BRIDGE Research & Innovation - Parliaments. Peace. Policy

የኢትዮጵያ እንደራሴዎች ምክር ቤት፣ በወርኃ ኅዳር የተለያዩ ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነቶቹን ከውኗል። ከእነዚኽ ዋንኛ ኃላፊነቶቹ መካከልም፣ ሕግ ማውጣት፣ የሥራ አሥፈፃሚ ተቋማት ሪፖርቶችን ማድመጥ እና የፌደራል ተቋማትን መጎብኘት፣ የውክልና ሥራ፤ እና የፓርላመንታዊ ዲፕሎማሲ ሥራ የሚጠቀሱት የወሩ የምክር ቤቱ አበይት ክንውኖቹ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም፣ ምክር ቤቱ የራሱን የሦሥት ወራት ሥራ አፈፃፀም ጨምሮ፣ ለእንደራሴዎቹም የዐቅም ማጎልበቻ ሥልጠና እንዲሰጥ ሲያደርግ፣ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የጸደቀበት ታላቅ ቀን እንደሆነ የሚታመነውን ኅዳር 29ን ዘክሯል። ይኽች የብሪጅ ዐሥረኛ ዕትምም፣ እኒህን የምክር ቤቱን የኅዳር ክራሞት ጨምሮ፣ የብሔር ብሔረ ሰቦች ሉዓላዊነትን የሚነግረውን ቀን እና ከቀኑ ባሻገር ባሉ ርዕሰ-ጉዳዮች ዙሪያ አጭር ዳሰሳዋን አካታ ቀርባለች።