BRIDGE Research & Innovation - Parliaments. Peace. Policy

የመካከለኛው ኢትዮጲያ ክልል ሕገ መንግሥስት ስለ ክልሉ ምክር ቤት

አንቀጽ 52. የክልሉ መንግስት ምክር ቤቶች

የክልሉ መንግስት የክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት ይኖሩታል፡፡

አንቀጽ 53.የምክር ቤቶች የወል ድንጋጌዎች

  1. እያንዳንዱ ምክር ቤት፡-

ሀ) ተጠሪነቱ ለምክር ቤቱ የሆነ የራሱን አፈ-ጉባዔ እና ምክትል አፈ-ጉባዔ በምክር ቤቱ ዉስጥ አብላጫ ድምጽ ባገኘዉ የፖለቲካ ድርጅት ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች አቅራቢነት
በምርጫ ይሰይማል፤ለሥራ የሚያስፈልጉ ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎችን ያደራጃል፤

ለ) የሥራ ዘመኑ አምስት ዓመት ሆኖ ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ ይሰበሰባል፡፡

  1. እያንዳንዱ የምክር ቤት አባል፡-

ሀ) በምክር ቤቱ ውስጥ በሚሰጠው ድምፅ ወይም አስተያየት ምክንያት አይከሰስም፤ አስተዳደራዊ እርምጃም አይወሰድበትም፤

ለ) ከባድ ወንጀል ሲፈፅም እንጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ አይያዝም በወንጀልም አይከሰስም፤

ሐ) የመረጠው ሕዝብ አመኔታ ባጣበት ጊዜ ከምክር ቤት አባልነቱ ይወገዳል፤ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፤

መ) በዚህ ንዑስ አንቀጽ (ሀ) ላይ የተደነገገው እንደ አግባብነቱ በየእርከኑ ለሚገኙ
ምክር ቤቶች እና አባላት ተፈፃሚነት አለው፤

ሠ) አንድ ሰዉ በአንድ ጊዜ የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አባል መሆን አይችልም፡፡


         ክፍል ሁለት

የክልሉ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣አደረጃጀት፣ሥልጣንና ተግባር

አንቀጽ 54. የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት

  1. ሁሉ አቀፍ፣ ነፃና ቀጥተኛ በሆነ፣ ድምጽ በምስጢር በሚሰጥበት ስርዓት በየአምስት ዓመቱ በህዝብ ይመረጣሉ፤
  2. በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች መካከል አብላጫ ድምጽ ያገኘ ተወዳዳሪ አሸናፊ በሚሆንበት የምርጫ ስርዓት ይመረጣሉ፤
  3. በንዑስ አንቀጽ 2 የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ልዩ ውክልና የሚያስፈልጋቸዉ የማህበረሰብ ክፍሎች በምርጫ በክልሉ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ይወከላሉ፤ ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል፤
  4. የመላው የክልሉ ህዝብ ተወካዮች ናቸው፡፡ ተገዥነታቸውም፡-

               ሀ) ለኢፌዴሪ ሕገ መንግስት፣ለክልሉ ሕገ መንግስት እና ለህግ

                ለ) ለክልሉ ህዝብ፤ እና

               ሐ  ለራሳቸው ህሊና ብቻ ነዉ፡፡

      5.ማንኛዉም የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የወከለዉን ህዝብ ማህበራዊ፣ አኮኖሚዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን መከታተል፣ ለምክር ቤቱ ማሳወቅ እና መፍትሔ ለማስገኘት ጥረት ማድረግ አለበት፤

  1. በዚህ ንዑስ አንቀጽ 1 እስከ 4 ያሉ ድንጋጌዎች እንደ አግባብነታቸው በየእርከኑ ለሚገኙ የምክር ቤት አባላት ተፈፃሚነት አላቸው፡፡

