የግብርና ዘርፍ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ውስጥ በ2015 በጀት ዓመት 32.1 በመቶ በላይ ድርሻ የሚሸፍንና የኢኮኖሚ መሠረት በመሆን ለማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ከፍተኛ አስተዋፅዖ የሚያበረክት የኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ ነው። የግብርናው ዘርፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በዘላቂነት የማሳደግ እና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን እውን የማድረግ ድርብርብ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል። በመሆኑም በቀጣዮቹ ዓመታት የሚኖረውን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሀገሪቱን ሕዝብ የመመገብና ሀገራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ፣ በመካከለኛ ጊዜ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት፣ ለኢንዱስትሪውና ለሌሎች ዘመናዊ ዘርፎች በቂ ግብዓትና የሰው ኃይል የማቅረብ፣ ለሌሎች ዘርፎች ምርቶች ገበያ ወይም ፍላጎት ማጎልበትና በስፋት የሥራ ዕድል የመፍጠር ሥራ ከግብርናው ዘርፍ ይጠበቃል።