“አዲሱ የታሪክ ምዕራፍ”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ.ር. ዐቢይ አሕመድ፣ በትናትናው ውሏቸው በትምህርት እና ተያያዥ ማኅበራዊ የመንግስታቸው ፖሊሲዎች ዙሪያ ዘርዘር ያሉ ነጥቦችን አንስተዋል። በትምህርት ዘርፍ ጥራት ያለው ትምህርት በፍትሓዊነት የማድረስ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስቀድመው የጠቅሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የትምህርት ጥራትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ታችኛው ትውልድ ላይ በማተኮር መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፤ ለዚህም ወደ 34ሺ መዋዕለ ሕጻናት ተገንብቶ የነገ የአገር ተረካቢዎቹ ሕጻናት እየተማሩ መሆኑን ገልጸዋል። በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ደረጃን የማሻሻል፣ የመምህራን ዐቅምን የማጎልበት፣ የተማሪዎችን የቴክኖሎጂ ዕውቀት እና ክህሎት የማሳደግ ሥራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል። የጤናውን ዘርፍ በተመለከተ ኹሉን ዓቀፍ የጤና ተደራሽነት እና ጥራት ለማሳደግ ልዩ ትኩረት በመስጠት በመከላከሉ እና አክሞ የማዳን ተግባራትን በማቀናጀት በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን የጠቀሱት የተከበሩ ዶ.ር. ዐቢይ፣ በዘርፉ በተሰራው ማሻሻያ ውጤት የተገኘ ቢሆንም ብዙ ሥራ ይጠይቃል ሲሉ ተደምጠዋል። በማሳያነት ያነሱት በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች 63 በመቶ መድረሱን እና የሚሞቱ እናቶች ቁጥርም መቀነሱን ሲሆን፤ ከጥቂት ወራት በፊት ተከስቶ የነበረው የማርበርግ በሽታን ሦሥት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር መቻሉንም በማሳየነት አክለው ጠቅሰዋል።
የነገውን ብርቱ ውድድር ለማሸነፍ የዛሬው ዝግጅት ወሳኝ መሆኑን ለእንደራሴዎች ሲናገሩ የተደመጡት የገዢው ፓርቲ ፕሬዝደንት፣ ወጣቶችን ለላቀ ስኬት ለማብቃት መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ረገጥ አድርገው ሲናገሩ ተስተውለዋል። ከአገሪቱ አምስት የዕድገት ምሰሶዎች መካከል አንዱ ቴክኖሎጂ እንዲሆን መደረጉ ለትውልድ የተሰራ ትልቅ መዋዕለ-ንዋይ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይም በሰው ሰራሽ አእምሮ ረገድ ኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየከፈተች መሆኗን አብራርተዋል። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በዓለም ኹለተኛ የሆነውን ግዙፍ የሰው ሰራሽ አእምሮ ዩኒቨርሲቲ ለመገንባት በከፍተኛ ፍጥነት እየሰራች ሲሆን፣ ይኽ ታላቅ የትምህርት ተቋም በሚቀጥለው አንድ ዓመት ውስጥ ሥራ እንደሚጀምርም ተናግረዋል። አባቶቻችን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ገንብተው በዓለም ስመ-ጥር እንዳደረጉት ኹሉ፣ ይኽ ዩኒቨርሲቲም ለኢትዮጵያ ልጆች የተሻለ ዘመንን እና ብሩህ የወደፊት እድልን ይዞ ይመጣል ሲሉ ተስፋቸውን ለእንደራሴዎቹ አጋርተዋቸዋል።
“ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ኮሜርሺያል ብድር አልተበደረችም”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ.ር. ዐቢይ አሕመድ፣ በትናንትው የዕለተ-ማክሰኞ የምክር ቤቱ ውሏቸው፣ ዘለግ ያለ ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች ቀዳሚው፣ ከዓመት ከመንፈቅ አንስቶ መንግስታቸው የተከተለውን የዐብይ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤቶችን በቁጥራዊ መረጃዎች ጭምር አስደግፈው ያብራሩበት ኢኮኖሚ ተኮሩ ርዕሰ-ጉዳይ ነበር። የኢኮኖሚው ማሻሻያ ዋንኛ ዓላማዎች፣ የዐብይ ኢኮኖሚ ስብራቱን ማረጋጋት፣ የኢኮኖሚ አቅጣጫዎችን ከግብርና መር ወደ ብዝሓ ዘርፍ ማሸጋገር እና የአገሪቷን የእዳ ጫና ማቃለል መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላዩ፣ በኹሉም መመዘኛ በኢትዮጵያ አመርቂ የኢኮኖሚ ስኬት ተመዝግቧል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበት፣ የሥራ አጥ ቁጥር መበራከት እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች በኢኮኖሚው እድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን በተመለከተ እንደራሴዎቹ ላነሱላቸው ጥያቄዎችን ሲመለሱም፤ በአገሪቱ የዋጋ ግሽበትን እና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ዘርፈ-ብዙ ተግባራት የተከናወኑ መሆናቸውን በማስታወስ፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም ምርት እና ምርታማነትን የበለጠ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። የኑሮ ውድነትን እና የዋጋ ግሽበትን ለመቀየር በቀጣይ በምግብ ማምረት፣ በቤት ግንባታ፣ በትራንስፖርት እና በትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ ዘርፎች ላይ መንግስት የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ መሆኑንም ለምክር ቤቱ አባላት ጠቅሰውላቸዋል። በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት በአገር ውስጥ ለ2.6 ሚሊየን ዜጎች የሥራ እድል የተፈጠረ ሲሆን፣ በውጭ አገራት ደግሞ ከ350 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል የተመቻቸላቸው መሆኑም ተሰምቷል።
በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበት፣ የሥራ አጥ ቁጥር መበራከት እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች በኢኮኖሚው እድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን በተመለከተ እንደራሴዎቹ ላነሱላቸው ጥያቄዎችን ሲመለሱም፤ በአገሪቱ የዋጋ ግሽበትን እና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ዘርፈ-ብዙ ተግባራት የተከናወኑ መሆናቸውን በማስታወስ፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም ምርት እና ምርታማነትን የበለጠ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። የኑሮ ውድነትን እና የዋጋ ግሽበትን ለመቀየር በቀጣይ በምግብ ማምረት፣ በቤት ግንባታ፣ በትራንስፖርት እና በትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ ዘርፎች ላይ መንግስት የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ መሆኑንም ለምክር ቤቱ አባላት ጠቅሰውላቸዋል። በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት በአገር ውስጥ ለ2.6 ሚሊየን ዜጎች የሥራ እድል የተፈጠረ ሲሆን፣ በውጭ አገራት ደግሞ ከ350 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል የተመቻቸላቸው መሆኑም ተሰምቷል።