አንቀጽ 55. የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስልጣንና ተግባር

  1. የክልሉ ከፍተኛ የህግ አውጪ አካል ነው፤
  2. የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ በክልሉ የውስጥ ጉዳዮች ላይ የበላይ የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት ነው፤
  3. የፌደራሉን ህገ መንግስት፣ ይህን ሕገ መንግስትና ሌሎች ህጎችን የማይፃረሩ ለክልሉ ተለይተዉ በተሰጡ እና በክልሉ ውስጥ ተፈፃሚ በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ ህጎችን ያወጣል፤
  4.  በዚህ ሕገ መንግስት አንቀጽ 47 በተደነገገው አግባብ የአደረጃጀት ጉዳዮችን ይወስናል፤ዝርዝር ህጎችን ያወጣል  የፌደራል መንግስት ስልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ ክልሉ ከሌሎች ክልል መንግስታት ጋር  የሚደረገውን ስምምነት መርምሮ ያፀድቃል፤
  5. በክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ ድምጽ ካለው ፖለቲካ ድርጅት የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ሹመት ያፀድቃሉ፤
  6. በርዕሰ መስተዳድሩ አቅራቢነት የክልል መስተዳድር ምክር ቤት አባላትን ሹመት ያፀድቃል፤
  7. የክልሉን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎችንና ፕሮግራሞችን ያፀድቃል፤
  8. የክልሉን የገቢ ምንጮች የሚመለከቱ ህጎችን ያወጣል፤ ለክልሉ መንግስት ተለይቶ በተሰጠው የገቢ ምንጭ ላይ በክልሉ ውስጥ ግብርና ታክስ ይጥላል፤
  9. የክልሉን መንግስት በጀት ያፀድቃል፤
  10. የክልሉን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና አስተዳደራዊ ሥራዎች የሚያከናውኑ፣ የሚያስተባብሩና የሚመሩ ልዩ ልዩ ቢሮዎችን፣ ኮሚሽኖችንና ሌሎች መሥሪያ ቤቶችን
    እንደ አስፈላጊነታቸው በሕግ ያቋቁማል፤
  11. የዳኞችን ሹመት በዳኝነት አስተዳደር ዋና ጉባኤ አቅራቢነት ያጸድቃል. በርዕሰመስተዳድሩ አቅራቢነት የክልሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ሹመት ያፀድቃል፤
  12. የኦዲትና ሌሎች የቁጥጥር አካላትን ያቋቁማል፣ ዋና ኦዲተሩን እና ምክትል ዋና ኦዲተሩን ይሾማል፤
  13. የዋና ኦዲተርና የቁጥጥር አካሉን አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር በህግ ይወስናል፤
  14. የክልሉን መንግስት ሰራተኞች አስተዳደርና የስራ ሁኔታዎችን በተመለከተ ህግ ያወጣል፤  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያፀድቃል፤
  15. የክልሉን ርዕሰ መስተዳድርና ሌሎች የክልሉን መንግስት ባለስልጣናት ለጥያቄ ይጠራል፣ የአስፈፃሚውን አካል አሰራር ይመረምራል፤ የማስተካከያ ሀሳብና የሥራ
    አቅጣጫ ይሰጣል፤ አመኔታ ባጣ ጊዜም እርምጃ ይወስዳል፤
  16. የራሱን ጽህፈት ቤት ያደራጃል፤
  17. በዚህ ሕገ መንግስት አንቀጽ 30 ስር የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ በህግ መሠረት ምህረት ያደርጋል፤
  18. የፖሊስ ሀይል ያደራጃል፤
  19. ሌሎች የክልሉን መንግስት በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ህግ ያወጣል፡፡

አንቀጽ 56. የፖለቲካ ስልጣን

  1. በክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ የፖለቲካ ድርጅቶች የክልሉን መስተዳድር ምክር ቤት ያደራጃል፣ይመራል ወይም
    ያደራጃሉ፣ይመራሉ፤
  2. በክልል የህዝብ ተወካይ ምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ የፖለቲካ ድርጅቶች ከክልሉ ህዝብ ተወካይ ምክር ቤት አባላት መካከል የምክር ቤቱን ዋና አፈ-ጉባዔንና ምክትል አፈ-ጉባዔን በማቅረብ ያሰይማል፣ያሰይማሉ፤
  3. የዚህ ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 ድንጋጌዎች እንደአግባብነታቸው በየእርከኑ ለሚገኙ ምክር
    ቤቶች ተፈፃሚነት ይኖራቸዋል፡፡

አንቀጽ 57. ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት

  1. የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የራሱ የሆነ አደረጃጀት ያለው ተጠሪነቱ ለምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ የሆነ ጽህፈት ቤት ይኖረዋል፤
  2. የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሀላፊ በአፈ-ጉባኤው አቅራቢነት በአስተባባሪ ኮሚቴ ይሾማል፤
  3. በምክር ቤቱ ስር ቋሚ ኮሚቴዎች ይደራጃሉ፤
  4. የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ስልጣንና ተግባራት የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚያወጣው ህግ ይወሰናል፤
  5. የዚህ አንቀጽ ድንጋጌ እንደ አግባብነቱ በየደረጃዉ ለተቋቋመ ምክር ቤት ተፈፃሚነት አለው፡፡

