
እንደራሴ በብሪጅ ሪሰርች እና ኢኖቬሽን በየወሩ እየተዘጋጀ ይቀርባል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ
- Admin
- MONTHLY DIGEST
ማዕከላዊ መንግሥቱ ኃይል የሚጠቀመው በምን ኹኔታ እና ምን ሲገጥመው ነው? የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ጉዳይስ? ኢኮኖሚውስ እንዴት ሰንብቷል? በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛው ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 21ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የተገኙት የአገሪቷ ርዕሰመንግሥት፣ ይኽን መሰሎቹን ጥያቄዎች ጨምሮ፣ በዛ ባሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ምላሾችን ሰጥተዋል፤ አኹናዊ የመንግሥታቸውን አቋሞችም አስረድተዋል። ኢኮኖሚው እንዴት ሰነበተ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ.ር. ዐቢይ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ በሠጡት ማብራሪያ፣ መንግስት በቀጣዬቹ ዐሥር ዓመታት የሚተገበር የልማት ዕቅድ ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል። ከዚኽ ባለፈም፣ የዐሥር ዓመቱን መሪ ዕቅድ መነሻ ያደረገ የአምስት ዓመት እና የአንድ ዓመት የተግባር ዕቅድ ተዘጋጅቶ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል። እንደራሴዎቹ በአገሪቷ ዐቢይ ኢኮኖሚ ዙሪያ ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል፣ በአምራች ዘርፉ ያለውን የጥሬ ዕቃ የአቅርቦት ችግሮች፣ የዐሥር ዓመቱ ዕቅድ ከየት ወዴትነት፣ የነዳጅ ድጎማ እና ሕገ-ወጥ ሽያጭ፣ ተጀምረው የተጓተቱ አገራዊ ፕሮጀክቶች እንዲኹም የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት መዘግየትን የተመለከቱት ጥያቄዎች ዋና ዋናዎቹ ነበሩ። ለእኒህ መሰሎቹ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ባለፉት ስምንት ወራት በዋና ዋና የዐቢይ ኢኮኖሚ አመላካቾች ታላላቅ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
በተያዘው የበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት ይኽን ስኬት ማጠናከር ከተቻለ፣ ኢትዮጵያ ከ8 ነጥብ 4 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት ታስመዘግባለች ሲሉም ገልጸዋል። ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ችግሮች ቢያጋጥሙም፣ ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ 8 ነጥብ 1 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቧን ያነሱት ዶ.ር. ዐቢይ፣ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የዕዳ ሽግሽግ መገኘቱንም ተናግረዋል። በቀደመው ሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም. ከተጀመረው ዐቢይ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ በነበረው ድርድር፣ የዕዳ ሽግሽግ ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያ አቋም ዕዳ እንዲሰረዝ ማድረግ መኾኑንም ሲናገሩ ተደምጠዋል። አኹን ኢትዮጵያ እየሞከረች ያለችው ከጥቅል አገራዊ ምርቷ ሰባት በመቶ ገደማ ገቢ ለማስገባት መኾኑንም የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሚቀጥሉት አራት ወራት አኹን ባለው ሂደት ከተኬደ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ስኬት ይመዘገባል ብለዋል።
