BRIDGE Research & Innovation - Parliaments. Peace. Policy

Home / COMMENTARY / የብሪጅ ዳሰሳዊ ምልከታ፡ በአዋጅ ቁጥር 1373/2017 ላይ የተደረገ

የብሪጅ ዳሰሳዊ ምልከታ፡ በአዋጅ ቁጥር 1373/2017 ላይ

ኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥቱ በክልሎቹ ውስጥ ጣልቃ የሚገባበትን ነባር አዋጅ አሻሽሏል። ምክር ቤቱ፣ መጋቢት 23 2017 ዓ.ም. ባካሄደው 22ኛ መደበኛ ስብሰባው፣ የቀረበለትን ይኽንኑ የማሻሻያ አዋጅ ያፀደቀው በኹለት ድምጸ-ተዐቅቦ በአብላጫ ድምጽ ሲሆን፤ ነባሩን አዋጅ ቁጥር 359/1995ን ተክቶ አዋጅ ቁጥር 1373/2017 በሚል አፅድቆታል።

ይኽ የተሻሻለው አዋጅ (ቁጥር 1373)፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን እና የፌዴራል መንግሥቱን ተቋማዊ አቅም በመገንባት ረገድ፣ በተለይም የፌዴራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል ጣልቃ የመግባቱ የመጀመሪያው ዙር በተገባደደ ማግስት ያጋጠሙ አሥተዳደራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት የሕግ እና ፖለቲካዊ ክፍተቶችን ለመድፈን ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ በሌላ በኩል በትግራይ ክልል ካጋጠመው ኹኔታ በመነሳት፣ በሌሎች የፌዴሬሽኑ አባላት ውስጥ መሰል ችግሮች ቢከሰቱ፣ ታጣቂ የፖለቲካ ቡድኖች የበላይነትን፣ የጊዜያዊ አሥተዳደሩ በልማት እና የአሥተዳደር ዘርፍ በሚጫወተው ሚና ዙሪያ ላይ እና ተያያዥ ጉዳዮች እንዴት እንደሚፈቱ አኹንም በግልፅ አለመቀመጡን ብሪጅ ተረድቷል።

በመሆኑም ይኽ አጠር ያለ ኅተታ የቀዳሚውን አዋጅ ውስንነቶች፣ በትግራይ ክልል ስላጋጠመው የሕግ እና የፖለቲካ ነባራዊ ክፍተቶች እንዲኹም የተሻሻሉ ጉዳዮችን እና አንድምታዎችን ይፈትሻል፡፡

የአዋጅ 359/1995 ውስንነቶች

በ1987ቱ ሕገ-መንግሥት በዝርዝር እንደተቀመጠው፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አወቃቀር፣ የብሔር፣ ብሔረ ሰቦች እና ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መርህ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የሕዝቦች ባህላዊ ማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ ከፍተኛ ልዕልና የተሰጣቸው የሕገ-መንግሥቱ ቀዳሚ አዕማድ ናቸው፡፡ አኹን እንዲሻሻል የተፈለገው ነባሩ አዋጅ 359 አስፈላጊ የሆነበት ምክንያትም፣ በመሠረታዊነት ይኽን በሕገ-መንግሥቱ የተደነገገውን የሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ቡድናዊ መብት የመጣስ አደጋ ሲገጥመው እና በተራዛሚውም ሕገ-መንግሥቱን የሚያናጉ ፖለቲካዊ ኹነቶች ሲፈጠሩ መሆኑ ግልፅ ነው። የነባሩ አዋጅ ጥቅል መነሾም፣ የፌዴሬሽኑ አባላት ወደ ሕገ-መንግሥታዊው ሥርዓት እንዲመለሱ እና ሥርዓቱንም ሊመጣበት ከሚችልበት የመናጋት ተጨባጭ አደጋ ለመካለከል ነበር። የተፈጠረውን ችግር ቀልብሶ፣ ፖለቲካዊ ሥርዓቱን ወደነበረበት ሕገ-መንግሥታዊ ድባብ ለመመለስም፣ በአዋጁ እንደተቀመጠው ጊዜያዊ አሥተዳደርን ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑ አሌ አይባልም።