ባለብዝሓ-ተዋናይ የኢኮኖሚ ዘርፍ ዕድገትን በመከተል በግብርናው እና በኢንዱስትሪው እንዲኹም በሌሎች ንዑስ የኢኮኖሚ ዘርፎች አመርቂ ውጤት እየተገኘበት ያለ በጀት ዓመት መሆኑን ሲያነሱም፣ መንግሥት በበጀት ዓመቱ 9.2 የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ አቅዶ በሠራቸው ውጤታማ አመላካች ሥራዎች በዓመቱ ማጠቃለያ 10.2 ጥቅል አገራዊ ዕድገት ለማስመዝገብ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠንከር አድርገው ሲናገሩ ተደምጠዋል። ለዚህም በበጀት ዓመቱ ለሚመዘገበው ጥቅል አገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት የመንግስት እና የዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) አመላካቾች ተቀራራቢ መሆናቸውንም አስታውሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ.ር. ዐቢይ ኢኮኖሚውን አስመልክቶ በጠነከረ ድምጸት ከተናገሩባቸው ጉዳዮች አንዱ፣ ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ኮሜርሻል ብድር አልተበደረችም ያሉበት የንግግራቸው ክፍል ነው። ‘ርሳቸው ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲኽ ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ኮሜርሻል ብድር እንዳልተበደረች ያነሱት ጠቅላዩ፣ ከለወጡ በፊት ኢትዮጵያ በጣም ብዙ ብድር እንደነበረባት እና አበዳሪ አገራት ኢትዮጵያ መክፈል አትችልምና አናበድርም ያሉበት ኹኔታ እንደነበረም አንስተዋል። ኢትዮጵያ ላለፉት ሃያ ዓመታት ለፕሮጀክቶች በሚል ሰበብ ጤነኛ ያልሆነ የብድር ስምምነት ወይንም ኮሜርሻል ብድር ከአንዳንድ አገራት በመበደር ለመክፈል ሳትችል መቅረቷንም ለእንደራሴዎቹ አስታውሰዋቸዋል። ኢትዮጵያ ብድር መበደር የማትችል የሚል ታርጋ ተሰጥቷት እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የተካሄደው የኢኮኖሚክ ማሻሻያ ይኽንን አሻሽሏል ብለዋል። ባለፈው ዓመት ዐሥር ፈጣን ዕድገት ከተመዘገበባቸው የዓለም አገራት መካከል አምስቱ አፍሪካውያን ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ከቀዳሚዎቹ አንዷ ናት ሲሉም በቀጥታ በተላለፈው ንግግራቸው ሲያወሱ ተደምጠዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት በኢኮኖሚው መስክ አስገራሚ መነቃቃት እያሳየች መሆኑን ሲናገሩም በማሳያነት ያነሱት፣ አገሪቷን አኹን ያላትን የውጪ ምንዛሬ ክምችት ነበር። መንግሥት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር በቢሊየኖች የሚቆጠር ድጎማ እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰው፣ አገሪቱ ባለፉት ስድስት ወራት በታሪክ የመጀመሪያ የሆነ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ አግኝታለች ብለዋል። በዚህም መሠረት ከሸቀጦች ንግድ 4.5 ቢሊየን ዶላር፣ ከአገልግሎት ዘርፍ 4.6 ቢሊዮን ዶላር፣ ከውጭ ሃዋላ 2.3 ቢሊየን ዶላር እንዲኹም ከውጭ ቀጥታ የመዋዕለ-ንዋይ ፍሰት ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ተገኝቷል ብለዋል። በዚኽ የተነሳም፣ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ክምችት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ ወደማይታወቅ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲው ፕሬዝደንት የዐብይ ኢኮኖሚ ማብራሪያቸውን በቁጥሮች አስደግፈውም ሲያብራሩ ተደምጠዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በለውጡ ጊዜ 8 ሚሊየን ሰዎችን በዓመት ያጓጉዝ እንደነበር እና ባለፉት ስድስት ወራት ግን 10 ነጥብ 7 ሚሊየን ሰዎችን ማጓጓዙን አንስተው፣ ዘንድሮ ደግሞ ቁጥሩ 22 ሚሊየን ይደርሳልም ብለዋል። በለውጡ ሰሞን 37 ሚሊየን ሰው ሞባይል ይጠቀም ነበር ያሉት ዶ.