አንቀጽ 58. የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባስልጣንና ተግባር፣ የስልጣን ዘመን

የክልሉ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የሚከተሉት ስልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡-

  1. የምክር ቤቱን መደበኛና አስቸኳይ ስብሰባዎች ይጠራል፤ይመራል፤
  2. ምክር ቤቱን በሶስተኛ ወገኖች ዘንድ ይወክላል፤
  3. የምክር ቤቱን ጽህፈት ቤት ያደራጃል፤ጠቅላላ የአስተዳደር ሥራዎችን በበላይነት ይመራል፤
  4. ምክር ቤቱ በአባሎች ላይ የወሰነውን የዲስፕሊን እርምጃ ያስፈጽማል፤
  5. የምክር ቤቱን ጽህፈት ቤት አደረጃጀት በህግ ያስወስናል፤
  6. የምክር ቤቱን ጊዜያዊና ቋሚ ኮሚቴዎችን ያስተባብራል፤
  7. በህግ የተሰጡትን ሌሎች ተግባራት ያከናዉናል፤
  8. የአፈ- ጉባኤው የስልጣን ዘመን ለተከታታይ ሁለት የምርጫ ዘመን የተገደበ ነው፤
  9. የዚህ አንቀጽ ድንጋጌ እንደ አግባብነቱ በየደረጃዉ ለተቋቋመ ምክር ቤት ተፈፃሚነት አለው፡፡

አንቀጽ 59. የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባስልጣንና ተግባር

የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ የሚከተሉት ስልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡-

  1. በአፈ-ጉባዔው ተለይተው የተሰጡትን ተግባራት ያከናውናል፤
  2. አፈ-ጉባዔው በማይኖርበት ወይም ሥራውን ለማከናወን በማይችልበት ጊዜ ተክቶ ይሰራል፤
  3. የአፈ- ጉባኤው የስልጣን ዘመን ለተከታታይ ሁለት የምርጫ ዘመን የተገደበ ነው፡፡

አንቀጽ 60. የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስብሰባ ጊዜ፣የራ ዘመን እና ውሳኔ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት

  1. ምክር ቤቱ በዓመት ቢያንስ ሁለት ጊዜ መደበኛ ስብሰባ ያደርጋል፤
  2. ከምክር ቤቱ አባላት ውስጥ ሁለት ሶስተኛ ከተገኙ ምልዓተ-ጉባኤ ይሆናል፤
  3. በዚህ ህገ መንግስት በተለየ ሁኔታ ካልተደነገገ በስተቀር ማናቸውም ውሳኔዎች የሚተላለፉት በስብሰባው ላይ ከተገኙት የምክር ቤት አባላት ውስጥ በአብላጫ ድምጽ ይሆናል፤
  4. የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን አንድ የምርጫ ዘመን ይሆናል፤
  5. ምክር ቤቱ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሄዶ ይጠናቀቃል፤
  6. የቀድሞው ምክር ቤት የሥራ ዘመን በተጠናቀቀ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አዲሱ ምክር ቤት ሥራውን ይጀምራል፤
  7. ምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ በማያደርግበት ወቅት አፈ-ጉባኤው አስቸኳይ ስብሰባ ሊጠራ ይችላል፤
  8. ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ከአንድ ሶስተኛ በላይ የሆኑት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ ከጠየቁ አፈ-ጉባዔው የምክር ቤቱን ስብሰባ የመጥራት ግዴታ አለበት፤
  9. የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ በግልጽ ይካሄዳል፣ ሆኖም ስብሰባው በዝግ እንዲካሄድ በምክር ቤቱ አባላት ከተጠየቀና ከምክር ቤቱ አባላት መካከልከግማሽ በላይ የሚሆኑት ጥያቄውን ከደገፉ ምክር ቤቱ ዝግ ስብሰባ ሊያደርግ ይችላል፤

አንቀጽ 61. የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ አጸዳደቅ እና የአሰራር ስነ-ስርዓት

