Meskerem
የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከሐምሌ 1 እስከ መስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት እረፍት ላይ ቢሰነብትም፣ የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ያሳለፈው በዋናነት የውክልና ሥራ በመሥራት ነበር፡፡ በዚኹ መስከረም ወር አበይት የፓርላማ ክንውን የነበረው፣ ፕሬዝዳንት ክቡር ታዬ አጽቀሥላሴ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ፣ የ2018 የመንግሥት ዋና ዋና የዕቅድ አቅጣጫዎችን በማቅረብ ያደረጉት ንግግር ነበር። በዚኹ ዕለት ለምክር ቤቱ አዲስ እና በጎ የአሰራር ጅማሮ የሆነው የኢቲቪ-ፓርላማ የቴሌቪዥን ቻናል መከፈቱም የተነገረበት ነበር፡፡ በተጨማሪም ለተቋማችን ብሪጅ ሪሰርች ኤንድ ኢኖቬሽን ግዙፍ የሥራ ምዕራፍን የሚከፍተው፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ጋር የተደረገው የጋራ ሥምምነትም አንዱ አንኳር የወሩ ግብር ነበር፡፡ ይኽች የብሪጅ ስምንተኛ እና የዓመቱ የመጀመሪያ ዕትምም፣ የምክር ቤቱን የመስከረም ክራሞት እና ተቋማችን ከምክር ቤቱ ጋር ያደረገውን የስምምነት ነጥቦች አጠናክራ ቀርባለች።