የኪዮቶ ፕሮቶኮል ከጸደቀ በኋላ የመጀመሪያው ይፋዊ የስምምነቱ ወገኖች ስብሰ ተካሄደ፤ ቡድኑም በየዓመቱ መገናኘቱን ለመቀጠል ተስማማ። የኮፕ ስብሰባዎች በተለምዶ የሚጀምሩት በጠቅላላ ጉባኤ ሲሆን፣ ተወካዮቹም ዋና ዋና የሚሏቸውን አጀንዳዎች ያቀርባሉ። ለተሳለጠ ውይይትም ሲባል አጀንዳው በተለያዩ የድርድር ቡድኖች ይከፈላል፤ አነዚኽም፣ የካርቦን ልቀት ቅነሳ፣ የአየር ንብረት መላመድ፣ የገንዘብ ድጋፍ ወይም ምንጭ ፋይናንስ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር የተሰኙት ናቸው። ከ‘ነዚህ ስብሰባዎች ጎን ለጎን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ሌሎች አካላት የፈጠራ መፍትሔዎቻቸውን የሚያሳዩባቸው የአዳራሽ ዕይታዎች እና የጎንዮሽ ኩነቶች ይካሄዳሉ። በእያንዳንዱ ጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይ አገራት የደረሱባቸውን ስምምነቶች ‘የኮፕ ውሳኔ’ ተብሎ በሚጠራው ሰነድ ውስጥ ተጠቃልለው እንዲወጡ ይደረጋል። እ.አ.አ. ከታኅሣሥ 3-14 ቀን 2007 በኢንዶኔዥያ ባሊ ከተማ የተካሄደው የባሊ ጉባኤ፣ የዓለምን የአየር ንብረት ለውጥ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በ2015 በፓሪስ በተካሄደው ኮፕ21 ላይ ደግሞ የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት ጸደቀ። እኒኽ የኮፕ ጉባኤዎች በ21ኛው ክፍለ ዘመንም በየዓመቱ መካሄዳቸውን ቀጥለዋል። በእነዚኽ ተከታታይ ጉባኤዎች ላይ አንድ ለየት ያለው ኹነት፣ የበዛ የካርቦን ልቀት እያስከተለች ነው ተብላ በብዙ የአየር ንብረት ተቺዎች ዘንድ የምትወቀሰው የአሜሪካ ጉዳይ ነበር። በለረጅም ጊዜ አሜሪካ ከሌሎች የአውሮፓ እና በማደግ ላይ ካሉ አገራት ጋር በሐሳብ ትለያይ ነበር፤ ምክንያቱም አገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚወሰኑ ግቦች መገደድ የለባቸውም ብላ ማመኗ ነበር። አሜሪካ የአየር ንብረት ለውጥ መፈታት ያለበት እያንዳንዱ አገር በፈቃደኝነት በሚያስቀምጠው ግብ ነው የሚል አቋም ይዛ ሰንብታለች። ሆኖም በቅርብ ዓመታት የኪዮቶ ፕሮቶኮል በፓሪስ ስምምነት ሲተካ አሜሪካ አመለካከቷን በይፋ ቀይራለች። በእነዚኽ መሰሎቹ ጉባኤዎች የታዩ ኹለት ታሪካዊ ምዕራፎችንም ማንሳት ያስፈልጋል። አንደኛው የኪዮቶ ፕሮቶኮል የተሰኘው ስምምነት ሲሆን፣ እ.አ.አ. በ1997 በጃፓን ኪዮቶ ከተማ የጸደቀ ዓለም አቀፍ ስምምነት ነው። ያደጉ አገራት የግሪንሃውስ ጋዝ ልቀታቸውን እ.አ.አ. ከ2008 እስከ 2012 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ1990 መጠን በ5.2 በመቶ እንዲቀንሱ የሚያስገድድ ነበር። ኹለተኛው የፓሪስ ስምምነት የተሰኘው ሲሆን፣ እ.አ.አ. በ2015 በኮፕ21 ላይ የጸደቀ ሕጋዊ አስገዳጅነት ያለው ስምምነት ነው። ዋና ግቡም የዓለም ሙቀት ከኢንዱስትሪ አብዮት በፊት ከነበረው ከ2 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንዳይጨምር፣ ከተቻለም በ1.5 ዲግሪ ሴልሺየስ ውስጥ እንዲገደብ ማድረግ ነው። አገራት በዚህ ስምምነት መሠረት የራሳቸውን የልቀት ቅነሳ ዕቅድም በየአምስት ዓመቱ እንዲያቀርቡ ይጠበቅባቸዋል። ምንም እንኳ ኮፕ ትልቅ ፋይዳ ቢኖረውም ቅሉ፣ በበለጸጉ እና በማደግ ላይ ባሉ አገራት መካከል ያለው የፖለቲካ ፍላጎት ልዩነት፣ የገንዘብ እጥረት እና የተገቡ ቃል ኪዳኖች አለመፈጸም ትልቅ ፈተና ሆነው ቀጥለዋል። ብዙዎች እንደሚሉትም፣ ያለ እነዚህ ዓለም ዓቀፍ ድርድሮች የዓለም ሙቀት በ5 ዲግሪ ሴልሺየስ ሊጨምር ይችል ነበር፤ ከዚኽ መንፈስ አኳያም፣ ከላይ እንደጠቅስነው ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ጥበቃ የሚሆኑ ኹነኛ ፖሊሲዎችን ቀርጻ ወደተግባር ከገባች ብትሰነባብትም፣ ሌሎች በተለይም የበለጸጉ አገራት ተግባራቸውን ማፋጠን ይኖርባቸዋል። በመጨረሻም፣ ይኽ ዕድል እንዲሳካ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጃቸውን ላዋጡ ኢትዮጵያውያን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የአፍሪካ ወንድሞች እንኳን ደስ አላችኹ ማለት እንሻለን።