  1. ምክር ቤቱ መክሮበት በአብላጫ ድምጽ የተስማማበት ህግ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ለፊርማ ይቀርባል፤
  2. ርዕሰ መስተዳድሩ በንዑስ አንቀጽ 1 የቀረበለትን ህግ በአስራ አምስት ቀናት ውሰጥ ካልፈረመ ህጉ በክልሉ ነጋሪት ጋዜጣ ታውጆ በሥራ ላይ ይዉላል፤
  3. ምክር ቤቱ የህግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ህግ ሊያወጣ ይችላል፤
  4. የምክር ቤቱን የአሰራር ሥነ ሥርዓት እና የአባላት የስነ ምግባር ደንብ ሊያወጣ ይችላል፣
  5. የዚህ አንቀጽ ድንጋጌ እንዳስፈላጊነቱ ለዞን፣ለልዩ ወረዳ፣ ለወረዳ፣ለከተማ አስተዳደር እና ለቀበሌ
    ምክር ቤቶች ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

አንቀጽ 62. ስለ ክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መበተን

  1. ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ ምክር ቤቱ የስልጣን ዘመን ከማብቃቱ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሔድ በክልሉ ምክር ቤት ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን ለማድረግ ይችላል፣
  2. በጣምራ የመንግሥት ሥልጣን የያዙ የፖለቲካ ድርጅቶች ጣምራነታቸው ፈርሶ በምክር ቤቱ የነበራቸውን አብላጫነት ያጡ እንደሆነ የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ተበትኖ በክልሉ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሌላ ጣምራ መንግሥት በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለመመስረት እንዲቻል ርዕሰ መስተዳድሩ የፖለቲካ ድርጅቶችን ይጋብዛል፤ የፖለቲካ ድርጅቶቹ አዲስ መንግሥት ለመመስረት ወይም የነበረውን ጣምራነት ለመቀጠል ካልቻሉ የክልሉ ምክር ቤት ተበትኖ አዲስ ምርጫ ይደረጋል፣
  3. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ወይም 2 መሰረት የክልሉ ምክር ቤቱ የተበተነ እንደሆነ ከስድስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አዲስ ምርጫ መደረግ አለበት፣
  4. ምርጫው በተጠናቀቀ በሠላሳ ቀናት ውስጥ አዲሱ የክልሉ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥራውን ይጀምራል፣
  5. የክልሉ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተበተነ በኋላ ክልሉን የሚመራው ሥልጣን ይዞ የነበረው የፖለቲካ ድርጅት ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች ጣምራ የዕለት ተዕለት የመንግሥት ሥራ ከማከናወንና ምርጫ ከማካሔድ በስተቀር አዲስ አዋጆችን፣ ደንቦችንና ድንጋጌዎችን ማውጣት ወይም ነባር ሕጎችን መሻርና ማሻሻል አይችልም፣
  6. የዚህ አንቀጽ ድንጋጌዎች እንደ አግባብነቱ በዞን፣ በልዩ ወረዳ፣ በወረዳ፣ በከተማ አስተዳደር እና በቀበሌምክር ቤቶች ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

                

   ክፍል ሦስት

የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት

አንቀጽ 63. የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አባላት

  1. የብሔረሰቦች ምክር ቤት በክልሉ የሚገኙት ብሔሮች፣ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቢያንስ በአምስት አባላት የሚወከሉበት ምክር ቤት ነዉ፤
  2. ከእያንዳንዱ ብሔር፣ብሔረሰብ፣ ህዝብ ቢያንስ በአንድ ሚሊዮን ህዝብ አንድ ተጨማሪ አባላት ይወከላል፤
  3. የብሔረሰቦች ምክር ቤት አባላት በዞን ወይም በልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች በአብላጫ ድምጽ ይመረጣሉ፤የዞን ወይም የልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች በራሳቸው ወይም በቀጥታ በህዝብ እንዲመረጡ በማድረግ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አባል እንዲወከል ያደርጋል፡፡
  4. በንኡስ አንቀጽ 3 የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ በዞን ወይም በልዩ ወረዳ ያልተወከሉ በወረዳ ምክር ቤቶች በአብላጫ ድምጽ ጸድቆ ይወከላሉ፡፡