ር. ዐቢይ፣ አኹን ላይ ከ97 ሚሊየን ሰው በላይ ሞባይል እንደሚጠቀም ጠቅሰዋል። ቁጥራዊ ማብራሪያቸውን ሲለጥቁም፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሲጀመር 48 በመቶ ያመርቱ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች 66 ነጥብ 3 በመቶ መድረሳቸውን ጠቅሰው፣ ‘ርሳቸው ሪፖርት ባቀረቡበት የጊዜ ሽፋን ውስጥ ባሉት ስድሰት ወራት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች የኃይል አጠቃቀም ብቻ 16 በመቶ አድጓል ብለዋል። ከኢንዱስትሪው በመለስ በማዕድን ንዑስ የኢኮኖሚ ዘርፎችም ከፍተኛ ያሉትን ዕድገት መንግስታቸው ማስመዘገቡን ሲያብራሩ፤ የብረት ምርት 36 በመቶ፣ የሲሚንቶ ምርት ደግሞ 28 በመቶ ጨምሯል ብለዋል። ሰሞነኛው የመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት የነዳጅ ዋጋን ከፍ እና ዝቅ እያደረገው እንደሚገኝ ለእንደራሴዎቹ ያስታውሱት ርዕሰ-መንግስቱ፣ መንግስታቸው ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል የነዳጅ ዋጋ የቀየረው ሰባት ጊዜ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፣ በየቀኑ ሲጨምር ዋጋውን ከተጨመረ ሕዝባችን ይጎዳል በሚል ይኽ አለመደረጉን ተናግረዋል።
የቀደመውን የዓመት ከመንፈቅ የዐብይ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ፣ የባሕር ማዶ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ መግባት ሀገር-በቀሎቹን ይጎዳ ይሆን በሚል ዙሪያ ከእንደራሴዎቹ ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ ባንኮች ባንክ መሆን ባለባቸው ደረጃ የማደግ ሂደታቸው በውድድር መታጣት ምክንያት ውስንነት ገጥሞታል ሲሉ ምላሻቸውን ጀምረዋል። ላለፉት ሦሥት ዐሥርታት የኢትዮጵያ ባንኮች ያለ ውድድር ብቻቸውን እንዲሰሩ መደረጉንም በማንሳት፣ የውጭ ባንኮች ቢገቡ ካፒታል እና ቴክኖሎጂ ስለሚያመጡ ለአጠቃላይ እድገት ብቻም ሳይሆን፣ የእኛንም ፋይናንሻል ሴክተር የማሳደግ ሚና ይኖራቸዋል ሲሉ የመንግስታቸውን አኹናዊ አቋም አብራርተዋል። “እኛ ስላለቀቀን የድሮ በሽታ በጣም በትንሹ ነው የከፈትነው እንጂ ያን ያህል የእኛንም ባንኮች በሚያጠፋ መንገድ የተከፈተ አይደለም” ሲሉም፣ የንዑስ ኢኮኖሚው ለባሕር ማዶ ባንኮች መከፈት አገራዊ ጉዳት እንደማያስከትል አጽንዖት ሰጥተው ሲናገሩ ተሰተውለዋል።
“አኹን የቸገረን የወልቃይት አካባቢ ነው”
ሰፋ ያለ የማክሰኞ ማለዳ ሰዐታቸውን በኢኮኖሚው ዙሪያ ያደረጉት ጠቅላዩ፣ ከዚያ ማብራሪያቸው ለጥቀው የአገር ቤቱን ፖለቲካ አስመልክቶ በተነሱላቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ሰፋ ያሉ ማብራሪያዎችንም ሰጥተዋል። ከጥንት እስከ ትናንት የኢትዮጵያ የሰላም እጦት ችግሮች ከሦሥት በኩል እንደሚነሱ ቀደም ብለው የጠቀሱት የአገሪቷ ጠቅላይ ጦር አዛዥ፣ አንደኛው ከጥንት የተጠባነው ልዩነቶቻችን በኃይል ብቻ የመፍታት ልምምድ ነው ሲሉ ተሰምተዋል። ከጥንት የመጣ ያሉት የባንዳነት ልምምድን በኹለተኝነት ጠቅሰው፣ ሦሥተኛው የጠላቶቻችን ኢትዮጵያ ካደገች የሚል ያልተቋረጠ ስጋት ሲሉ መነሾዎች ያሏቸውን ጠቅለል አድርገው በማንሳት ወደ ቀሩት ፖለቲካ ተኮር ማብራሪያዎቻቸው ተሻግረዋል። “አልጋ አካልን፤ ውይይትም ልብን ያሳርፋል” ያሉት የተከበሩ ዶ.ር. ዐቢይ፣ መወያየት ብዙ ስብራቶችን እንደሚጠግንም ተናግረዋል። የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ማወያየቱን እና አጀንዳ ማሰባሰቡን በመጥቀስም፣ ውይይቱ ለኹሉም ክፍት ነው ሲሉ፣ በተሰበሰቡ አጀንዳዎች ፍላጎቶቻችን ተቀራራቢዎች ናቸው ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
