BRIDGE Research & Innovation - Parliaments. Peace. Policy

Home / MONTHLY DIGEST / የምክር ቤቱ ሕግ የማውጣት ተግባሮች

የምክር ቤቱ ሕግ የማውጣት ተግባሮች

በተጠቀሰው መጋቢት ወር፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኹለት አዋጆችን ያጸደቀ ሲሆን፣ አንድ ረቂቅ አዋጅን ለሚመለከተው የቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ ልኳል፤ ከዚኽ በተጨማሪ፣ ሦሥት የአስረጂ መድረኮችን በረቂቅ ሕጎቹ ላይ አከናውኗል፡፡

የጸደቁ ሕጎች

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በወርሃ መጋቢት ካፀደቃቸው ሕግጋት አንዱ፣ የተመሠከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲቲዩት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን ነበር። በ19ኛው መደበኛ ስብሰባው፣ የቀረበለትን ይኽንኑ ረቂቅ የተመለከተው ምክር ቤቱ፣ አዋጁን በመርመር፣ አዋጅ ቁጥር 1372/2017 በማድረግ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው የተከበሩ ደሳለኝ ወዳጄም፣ ሪፖርት እና የውሳኔ ሐሳቡን ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት፣ አዋጁ በኢትዮጵያ ዓለም ዓቀፍ የተመሠከረላቸው ባለሙያዎችን ለማፍራት አቅም የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የሒሳብ ባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ በዘርፉ እየተከሰተ ያለውን የገንዘብ ብክነት ከማስቀረት ባለፈ፣ የሕዝብ እና የአገርን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችል ረቂቅ መሆኑንም ሰብሳቢው አስገንዝበዋል፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው ዶ.ር. ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው፣ ረቂቅ አዋጁ ዓለም ዓቀፋዊ እና አህጉራዊ ተሞክሮዎችን መሠረት ያደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ የፋይናንስ አቅምን ለማሳደግ፣ ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን የሚያጠናክሩ የሒሳብ አያያዝ፣ ኦዲት እና የፋይናንስ መረጃዎችን የማስተዋወቅ ሚናው ከፍ ያለ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡

በኹለተኝነትም ምክር ቤቱ፣ አኹን በሥራ ላይ ያለውን የፌዴራል መንግሥቱ በክልሎች ውስጥ ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በሚል በ1995 ዓ.ም. የወጣውን አዋጅ አሻሽሏል። በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ የተከበሩ ዶ.ር. ተስፋዬ በልጅጌ እና የፍትሕ ሚኒስትሯ ሃና አርያ ሥላሴ፣ አዋጁ እንዲሻሻል ያስፈለገባቸውን የተለያዩ ምክንያቶች ለእንደራሴዎቹ አብራርተዋል። ምክር ቤቱ፣ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ባካሄደው 22ኛ መደበኛ ስብሰባው፣ የቀረበለትን ይኽንኑ የማሻሻያ አዋጅ ያፀደቀው በኹለት ድምጸ-ተዐቅቦና በአብላጫ ድምጽ ሲሆን፤ ነባሩን አዋጅ ቁጥር 359/1995ን ተክቶ ‘የፌደራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ የወጣ ሻሻያ አዋጅ፣ አዋጅ ቁጥር 1373/2017’’ በሚል አፅድቆታል። የአዋጁን የማሻሻያ የውሳኔ ሐሳብ ያቀረቡት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ የተከበሩ ዶ.ር. ተስፋዬ በልጅጌ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሥተዳደርን እንደምሳሌ በማንሳት፣ የአሥተዳደሩ ዘመን በቀደመው አዋጅ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ክልሉ ካለበት ነባራዊ ኹኔታ ጋር የማይጣጣም ሆኖ በመገኘቱ በአዋጁ አተገባበር ወቅት ክፍተት ተፈጥሯል ሲሉ የማሻሻያውን አስፈላጊነት አብራርተዋል፡፡ (ስለዚኹ አዋጅ ዳሰሳዊ ምልክታችንን ገጽ 18 ላይ ይመልከቱ)።