ነገር ግን አዋጁ የጊዜያዊ አሥተዳደር ቆይታን በኹለት ዓመታት ብቻ ከመገደቡ ባለፈ፣ ለጊዜያዊ አሥተዳደሩ መቋቋም መነሾ የሆኑት ኹሉም ነባራዊ ችግሮች በዚህ የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ይፈታሉ ብሎ ማመኑ የሚከተሉትን ውስንነቶች አዋልዷል፡፡

የአዋጁ አንቀጽ 15 ቁጥር 3፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተጠቀሰው ክልል ችግር አልተፈታም ብሎ ካመነ፣ የመቆያ ጊዜውን ከሥድስት ወራት ላልበለጠ ጊዜ ብቻ የማራዘም ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ይኽ ደግሞ፣ በትግራይ ክልል እንደታየው፣ ነባራዊ ኹኔታን ያገናዘበ አልነበረም።

ሕገ-መንግሥታዊ እክል በተፈጠረበት ክልል ውስጥ የሚቋቋመውን ጊዜያዊ አሥተዳደር ቆይታን ለማራዘም ውሳኔ እንዲሰጥ ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣን የተሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በዓመት ኹለት ጊዜ ብቻ የሚሰበሰብ መሆኑ፣ በእነዚኽ የስብሰባ ቀነ-ቀጠሮ ክፍተቶች መካከል፣ አዋጁ እንዲፈታቸው የሚጠበቅበት ችግሮች እየተባባሱ ከመሄዳቸው ባሻገር፣ ከቁጥጥር ውጪ ሊወጡ የሚችሉበትን ዕድል ያሰፋል። ይኽም ሰፊ ሕገመንግሥታዊ የአተገባበር ክፍተቶችን ወደመፍጠር ሊያሻግራቸው ይችላል።

እነዚህ እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች፣ ከኹለት ወራት በፊት የአሥተዳደር ዘመኑ በተጠናቀቀው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሥተዳደር ክንውን ላይ እስከታዩበት ጊዜ ድረስ፣ በንድፈ-ሐሳብ ደረጃ ብቻ የነበሩ ቢሆንም በተጨባጭ መከሰት መቻላቸው አዋጁን ማሻሻልን አስገዳጅ አድርጐታል፡፡

ትግራይ እንደ ማሳያ

የፌዴራል መንግሥቱ ሕወሓትን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ጦርነት ቀስቅሷል በሚል በመወንጀል፣ ሕወሓት መራሹን ክልላዊ መንግስት አስወግዶ ጊዜያዊ አሥተዳደር ካቋቋመበት ጊዜ አንስቶ፣ በርካታ ሕግ-ነክ ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይተዋል፡፡ ጊዜያዊ አሥተዳደሩ፣ ምርጫ እንደማድረግ ያሉ የተቋቋመባቸውን ግቦች ሳይፈፅም የቆይታ ጊዜውን ካገባደደ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እስኪሰበሰብ ድረስ ውሳኔ መስጠት የሚችለው ሕገ-መንግሥታዊ አካል ማን ነው? የአሥተዳደሩ መቋቋምን አስፈላጊ ያደርጉት ችግሮች እየተባባሱ ቢሄዱስ ፈጣን እርምጃዎች ለመውሰድ ምን ዓይነት ሕገመንግሥታዊ መሠረቶች አሉ? በትግራይ ያሉት የፖለቲካ ኃይሎች ግጭት ውስጥ ባሉበት ኹኔታ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንዴት መመለስ ይቻላል? የተፈቀደው የአሥተዳደሩ ዘመነ-ሥልጣን ተገባዶም ክልሉ ከቀውስ መውጣት ባይችል ምን ዓይነት ሕጋዊ እና አሥተዳደራዊ መውጫ መንገዶች አሉ? የሚሉት ተጠቃሾቹ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡

እነዚህ እና ሌሎች በዝርዝር ሊኬድባቸው የሚቻልባቸው ተያያዥ ችግሮች በተጨባጭ መታየታቸው፣ ለነዚኽ ችግሮች ሊሰጡ የሚችሉት ሕጋዊ ምላሾች ከነባሩ አዋጅ ማዕቀፍ የሚያስወጡ እንደመሆናቸው፣ የፌዴራል መንግሥቱ አፋጣኝ ዕርምጃዎችን እንዲወስድ ማስገደዳቸው ግልፅ ነው።ከዚኽ አኳያ ነገሮቹን ስናጤናቸውም፣ በነባሩ አዋጅ መንፈስ እና በተጨባጭ ፖለቲካው መካከል ያሉትን ክፍተቶች አጉልቶ አሳይቷል።

በመሆኑም፣ አዋጅ 1373/2017 ችግርን ለመቅረፍ አስቀድሞ የተወሰዱ እርምጃዎች ያልፈቷቸውን ፖለቲካዊ እና ተቋማዊ ችግሮች ግንዛቤ ውስጥ ከትቶ የተቀረፀ ማሻሻያ ሕግ ነው፡፡እንዲኽ ዓይነት የሕግ አወጣጥ ሂደቶች አልፎ አልፎ የሚደረጉ እና የችግሮችን መባባስ ለመከላከል ጥቅም ላይ የሚውሉ ቢሆንም፣ የሕግን ተገማችነት እና ሕገ-መንግሥታዊ ሂደትንን እንዳይሸረሽረው መጠንቀቅ እንደሚያሻ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ሕጎች በሚወጡበት ጊዜ መጪውን ጊዜ ግምት ውስጥ የሚከቱ እና እንደ ተጨባጭ ኹኔታዎች መሻሻል የሚያስፈልጋቸው ከመሆኑም በላይ፣ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግስታት በሕገ-መንግሥቱ የተሰጧቸውን ሥልጣኖች በአግባቡ እንዲወጡ የሚያበረታታ መሆን ይኖርበታል፡፡

እነዚህ እና ሌሎች በዝርዝር ሊኬድባቸው የሚቻልባቸው ተያያዥ ችግሮች በተጨባጭ መታየታቸው፣ ለነዚኽ ችግሮች ሊሰጡ የሚችሉት ሕጋዊ ምላሾች ከነባሩ አዋጅ ማዕቀፍ የሚያስወጡ እንደመሆናቸው፣ የፌዴራል መንግሥቱ አፋጣኝ ዕርምጃዎችን እንዲወስድ ማስገደዳቸው ግልፅ ነው።ከዚኽ አኳያ ነገሮቹን ስናጤናቸውም፣ በነባሩ አዋጅ መንፈስ እና በተጨባጭ ፖለቲካው መካከል ያሉትን ክፍተቶች አጉልቶ አሳይቷል።

የማሻሻያው ይዘቶች

ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ተጨማሪ ሥልጣን ስለመስጠት፤

የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በዓመት ኹለት ጊዜ ብቻ የሚሰበሰብ እንደመሆኑ፣ በየትኞቹም ክልሎች ውስጥ የማዕከላዊ መንግሥቱን ጣልቃ-ገብነት የሚያስገድዱ ኹኔታዎች ሲፈጠሩ፣የፌደሬሽን ምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ለማዘዝ የሚያስችል ሥልጣን ተሰጥቶቷል። ይህም በአዋጅ 359 የነበረውን ውስኑነት ከመቅረፉ ባለፈ፣ የፌዴራል ተቋማቱ ፈጣን ምላሽ የመስጠት ችሎታቸውን ያዳብራልና ጉልህ የሆነ የአዋጁ ማሻሻያ ነው፡፡

ከዚኽ አንፃርም፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በሚሰበሰቡበት ጊዜ፣ የአፈ-ጉባኤውን ውሳኔ መርምረው ውሳኔ የሚያሳልፉ እንደመሆናቸው፣ የማሻሻያው መንፈስ በፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የተወከሉትን የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሕገ-መንግስታዊ በጋራ የመወሰን ሥልጣንን ያስጠብቃል፤ ያጠብቃልም፡፡

