
እንደራሴ በብሪጅ ሪሰርች እና ኢኖቬሽን በየወሩ እየተዘጋጀ ይቀርባል።
የብሪጅ ዳሰሳዊ ምልከታ፡ የመስክ ስራዎች
- Admin
- COMMENTARY
የኢትዮጵያ እንደራሴዎች፣ ወደ ‘ምርጫ ወረዳዎቻቸው በመሄድ፣ ከወከሏቸው መራጮቻቸው እና በየአካባቢዎቻቸው ከሚገኙ ተቋማት ጋር በቀጥታ በመገናኘት የመስክ ጉብኝቶችን አድርገዋል። በዚኽ የመስክ ጉብኝቶቻቸውም፣ በሄዱባቸው አካባቢዎች ስለተከናወኑና በመከናወን ላይ ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎችን እና ተግዳሮቶችን በመገምገም ተጨባጭ መረጃ ማግኘት ችለዋል። በዚኽም፣ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን ከመወጣት ባሻገር የመንግሥትን እና የኅብረተሰቡን ግንኙነት ወደ ተሻለ ከፍታ ያስቻሉ ኹነቶችን ፈጥረዋል።
ለማሳያ ያህልም፣ እንደራሴዎች በመጋቢት ወር ውስጥ ካደረጓቸው የመስክ ጉብኝቶች መካከል፣ የኮይሻ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብን እና የኮምቦልቻን ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ላይ ያደረጉት ጉብኝት ተጠቃሽ ነው። እንደራሴዎቹ በዚኽ የመስክ ምልከታቸው ያካተቱት፣ ከግብርና እስከ መሠረተ-ልማት እና አደጋ መከላከል፤ እንዲኹም የመንግሥት አገልግሎትን እስከ ማሻሻል ያሉትን የጨመረ ነበር። የመስክ ምልከታዎቻቸው በቅርብ ከሚያገኙት አዲስ አበባ ጀምሮ፣ ራቅ ያሉትን እስከ ከፋና ጋሞ ዞኖችን ያካተቱ እንደመሆናቸው፣ ይኽን መሰሎቹ የቋሚ ኮሚቴዎቹ ምልከታዎች፣ እንደራሴዎቹን ሙሉ ስዕል እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋሉ።
በዚኽ የመጀመሪያ ዕትማችን የሚኖረን የብሪጅ ዳሰሳዊ ምልከታ፣ እንደራሴዎቹ ኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ ፓርክ ጉብኝትን በዓበይትነት ያነሳል። ምንም እንኳን፣ እንደራሴዎቹ የውክልና ሥራዎቻቸውን በዚኽ መልኩ እየተወጡ ቢሆንም፣ በመስክ ምልከታቸው ወቅት ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች የመፍትሔ አካል ለመሆን የክትትል ሥርዓት መከተል ያስፈልጋቸዋል፤ ይኽ የክትትል ሥርዓት እስከ አኹን ካለም ለሕዝብ ግልጽ መሆን ይኖርበታል ብለን እናምናለን፤ ከዚኽ በተጨማሪም፣ የእንደራሴዎቹ ምልከታ ያስከተላቸው ለውጦች መኖር አለመኖራቸው በተለይም የመስክ ምልከታው ለተደረገባቸው ተቋማት ኹነኛ ሚና ይኖረዋልና፣ ይፋ መደረግ እንዳለበት ብሪጅ ያምናል። በዚኽ ጉዳይ ለምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፣ ለምሳሌ የኬንያ እንደራሴዎች ከሕዝብ ጋር ከሚያገናኟችው መድረኮች በተጨማሪ፣ በየምርጫ ክልሎቻቸው ቢሮዎች ብቻም ሳይሆን፣ ቅሬታዎችን የሚቀበሉና የሚመለከቷቸውን የልማት ፕሮጀክቶችን የሚከታተሉ ሠራተኞች ጭምር አሏቸው።[1] ከዚኽ መገናኚያ አማራጭ በተጨማሪም፣ የዲጂታል እና የማኅበራዊ ሚድያን በመጠቀም ከመራጮቻቸው ጋር ይወያያሉ። ከዚኽ ባለፈም አንዳንድ የአገሪቷ እንደራሴዎች፣ በየአካባቢዎቻቸው ስላሉ ማኅበረ-ፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች አልያም በሂደት ላይ ባሉ ፕሮጀክቶች ማኅበረሰባዊ ቅቡልና ዙሪያ የተዋቀረ ግብረ መልስ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ የመነሻ ጥናቶችን ያካሂዳሉ።