"ባንዳነት ያቆስላል እንጂ አይገድልም” ሲሉ በበካር ድምጽ የተናገሩት ጠቅላዩ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ዘላቂ ሠላም እንዳይሰፍን ምክንያት የሆነው በባንዳ እና በባዳ የቅንጅት ተግባር መሆኑን ገልፀዋል። ወደ ነጠላ ፖለቲካዊ ርዕሰ-ጉዳይ ሻገር ብለውም፣ የወልቃይትን ጉዳይ ያነሱት ዶ.ር. ዐቢይ፣ “የወልቃይትን ጉዳይ እኔም እናንተም አትወስኑም፤ የሚወስነው የዚያ አካባቢ ሕዝብ ነው" ሲሉ በዕለተ-ማክሰኞቹ ውሏቸው ላገኟቸው እንደራሴዎች ነግረዋቸዋል። ሰፋ ባለው የዚኹ የወልቃይት ንግግራቸው፣ “የተፈናቀሉ ሰዎች መመለስ ይፈልጋሉ፤ ቀድመው የነበሩበት አካባቢም ይምጡልን ይላሉ፤ ማነው የያዛቸው ነው ጉዳዩ” ሲሉም ማብራሪያቸውን መጥይቃዊ ምላሽ አክለውበታል። ከዚያ ባለፈም፣ “በራያ አይታችኋል፤ ሰው ተመልሷል እየኖረ ነው። በጸለምት አይታችኋል፤ ሰው ተመልሷል እየኖረ ነው። ብዙው ኦሮሚያ አካባቢ ተመልሷል እየኖረ ነው። የቸገረን አሁን የወልቃይት አካባቢ ነው።” ሲሉ የተደመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ.ር. ዐቢይ አሕመድ፣ “ሰዎቹ መመለስ ስለማይፈልጉ ሳይሆን፣ ተፈናቃይን መያዣ ያደረገ ፓለቲካ ኢትዮጵያ ውስጥ በመኖሩ ነው” ሲሉም ምክንያት ያሉትን አስቀምጠዋል። የኔ ቢጤዎች ልጆቻቸውን መለመኛ እንደሚያደርጉት፣ አንዳንድ ፓርቲዎች ተፈናቃይን የራስ ህልውና ማቆያ ያደርጓቸዋልም ብለዋል። በወልቃይት ጉዳይ መንግስታቸው የያዘውን አቋም ሲያስረዱም፣ “ፌደራል መንግስት እያለ ያለው ሰው አይፈናቀል፤ ወደነበረበት ይመለስ፤ ራሱን ያስተዳድር ራሱ ይወስነው ነው። አንድ ሰው እዚህ ተቀምጦ ከሚወስን በሪፈረንደም፣ በሕጉ አግባብ ይወሰን ነው” ሲሉም ተሰምተዋል።
ትግራይን የሚነካውን የወልቃይትን ጉዳይ አያይዘው ወደ ትግራይ ፖለቲካ የዞሩት የተከበሩ ዶ.ር. ዐቢይ፣ የትግራይ ሕዝብ አሁን ካለበት ችግር ወጥቶ ራሱ ተግቶ ሠርቶ መለወጥ የሚፈልግ ሰላም ወዳድ ሕዝብ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። የትግራይ ሕዝብ ሰላም፣ ልማት ይፈልጋል፤ ከሌሎች ወንድም ኢትዮጵያውያን ጋርም በጋራ መሥራት እና ማደግ ይፈልጋል ያሉት ዶ.ር. ዐቢይ፣ ነገር ግን የትግራይ ሕዝብ በፖለቲካ አውድ ውስጥ መድረክ እንጂ ተዋናይ መሆን አልቻለም፤ መድረኩን ሌሎች ይጫወቱበታል እንጂ ራሱ አይጫወትም ብለዋል። በትግራይ ያሉ ፖለቲከኞችም ከአጃቢ ተዋንያን ወደ መሪ ተዋንያን መሸጋገር እንዳለባቸው አመላክተው፣ ለዚኽ ደግሞ አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
በእንደራሴዎቹ ምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ.ር. ዐቢይ አሕመድ፣ በቀጣዩ 7ኛ ብሔራዊ ምርጫ ዙሪያም ጥያቄ ተነስቶላቸው ምላሽ ሰጥተዋል። የዘንድሮው ምርጫ ከቀደሙት የተሻለ ይሆናል ሲሉ የተደመጡት የብልጽግናው ፕሬዝደንት፣ የዘንድሮው ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሓዊ እና አካታች ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት ከተካሄዱት ምርጫዎች የተሻለ እንዲሆን አበክረን ነው እየሰራን ያለነው ሲሉም አክለዋል።የመንግሥት ኃላፊዎች በተለያዩ ክልሎች ተንቀሳቅሰው እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን እኔ የተሻለ ምርጫ ይኖራል እያልኩ ነው፤ አንዳንዶች ሰግታችኋል፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መልሱ በውጤት እንየው ነው ሲሉም ተደምጠዋል። ምርጫው ባለፈው ከነበረው ምርጫ አሳታፊ እንዲሆን ይሰራል በማለትም፣ "የአንድ ፓርቲ ድምጽ ለኢትዮጵያ አይጠቅማትም" ብለዋል። አክለውም የኔ እምነት ይኽ ፓርላማ አኹን ካለው የአምስት እና የዐሥር ሰዎች ድምጽ፣ በአምስት እና ዐሥር እጥፍ ያድጋል የሚል እንደሆነ ተናግረዋል።