ለጊዜያዊ አሥተዳደሮች የሚሰጥ የጊዜ ገደብ

ነባሩ አዋጅ፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከሚመጣ አደጋ እንዲከላከሉ የሚቋቋሙ ጊዜያዊ አሥተዳደሮች የተመደበላቸው ጊዜ ሲያበቃ፣ ከሥድስት ወራት በላይ ማራዘም እንደማይቻል ደንግጎ ነበር። ያም ሆኖ፣ መጠነ ሰፊ ደም አፋሳሽ ግጭቶች እና ውስብስብ የፖለቲካ ኹኔታዎች ለሚገጥሟቸውጊዜያዊ አሥተዳደሮች ተጨማሪዎቹ ሥድስት ወራት በቂ አለመሆናቸውን በትግራይ ክልል ከነበረው ኹኔታ በተጨባጭ መረዳት ተችሏል፡፡ ይህን ግንዛቤ ውስጥ በመክተትም አዋጅ 1373/2017፣ የአሥተዳደሮቹን ጊዜ እስከ አንድ ዓመት ማራዘም እንደሚቻል እና አስፈላጊ ከሆነም በድጋሚ ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ሊራዘም እንደሚች ደንግጓል፡፡

የማሻሻያው ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ጠንካራ ጎኖች

  • በፌዴሬሽን ምክር ቤት ስብሰባ መዘግየት ምክንያት፣ የማዕከላዊ መንግሥቱን ሕገመንግሥታዊ መብቶችን የማስከበር ኃላፊነት እንዲወጣ ለማድረግ አፋጣኝ ሕጋዊ መደላደልን መፍጠሩ፤
  • የሚቋቋመው ጊዜያዊ አሥተዳደር የተፈጠሩትን ሕጋዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች መፍታት የማይችልባቸው ገደቦች ሲያጋጥሙት፣ የቀሩትን ሕገ-መንግሥታዊ ተግባራት እንዲፈፅም አስፈላጊ ሲሆን ከሥድስት ወራት በላይ እንዲኖረው መፈቀዱ፤
  • የጊዜያዊ አሥተዳደሩን ቆይታ ማራዘም ሲያስፈልግ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ካለባቸው ተደራራቢ ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነት አኳያ ምክር ቤቱን በአጭር ጊዜ ስብሰባ በመጥራት ውይይት አድርጎ ውሳኔ ለመሥጠት የሚያስቸግር ኹኔታን ግንዛቤ ውስጥ መክተቱ፤
  • የሕጎች መሻሻል አንዱ ገፊ ምክንያት፣ ከነባራዊ ኹኔታዎች ጋር መናበብ መቻላቸው ከመሆኑ አኳያ፣ ማሻሻያው ለትግራይ ክልል አኹናዊነት ምላሽ ሊሰጥ መቻሉ፣ ከጠንካራ ጎኖቹ መካከል ሊጠቀሱ የሚችሉት ናቸው።

ደካማ ጎኖች

  • ምንም እንኳን ማሻሻያው የፌዴሬሽን ምክር ቤቱን በአጣዳፊ ሰብስቦ ውሳኔ መስጠት አለመቻልን ተንተርሶ፣ የጊዜያዊ አሥተዳደሩን ርዝማኔ ጉዳይ ለአፈ-ጉባኤው መስጠቱ በጎ ጎኑ ቢሆኑም ቅሉ፣ የአፈ-ጉባኤውን ውሳኔ ምክር ቤቱ እንዲያፀድቅ መደንገጉ፣ በአፈ-ጉባኤው ውሳኔ እና በፌዴሬሽን ም/ቤት አባላት የመሰብሰቢያ ጊዜ መሀል ያለው ክፍተት ተጠያቂነትን የሚያላላ እንዳይሆን ያሰጋል፤
  • የጊዜያዊ አሥተዳዳሮች የአሥተዳደር ጊዜ በተራዘመ ቁጥር፣ በሕዝቦች የቋንቋ ማንነት ላይ የተመሠረተውን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አወቃቀር በተለይም የክልል ራስ ገዝ አስተዳደርን የማዳከም ስሜት ሊፈጥር ይችላል፡ ፡ ሕጋዊ ትክክለኝነት ቢኖረውም፣ የፖለቲካ ስሜቶችን እንዳያከራቸውም ያሰጋል፡፡