ረቂቅ ሕጎች

የእንደራሴዎቹ ምክር ቤት፣ መጋቢት 9 2017 ዓ.ም. ባካሄደው 20ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 16/2017ን፣ ለዝርዝር ዕይታ በሙሉ ድምጽ ለውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶቷል። በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር የሆኑት የተከበሩ ዶ.ር. ተስፋዬ በልጅጌም፣ ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ተጠሪ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያም፣ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር የቅድመ-አደጋ፣ የአደጋ ወቅት እና ድህረአደጋ ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ የፌዴራል እና የክልል አሥተዳደር ተቋማት የውስጥ አቅም ለመገንባት አዋጁ ማስፈለጉን አንስተዋል።1

ከዚያ ባለፈም፣ ቅጽበታዊ አደጋ ሲከሰት እና ከአቅም በላይ ሲሆንም የአስቸኳይ ጊዜ እወጃ ሥርዓት ከመዘርጋት አንስቶ ተግባራዊ ለማድረግ ጭምር ይኸው ረቂቅ ማስፈለጉን ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል። እንደ ረቂቅ አዋጁ ማብራሪያም፣ በቅድመ አደጋ፣ አደጋ እና በድህረ-አደጋ ወቅቶች ለሚወሰዱ የአደጋ ሥጋት ቅነሳ፣ ምላሽ እና መልሶ ማቋቋም የሚሆን የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ምላሽ ፈንድ ይቋቋማል። ፈንዱም ከሠራተኞች ደመወዝ ላይ ከሚቆረጥለት ገቢ በተጨማሪ ከባንኮች እና ከተለያዩ የፋይናንስ እና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ፣ ከፌዴራሉ መንግሥት፣ ከኹለቱ ከተማ አሥተዳደሮች እንዲኹም ከጠቅላላው ዓመታዊ በጀት በድርሻ እንደሚሰበሰብም ተብራርቷል፡፡2

የአስረጂ መድረኮች

ምክር ቤቱ ባሳለፍነው መጋቢት ወር በደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ እና የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ቲንክ ታንክ አልያም ጥናታዊ የፖሊሲ ግብዓት አውጪ ቡድን ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብን ጨምሮ፣ ኹለት የአስረጂ መድረኮችን አካሂዷል፡፡

የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ በሚል ስያሜ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ተከትሎም፣ የምክር ቤቱ የውኃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢ እና የአካባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ከተባሉ ባለድርሻዎች ጋር ሰፋ ያለ የአስረጂ መድረክን አካሄዷል። መጋቢት 15 ቀን በዋለው መድረክ ላይ የተገኙት የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሪክተሯ ሌሊሴ ነሜ፣ ረቂቅ አዋጁ የግል ዘርፉን ከትርፋማነት ጎን ለጎን የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ ከመንግስት ጋር እንዲሠሩ ዕድል ይፈጥራል ሲሉ የአዋጁን አስፈላጊነት አብራርተዋል። ነባሩ አዋጅ (ቁጥር 513/1999) 18 ዓመታትን ያስቆጠረ እንደመሆኑ፣ ከደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ ጋር በተያያዘ ለገጠሩ የማኅበረሰብ ክፍል ብዙ ትኩረት ያልሰጠ መሆኑንም ሌሊሴ ጨምረው አንስተዋል።3

የእንደራሴዎቹ ምክር ቤት፣ መጋቢት 29 2017 ዓ.ም. ላይ ያካሄደው ኹለተኛው የአስረጂ መድረክ፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ቲንክ ታንክ ቡድን ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብን የተመለከተው ነበር። የከተማ እና መሠረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባዘጋጀው ይኸው የአስረጂ መድረክ፣ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የዘርፉ ሙያተኞች ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው ተገልጿል። ከዚኽ ባለፈም፣ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታው የትም ጌታ አሥራት፣ በዚኽ ወቅት የኢትዮጵያን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ያሉበትን ዘርፈ ብዙ ማነቆዎችን በመፍታት ወደ ላቀ የእድገት ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባ ተናግረዋል። መንግስትም የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለማሳደግ የዘርፉን ሙያተኞች በማቀራረብ ለአገር የሚጠቅሙ ሐሳቦችን በጋራ ለማፍለቅ ዝግጁ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ለመድረኩ ተሳታፊዎች ጨምረው አብራርተዋል። መድረኩን ያዘጋጀው የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ እሸቱ ተመስገን በበኩላቸው፣ ከባለድርሻ አካላት አስተያየት በማሰባሰብ ለረቂቁ ግብዓት እንዲሆን ለከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

English