ወደ እኛ አገር መለስ በማለትም፣ ለማሳያነት ባነሳነው የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የእንደራሴዎቹ ጉብኝት ዙሪያ ጥቂት ምክረ-ሐሳቦችን መሰንዘር እንሻለን። ከላይ እንደተጠቀሰው፣ በምክር ቤቱ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጉብኝታቸው ወቅት የተመለከቷቸውን እንደዝቅተኛ ደመወዝ እና ያልተሟላ የኑሮ ኹኔታ ዙሪያ ለፓርኩ የሥራ ኃላፊዎች ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። ከዚኽ አንፃርም፣ እንደ ብሪጅ ዕይታ፣ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ይኽን መሰሉን ማሳሰቢያ ከመስጠት ባሻገር፣ ማሳሰቢያቸው መፈፀሙን/አለመፈፀሙን የሚከታተሉበትን ሥርዓት በመዘርጋት ዘላቂ ክትትል ማድረግ ይገባቸዋል። ከአራት ዓመታት በፊት የተሰራው የዓለም ባንክ ጥናት[2] እንደሚያሳየው፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውስጥ የሚከፈለው ክፍያ፣ ከአካባቢው የመሠረታዊ ፍላጎቶች ወጪ ጋር ሲነፃፀር በሌሎች የአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ዘርፎች ከሚከፈለው ክፍያ ጋር ተመሳሳይ ነበር። ምንም እንኳን ሌሎች ጥናቶች፣ በክፍያ ዙሪያ አከራካሪ መረጃዎችን ቢያመለክቱም፣ የባንኩ ጥናት የሠራተኞች አማካኝ ጥቅል ክፍያ፣ በአካባቢው ካለው የድኅነት ወለል አንፃር ሲለካ ከሚገኘው የክፍያ ምጣኔ አኳያ ወደ አራት ዕጥፍ ገደማ ከፍ የሚል እንደነበር ያሳያል። ነገር ግን ይኸው ጥናት፣ የማካካሻ እና የክፍያ መዋቅር በኢንዱስትሪዎች መካከል በእጅጉ መለያየት እና በቂ የሆነ መረጃ አለመኖርን እንደችግር አንስቷል። በተለይ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ከተፈጠረው የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም እና የምግብ ዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ፣ የኢንዱስትሪው ፓርክ ሠራተኞች በምን ልክ ኑሯቸው እንደታወከ የቋሚ ኮሚቴው አባላት አስቀድመው ከፊል የመስክ ግምገማ ማድረግ የሚችሉበት ዕድል ቢኖር ጉብኝታቸውን የተሻለ ያደርግ እንደነበር ግልፅ ነው።
ከዚኽ ባለፈም፣ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያያዞ፣ የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ከነበረችበት፣ ከሰሃራ በታች ላሉት አገራት ከተሰጠው ከአፍሪካ ከቀረጥ ነፃ የንግድ ዕድል (አጎዋ) ማገዱ ይታወሳል። እንደሚታወቀው ይኽ ዕገዳ፣ በተለይም እንደ ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪያል ያሉትን የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ክፉኛ ጎድቷቸዋል። ከዚኽ አኳያም፣ ፓርኩን የጎበኙት እንደራሴዎች ይኽ ዕገዳ በፓርኩ ሠራተኞች አኹናዊ የሥራ ኹኔታ ላይ ምን አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳደረገ እና ፓርኩም በዕገዳው ያጣቸውን የውጪ ምንዛሬን ጨምሮ፣ የሠራተኞችን ከሥራ ገበታቸው መባረር ጉዳይ ላይ በቂ ዳሰሳ ማድረግ እንደነበረበት ብሪጅ ያምናል። ከእነዚኽ ጉዳዮች በተጨማሪ፣ በአካባቢው ስላለው የድኅነት ወለል፣ የሠራተኞች የደመውዝ ገቢ ግብር ኹኔታ፣ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ ስለሚደረገው መንግስታዊ ጥበቃ እና የኢንዱስትሪ ፓርኩ ሠራተኞች ስላሏቸው ተደራጅቶ መብታቸውን የመጠየቅ መብት ዝርዝር ትንተና ላይ የተመረኮዘ የመስክ ጉብኝቶች ሊደረግ ይገባ እንደነበርም ማስታወስ ያሻል። ከእነዚኽ ወሳኝ ጉዳዮች በተጨማሪም፣ እንደራሴዎቹ ለመስክ ጉብኝት በሚሄዱባቸው ወቅቶች ማብራርያ የሚሰጧቸውን ግለሰቦች እና ተቋማት እንዴት እና ለምን እንደሚመርጡ፣ ለመራጮቹ ግልፅ መሆን ይኖርበታል እንላለን። በፓርኩ የእንደራሴዎቹ የመስክ ምልከታ በኩል ያቀርብነው አጭር ምልከታ፣ ወደፊት በሌሎች ተቋማት ላይ የሚደረጉ ጉብኝቶች እነዚኽን መሰል የምክረ-ሐሳብ ነጥቦችን ግንዛቤ ውስጥ ያካተቱ እንደሚሆኑም ተስፋ እናደርጋለን።
አጠር ያለውን ዳሰሳዊ ምልከታችንን ለመጠቅለል ያህልም፣ እንደራሴዎቹ አኹን ባለው የምልከታ ሽፋናቸው ኹሉንም አዎንታዊ እና አሉታዊ ገፆችን በሙሉ መዳሰስ የሚያስችል አቅም ስለማይኖራቸው፣ ለፖሊሲ ግምገማ እና መሻሻል ሊያደርጉት የሚችሉትን አስተዋጽዖ መገደቡ አይቀርም። ያም ሆኖ ግን፣ ወደ ፌዴራልም ሆነ ክልላዊ ተቋማት ተኪደው የሚደረጉ የመስክ ምልከታዎች፣ ከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ጋር ከሚደረጉት የተለዩ ውጤቶች ስለሚኖራቸው የምልከታችውን አድማስ በማመጣጠን እና በማቀናጀት አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ፖሊሲዎችን እና ሕጎችን ለመቅረጽም ሆነ ለማሻሻል በቂ የመረጃ ግብዓት ይሰጣቸዋል የሚለው የብሪጅ ዕምነት ነው።
ከእነዚኽ አጭር ዳሳሳዎች አንፃርም፣ ብሪጅ ሪሰርች ኤንድ ኢኖቬሽን የሚከተሉትን የማሻሻያ ምክረ-ሐሳሳቦች ያቀርባል።
- እንደራሴዎቹ፣ የተቋማት ቁጥጥር ሥራቸውን፣ እንዲኹም የፖሊሲ እና የሕግ ማውጣት ተፅእኖዎቻቸውን ለማጎልበት የሚረዷቸው የተደራጁ የክትትል ማዕቀፎች ያስፈልጓቸዋል። ከዚኽ በተጨማሪም የሚያቀርቧቸውን የፖሊሲ፣ የአሰራር እና የሕግ ማሻሻያዎችን ሪፖርት ከማድረግ ባሻገር፣ ያቀርቧቸው እነዚኹ የአሰራር እና የሕግ ማሻሻያዎች በተግባር እንዲውሉ ተፅዕኖ በማድረግ ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል እንላለን።
- የኢፌዴሪ እንደራሴዎች፣ ከሚከውኗቸው መደበኛ የመስክ ምልከታዎች ባሻገር በርካታ ሐሳቦች ሊገኙባቸው የሚችሉትን የማኅበረሰብ ውይይቶች ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል እንላለን፤ ይኽን መሰሎቹ የውይይት መድረኮችም፣ የታችኛው ኅብረተሰብ ክፍል ድምጾች በፖሊሲ እና በሕግ ማሻሻያ አልያም ቀረጻ ውስጥ እንዲካተቱ ይረዳቸዋል፤ እንደ ብሪጅ ዕምነትም፣ እንደራሴዎቹ እኒህን ድምፆች በሚገባ በሚወጡም ሆኑ በሚሻሻሉ ሕግጋት ውስጥ ማካተት ይኖርባቸዋል።
- የሕዝብ ተወካዮቹ፣ ማኅበራዊ ተጠያቂነትን ማስፈን የሚችሉ ፕሮጀክቶች እንዲስፋፉ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው ግልጽ ነው፤ ከዚኽ አንፃርም፣ በሕዝብ ተሳትፎ የሚገኙ ልማት ተኮር ግብረ-መልሶች፣ በየትኛውም የመንግሥት ዕርከን እና በሚመለከተው የኅብረተሰብ ክፍል መካከል ግልጽነትን፣ ተጠያቂነትን እና መተማመንን ማስፈን መቻላቸው ግልጽ ነው፤ ነገር ግን፣ ከዚኽ ባሻገር እንደራሴዎቹ፣ እነዚኽን ግብረ-መልሶች በፖሊሲ ቀረፃ እና በሕግ ማውጣት ሂደቶች ውስጥ ግብዐት እንዲሆኑ ማስቻል ይጠበቅባቸዋል እንላለን። ለዚኽም ከዓለም ዓቀፍ፣ አህጉር ዓቀፍም ሆኑ ቀጠና ተኮር ተቋማት እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ያሏቸውን አጋርነቶች ማጠናከር እንደሚያስፈልጋቸው ማስታወስ ያሻል።
እንደራሴዎቹ ያደረጓቸው የመስክ ምልከታዎች ዘርፈ ብዙ እንደመሆናቸው፣ የተለያዩ ዘርፎችን ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት ለፖሊሲ ቀረፃ እና ለሕግ የማውጣት ሥራ ግብዐት በመሆን ያገለግላሉ። ከዚኽ የሚገኘውን ጥቅም እና የተወካዮች ተፅዕኖ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግም፣ እንደራሴዎቹ ከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ጋር ያላቸውን ትስስሮሽ ማጎልበት፣ የፖሊሲ ቀረፃ እና ሕግ የማውጣት ተጽዕኗቸውን ማጠናከር፣ እንዲኹም ጠንካራ የሆነ የክትትል ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋቸዋል ብለን እናምናለን፤ ምክንያቱም፣ ኢትዮጵያውያን መርጠው በላኳቸው ተወካዮቻቸው በኩል፣ ተስፋ እና ስጋታቸውን ማንፀባረቅም ሆነ ለሰላም እና ለልማት በአንድነት መረባረብ የሚቻላቸው፣ ይኽ ሲሆን ብቻ ነውና።