BRIDGE Research & Innovation - Parliaments. Peace. Policy

  1. Home
  2. /
  3. Books
  4. /
  5. የምክር ቤታችን ዕድል ኃይለ ሥላሴ የዤኔቭ…

ይኽ፣ ‘የምክር ቤታችን እድል (ከልጅነት እስከ እውቀት) ኃይለ ሥላሴ የዤኔቭ ቁልፍ’ በሚል ርዕስ፣ የአጼ ኃይለ ሥላሴ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ቃል ተቀባይ በነበሩት ከበደ እንግዳ ሰው፣ በ1953 የተደረሰ ጠቃሚ የታሪክ ምንጭ የሆነ ድርሳን ነው። “የምክር ቤታችን እድል” የሚለው ቀዳሚ ሐረግ አስቀድሞ እንደሚያመለክተን፣ በዚያ ዘመን የነበረውን የአጼውን መንግሥት አወቃቀር፣ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶችን እና በወቅቱ የነበሩ ባለሥልጣናትን አካባቢያዊ ከየት መጤነት ጨምሮ፣ የዘመኑን ሥርዓታዊ ፍሬ-ነገር በቅጡ ያሳየናል። መጽሓፉን ከዘውግ አኳያ፣ እንደ ታሪካዊ ማስታወሻ ልንመድበው የሚያስችለንም፣ ደራሲው የቅርብ ምስክር የነበሩባቸውን በተለይ የሕግ መምሪያ ምክር ቤቱን የቅርብ ክስተቶች ከእነ ተዋንያኑ የጊዜ ምጣኔውን ሳይዘነጋ መተረኩ ነው። ስለ ንጉሠ ነገሥቱ የቅርብ አማካሪዎች፣ ሚኒስትሮች እና በብዙ ጠቃሚ የኢትዮጵያ የታሪክ እና የባህል መዋቅር መጻሕፎቻቸው ከምናውቃቸው ብላታ መርስዔ ኅዘን ወልደ ቂርቆስ አንስቶ ደጃዝማች አሥራተ ካሳን የመሳሰሉ የጃንሆይ ዋንኛ የልሂቅ ስብስብ ትምህርት እና የሥልጣን ተዋረዶችን መያዙም የመጽሓፉን ምንጭነት ከፍ ያደርገዋል። የሕግ መምሪያ ምክር ቤቱን የመጀመሪያውያኑን የሕዝብ እንደራሴዎች ማንነት አስመልክቶም ዘርዘር ያሉ መረጃዎችን ይዟል። ይኽ ጠቃሚ ድርሳን፣ በምክር ቤቱ ውስጥ የነበሩትን የተለያዩ ኮሚቴዎችንም ከእነአባላቱ ሲያቀርብ፣ ከሕግ ሥራ እስከ መከላከያ፣ ከውጪ ጉዳይ እስከ የኢኮኖሚ እና በዚያ ዘመን አጠራር ፊናንስ ኮሚቴዎች ድረስ ያሉትን ከ‘ነአባላቱ ማንነት ያስነብበናል። የዘመኑ የሕዝብ እንደራሴዎቹ ምክር ቤት ያወጣቸው ሕጋግት እና ከተለያዩ አገራት ጋር የፈጸማቸው ስምምነቶችን መያዙም፣ ለታሪካዊ ጥናት ያለውን ፋይዳ ከፍ ያደርገዋል። በተለይም ጸሓፊው አባል የነበሩበት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱን አሰራር እና ደንብ ማወቅ ለሚሻ አንባቢ ዐይን ገላጭ መረጃዎችን ይዟል።