አንድምታዎች

ከላይ በአጭሩ የዳሰስነው ይኽ የተሻሻለው አዋጅ 1373/2017፣ የነባሩን አዋጅ 359ን ውስንነቶች በቀረፈ መልኩ ከፀደቀበት መጋቢት 23 ጀምሮ ወደሥራ ገብቷል፡ ፡ አዋጁም፣ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀውሶች ሲገጥሟት በሆነ ልክ ችግር መፍቻ ዘዴ ሆኖም እንደሚቀጥል ይታመናል፡፡ አዋጁ በተቀመጠለት የማሻሻያ መንፈስ ከተተገበረ፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በቅጡ ለማስከበርም ይረዳል የሚል ዕምነት አለ፡፡ ይኽ ካልሆነ ግን፣ አሳታፊነትን እና የብዝሓ ብሔርነትን ቅርጽ ይዞ የተነሳውን ሕገ-መንግሥት እንዳይሸርሸር ያሰጋል፡፡ እንደማንኞቹም ሕግጋት፣ ይኽም ማሻሻያ እንዲደረግለት የተገደደው ሕግም ብቻውን ለሚፈጠሩ ፖለቲካዊ ቀውሶች መፍትሔ እንደማያመጣ ግልጽ ነው፤ የሕጉ ትግበራ የታለመለትን መፍትሔ እንዲያመጣ ከተፈለገ፣ ከሕጉ ጋር ተናባቢ የሆኑ ተቋማዊ ለውጦችን ማምጣት አስፈላጊ ነው። በተለይም ተጨማሪ የጊዜያዊ አሥተዳደሩን ማራዘሚያዎች ማስቀረት የሚቻለው፣ ያ እንዳይከሰት የሚያረጋግጡ አንዳንድ ፖለቲካዊ እና ተቋማዊ እርምጃዎችን መውሰድ ሲቻል ብቻ ነው። ከዚኽ አኳያም፣ የሚቋቋመውን ጊዜያዊ አሥተዳደር የሥልጣን ዘመን ማራዘም መቻሉ ብቻ፣ ሥራ አሥፈፃሚውን በአስቸኳይ መንፈስ ሥራዎቹን እንዳይሠራ እንዳያዘናጋው አንዳች መላ ማበጀትም አስፈላጊ ይሆናል። ከዚኽ በተጨማሪም፣ የክትትል እና የቁጥጥር መላዎችን መንደፍና መተግበር፣ እንዲኹም የጊዜያዊ አሥተዳደሮችን የአፈፃፀም መመዘኛዎች በግልጽ ማስቀመጥ፣ አዋጁ የተቀመጠለትን ግብ ለማሳካት ዓይነተኛ አበርክቶ እንደሚኖራቸው ማስታወስ እንሻለን።

መደምደሚያ

የአዋጅ 1373/2017 መጽደቅ አገራዊ አንድነትን እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ለማጽናት እንዲኹም ብዝሓነትን እና ያልተማከለ አሥተዳደርን ለማረጋገጥ ነባራዊ ሕጎችን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ አሳይቷል፡፡ አዋጁ የቀደሙ ከፍተቶችን ለመሸፈን ጥረት የሚያደርግ ቢሆንም፣ ውጤታማነቱ የሚረጋገጠው ግን እንደ ማኅበረሰብ በምናራምደው የፖለቲካ አቋም ብቻ ነው፡፡ የሕገ-መንግሥቱ መሠረታዊ ዕሴቶች የሆኑት ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እና በጋራ የመወሰን ሥልጣን እንዳይሸረሸሩና የጊዜያዊ አሥተዳደሮቹን እንዲኹም የማዕከላዊ መንግሥቱን ጣልቃ-ገብነቶች በጊዜያዊነቶች ላይ ብቻ እንዲገደቡ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤ ይኽ እንዲሳካ ደግሞ፣ ሥልጣን እና ተጠያቂነትን የማይነጣጠሉ ኃላፊነቶች እና ግዴታዎች ማድረግ ተገቢ ነው ብለን እናምናለን፤ ስለምን ቢሉ፣ ጠንካራ እና በዴሞክራሲያዊ ኅብረ-ብሔራዊ መርህ ላይ የተመሠረተ ፌዴራሊዝም የሚተገበረው በዚህ መንገድ ብቻ ነውና!

English