የዋጋ ንረትን እና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እየተሠራ ያለው ሥራ አበረታች መኾኑን ሲናገሩ የተደመጡት እንደራሴዎቹም፣ የምግብ ዋጋ ግሽበት መቀነሱን አስመልክቶ ሪፖርት ቢቀርብም፣ ሪፖርቱ ከእውነታው ጋር ምን ያክል የተቀራራበ ነው? ሲሉም ጥያቄያቸውን ወርውረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው፣ የዋጋ ንረትን ለማሻሻል እየተሠራ መኾኑን አንስተው፣ የዋጋ ግሽበትን ግን መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል፤ የምርት መጨመር፣ የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ እና ሌሎች ሥራዎች የዋጋ ንረቱን ቀንሰውታል ሲሉም ተሰምተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ የታጠቁ ኃይሎችን፣ “አያዋጣም ተዉት” ብለዋል።
ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን በውይይት እና በድርድር የመፍታት ልምምዳችን አነስተኛ ነው ሲሉ የተደመጡት እንደራሴዎቹ፣ መንግስት ፖለቲካዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት እንዲያብራራ ጠይቀው ነበር፡፡ መንግስት ሰላምን ያስቀደመ እና ለሰላም የሚተጋ መሆን አለበት ሲሉ ምላሻቸውን የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ መንግስት በብቸኝነት ኃይል የመጠቀም ሥልጣን ያለው በመሆኑ ዘላቂ ሰላምን እና ፍትሓዊነትን ለማረጋገጥ ወደ ግጭት ሊገባ እንደሚችል ተናግረዋል። መንግስት በብቸኝነት ኃይል የመጠቀም መብት ያለው አካል ስለኾነ ለዘላቂ ሰላም ሲል ይዋጋልም ብለዋል፡፡ ከተለያዩ ታጣቂዎች ጋር ይደረጋሉ ስለሚባሉ ድርድሮችም ሲያወሱ፣ መንግስታቸው ለሰላም እጁ የተዘረጋ መሆኑን በማንሳት፣ በድርድር እና በሰለጠነ መንገድ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ሁሌም ቢሆን ዝግጁ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የምንዋጋቸው መድኃኒት አውጥተው የሚደፉ፤ ማዳበሪያ እንዳይደርስ የሚያደርጉ፣ ነገር ግን ለሕዝብ እንታገላለን ባይ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለሕዝባቸው ትምህርት ምን ያደርግላቸዋል ብለው የሚያስቡ ናቸውም ሲሉ ተሰምተዋል። ነውጠኛ ነፃ አውጭ ነን ባዮች መጀመሪያ ተጎጂ የሚያደርጉት የራሳቸውን ሕዝብ ነው ያሉት ዐቢይ፣ ስለምንታገልልህ እንገድለሃለን፤ እኛ ታጋዮች ስለኾን የምናደርገው ሁሉ ትክክል ነው ይሉታል ሲሉም በዚኹ ማብራሪያቸው ላይ አንስተዋል። ጦርነት እንደማይጠቅም በወሬ ሳይኾን በተግባር አይተነዋል ነው ያሉት ጠቅላዩ፣ መከላከያ ተወጥሯል ጦርነት እናንሳ የሚሉ አሉ፤ ምክሬ ግን አያዋጣም፣ አይኾንም ተዉት የሚል ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የቀይ ባህር ጉዳይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ.ር. ዐቢይ፣ መንግስታቸው በባሕር በር ጉዳይ ላይ ያለውን አኹናዊ አቋም ባብራሩበት በዚያ የእንደራሴዎቹ ውሎ፣ የቀይ ባሕር ፍላጎታችን ከሶማሊያ፣ ጅቡቲ እና ኤርትራ ጋር የሚያዋጋ መሆን የለበትም ብለዋል። ቀይ ባሕር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው ሲሉ በድጋሚ ለምክር ቤቱ አባላት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ 130 ሚሊዮን ሕዝብ ተዘግቶበት እስር ቤት ውስጥ ሊኖር አይችልም ብለው ሲናገሩም ተደምጠዋል። በዚኽ ቀይ ባሕር ተኮር ማብራሪያቸው ኤርትራን ደጋግመው ያነሱት ዐቢይ፣ የኤርትራ ሕዝብ ወንድም፣ ምስኪን እና እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ ለማደግ የሚፈልግ ሕዝብ ነው ሲሉ ገልጸው፤ ተባብረን መልማት እና መሥራት እንጂ አንዱ አንዱን መውጋት የእኛ እቅድ አይደለም ሲሉም አኹናዊውን የመንግስታቸውን አቋም ለእንደራሴዎቹ አጋርተዋቸዋል። በዚያ ማብራሪያቸውም፣ ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ስትል ኤርትራን የመውረር ፍላጎት የላትም ሲሉም አበክረው ተናግረዋል። የባሕር በር ጥያቄን ማንሳት ነውርነቱ አቁሟል ሲሉ የተሰሙት ዶ.ር. ዐቢይ አሕመድ፣ የዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ አቋምም በዓለም ላይ ትልቅ አገር ሆኖ የባሕር በር የሌለው የለምና፣ የባሕር በር የማግኘቱ ጉዳይ በሰጥቶ መቀበል መርህ ሊሆን ይገባል የሚል ነው ሲሉም ለምክር ቤት አብራርተዋል።