አንቀጽ 64. የብሔረሰቦች ምክር ቤት ስልጣንና ተግባር

  1. የክልሉን ሕገ መንግስት ይተረጉማል፤
  2. የክልሉን ሕገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ ያደራጃል፤
  3. የክልሉ ብሔሮች፣ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የዞን፣ የልዩ ወረዳ እና የወረዳ አስተዳደር መብት የሚነሱ ጥያቄዎች በዚህ ሕገ መንግስት መሰረት ይወሰናል፤
  4. የክልሉን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተው አንድነት እንዲጠናከር እና እንዲጎለብት ያደርጋል፤
  5. በክልሉ ውስጥ በሚገኙ አስተዳደር እርከኖች መካከል ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሔ ያፈላልጋል፤ውሳኔ ይሰጣል፤
  6. በክልሉ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች መካከል ሊነሱ የሚችሉ አለመግባባቶች እልባት እንዲያገኙ ያደርጋል፤ውሳኔ ይሰጣል፤
  7. በክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልዩ ውክልና የሚያስፈልጋቸዉ ማህበረሰብ ክፍሎችን በህግ ይወስናል፤
  8. የክልሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ በሚጎለብትበት ሁኔታ ላይ ይሰራል፤
  9. የክልሉ ሕገ መንግስት ማሻሻያ ሀሳብ በማመንጨትና በማሻሻል ሂደት ዉስጥ ይሳተፋል፤
  10. ከአጎራባች ክልል መንግስታት ጋር በሚነሱ አለመግባባቶች እና የወሰን መካለል ጥያቄዎች ከክልሎቹ ጋር በጋራ አጥንቶ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል፤ አፈፃፀሙንም ይከታተላል፤
  11. የራሱን በጀት ለክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ያስወስናል፤
  12. የራሱ የሆነ አደረጃጀት ያለው፣ በዋና አፈ ጉባዔ አቅራቢነት የሚሾም፣ ተጠሪነቱ ለምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ የሆነ ኃላፊ ያለው ጽሕፈት ቤት ይኖረዋል፤ ዝርዘሩ በህግ ይወሰናል፤
  13. የራሱን አፌ-ጉባዔና ምክትል አፈ-ጉባዔ ይመርጣል፤
  14. ልዩ ልዩ ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎችን፣የስራ ክፍሎችን ያቋቁማል፤ ያስተዳድራል፤
  15. የክልሉን የበጀት ቀመር ይወስናል፤ የበጀት ክፍፍል ፍትሀዊነትን፣የብሔሮች፣ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል፣ይከታተላል፤ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል፡፡

አንቀጽ 65. የውሳኔ እና ሥነ-ስርዓት ደንቦች

  1. ከአባላቱ መካከል ሁለት ሶስተኛ የተገኙ እንደሆነ ምልዓተ ጉበዔ ይሆናል፤
  2. ማንኛዉም የምክር ቤቱ ዉሳኔ ስብሰባ ላይ በተገኙ አባላት አብላጫ ድምጽ ይተላለፋል፤
  1. የምክር ቤቱን የአሰራር ሥነ-ሥርዓት እና የአባላት የሥነ-ምግባር ደንብ ሊያወጣ ይችላል፡፡

አንቀጽ 66. የብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ-ጉባስልጣንና ተግባር፣ የስልጣን ዘመን

  1. የምክር ቤቱን አስቸኳይ እና መደበኛ ስብሰባዎች ይጠራል፣ይመራል፤
  2. ምክር ቤቱን ይወክላል፣ጠቅላላ የአስተዳደር ሥራዎችን ይመራል፤
  3. ምክር ቤቱ በአባላት ላይ የወሰደውን የዲስፒሊን እርምጃ ያስፈጽማል፤
  4. የምክር ቤቱን ጽህፈት ቤት ያደራጃል፤
  5. የምክር ቤቱን ጊዜያዊና ቋሚ ኮሚቴዎችን ያስተባብራል፤
  6. በምክር ቤቱና በህግ የተሰጡትን ሌሎች ተግባራትን ያከናውናል፤
  7. የአፈ- ጉባኤው የስልጣን ዘመን ለተከታታይ ሁለት የምርጫ ዘመን የተገደበ ነው፡፡

አንቀጽ 67. የብሔረሰቦች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባስልንና ተግባር

  1. አፈ-ጉባዔው በማይኖርበት ወይም ሥራውን ማከናወን በማይችልበት ጊዜ ተክቶ ይሰራል፤
  2. በአፈ-ጉባዔው ተለይተው የተሰጡትን ተግባራት ያከናውናል፤
  3. የምክትል አፈ- ጉባኤው የስልጣን ዘመን ለተከታታይ ሁለት የምርጫ ዘመን የተገደበ ነው፡፡