
እንደራሴ በብሪጅ ሪሰርች እና ኢኖቬሽን በየወሩ እየተዘጋጀ ይቀርባል።
የምክር ቤቱ የውክልና ሥራ
- Admin
- MONTHLY DIGEST
ኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከሚጠበቁባቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል አንዱ የውክልና ሥራ ነው። እንደራሴዎቹም ወደ ‘ምርጫ ወረዳዎቻቸው በመሄድ የወከሏቸውን ማወያየት እና ጥያቄዎቻቸውን መስማት፣ በዓመት ኹለት ጊዜ የሚከውኑት ተግባር ነው። ከዚኽ አኳያም፣ የምክር ቤቱ አባላት ይኽንኑ የውክልና ሥራቸውን ከየካቲት ወር በመቀጠል በመጋቢት ወርም ከውነዋል።
በተጠቀሰው መጋቢት ወር ላይም፣ ከ40 በላይ የሚሆኑ የመራጭ -ተመራጭ መድረኮች ሲካሄዱ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ኢትዮጲያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሶማሌ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ውይይቶቹ የተካሄዱባቸው ክልሎች ነበሩ። በእነዚኽ ክልሎች በተካሄዱት ውይይቶችም፣ ሰፋ ያሉ አገራዊ እና አካባቢያዊ አጀንዳዎች በጥልቀት ተዳስሰዋል።
በመጋቢቱ የእንደራሴዎቹ የውይይት መድረኮች ላይ፣ በኹለተኝነት ተደጋግመው ከተነሱት አገራዊ ጉዳዮች መካከል የሰላም እና የጸጥታ እንዲኹም የመሠረተ-ልማት ግንባታ መጓተቶች ቀዳሚዎቹ ሆነዋል። በኦሮሚያ (ሰሜን ሸዋ፣ ቡኖ በደሌ)፣ ሶማሌ፣ ደቡብ (ወላይታ፣ አሪ) እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ውስጥ በተካሄዱት የውይይት መድረኮች፣ በሰላም ዕጦት የወደሙ ትምህርት ቤቶች እና ጤናን ጨምሮ የሌሎች ተቋማት መልሶ ግንባታ፣ የውኅ አቅርቦት መቋረጥ፣ የባንክ አገልግሎቶች ዕጥረት እና ሕገወጥ የድንበር ንግድን የመከላከል አስፈላጊነት ላይ ሰፋ ያሉ ውይይቶች ተደርገዋል። የሠላም እና የፀጥታ ጉዳይ በጣም አንገብጋቢ ጉዳይ በመሆኑ መንግስት ዘላቂ ሠላም ማስፈን እና የዜጎችን መብት ማስከበር እንዳለበት ተነስቶም ምክክር ተካሄዶበታል።
ከእነዚህ ኹለት አንኳር ጉዳዮች በተጨማሪም፣ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች፣ የተፈናቃዮች ወደቀያቸው የመመለሳቸው ኹኔታ፣ የልማት ዕቅዶች አፈፃፀም መጓተት እና
የመንገድ ሥራዎች መጓተቶች በመራጮቹ በኩል ተነስተው ውይይቶች ተካሂደውባቸዋል። ከአራት ዐሥርት በላይ በሚሆኑት እነዚያ የተመራጭ-መራጭ ውይይቶች ላይ የተነሱት እነዚኽ ብቻም ሳይሆኑ፣ ከመድኅኒት ዕጥረት እስከ የመብራት እና የስልክ ግንኙነት አገልግሎት መጓደል፤ ከሥራ አጥነት እስከ የኑሮ ውድነት፤ ከማዳበሪያ ዋጋ ንረት እስከ የግብርና ግብዓት አቅርቦት ውስንነት፤ እንዲኹም የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ጉዳይ እና ከልማት ጋር የተያያዙ የግብር ክፍያዎች መዘግየት በእነዚያ ውይይቶች ተደጋግመው የተነሱ አጀንዳዎች ነበሩ።