ከቀጣዩ የ2018 ምርጫ ባለፈም፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ጉዳይ በፖለቲካ ተኮሩ የማብራሪያቸው ክፍል ያነሱት ጠቅላይ ጦር አዛዡ፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ደረሰበት ያሉትን የጥንካሬ ደረጃ ይፋ አድርገዋል። በለውጡ መጀመሪያ አንድ መብረር የሚችል ሄሊኮፕተር ብቻ የነበረው አየር ኃይላችን፣ ዛሬ ላይ የተለያየ ስም እና ተግባር ያላቸው ከ100 በላይ ዘመናዊ አውሮፕላኖች ባለቤት ሆኗል ሲሉም ማብራሪያቸውን በቁጥሮች ጭምር አስደግፈዋል። ዝግጅቱ የአገርን ምሰሶ የሚገዳደሩ ኃይሎች ከመጡ ኢትዮጵያን ለማጽናት እና ለማስቀጠል የታለመ የጥንካሬ መገለጫ መሆኑን ያነሱት አዛዡ፣ ከባንዳዎች የበለጠ ሀብት ካላመነጨን በስተቀር በሚዲያ እና በዲፕሎማሲ ጫና ይፈጠራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መፍትሔው ብቃትን በማጎልበት ጠንክሮ መገኘት መሆኑን አሳስበዋል።
“ጸቡ የተጀመረው...”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ.ር. ዐቢይ አሕመድ፣ በትናንቱ የግማሽ ቀን ውሏቸው፣ ከማኅበረ-ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ተኮር የስድስት ወራት የመንግስታቸው ውጤቶች እና ቀጣይ ዕቅዶች ባለፈም፣ በዲፕሎማሲው እና በቀንዱ ዙሪያም ጠንከር ያሉ ነጥቦችን በማብራሪያቸው ላይ አንስተዋል። የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ፣ ከሳምንት በፊት ከአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በኩል ለተሰማው ንግግር ጠቅላዩ ጠንካራ ምላሽ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅት አንድም ብድር እና እርዳታ ከየትኛውም ወገን አለመውሰዷን ተናግረዋል። “በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ቁርጠኛ አቋም፣ በአገርም ውስጥ ከአገር ውጪም ባሉ ኢትዮጵያውያን በቁርጠኝነት ጨክነው በጋራ ቆመው ስለሠሩ የተከወነ ፕሮጀክት ነው" ሲሉ ለግድቡ ግንባታ ብድርም ሆነ እርዳታ አገሪቷ እንዳልወሰደች አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በገንዘብ መደገፏን በቅርቡ በተደጋጋሚ ሲናገሩ የቆየ ሲሆን፣ ይህንን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ.ር. ዐቢይ ምላሽ በከፍተኛ የአገሪቷ መሪ ደረጃ የተሰጠ ይፋዊ መልስ ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውን ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ገንብታ ብቻ እንዳልቆመች በመግለጽ፣ ከአፍሪካ ሦስተኛ የሆነውን ኮይሻን እየሠራች ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የግዙፍ ፕሮጀክቶች ሥራ አለመቆሙን ለእንደራሴዎቹ የነገሯቸው ጠቅላዩ፣ ከአፍሪካ አንደኛው የኤርፖርት ግንባታም ተጀምሯል ብለዋል።
ከሕዳሴው ግድብ በመለስ፣ የኤርትራን ጉዳይም ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ እስከዛሬ ከመንግስታቸው በይፋ ያልተነገሩ ጉዳዮችን በዚኹ የዕለተ ማክሰኞች ውሏቸው ሲያነሱ ተሰተውለዋል። በዚኽም፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት በኤትርትራ ወታደሮች ተፈጸሙ ስላሏቸው ውድመቶች የዘረዘሩት ጠቅላይ ጦር አዛዡ፣ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል አለመግባባት የጀመረው ኢትዮጵያ ቀይ ባሕር ጉዳይን ስታነሳ ነው የሚሉ ወገኖች መኖራቸውን በማንሳትም፣ ይህ ስህተት መሆኑን ተናግረዋል። በኹለቱ አገራት መካከል አለመግባባት የተጀመረው በሰሜኑ ጦርነት ወቅት መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የተለያዩ ጥፋቶች በኤርትራ ወታደሮች መፈጸማችን ተናግረዋል። “ኤርትራ ከተፈጠረች ጊዜ ጀምሮ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ችግር ነበረ፤ እኛ ከመጣን በኋላ አያስፈልገንም ይቅርብን ብለን ለምነናል" ሲሉም ለእንደራሴዎቹ ተናግረዋል። “ፀቡ የተጀመረው ብዙዎች እንደሚያስቡት የቀይ ባሕር ጉዳይ ሲመጣ አይደለም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “በትግራይ ውጊያ ሲጀመር በመጀመሪያው ዙር ወጊያ ሽሬን ካስለቀቅን በኋላ የኤርትራ ጦር ከኋላ የአንዳንድ ግለሰቦችን ቤት፣ ፎቅ ማፍረስ ሲጀምር ፀብ ተጀምሯል፤ አልተናገርንም እንጂ” ሲሉም፣ የጸቡን መነሾ ያሉትን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጠቅሱ ተሰምተዋል። “አክሱምን ይዘን ስናልፍ፣ አክሱም ገብቶ ወጣቶችን በጅምላ ሲረሽን ፀብ ተፋፍሟል፤ አድዋን ይዘን ስናልፍ፣ አድዋ ሄዶ ፋብሪካዎችን ሲፈታታ፣ ሲሰርቅ ፀብ ተጋግሏል” ያሉት ጠቅላዩ፣ “አዲግራት ደርሰን የመድኃኒት ፋብሪካውን የሚነቀለውን ነቅሎ የማይነቀለውን ሲያፈራርስ ፀቡ ጫፍ ደርሷል፤ ግን ያኔ የኢትዮጵያ መንግስት በዚኽም በዚያም ለመዋጋት አቅም አልነበረውም” ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኽንን ጉዳይ በተመለከተ ከኤርትራ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እንዲነጋገሩ የቀድሞውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸውን እንዲኹም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትን ደመቀ መኮንንን ወደ ኤርትራ መላካቸውን ጭምርም ተናግረዋል። ይሄ ጸብ ተፋፍሞ ሄዶ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲፈረም፣ “እንዴት ሕወሓት ሳይጠፋ፣ ትግራይ ሳይወድም ፊርማ ይደረጋል በሚል ነው ፀቡ ጫፍ የደረሰው" ሲሉም የጸቡ መነሾ ያሉትን ሂደት ለእንደራሴዎቹ አብራርተውላቸዋል።
ከኤርትራ ተኮሩ ማብራሪያቸው ለጥቀው ወደ ሰንባቹ የባሕር በር ጉዳይ የተሻገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በቀደሙት የምክር ቤት ውሏቸው ያነሷቸውን የመንግስታቸውን አቋሞች በድጋሚ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። የአፍሪካ ቀንድ እንዳይቀደድ የተሰፋ፣ እንዳይጣመር የተቀፈደደ አካባቢ ነው ሲሉ የተሰሙት ዶ.ር. ዐቢይ፣ እንዳንለያይ አንድ ዓይነት ዘር፣ቋንቋ፣ ባህል አለን፤ እንዳንጣመር እና አብረን እንዳንሰራ ደግሞ ብዙዎቻችን ብሔራዊ ጥቅማችን ላይ አይደለም እየሰራን ያለነው ሲሉም፣ ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት እና ከፍተኛ ፉክክር ያለበት አከባቢ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል። “ቀይ ባሕር እና ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ተነጣጥለው መኖር አይችሉም” ያሉት የተከበሩ ዶ.ር. ዐቢይ አሕመድ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ቀይ ባሕርን ለመጠቀም ሰው ልግደል አላለም፤ በውውይት እና በስምምነት እንዲኹም በገበያ ሕግ እና በድርድር ጉዳዩን እንፍታው ነው ያልነው ብለዋል። እኛም ማጋራት አለብን፤ እነሱም ማገዝ አለባቸው፤ ኢትዮጵያን ጎድቶ ትርፋማ መሆን አይቻልምም ሲሉ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የባሕር በር አያስፈልጋትም ብሎ የሚያስብ ሰው አንድ ተፈጥሯዊ ሕግ የሳተ ነው ያሉት ርዕሰ-መንግስቱ፣ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በተመለከተም በዲፕሎማሲ እና በሰጥቶ መቀበል ለማሳካት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሆኖም “በባሌም ሆነ በቦሌ እንደተባለው ግን አይቀርም ማለት ነው” ሲሉ አክለዋል።